Saturday, 27 April 2013 10:21

የቢሊዮነሮች መንደር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ለእረፍት ጊዜና ለመዝናኛ የሚፈለጉ አሸዋማ የባህር ዳርቻዎች በጣም ውድ ናቸው። ካርበን የተሰኘችው የካሊፎርኒያ መንደር ደግሞ የአለማችን እጅግ ውድ የባህር ዳርቻ ነች። በእረፍት ጊዜ ጎራ የሚሉበትን ቤት በመግዛት ወይም በመገንባት፣ በካርበን የባህር ዳርቻ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተደረደሩት ቢሊዮነሮችና ሚሊዮነሮች ናቸው - ፎርብስ መፅሄት እንደዘገበው። 1. (ጆል ሲልቨር)፡ “ማትሪክስ” በተሰኙት ፊልሞች ከፍተኛ ገቢ ያገኘው ሲልቨር፣ በአካባቢው ከ80 አመት በላይ ያስቆጠረ የተንጣለለ ቤት በ$14.4 ሚሊዮን ገዝቷል። ሁለት ቢሮ፣ ጂም፣ መዋኛና የቴኒስ መጫወቻ አሉት። 2. (ፖል አለን)፡ ከቢል ጌትስ ጋር ማይክሮሶፍትን በመመስረት ዛሬ የ$15 ቢሊዮን ጌታ የሆነው ፖል አለን፣ አምስት መኝታ ቤት፣ ፊልም መመልከቻ ክፍል እንዲሁም መዋኛ ያካተተውን ዘመናዊ ቤት በ$25 ሚሊዮን ገዝቷል። 3. (ጄሚ ማካርት)፡ ሚሊዮነሯ በዚህ የባህር ዳርቻ ከአንዲት የፊልም ተዋናይት የገዛችው ቤት ከ$27 ሚሊዮን በላይ የሚያወጣ ነው። 4. (አሮን ሚልካን)፡ በፊልም ኩባንያ ሃብት ያፈራው አሮን ሚልካን የ$4.2 ቢሊዮን ጌታ ነው።

ከ15 አመት በፊት የገዛው ቤተመንግስት የመሰለ 6 መኝታ ቤት፣ የተንጣለለ መዋኛና የፊልም ማሳያ ክፍል አሉት። ዋጋው $7.3 ሚሊዮን ነው። 5. (ሄም ሳባን)፡ የቴሌቪዥን ቢዝነስን ጨምሮ በበርካታ ኢንቨስትመንቶች የ$3.1 ቢሊዮን ባለቤት የሆነው ሳባን፣ $8.1 ሚሊዮን የሚያወጣው የእረፍት ጊዜ መኖሪያ ቤቱ፣ 9 መኝታ ቤቶችን ይዟል። 6. (ጀፍሪ ካትዘንበርግ)፡ በፊልም ኩባንያ ድሪምወርክስ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ካትዘንበርግ፤ ባለ መዋኛ መኖሪያ ቤቱ $3.3 ሚሊዮን ያወጣል። 7. (ላሪ አሊሰን)፡ የኦራክል ኩባንያ መስራች በአለማችን 5ኛው ሃብታም አሜሪካዊ ነው። ሃብቱ $43 ቢ ይገመታል። አምና 9 መኝታ ቤቶች ያሉት ባለ3 ፎቅ መኖሪያ ቤት የገዛው በ$37 ሚሊዮን ነው። በአካባቢው ከ10 በላይ ቤቶችን ገዝቷል። 8. በሬስቶራንት ስራ ሚሊዮነር የሆነው ፒተር ሞርተን ከ15 አመት በፊት በገዛው መሬት $3.4 ሚሊዮን የሚያወጣ የተንጣለለ ቤት አለው።

9. ከሆሊውድ የመዝናኛ ንግድ ወደ ሬስቶራንት ቢዝነስ የገባው ሜር ቲፐር፣ አምስት መታጠቢያ ገንዳዎችን የያዘ ባለሁለት መኝታ ቤት ንብረቱን የገዛው ከ20 አመት ገደማ በፊት ነው። ዋጋው $2 ሚሊዮን 10. ከቢሊዮነሮች ተርታ የተሰለፈው ካናዳዊ ጀራልድ ሽዋርትዝ፣ ከአምስት አመት በፊት ሶስት ጎረቤታም ግቢዎችን ገዝቶ ያስገነባው ግዙፍ ቤት $19 ሚሊዮን ያወጣል። ጠቅላላ ሃብቱ $1.4 ቢሊዮን ነው። 11. በሙዚቃና በፊልም ቢዝነሶቹ ከአለማችን ሁለት መቶ ሃብታሞች መካከል አንዱ የሆነው ዳቪድ ጋፈን፣ 4 ግቢዎችን ገዝቶ በማዋሃድ ነው መዋኛ ገንዳ ያለው ቤት የገነባው። ዋጋው $6 ሚሊዮን ነው። ጠቅላላ ሃብቱ ደግሞ $6 ቢሊዮን። 12. ኢሊ ብሮድ ከ14 አመት በፊት በገዛቸው ሁለት ግቢዎች ላይ ያሰራው፣ መስተዋት የበዛበት ቤት $5.1 ሚሊዮን ያወጣል። በአሜሪካ ባሉት የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች $6.3 ቢሊዮን ባለሃብት ሆኗል።

Read 2692 times