Saturday, 20 April 2013 12:06

መፈክር አልባ ሰልፈኛ!

Written by  ቢኒያም ሐብታሙ
Rate this item
(1 Vote)

በቃ ጦቢያ እንዲህ ሰልፍ አፍቃሪ ሆና ትቅር? እውነቴን እኮ ነው፣ ለትንሽ ትልቁ መሰለፍ የዕለት ተዕለት ተግባራችን እየሆነ መጥቷል፡፡ ነጋዴዎች ገዢ ሲሰለፍላቸው፣ የመንግስት ሰራተኞችም ባለጉዳይ ሲደረደርላቸው ደስታቸው ነው፡፡ ይብዛም ይነስም ሁላችንም ባለችን አቅም ማሰለፍ እንወዳለን፡፡ መንግስትም ግለሰብም፤ ዕድርም ጠበልም … ያሰልፉናል፡፡ እግረኛም ሁኑ ባለ መኪና በቀን ውስጥ ትንሽም ብትሆን ሳትሰለፉ የምትውሉባት አጋጣሚ አትጠፋም፡፡ የትምህርት ቤት፣ የዳቦ ቤት፣ የማደያ፣ የቀበሌ አልያም ክ/ከተማ፣ የኢሚግሬሽን፣ የአውቶቢስ፣ የሲኒማና የቲያትር ቤት ሰልፍ፣ የታክሲ ሰልፍ…ብቻ ምን አለፋችሁ ሰልፍ በያይነቱና በየቦታው ሞልቶላችኋል፡፡ አንዳንዴ ሳስበው መንግስትም ሰልፉን እያየ መፍትሄ የማይፈልገው … ይሄ ህዝብ የ “ሰላማዊ ሰልፍ” ረሃቡን ይወጣ” እያለ ይመስለኛል፡፡ ችግሩ ግን መፈክር አልባ ሰልፍ መሆኑ ነው፡፡ መፈክር የሌለው ሰልፈኛ! የጦቢያ ሰው መቼም ስም አወጣጡ የሚገርም እኮ ነው፡፡ የሀበሻ ወላጅ ለልጁ ሰልፉ፣ ሰልፍነሽ፣ ሰልፏ እያለ ሁሉ ስም ያወጣል፡፡ ውሸት እንዳይመስላችሁ፡፡

የድሮ ሰራተኛችን ስሟ ሰልፏ ነበር፡፡ እርግጠኛ ነኝ Line ወይም Queue ብሎ ለልጁ ስም የሚያወጣ ፈረንጅ አይኖርም፤ ካለም ወይ ኢትዮጵያዊ ያገባ አልያም ኢትዮጵያ የገባ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ወግ ትዝ አለኝ፡፡ ሴትየዋ ከሰፈር ሰው አይስማሙም አሉ፤ በቃ በትንሽ ትልቁ ከሰው የሚናቆሩ፣ ከጐረቤት የሚሰዳደቡ ቢጤ ስለሆኑ የአካባቢው ሰው ሁሉ አግልሏቸዋል፡፡ ታዲያ የውሻቸውን ስም ምን ብለው እንዳወጡለት ታውቃላችሁ? “ምን ሊጐዱህ” እናም ግቢያቸው ውስጥ ሆነው ጐርደድ ጐርደድ እያሉ ለጐረቤት በሚሰማ ድምጽ ጮክ ብለው “ምን ሊጐዱህ … ምን ሊጐዱህ” እያሉ ይጠሩታል፤ “ናስቲ ምን ሊጐዱህ…ምን አባታቸውንስና ነው! ማነው የመታህ? ደግሞ አይዞህ!” እያሉ ያባብሉታል፣ ያሻሹታል -የራሳቸውን ስሜት በውሻቸው አስመስለው… በነገራችን ላይ ይሄን ሁሉ ወግ የት ሆኜ እንዳውጠነጠንኩት ታውቃላችሁ? (አታውቁም! እዚሁ ገርጂ የቦሌ ድልድይ ጋ የታክሲ ወረፋ ቆሜ እየጠበቅሁ ነው፡፡ ሰልፉ ረጅም ስለሆነ ረጅም ሃሳብ አሳስቦኛል፡፡

ለዚያውም በጠዋት ተነስቼ፣ ከፊል “ደመናማ” ሆኜ … ማለትም ከፊል እንቅልፋማ ሆኜ ነው፡፡ ይሄ የታክሲ ሰልፍ የሚባል ነገር ከመጣ በኋላ እንቅልፌን በአግባቡ ሳልጠግብ እየተነሳሁ ተቸግሬያለሁ፡፡ እርግጥ ነው ሰልፉ ለሴቶች፣ ለህፃናትና ለአቅመ ደካሞች ፍትሃዊ አሰራር የፈጠረ ቢሆንም ለእንደኔ አይነቱ ጐረምሳ ግን ጠዋት ጠዋት የምሰራትን ፑሻፕ ከንቱ አድርጎብኛል፤ ምክንያቱም ሰልፍ ላይ ግፊያ የለማ! ግፊያ ከሌለ ደግሞ አቅሜን አላሳይም፡፡ በአንድ በኩል ይህ ሰልፍ በመጀመሩ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ እንዴት? አትሉም፣ በቃ ታክሲ ለመያዝ ስትጋፉ ስልኮቻችሁንና ዋሌቶቻችሁን ላጥ የሚያደርጉ ሌቦች አፈር በላቸዋ! ግርግር ለሌባ ይመቻል አይደል የሚባለው፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ ‘የታክሲ ግፊያ ሌቦች’ በአሁኑ ሰዓት አጭር ስልጠና እየወሰዱ ነው፤ ስልጠናው ‘የሰልፍ ላይ መንጩ’ የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን የስልጠናውም ዋና አላማ ስነ-ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ እንዴት ወደ ኪስ ተገብቶ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን መስረቅ እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ተግባራዊ ስልጠና መሆኑን ያልታመኑ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ካሁን በኋላ በግርግር አትሰረቁም ማለት ነው፤ ይልቁንም በእርጋታና በስነ-ሥርዓት እንጂ፡፡ የታክሲ ሰልፍ በእኔ አተያይ እንደሌሎች ተራ ሰልፎች አይደለም፡፡ እንደውም ከተራ ሰልፍነት በዘለለ አያሌ ጥቅሞችን ሊያስገኝ የሚችል ነው ባይ ነኝ፡፡

ከአያሌ ጥቅሞቹም መካከል አንዱ የስራ ዕድል ፈጣሪነቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ግንባር ቀደም ወጣቶች በቀድሞ አጠራራቸው የመንደር ቦዘኔዎች በቅርቡ ‘ህዳሴ የታክሲ ላይ ወረፋ ያዦች የህብረት ስራ ማህበር’ በሚል ተደራጅተው ወረፋ በመያዝ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያከራዩ … (አሃ! ይሄ ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢ ያስብላቸው ይሆን እንዴ?) እንደሚሸጡ ይጠበቃል፡፡ ታዲያ ወረፋውን ከፍሎ ያስይዘ የኔ አይነቱ እንቅልፋም ሀሳቡን ጥሎ ለጥ ብሎ፣ ስልክ ሲደወልለት ብቻ ጎርደድ ጎርደድ እያለ መጥቶ ታክሲው ውስጥ መግባት ነው፡፡ ያው የቀረው ተሰላፊ ደግሞ እንደተለመደው “እንዴ! ምንድነው እኛ ተሰልፍን የለ እንዴ?!” ምና ምን … ምና ምን … ጉሩምሩምታ ሲያሰማ ቀብራራው እኔ “ዝም በል ባክህ! ከፍዬ እኮ ነው ሰልፍ ያስያዝኩት… እንዳንተ በነፃ የተሰለፍኩ መሰለህ እንዴ” ብዬ ይህንን ግሳፄና ክፍያ የሚፈራውን የሃበሻ ልጅ ውሃ አደርገዋለሁ፡፡

ቁጥር ሁለት የስራ ዕድል ደግሞ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ጥቃቅንና አነስተኛ ካፌዎች ሊፈጠሩ የሚችሉበት አጋጣሚ መኖሩ ነው፡፡ ‘ይቻላል ቁርስ ቤት’ አይነት ሱቅ በደረቴ ቁርስ ቤቶችን ጠብቁ፡፡ ይሄ መንገድ ላይ መፀዳዳት እንጂ መመገብ አይሆንለትም እየተባለ የሚሞካሸው ማህበረሰባችንን ቀለል ያሉ ቁርሶችን … እንደ ሻይ በዳቦ አጫጭር ሰልፎች ላይ፤ እንዲሁም ከፉል እስከ ፍርፍርን ደግሞ ረጃጅም ሰልፎች ላይ በመሸጥ በጊዜ እጥረት ሳይሆን በእንቅልፍ እጦት የተነሳ የአመጋገብ ባህሉን እንዲያዘምን ማድረግ … በዚያውም የትላንት “የሰፈር ቦዘኔዎች”ን የዛሬ ግንባር ቀደም ነጋዴ ወጣቶች እንዲሆኑ ማገዝ … በነገራችን ላይ የታክሲው ጉዞ ከሚፈጀው ጊዜ ይልቅ የሰልፉ ርዝመት ስለሚበልጥ ድርጅቶች፤ ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን በሬዲዮ ከሚያስተዋውቁ ይልቅ እነዚህ ሰልፎች አካባቢ ተንቀሳቃሽ ቢልቦርድ በማቆም ወይም ፍቃደኛ ተሰላፊዎችን ማስታወቂያ በማስያዝ ቢያስተዋውቁ፣ ይበልጡኑ ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡

ሰልፎቹ ሊያስገኙ የሚችሉትን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በጥቂቱ ከላይ ለመግለፅ ሞክሬአለሁ፡፡ እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ልለፍ፡፡ እነዚህ ሰልፎች ህዝቡ ስለ ኑሮ ውድነቱ፣ ስለ ፖለቲካው፣ ስለ አገር ልማቱ፣ ስለ ገቢ መቀነስ ስለ ሆድና መንገዶቻችን መስፋት ወዘተ የሚማከርባቸውና የሚያማርርባቸው መድረኮች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶች ቀልዶችን የሚሰነዛዘሩባቸውና የሚዝናኑባቸው፣ ባስ ሲልም የሚጠባበሱባቸው ቦታዎች ሆነዋል፡፡ ወደፊት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የታክሲ ወረፋ ወደያዙ ሰልፈኞች መጥተው ቢቀሰቅሱ ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፓርቲዎች በመኪና እየዞሩ ቤንዚንና ጎማቸውን ከሚጨርሱ እነዚህ ሰልፎች ጋ ቆመው ቢቻል ኩኪስና ሃይላንድ እያደሉ፣ ካልሆነም ደግሞ አበል እየሰጡ መፈክር ቢያሲዙንና የምረጡኝ ሲንግላቸውን ቢለቁብን ሰልፋችን አንድም አሰልቺ፣ አሊያም መፈክር አልባ አይሆንም እላለሁ፡፡ በሉ ሰልፌ ደርሶ ታክሲ ውስጥ ገብቻለሁ፤ ቸር ሰንብቱ፡፡ ሰልፍ ለዘላለም ትኑር!

Read 2455 times