Saturday, 27 April 2013 10:35

የኩማ አስተዳደር ስኬቶችና ጉድለቶች

Written by  በጃፋር ባሌማ (JABALEMA@yahoo.com)
Rate this item
(1 Vote)

ወቅቱ ሀገር አቀፍ የወረዳና የቀበሌ ምርጫ የተካሄደበትና አዲስ አስተዳደር የሚዋቀርበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ ታዲያ እየተሠናበተ ያለው “የኩማ ካቢኔ” ባለፉት አምስት ዓመታት ምን ስኬቶችን አስመዘገበ፤ በየትኞቹ ስራዎችስ ወደ ኋላ ቀረ ብሎ መፈተሽ ለመጭው አስተዳደር ትምህርት ከመስጠቱ ባሻገር፤ ትኩረት ሊሠጣቸው የሚገቡ ዘርፎችን ለመለየትም ያስችላል፡፡ አስተዳደሩን የሙጥኝ ብለው የተጣበቁ “በሽታዎችን” ለይቶ ለማከምም ያግዛል፡፡ ግንቦት 2000 ዓ.ም፣ ቀድሞ ለመግባት ዳር ዳር የሚለው የክረምት ዝናብ አዲስ አበባን ቅዝቃዜ አላብሷታል፡፡ በወቅቱ የተካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ለአዲስ አበባም አዲስ አስተዳደር የሚፈጥርላት ስለነበር በጉጉት ተጠብቋል፡፡ በእርግጥ ከምርጫ 97 ቀውስ በኋላ ህዝቡ ከተዳፈነ የምርጫ ስሜቱ አልተነቃቃም ነበር፡፡ ተቃዋሚዎችም የተዳከሙበት ጊዜ ነው፡፡

ያም ሆኖ ገዥው ፓርቲ የከተለው አዲስ ስልት የምርጫውን ሂደት እንዲነቃቃ አድርጎት ነበር፡፡ 103 (አሁን 116 ደርሷል) የቀበሌ ምክር ቤቶች በእያንዳንዱ 300 የም/ቤት አባላት፣ በ10 ክፍለ ከተማ እስከ 200 እና በማዕከል 180 ድረስ በድምሩ 34ሺ ገደማ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዕጩ ተመራጭ ሆነው መቅረባቸው ይታወሳል፡፡ (በነገራችን ላይ ሁሉም ተቃዋሚዎች 36ሺ የሚደርሱ አባላት አልነበራቸውም) በምርጫው እንደተጠበቀው ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ አሸነፈ፡፡ በነገራችን ላይ የቤት ለቤት ቅስቀሳ፣ የ1ለ5 ጥርነፋ የተሞከረው በዚህ ምርጫ ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ያኔ በስልጣን ላይ የነበረው የባለ አደራው አስተዳደርም ቢሆን ኢህአዴግ ዛሬ በሃላፊነት ላይ ያስቀመጣቸውን ካድሬዎች ይዞ በሙሉ ጉልበቱ ተግቷል፡፡

እንደአለመታደል ሆኖ የተቃዋሚ ጐራው በእርስ በርስ ክፍፍል የተዳከመበት ጊዜ ነበር፡፡ የኩማ አስተዳደር ስራ ጅማሮ የአስተዳደሩ ካቢኔ ስብስብ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ኢህአዴግ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ኩማ ደመቅሳን ከንቲባ አድርጎ ሲያመጣ፣ በሚዲያ ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ የነበራቸውን አቶ ከፍያለው አዘዘ (ዛሬ ከአገር ተሰደዋል) በምክትል ከንቲባነት ሾማቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሚኒስትርነት የተሾሙ የዲኢህዴን ተወካዮችን ጨምሮ “ጠንካራ ካቢኔ” የሚባል አደረጃጀት ተፈጥሮ ነበር፡፡ አስተዳደሩ ቀዳሚ ስራ አድርጎ ያያቸው መዋቅሩን ማደራጀት፣ BPR ና BSC የመሠሉ የአሰራር ማሻሻያ ጥናቶችን ማካሄድ ነው፡፡ በአዲስ መልክ በየደረጃዉ 16ሺ ገደማ ሠራተኛ በመቅጠር ነባሩን ጨምሮ 41,913 የመንግሥት ሠራተኞች ነበሩት፡፡

የከተማዋ አስተዳደር የከተማዋን የ10 ዓመት ፍኖተ ተግባር (Road Map) እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ነድፎ ዘርፈ ብዙ ጥረት ማድረጉም እንደ መልካም ጅምር ይጠቀሳል፡፡ በመንገድ ግንባታ፣ በቤቶች ልማት ፕሮጀክት፣ በመጠጥ ውሃ፣ በማህበራዊ ተቋማትና ቢሮዎች ግንባታ አስተዳደሩ ያከናወናቸው ስራዎች ከቀድሞው “የተሻለ” የሚባሉ ነበሩ፡፡ ያዝ ለቀቅ የታየበት ቢመስልም በሪል እስቴትና ህገወጥ ማህበራት ስም የተዘረፈ መሬት ለማስመለስ የተደረጉ ጥረቶችም የሚናቁ አይደሉም፡፡ አስተዳደሩ ያጋጠሙት ተግዳሮቶችና ወደ ኋላ የቀረባቸው ስራዎችም ቀላል አይመስሉም፡፡ አቶ ሠለሞን የተባሉ የአስተዳደሩ ባለሙያ ሲናገሩ፤ “ስራዎች መመዘን ያለባቸው ከህዝብ ጥቅምና አስተዳደሩ ከአራት ዓመት በፊት ካወጣው የስትራቴጂክ ዕቅድ አንፃር መሆን አለበት” ይላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በአፈፃፀም የታዩ ግድፈቶችና በአስተዳደሩ ድክመት የከሸፉ ዕቅዶች በግልፅ ወጥተው ትምህርት ሊወሰድባቸው እንደሚገባም ያስረዳሉ፡፡ የመልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ተግዳሮቶች የአዲስ አበባ መንግስታዊ መዋቅር ሰፊና እስከታች የወረደ ቢሆንም ደረጃውን የጠበቀና በቴክኖሎጂ የታገዘ አይደለም፡፡

በአስተዳደሩ ስትራቴጂክ ዕቅድ ገፅ 102 ላይ “በከተማዋ አስተዳደር ሥር የሚገኙ ተቋማት በሙሉ በICT መረብ እንዲገናኙና በዘላቂነት ቀልጣፋ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት እንዲፈጠር ይደረጋል” ይላል፡፡ አፈፃፀሙ ግን ይሄን አያሳይም፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሙንኬሽን ኤጀንሲ ተቋቁሞ ባለሙያ እየመደበ፣ ኔትወርክና የመረጃ ቋት (ሰርቨር) እየዘረጋ ቢሆንም እንኳን እስከ ወረዳ ሊወርድ ቀርቶ የማዕከል መስሪያ ቤቶችንም አላደረሰም፡፡ “በBPR ጥናት ሴክተሮች መረጃ በፋክስ አቶሜሽን የሚለዋወጡበት ስርዓት ይዘረጋል ብለን ብንነሳም አልተሳካም” ይላሉ - የአስተዳደሩ ባለሙያ፡፡ አሁንም በኋላ ቀር መንገድ ደብዳቤ በመፃፃፍ የሚባክነው ጊዜ፣ ሀብት (የመኪና ነዳጅ) እና ጉልበት ቀላል አይደለም፡፡ በየቦታው ኮምፒዩተር በገፍ ቢገዛም ያለ ጥቅም የተቀመጠው ይበዛል፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ ሰርቨር ያሉ ውድ መሳሪያዎች ያለ ስራ ይቀመጣሉ በማለት የዘልማድ አሰራሩን ይተቻሉ፡፡

በየጊዜው በሚደረግ የቢሮ መቀያየር የሚበላሸው የኔትወርኪንግ ሲስተም (በቅርቡ ለመሬት አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ኮክቴል አዳራሽ የተዘረጋው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ፤ የወጣበት ኬብልና ሲስተም ተበጣጥሶ ቢሮው መቀየሩን ልብ ይሏል) ያለ ተቆጣጣሪ ባክኗል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ተግዳሮቶች የመረጃ አያያዙንም ሆነ አገልግሎት አሰጣጡን በመረጃ ለማሳለጥ አልተቻለም፡፡ ለውጡም ዘገምተኛ እንደነበረ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ “የአስተዳደሩ ሠራተኞች በስራ ውጤታቸው የሚመዘኑበት ሥርዓት በተሟላ መንገድ ይዘረጋል” የሚለው የአቅም ግንባታ ግብም ህልም ሆኖ ቀርቷል፡፡ በጣት የሚቆጠሩ መስሪያ ቤቶች - መገናኛ ብዙሃን፣ ከንቲባ ፅ/ቤትና የቤቶች ልማት የአቅም ግንባታ ከመጀመራቸው ባለፈ (ያዝ ለቀቅ ቢሆንም) ራሱ አቅም ግንባታ ቢሮ እንኳን የሰው ሃይሉን አፈፃፀም የሚመዝንበት ስርዓት እንደሌለው ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ፡፡

አቶ በሃይሉ የተባሉ ሌላው የአስተዳደር ባለሙያ ስለዚሁ ሲያስረዱ፤ “ቢ.ኤስ.ሲ የሚባለው የምዘና ስርዓት እንዲጠና በሚሊዮን የሚቆጠር ብር በጀት ተመድቦ ለሦስት ወር ከየሴክተሩ ባለሙያዎች ቢሰለጥኑም ያለ ውጤት ቀርቷል፡፡ የምዘና ሥርዓቱ ባለመተግበሩ አንዳንድ የስራ ሃላፊዎች ለራሣቸው ኔትወርክ ያመቻቸውን እንዲሾሙና እንዲሸልሙ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ በብዙሃኑ ሰራተኛ ውስጥም “ሠራህ አልሠራህ ለውጥ የለውም” የሚል ተስፋ ቆራጭነት ይንፀባረቃል፡፡ አሁን የተያዘው መንገድ በዘመቻ መልክ “የተቀደደ በርሜል የመሙላት” አይነት ጥድፊያ እንጂ በስርዓት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል እንዳልሆነ ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡ ለዚህ ችግር ዋነኛ ተጠያቂዎቹ ደግሞ የየመስሪያ ቤቶቹ ሃላፊዎች እንደሆኑ ይጠቁማሉ፡፡ የኢኮኖሚ ልማት ተግዳሮቶች የሀገራችን ከተሞች የኢኮኖሚ ልማት ሲነሳ በቀዳሚነት የሚጠቀሠው መሬት ነው፡፡ ሀብቱ የጋራ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣና የዕድገት መሰረት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአሁኑ ካቢኔ የመሬት ልማት ሴክተሩን ለማስተካከል ሦስት ጊዜ ቢሮ ቀይሯል፡፡ ሦስት ጊዜ አደረጃጀት ሠርቷል (በጥናት የባከነውን ጊዜ ያስታውሷል) አሁን የተበታተኑ ተቋማትና ከተማ ስራ አስኪያጆች ጽ/ቤት የነበረው መስሪያ ቤት “የመሬት አስተዳደርና ልማት ቢሮ” ተብሎ በምክትል ከንቲባ ደረጃ እየተመራ ነው፡፡ የቀድሞ የከተማዋ ምክር ቤት አባል ወ/ሮ አስቴር ስንታየሁ፤ “የከተማዋን ማስተር ፕላን ከልሶ በማስተካከል፣ የሪል እስቴትና ማህበራት ህገ ወጥ የመሬት ዝርፊያና የመሬት ሙስና ላይ ያለውን ሽሚያ ለማስታገስ አስተዳደሩ ጥሩ ጥረት አድርጓል፡፡ ውጤትም አሳይቷል” ይላሉ፡፡

በአምስት ዓመቱ የአስተዳደር ዘመን በመሰረተ ልማት የተሟላ 8ሺህ 693 ሄክታር ቦታ ለማዘጋጀት የታሠበው ዕቅድ ግን ወደ ኋላ ቀርቷል፡፡ የተቀናጀ የመሬት ልማት የመረጃ ስርዓት መጀመሩ መልካም ቢሆንም ለሁሉም ህጋዊ ባለ ይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ለመስጠት የተጀመረው ስራ፣ ከ60ሺ በላይ ይዞታዎች ማለፍ አልቻለም ሲሉ ወ/ሮ አስቴር አፈፃፀሙን ይገመግማሉ፡፡ ከ1983 ወዲህ በተለያየ ህገወጥ መንገድ መኖሪያ ቤት ሠርተው መኖር የጀመሩ (በቦሌ፣ በኮልፌና ንፋስ ስልክ ይበዛሉ) የተሰጣቸው ውሳኔ አለ፡፡ “ፕላኑን ጠብቀው (በመጠነኛ ማስተካከያ) ህጋዊ እንዲሆኑና ውሃ፣ መብራትና ካርታ እንዲያገኙ” የሚል፡፡ በእነዚህና በመልሶ ማልማት አካባቢ የሚፈፀሙ ሙስናዎች ተደባብሰው ማለፋቸው ግን ብዙዎችን ያስቆጫል፡፡ ወ/ሮ አስቴርም ይህንኑ ይጋራሉ፡፡ “አዲስ አበባ ውስጥ ቀደም ሲል ጀምሮ በርካቶች በመሬት ህገወጥ ወረራና ዝርፊያ እንደበለፀጉ ይታወቃል፡፡ ለምን የህገወጦች ጉዳይ እንደሚድበሰበስ አይገባኝም!?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን ፀረ ሙስናም አስተማሪ እርምጃ እየወሠደ ሌላው እንዲማርበት ባለማድረጉ ሙስናው የግለሰቦች ሳይሆን “መንግስታዊ ሙስና” ሊመስል በቅቷል በማለት ይወቅሳሉ፡፡

አስተዳደሩ ግንባታ ባልጀመሩ ባለሀብቶች ላይ የሚወስደው እርምጃም ከሀሜት የራቀ አይደለም፡፡ አንዳንዶች አምስት ስድስት የከተማዋን ቁልፍ ቦታዎች አጥረው ዝም ሲባሉ፤ አውቀው ያንቀላፋሉ፡፡ ሌላው አንድም ብትሆን ካልገነባ ይቀማል ይላሉ ተችዎች፡፡ አስተዳደሩ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከ7ቢ. ብር በላይ በማውጣት የመሰረተ ልማት፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የትምህርትና ጤና ተቋማት ግንባታዎችን አከናውኗል፡፡ 33 የጤና ጣቢያዎች ግንባታ፣ 121 የት/ቤቶች ማስፋፊያና ዕድሳት፤ የየካቲት 12 እና ሚኒሊክ ሆስፒታሎች ማስፋፊያ፤ የ78 ወረዳዎች ቢሮ ግንባታ፣ የስድስት ክፍለ ከተሞች ጽ/ቤቶች ስራና የአራት ትልልቅ የቢሮ ህንፃዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት የተካሄደው ግንባታ መልካም ሊባል እንደሚችል የሚናገሩ ታዛቢዎች፤ የሚታዩ ክፍተቶች ግን መፈተሽ አለባቸው ይላሉ፡፡ የግንባታ ስራዎች መቶ በመቶ የጥራት ስታንዳርዱን ጠብቀው ይከናወናሉ ቢባልም የጥራት ችግር ያለባቸው አፈፃፀሞች ታይተዋል፡፡ በወራት ዕድሜ ሳያገለግሉ የተገጣጠቡ መንገዶች፣ ፍሳሽ መውረጃ አጥተው ቱቦም መንገድም የመሰሉ ኩሬዎች በቢሊዮን የሚገመት ሀብት ፈሰውባቸዋል፡፡ ችግር የነበረባቸው ኮንትራክተሮችና ሱፐርቫይዘሮችስ “ምን ያህሉ ተጠየቁ” የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም፡፡ የመኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራም ተግዳሮቶች አዲስ አበባ የከፋ የመኖሪያ ቤት ችግር ካለባቸው አምስት የዓለም ዋና ከተሞች አንዷ ናት፡፡

አብዛኛው ነዋሪ የተሟላ መፀዳጃና መታጠቢያ ለሌለው አልያም ከአንድ ክፍል ባልበለጠ ቤት ከአቅሙ በላይ ኪራይ እየከፈለ ኑሮውን የሚገፋባት “ቤት አጥ!” ከተማ ነች፡፡ ለዚህም ነው አስተዳደሩ በዓመት 50ሺ ቤቶችን ለመገንባት አቅዶ የተነሳው፡፡ የኩማ ካቢኔ በስራ ዘመኑ 250ሺ ቤቶችን በመገንባት 1.2 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ተጠቃሚው እንደሚያደርግ ግብ ነድፎ ነበር፡፡ ከሰሞኑ በኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት የወጣው መረጃ ግን ይሄን አያሳይም፡፡ አስተዳደሩ በባለአደራው አመራር የተጀመሩ 40ሺ ገደማ ቤቶችን አጠናቆ ለህዝብ አስተላልፏል፡፡ በራሱ የጀመራቸውን 15ሺ ቤቶችም ለባለዕድለኞች ያደረሰ ሲሆን 95ሺ ቤቶች ገና በግንባታ ላይ ናቸው (አብዛኛው ከ60% በታች የግንባታ ሂደት ላይ ናቸው) ከዚህ አንፃር የአስተዳደሩ አፈፃፀም ወደኋላ ቀርቷል ማለት ይቻላል፡፡ ዕጣ ወጥቶላቸው ከዓመት በላይ የሚጠብቁ፣ መብራትና ውሃ ማግኘት በምኞት እየቀረ የሚቸገሩ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡

በአንድ ዓመት ያልቃል የተባለው የልደታ ፕሮጀክት እንኳን በሦስት ዓመትም ለተጠቃሚ አለመድረሱ፣ ሴክተሩ ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው አመላካች ነው፡፡ “የከተማዋን የቤት እጥረት ለማቃለል የግሉ ባለሀብት ተሳትፎ አሁን ካለበት 40 በመቶ ወደ 70 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል” የሚለው ግብም ሙሉ በሙሉ እንዳልተሳካ ይነገራል፡፡ በሪልእስቴት ልማት ስራ ላይ የተሰማራው ኢንጂነር ሸዋቀና ጣና “የሪል እስቴት ኢንዱስትሪው ወደኋላ እየተመለሰ ነው” ይላል፡፡ በአንድ በኩል አልሚዎች ቦታውን በቅናሽና ከአርሶአደሩ በተለያየ መንገድ ወስደው ማልማት ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ በኩል አስተዳደሩ የመሬትን ዋጋ ከማናሩ በላይ ማበረታቸውን ሊያስቀጥል አልቻለም፡፡ በዚህ ላይ የገቢያው መጥፋትና የነዋሪው አቅም ማጣት ቀደም ሲል ወደ ዘርፉ የገቡትንም እያስወጣ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በህገወጥ ሪልእስቴት አልሚዎች ስም በሁሉም ላይ የተደረገ የሚመስል ዘመቻም ነቃፊ ባህሪ እንደነበረው ኢንጂነሩ ይናገራል፡፡ በዚህ ላይ ለግንባታ ማህበራትና ለግለሰብ ቤት ገንቢዎች ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ፣ አስተዳደሩ በሙሉ አቅሙ “ቤት ገንቢ ነኝ” እያለ ዘርፉ እንዴት 70 በመቶ ያድጋል? ሲልም ይጠይቃል፡፡

ስለዚህ ዕቅዱ ወይም አፈፃፀሙ መፈተሽ አለበት ባይ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የመልሶ ማልማት (Renwal) ፕሮግራሙ ነው፡፡ ዛሬ ልደታ፣ ካሳንቺስና አራት ኪሎ ታሪክ ሆነው ጠፍተዋል፡፡ በአዲስና ዘመናዊ መንደር እየተቀየሩ መጥተዋልና፡፡ ያም ሆኖ አስተዳደሩ በአምስት ዓመታት ውስጥ “በከተማዋ ያረጁና የተጨናነቁ አካባቢዎች ከሚገኙ 90 በመቶ ቤቶች ውስጥ 50 በመቶ መልሰው እንዲለሙ ይደረጋል!” የሚለው የጦዘ ምኞት (Over ambition) እንዳልተፈፀመ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በከተማዋ መፍረስ ካለባቸው 280ሺ ገደማ ቤቶች ከ6ሺ ቤቶች በታች ፈርሶ 52 ሄክታር መሬት ብቻ ነው የፀዳው፡፡ ከዚህ አንፃር አፈፃፀሙ ከ5 በመቶ በታች ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የአስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው፤ የመልሶ ማልማት ስራ እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም፤ በርካታ ፈተናዎች የተጋረጡበት ነው ይላሉ፡፡ ህዝቡን ማሳመን፣ ምትክ ቦታ ማመቻቸት፣ እንዲሁም የደባልና ህገወጥ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ለአመራሩ ፈታኝ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሂደት ጥገኛ የሆኑ አመራሮችና ደላሎች ተሞዳሙደው መዝረፋቸው፤ እንዲሁም የካሳ ጉዳይና መሰል ተግባራት አስተዳደሩን ሲፈትኑት ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት የከተማዋን 50 በመቶ መቀየር የሚለው ዕቅድ ከጅምሩም በጥናት ላይ ያልተመሠረተና ምኞት የበዛበት መሆኑን ብዙዎች፡፡

ክፍት በተደረጉ ቦታዎች ላይ እየተከናወነ ያለው ግንባታ ፍጥነትም በቂ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ “አስተዳደሩ ለኮንዶሚኒየምና መንግስታዊ ተቋማት የሚሠራቸው ግንባታዎች ቢፋጠኑም የባለሀብቶች እንቅስቃሴ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ የሸራተን ማስፋፊያን መመልከት ይቻላል፡፡ በድምሩ ሲታይ የመልሶ ማልማት ስራው በማዕከል ጠንካራ መስሪያ ቤት እየተመራ ከወረዳና ክ/ከተማ ደካማ መዋቅር ካልወጣ፣ ሌላ 50 ዓመት ሊፈጅ ይችላል የሚልም ስጋት መሰንዘሩ አልቀረም፡፡ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ ግን በየትኛውም የአፍሪካ ሀገር ተሞክሮ ያልተሳካ ከተማ አፍርሶ የመገንባት ስራ በኢህአዴግ በሚመራው አስተዳደር እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ ስራው አዲስ ከመሆኑና ከሚጠይቀው ሀብትና አቅም አኳያ መውደቅ መነሳት ቢያጋጥምም በትክክለኛው መስመር እየሄደ ነው ሲሉም ስኬትን አብስረዋል፡፡ ከቤቶች ግንባታ (ልማት) ጋር በተያያዘ አስተዳደሩ ከአንድ ዓመት ወዲህ ይፋ ያደረጋቸው ፕሮግራሞች አሉ - 40/60፣ በ90/በ10 ወይም 20/በ80 የተባሉ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች፡፡

እነዚህ “ስራቸው ተጀምሯል” ቢባልም እንቅስቃሴ አልታየባቸውም፡፡ በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት አምስት ዓመታት አቅዶ የሠራቸው ተግባራት የመኖራቸውን ያህል በወረቀት ብቻ የቀሩ እቅዶችም ብዙ ናቸው፡፡ ያልተሳኩት ዕቅዶች በምን ምክንያት ወደኋላ እንደቀሩ ግን ተጠንቶ ለህዝብ መቅረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ በክህሎትና የአመራር አቅም እጥረት፣ በህዝቡ ተባባሪ ያለመሆን፣ በቁርጠኝነት መጥፋት፣ በዳተኝነት ወይስ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት? እውነቱ ህዝብ ግልጽ ሊሆንለት ግድ ይላል፡፡ የመጭው አስተዳደርም ሆነ ህዝቡ ሊማርበት የሚችለውም እንዲያ ሲደረግ ብቻ ነው፡፡

Read 2480 times