Print this page
Saturday, 27 April 2013 10:37

የጠ/ሚ ኃይለማርያም ሪፖርት - በሁለት ሸክሞች የተጨናነቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)
  • 1 የአቶ መለስ ዜናዊ ምትክ መሆናቸውን ለማስመስከር የሞከሩበት ነው ግዙፎቹ እቅዶች (ለምሳሌ የባቡር ፕሮጀክት) መጓተታቸውንና የገንዘብ ችግርን በሚመለከት፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል የተፈናቀሉ ሰዎች ዙሪያ ትችት አዘል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ጠ/ሚ ኃይለማርያም ለፓርላማው የሰጡት ምላሽ፣ የአቶ መለስን ዘዴ የተከተለ ነው - “መንግስት ላይ በተሰነዘረው ትችት ላይ የባሰ ትችት የመጨመር ዘዴ”
  • 2. የማይሳካ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጣብቂኝ ሆኖባቸዋል ግዙፎቹ የግድብ፣ የባቡር፣ የኢንዱስትሪ. የኤክስፖርት እቅዶች፣ እንዲሁም የእህል ምርት ለማሳደግና ስራ አጥነትን ለማቃለል የወጡ እቅዶች የማይሳኩ መሆናቸውን ከምር አምነው ለመቀበል አልደፈሩም። እቅዶቹ “በተያዘላቸው ጊዜ እየተተገበሩ ናቸው” እያሉ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ግን ደግሞ “የመቀነስ አዝማሚያ ታይቷል” ይላሉ።

እውነት ለመናገር ኢህአዴግ በ”ስሜት” ተነሳስቶ በ2002 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ያዘጋጀው “የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ” አልሳካ ያለው በጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ድክመት አይደለም። እቅዱ እንደማይሳካ በተግባር የታየው በመጀመሪያው አመት በ2003 ዓ.ም ነው። አምና ደግሞ፤ የእቅዱ ውድቀት አፍጥጦ ወጣ። በዚህ በዚህ፣ አቶ ኃይለማርያም ከሌሎች የኢህአዴግ መሪዎች የተለየ ተጠያቂነት ሊጫንባቸው አይገባም። በአብዛኛው የመንግስት ፕሮጀክቶች በማስፋፋት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በአምስት አመት ውስጥ በእጥፍ ለማሳደግ ታስቦ እቅድ መውጣቱ ነው ዋነኛው ጥፋት። በመንግስት ፕሮጀክቶችና ኮርፖሬሽኖች አማካኝነት አገር ሊያድግ እንደማይችል በደርግ ዘመን በደንብ ታይቷልኮ።

የኢህአዴግ “የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድም” ከውድቀት ሊያመልጥ የማይችለው፤ እንደ ደርግ እቅድ የግል ኢንቨስትመንትንና የግል ጥረትን የሚያጣጥ በመሆኑ ነው - በአጭሩ በአቶ ሃይለማርያም ድክመት አይደለም የኢህአዴግ እቅድ ሳይሳካ የሚቀረው። ይልቅስ፣ ጠ/ሚ ኃይለማርያምን ተጠያቂ የምናደርጋቸው፤ የአምስት አመቱ እቅድ እንደማይሳካ እየታወቀ፤ “እየተሳካ ነው፤ እንደታቀደው እየተሰራ ነው” ብለው ሊያድበሰብሱ ከሞከሩ ነው። በእርግጥ፤ እቅዱ እየተሳካ አለመሆኑን ሙሉ ለሙሉ አልካዱም። የእርሻ ምርት እንደታሰበው አላደገም ብለዋል። ኤክስፖርትም እንዲሁ።

“የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ምርታማነት”ም የተወራለት ያህል እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። እንዲያም ሆኖ፤ እቅዱን አለመሳካት ሙሉ ለሙሉ ባይክዱም፤ ሙሉ ለሙሉም አምነው አልተቀበሉም። “የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ”፤ ከሞላ ጎደል በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እየተተገበረ እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ የገለፁት። ለመሆኑ የትኛው እቅድ ነው፤ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እየተከናወነ የሚገኘው? ካሁን በፊት እንደጠቀስኩት፣ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንኳ በእቅዱ መሰረት እየተከናወነ አይደለም። በጣም ተጓቷል። በአምስት አመት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ነበር የተባለው። ግን በሁለት አመት ውስጥ የተከናወነው ስራ፣ 18 በመቶ ብቻ ነው። በዚህ ስሌትም፣ ግንባታው 11 አመት ሊፈጅ ይችላል። “የግልገል ጊቤ 3” ግንባታም እንዲሁ፤ በእቅዱ መሰረት ሊሄድ አልቻለም። በ1998 ዓ.ም የተጀመረው የግልገል ጊቤ 3 ሃይል ማመንጫ፣ የዛሬ ሁለት አመት ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ስራ እንዲገባ ታቅዶ ነበር። አልተሳካም።

እቅዱ ተከልሶ፣ የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜው ወደ ዘንድሮ ተራዘመ። ግን እንኳን ዘንድሮ በሚቀጥለው አመትም አይጠናቀቅም። ግንባታው ገና 71% ላይ ነው። ቢያንስ ተጨማሪ ሶስት አመት ሳያስፈልገው አይቀርም። እናም በ2002 ዓ.ም ወደ ሁለት ሺ ሜጋ ዋት ገደማ የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም፣ በ50 በመቶ እንዲያድግና ዘንድሮ ሶስት ሺ ሜጋ ዋት እንዲደርስ የወጣው እቅድ አልተሳካም። እዚያው ከነበረበት ደረጃ ፈቅ አላለም። ከሁሉም የላቀ ትኩረት የተሰጣቸው ግድቦች፣ በተያዘላቸው እቅድ ሊከናወኑ ካልቻሉ፣ ሌሎቹ እቅዶች ምን ያህል እንደሚጓተቱ አስቡት። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተጠቀሱት ግዙፍ የሳሙናና የወረቀት ፋብሪካዎችም ድምፃቸው የለም። ዋነኛ የእድገት መሰረት ይሆናሉ ተብለው በመንግስት በጀት የተመደበላቸው አነስተኛና ጥቃቅን አምራች ተቋማትስ? ከቁጥር የሚገባ ለውጥ አልተመዘገበም። ፈፅሞ የእድገት ምልክት አልታየባቸውም። እንዲያውም፣ ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ሲነፃፀሩ፣ አነስተኛና ጥቃቅን አምራች ተቋማት ወደ ኋላ እየቀሩ መሆናቸውን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ለነገሩ፣ በኢህአዴግ ጉባኤ ላይም በግልፅ ተጠቅሷል።

የአምናው የእርሻ ምርት እድገትም እንዲሁ የእቅዱን ግማሽ አያክልም። በአማካይ በነፍስ ወከፍ ስሌት፣ የእርሻ ምርት በ6 በመቶ እንዲያድግ ቢታቀድም፣ በተግባር ግን ከ2.5 በመቶ ያለፈ እድገት አልተገኘም። ብዙ የተወራላቸው አዳዲስ 10 የስኳር ፋብሪካዎችም ገና ብቅ አላሉም። ከ8 አመት በፊት የተጀመሩ ነባር የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች እንኳ፣ በወጉ ሊጠናቀቁ አልቻሉም። የስኳር ምርት በሶስት እጥፍ አድጎ ዘንድሮ 10 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ይደርሳል ተብሎ ነበር - በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ። እህስ? የዛሬ አራት አመት ከነበረበት ደረጃ ትንሽ እንኳ ፎቀቅ አላለም። እንዲያውም ወደ ታች ወርዷል፤ ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በታች ሆኗል። ከአገር ውስጥ ፍጆታ የሚበልጥ ስኳር ተመርቶ፣ ዘንድሮ በኤክስፖርት ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ገደማ ገቢ ይገኝበታል ተብሎ ነበር። ጠብ ያለ ነገር የለም። እንዲያውም የአገር ውስጥ ፍጆታን ለማሟላት ከውጭ ስኳር ለማስመጣት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ወጪ ተደርጓል። ባቡርስ? የባቡር ነገርማ ከሌሎችም የባሰ ሆኗል። የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ እንደተጠቀሰው ቢሆን ኖሮ፤ አገሪቱ ዘንድሮ 1700 ኪሎሜትር የባቡር ሃዲድና የባቡር ትራንስፖርት ይኖራት ነበር። ቢያንስ ቢያንስ የጂቡቲ መስመር ተሰርቶ አገልግሎት መስጠት ይጀምር ነበር። ግን እንደ እቅዱ አልሆነም። እስካሁን የተሰራው ሃዲድ “የ650 ኪሎሜትር 15%” ነው ተብሏል።

ቢበዛ ከመቶ ኪሎሜትር አይበልጥም ማለት ነው። የጂቡቲ መስመር ሁለተኛው ደግሞ ገና የአፈር ቁፋሮ ላይ ነው። ወደ ሰሜን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የተባሉት የባቡር መስመሮችማ ገና ዲዛይናቸው አላለቀም። የኮንዶሚኒዬም ቤት ግንባታም ተመሳሳይ ነው። ስለ ኮንዶሚኒዬም ብዙ ብዙ እቅዶች ሲዘረዘሩና በሪፖርት ሲቀርቡ አይገርማችሁም? በየአመቱ 50ሺ ኮንዶሚኒዬም ቤቶች ይገነባሉ ሲባል ትዝ ይላችኋል - በ97 ዓም። አንድ ሶስተኛውን እንኳ ማሟላት አልተቻለም። በእድገትና ትራንስፎርሜሽ እቅድ ላይ፣ አመታዊው የግንባታ መጠን ወደ 30ሺ ዝቅ እንዲል ተደረገ - በሶስት አመት 90ሺ መሆኑ ነው። ይሄም አልተቻለም። በሶስት አመት ውስጥ ለነዋሪዎች የደረሱ አዳዲስ የቤት ግንባታዎች ሲቆጠሩ፣ በአመት ከአስር ሺ አይበልጡም - የእቅዱ 30 በመቶ እንደማለት ነው። ጠቅላላ የኢኮኖሚውን አዝማሚያ በግልፅ የሚያሳይ ሌላ መረጃ ከፈለጋችሁ፤ በኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ መመልከት ትችላላችሁ። የእድገትና የትራንፎርሜሽን እቅድ የተዘጋጀው፤ በ2002 ዓ.ም ከሸቀጦች ኤክስፖርት 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከተገኘ በኋላ ነው።

አምስት አመት ውስጥ በአራት እጥፍ አድጎ 8 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ ታስቦ በወጣው እቅድ መሰረት፣ ዘንድሮ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የኤክስፖርት ገቢ መገኘት ነበረበት። ግን ሊሆን አይችልም። ለዚህም ነው እቅዱ ተከልሶ፣ በዚህ አመት ከኤክስፖርት 3.7 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት የታቀደው። ይሄም አልተሳካም። በስምንት ወራት ውስጥ የተገኘው የኤክስፖርት ገቢ 2 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው። በአመቱ መጨረሻ ቢበዛ ቢበዛ 3 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል። የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ፈፅሞ ሊሳካ እንደማይችል ሁነኛ ማረጋገጫ የሚሆንብን፣ ይሄው የኤክስፖርት ገቢ ዝቅተኛነት ነው። ለምን ቢሉ፤ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ አገኛለሁ በሚል ሃሳብ መንግስት ያቀዳቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሊሆኑ አይችሉም። በትምህርትና በስልጠና በኩልስ፣ እቅዱ እየተሳካ ነው? ቃላትን ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች ምን ያህል ብዙ እንደሆኑ የተለያዩ ጥናቶችን በማጣቀስ መልስ መስጠት ይቻላል። ግን፣ በኢትዮጵያ ሬድዮ የተሰራጨ አንድ ዜና ብቻ በመስማት የአገሪቱን የትምህርት ሁኔታ አዝማሚያውን መገመት የሚቻል ይመስለኛል።

የቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ ከወዳደቁ እቃዎች መበየጃ ተሰራ የሚል ነው የዜናው ርዕስ። በኢትዮጵያ ሬድዮ የምንሰማቸው ዜናዎች “አስገራሚ” አይደሉ? ረቡዕ ማታ ሁለት ሰዓት ላይ፣ የእለቱ ሁለተኛ ትልቅ ዜና፣ በጅጅጋ የቴክኒክ ኮሌጅ፣ ከወዳደቁ ነገሮች መበየጃ እንደተሰራ ይገልፃል። በየጉራንጉሩ የሚዘጋጀውን መበየጃ፣ ለአንድ የቴክኒክ ኮሌጅ እንደ ትልቅ ስራ መቆጠር የጀመረው ከመቼ ወዲህ ይሆን? ግርድፍ “ትራንስፎርመር” እንደማለትኮ ነው። ከመበየጃ ጋር ሲነፃፀር፣ የሞባይል ቻርጀር እጅግ የተራቀቀ “ትራንስፎርመር” ነው። የኮሌጁ አስተማሪዎችና ተማሪዎች፣ መበየጃ ለመስራት መጣራቸው ስህተት ባይሆንም፣ መበየጃው “ከወዳደቁ ነገሮች” የተሰራው ኮሌጁ ምን አይነት ቢሆን ነው? መበየጃ ለመስራት የሚያስችል ቁሳቁስ ከሌለው፣ እንደ ሞተርና ጄነሬተር የመሳሰሉ ነገሮችን ለማደስማ ጨርሶ አይታሰብም ማለት ነው። የቴክኒክ ኮሌጅ እንዲህ ነው? ካስታወሳችሁ፣ የረቡዕ ማታ የመጀመሪያ ዜና፣ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ለፓርላማ ያቀረቡትን ሪፖርት የሚመለከት ነበር። ለኢንዱስትሪ ምርትና ልማት ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው የገለፁት ጠ/ሚ ኃይለማርያም፣ ለቴክኒክ ትምህርት ስለሚመደበው በጀትና ስለ ትምህርት ጥራት ልብን የሚያሞቅ ሪፖርት ዘርዝረዋል። ታዲያ ይህንን “የምስራች” የሚያፈርስ “የመበየጃ” ዜና ወዲያውኑ ተከትሎ መቅረቡ አይገርምም?

Read 9418 times Last modified on Saturday, 27 April 2013 13:31
Administrator

Latest from Administrator