Saturday, 20 April 2013 11:54

“ኢህዴግን የመሰለ ፓርቲ በአፍሪካ የለም” አቦይ ስብሃት ነጋ

Written by 
Rate this item
(10 votes)
  • ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ፓርቲነት ባህሪም፣ ይዘትም፣ ቅርፅም የላቸውም
  • አስመራ ያለው ፀሃይ የጠለቀችበት ጠንቀኛ መንግስት ነው
  • ከመለስ በኋላ ህወሓት ተቀባይነት አጥቷል የሚባለው ስህተት ነው

የህወኃት መስራች እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አለማቀፍ የሠላምና ልማት ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቦይ ስብሃት ነጋ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ላቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡

የመለስን ፋውንዴሽን በአዋጅ ማቋቋም ለምን አስፈለገ? የመንግስትን ጣልቃ ገብነት እንዴት ያዩታል? 54ሺ ሰማዕታት እያሉ እንዴት ለአቶ መለስ ብቻ ተለይቶ ፋውንዴሽን ይቋቋማል የሚሉ ወገኖች አሉና የእርሶ ምላሽ ምንድን ነው? በአፍሪካም በሌላም በሰው ስም የተቋቋሙ ፋውንዴሽኖች አሉ፡፡ እንዴት እንደተቋቋሙ አላውቅም፡፡ የመለስ ፋውንዴሽን በመንግስት አዋጅ መቋቋሙ ተገቢ ባይሆን ኖሮ የኛ ሰዎች አያደርጉትም ነበር፡፡ ለመሆኑ የሚከለክል ሕግ አለ ወይ? 54 ሺ ሰማዕታት ምናልባት የትግራይ ሰማእታት ብቻ ነው ሊሆኑ የሚችሉት፡፡ የአሁኒቱ አዲሲቱ ኢትዮጵያ፣ መላ ህዝቦች የጠራ ኢትዮጵያዊ ኘሮግራም ባይኖራቸውም፣ ከዚህ የከፋ የለም በማለት ማእከላይ መንግስትን የተዋጉበት ዘመንና የከፈሉት የንብረትና የህይወት ዋጋ የሚታወቅ ይመስለኛል፡፡

ከዚህ የከፋ ሲኦል የለም ብሎ ያለ ብቁ መሪ ሲፋለም የሞተውም ሰማእት ነው፡፡ ለነዚህ ሰማእታት በየክልሉ መታሰቢያ የተሰራላቸውም እየተሰራላቸውም ያለ ይመስለኛል፡፡ አልተረሱም፡፡ እነዚህ በየክልሉ ያሉ መታሰቢያዎች የመለስም መታሰቢያዎች ናቸው፡፡ የመለስ ፋውንዴሽንም የሁሉ የሃገሪቱ ሰማእታት ፋውንዴሽን ነው፡፡ ነጣጥሎ ማየት ሳይንሳዊም ፍትሃዊም አይደለም፡፡ ሁሉም ሰማእታት መንፈሳዊና ህሊናዊ ግንኙነት አላቸው፡፡ ለመላ የአትዮጵያ ህዝብም ዘልአለማዊ የህዝባዊነት ሃይል መልእክት እያስተላለፉ ይኖራሉ፡፡ አሁን የሚያሰጋው የመለስ ራእይ እንደቁምነገር ሳይሆን እንደመፈክር ይዞ በጥገኝነት ተዘፍቆ የነበረው እንደ መደበቂያ፣ አዲሶች ሊጨማለቁ የፈለጉ ደግሞ እንደ መታወቂያ ይዘው፣ ለአመታት ተዘፍቀንባቸው የነበሩ ችግሮችን እንዳንፈታ፣ እንደመጋረጃ እንዳይጠቀሙበት ነው፡፡ በታሪክ መኖር ባህላችን ነውና፡፡ ኢህአዴግ አንድ ውህድ ፓርቲ መሆን አለበት የሚሉ ሃሳቦች አሉና በእርሶ በኩል ያለው እይታ ምንድን? ኢህአደግ ስሙ እንደሚያመለክተው አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ኘሮግራም ይዞ የተነሳ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡

የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን በልማታዊ መስመር እየመራ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ካፒታሊዝምን በመላ ኢትዮጵያ ለማስፈን ነው ዓላማው፡፡ ይህ እንደህልም እናየው የነበረና፤ በሌላ አገር ስናየውም ስንቀናበት የነበረ የማንነታችን ታላቅ የእድገት ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ህልም የሚመስል ግን ሊፈፀም እንደሚችል ምልክት የታየበት የካፒታሊስት ስርዓት፣ ተጠቃሚ ሆነው በቆራጥነት ሊታገሉ የሚችሉት አርሶ አደሩ፤ አነስተኛው ባለሃብትና አብዮታዊ ምሁራን ናቸው፡፡ እነዚህ አራቱ መደቦች የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መሰረቶች ናቸው፡፡ ልማታዊው ባለሃብትንም እንደቆራጥ አጋር ይወስደዋል፡፡ ይህ መደብ በሂደት ሃላፊነቱን በወሳኝነት እየተረከበ ይሄዳል፡፡ አሁን ግን በጥራትም በብዛትም ደካማ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ሁኔታ እያለም በካፒታሊዝም ግንባታና ዲሞክራሲን በማስፈን ረገድ ሚና አለው፡፡ በኢትዮጵያ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ /የካፒታሊዝም ስርዓት ግንባታ/ ነቀርሳ የሆነው ጥገኛው ነው፡፡

የጥገኝነት አመለካከት በተግባር የሚገለፀው እጅግ በጣም ብዙ በሆኑ መንገዶችና አግባብ ነው፡፡ እጅግ በጣም የህዝብ፣ የሃገር ጠላት ተደርጐ ነው መወሰድ ያለበት፡፡ የጥገኝነት አመለካከትና ተግባር በባለስልጣን ይሁን በባለ ሀብት፤ አገር በመበታተን አይን ቢታይ ከውጭ ወራሪ የባሰ ነው፡፡ ስለዚህ አደረጃጀቱ በግንባር ይሁን በውህድነት፤ የሚለው የመልክ ለውጥ እንጂ የአሰላለፍና፤ የፖለቲካ ይዘቱን አይቀይረውም፡፡ ጉዳዩ በጉባኤው ተነስቶ ይጠናል ተብሏል፡፡ ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ግን የአብዮቱ ሃይሎች በመሉ በኘሮግራሙ ዙርያ ፀረ ጥገኝነት ማሰለፉና ጥገኝነትን መቆጣጠሩ ነው፡፡ እግረ መንገድ በኘሮግራም ደረጃ የኢህአዴግን የመሰለ የጠራና የወቅቱን የሃገር የእድገት ችግሮች የሚፈታ ኘሮግራም ያለው ፓርቲ በአፍሪካ የለም፡፡

በፓርቲ ብቻ ሳይሆን በመንግስት ባህሪ ደረጃም ኢህአዴግ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የዚህን ብርቅና የላቀ ድርጅት፣ የአደረጃጀት መልክ ከማየት በፊት፣ ኘሮግራሙን ማወቅና ለተፈፃሚነቱ ቅድሚያ መስጠት ይሻላል፡፡ ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ ህወሓት በትግራይ ህዝብ ያለው ተቀባይነት ቀንሷል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ብዙ የህዝብ እሮሮ እና የመልካም አስተዳደር እጦት በትግራይ ውስጥ ይታያል ይባላል፡፡ በክልሉ ባለው የስራ አጥነት ችግርም በርካቶች ወደ አዲስ አበባ እየተሰደዱ እንደሆነም ይነገራል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ? በትግራይ የተሰሩ በጐ ነገሮች አሉ፡፡ ግን እንደሌላው ክልል ስራ አጥነት፤የመልካም አስተዳደር እጦትና ሌሎች የጥገኝነት መገለጫዎች ድሮ መለስ እያለም ነበሩ፡፡ ከመለስ በኋላ አዲስ የመጡ ችግሮች አይደሉም፡፡ የህወሓት ኘሮግራም ብቁና በመሰረቱ የማይቀየር ነው፡፡ ድርጅቱ ከመለስ በኋላ ተቀባይነት አጥቷል የሚል አባባል ስህተት ነው፡፡ መጠናከር ግን ያስፈልገዋል፡፡ የመጠናከር ኘሮግራም በህወሓት በየወቅቱ እንደአስፈላጊነቱ የሚመጣ ኦፊሴላዊ ኘሮጀክት ነበር፡፡ ህወሓት እጅግ በጣም ታሪካዊ ድርጅት ስለሆነ፣ በይሉኝታ ምክንያት ድክመትን ደብቆ አድበስብሶ ማለፍ ባህሉ አይደለም፡፡ ከመጠናከር፤ ከመታደስ የሚያፈገፍግ ድርጅት አይደለም፡፡ በየወቅቱ አስፈላጊው ዋጋ እየተከፈለበት የመጣ ህዝባዊ ድርጅት ነው፡፡ ድሮም አሁንም የጥንካሬ ምንጩ አባላቱና ህዝቡ ናቸው፡፡

የህውሓት ከፍተኛ አመራር ውስጥ ባልና ሚስት በርከት እያሉ መሆናቸው “የቤተሰብ ፓርቲ” ያስብለዋል የሚሉ አሉ፡፡ ቀደም ሲል አቶ መለስ እና ባለቤታቸው፤ አሁን ደግሞ አቶ አባይ ወልዱና ባለቤታቸው የስራ አስፈፃሚ ቦታ ላይ መቀመጣቸውን መነሻ በማድረግ በዚህ ቅሬታ የገባቸው አካላት ህወሓት እያከተመለት ነው ይላሉ … ባለፉት ጉባኤዎች አምስት ባልና ሚስት በህወሓት ከፍተኛ አመራር ነበሩ፡፡ አሁን ያሉት ባልና ሚስት ሁለት ናቸው፡፡ “በርከት ብለዋል” የሚለው ጥያቄ ከየት እንደሚመጣ ለኔም ለሌላም የሚገባው አይመስለኝም፡፡ የአሁኑ ጥንዶች ለስራው ብቁ ታጋዮች ናቸው፡፡ ግን ደግሞ ብቃት ተነፃፃሪ ነው፡፡ ስለዚህ አልጠየከኝም እንጂ እኔ በበኩሌ (በግሌ) እነዚህ ሁለቱም ሆኑ ሌሎች ሳይተኩ የቀሩ (ጥቂቶች) ጭምር አሁን በወጡትና በሌላ አዲሶች መተካት ነበረባቸው፡፡ ግን ከፍተኛው የህወሓት አካል ጉባኤው፤ ስለመረጣቸው መቀበል ነው ያለብን፡፡

ብዙ ነገር አያጐድልም፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል? ህዝብ ከህዝብ የሚያጣላ፣ ህዝብን የሚፈራ ፀረ - ህዝብ የሆነ መንግስት ብቻ ነው፡፡ ህዝቦች የሚያፋቅር እንጂ የሚያጣላ ጥያቄ የላቸውም፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች አለመተማመን ካለ፣ ድሮ አዲስ አበባ የነበሩ መንግስታትና አሁን ደግሞ (ከነሱ የባሰ) አስመራ ያለው መንግስት የፈጠሩት ነው፡፡ በኢህአዴግ ዘመንም ቢሆን በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ በኢትዮጵያ የበላይነት ይዞ የነበረው፣ ከወላጆቹ የማይተናነስ የቀኝ ዘመም አርበኝነት/ ultra rightist patriotism/ አብሶት፣ የሰላም መፍትሄ ዕድል አልሰጥም ብሎ አስመራ ካልደረስኩ፣ አሰብን ካልያዝኩ ብሎ ነበር፡፡ ይህ አይነት አርበኝነት አሁን በኢትዮጵያ የለም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሃይል ህዝባዊና የሰላም ሃይል ነው፡፡ በርግጥ የኤርትራ ህዝብ ወንድም ህዝብ ነው ከሚል “አሰብ የኛ ነው” የሚል ጨርሶ ጠፍቷል ማለት አይደለም፡፡ ግን የተዳከመና ጊዜው ያለፈ ነው፡፡ ስለዚህ እንዳልኩት አስመራ ያለው ሃይል ፀሃይ የጠለቀችበት ጠንቀኛ መንግስት ነው፡፡

የኤርትራ ህዝብ ከዚህ ዓይነት ስርዓት ከተገላገለ፣ ኤርትራ ነፃነትዋን ይዛ ከኢትዮጵያ ጋር በጣም የጠበቀና ልዩ ግንኙነት የምታደርግበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ይህን የተዳፈነና የታመቀ የሁለቱን ህዝቦች ሃይል የሚያቆመው ምንም ነገር የለም፡፡ እኛ ከአካኪ ዘራፍ እንደተገላገልነው ሁሉ የኤርትራ ህዝብም መገላገሉ የማይቀር ነው፡፡ ይህ መሬት፣ ይህ ዳገት፣ ይህ ወንዝ … የሚባለው በህዝቦች ወንድማማችነት መተካቱን ሊያቆመው የሚችል ሃይል ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ጐረቤት ህዝቦች በፊት በሁለቱ ህዝቦች መካከል ልዩ ግንኙነት ይፈጠራል፡፡ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ ነው ስለሚባለው የሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት ምን ይላሉ? ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ ነው ከተባለ ወደ ሃያ ዓመት ይጠጋል፡፡ ግን እስካሁን ለምን ተሸርሽሮ አላለቀም? አሁን ያለው የግል ኘሬስ ባብዛኛው ፤አንዳንዶቹ እየተሻሻለ ነው ቢሉም፤ እኔ አልፎ አልፎ እንደማየው ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሃይማኖትም ሆነ በሌላ … ወገን ከወገን የሚያጣላ፤ ለአመፅ የሚሰብክ፤ ስለ ኢህአዴግ መጥፎ ነገር እንጂ ስለሃገሪቱ መሰረታዊ፤ ታሪካዊና ባህላዊ ጉዳዮችና ሌሎች ማነቆዎች ብዙም የማያነሳ ነው፡፡ ከፓርቲ ጉዳይ ባሻገር ስለሃገራዊ ግንባታ ጉዳይ ብዙም ደንታ ያለው አይደለም፡፡

ስለ ሃይማኖት መቻቻል፤ ከታሪካችን የወረስናቸውና የእድገት ማነቆ ስለ ሆኑት ጠባብነት ፤ትምክህት፤ታታሪነት፤ባለሞያነት ወዘተ አይፃፍም፡፡ ባጭሩ መሰረታዊ የሆኑ ያገር ግንባታ ጉዳዮች የማይታይበት፤ ከዚህ አለፍ ብሎም ስለግለሰቦችና ስለአመፅ ወይም ደህና ከተባለ ስለኢህአዴግ መጥፎነት የሚጽፍ ነው፡፡ የሌሎች የአፍሪካ አገሮች የግል ኘሬስና የኛን ስናወዳድረው ፤ እነሱ የሌሎች አገርን ማእከል አድርገው ነው የሚፅፉት፡፡ ሃገራዊ ጥቅም ያስቀድማሉ፡፡ የኛ የግል ኘሬስ ደረጃው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ የሞያና የሃገራዊ አመለካከት ደካማነት ካለፈው ስርዓት የወረስነው ነው፡፡ የተከለከለ ስለነበር አልለመድንም፡፡ ለመብቃት ደግሞ ጊዜ ወሰደብን፡፡ ባጭሩ ግን በኔ እምነት፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዓመፅን የሚሰብኩ ሁሉ፤ ሃገራዊ ክህደት ስለሆነ አደጋ አያመጡም እየተባሉ በቸልተኝነት ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ ኘሮግራሙ የሆነ ይሁን ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ ለሚካሄደው የሃገር ግንባታ እንከን የሚፈጥር የግል ኘሬስና ፀሃፊዎችን መታገስ አይገባም፡፡ ኢህአዴግ ያለ ጠንካራ ተፎካካሪ በምርጫ መሳተፉ የመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ ላይ ያለው ተጽእኖ ምንድነው? ኢህአዴግ “ጠንካራ ተቃዋሚ” የለም ይላል፡፡?ኢትዮጵያ ውስጥ አስተዋይና ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የመገንባትና የመምራት አቅም ያለው ዜጋ ጠፍቶ ነው ወይስ በኢህአዴግ ጫና ሳቢያ ነው? የኢህአዴግ ሚና በዚህ ረገድ ምን መሆን አለበት? አሁን በኢትዮጵያ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ምናልባት አንድ ወይም ሁለት ይገኙ እንደሆነ እንጂ፤ በፓርቲ ምንነት አንፃር ካየናቸው ፤ የፖለቲካ ፓርቲነት ባህሪም ይዘትም ቅርፅም የላቸውም፡፡

አንድ ፓርቲ የሚገነባው ፖለቲካዊ ስርዓት በጥራት አስቀምጦ፤ የዚህ ስርዓት ሞተር ናቸው የሚባሉትን መደቦች፤ወይም መደብ ወይም የህብረተሰብ ክፍሎች ለይቶ በማስቀመጥና ከዚህ መደብ ወይም ወገን ጋር የጠበቀ ግንኙነት በማድረግ ነው፡፡ የኛ ተቃዋሚዎች በኢህአዴግ ጠላትነት ብቻ ነው የተሰለፉት፡፡ ወዳጃቸውን፣ ወገናቸውን፣ መሰረታቸውን፤ ሳይለዩ ጠላት ብቻ ያስቀመጡ ሰዎች (ቡድኖች) በየትኛው መለኪያ የተቃዋሚ ፓርቲ ስም ይሰጣቸዋል?ለምንገነባው ስርዓት ወዳጅ፤ ጠላት/ተቀናቃኝ/ ብሎ በመፈረጅ ነው ትግሉ መጀመር ያለበት፡፡ የሚገነቡት ስርዓት ምንድነው? የሚገነቡት ስርዓት ተቃናቃኝ ማነው? ተሰላፊ ወዳጅስ ማነው? የትኛው መደብ ወይ የትኞቹ መደቦች ናቸው ወዳጆች ?ባጭሩ በኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ የሚጠራቀሙት የተለያየ ቅሬታና ፍላጐት ያላቸው፣ በመሰረታዊ አመለካከት የማይገናኙ ግለሰቦች ናቸው፡ የኔ ጥያቄ ሁኔታቸው በሂደት እየመነመነም ቢሆንም ለምን ይህን ያህል ጊዜ በሚያሳዝን ሁኔታ ቆዩ የሚለው ነው፡፡ እኔ ለዚህ ጥያቄ ያሉኝ መልሶች ሶስት ናቸው፡፡ አንዱ በኢህአዴግ ውስጥ ያለ የጥገኝነት አመለካከትና ተግባር የሚያስጐመጃቸው ይመስለኛል፡፡ ስልጣን ብንይዝ በወገን የመስራት፤የመስረቅ ወዘተ ወዘተ እድል ይኖረናል ከሚል ያለአግባብ የሚያበለፅግ ወንበርን አሻግሮ የማየት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ የመጣ ይምጣ፣ ሸምጥጦ መብላት፤ በወገን ለወገን አለአግባብ መስራት፤ ፍርድ ማዛባት የለም ብሎ ኢህአዴግ ደረቅ የስራና የልፋት፤ የህዝባዊ ውጤት ወንበር ብቻ ያሳያቸው፡፡

ሁለተኛ በህዝቡ በተለይ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መሰረት በሆኑ መደቦች፤ የጥገኝነት አመለካከትና ተግባርን በቅፅበት የሚያቃጥል እሳት መለኮስ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አሁን ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እሳት ይበላቸውና፣ ሕብረ ብሄር ልማታዊ ፓርቲ፤ ባለሃብቱና ላብ አደሩ በየፈርጃቸው እየተደራጁ፣ ቀስ በቀስ እያደጉ ወደ ስልጣን ይጓዛሉ፡፡ በመርህ ደረጃ የኢህአዴግ ዓላማም ፍላጐትም ይህ ነው፡፡ አሁን ያሉ ወንድሞቻችንና ጓደኞቻችን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ ከኤምባሲ ወደ ኤምባሲ ከመንከራተትና ከውርደት ይገላገላሉ፡፡ ሶስተኛ መፍትሄ፤ የምርጫ ቦርድ ስለፓርቲ ምንነት አጥንቶ፣ ደረጃውን የጠበቀ የፓርቲ መስፈርት ቢያወጣና ቢያስተካክል ሁሉም ወደየስራቸው ይገባሉ፡፡ በነገራችን ላይ በዓለም ላይ ከጥይት፣ ከዱላ፣ ከግድያ፣ ከእስራት… ውጭ በዲሞክራሲያዊ አግባብ ያደገ ካፒታሊዝም የለም፡፡ እንደነሱ እንሁን ማለቴ ግን አይደለም፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እየተፈጠረ ያለው የብሔር መፈናቀል፣ ብሔር ተኮር የሆነው የአገሪቱ ፌዴራሊዝም ውጤት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርሶ ምን ይላሉ? በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ የሚደረገው መፈናቀል ከፌደራሊዝም ጋር ግንኙነት ያለው አይመስለኝም፡፡ ጉዳዮቹን በዝርዝር አላውቃቸውም፡፡ መንስኤው ግን ሁለቱ ክልሎች ትኩረት ሰጥተው አለማየታቸው ይመስለኛል፡፡ መንስኤው ይህም ይሁን ሌላ በምንም ዓይነት መልኩ መሆን ያልነበረባቸው መጥፎ አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ የሆኖ ሆኖ መንግስት እርምጃ እየወሰደ ያለ ይመስለኛል፡፡

ከእንግዲህ ወዲህ የሚያጋጥም አይመስለኝም፡፡ የኢህአዴግ አንጋፋ መሪዎች በአዳዲሶች እየተተኩ ነው፡፡ ይሄ መተካካት አንጋፋዎቹ ላይ የፓርቲ ህልውና ስጋት ይፈጥርባቸው ይሆን? መተካካት በፊት የነበረና አሁንም ያለ ባህርያዊ ጉዞ ነው፡፡ ኢህአዴግ መሰረቴ ካላቸው መደቦች ውስጥ በትግል ተወልዶ በትግል እያደገ፤ በህዝብ ፊት ውጤት እያስመዘገቡ ለሚመጡ ካድሬዎች አመራርን እየተኩ እንዲሄዱ የሚያስችል አሰራር አለው፡፡ ላስቀረው ልወርውረው ብለህ እንደፈለክህ ልታደርገው የማትችል ሃይል ገንፍሎ ከታች ቢመጣ በአስተዳደራዊ እርምጃ ሳይሆን በሂደት የሚመጣ ሃይል ነው ተኪ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ተኪ ሃይል በተደራጀ ሂደት እንጂ በጓዳ አይፈጠርም ማለቴ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ከአምናው አመራር የዘንድሮው አመራር የሚበልጥ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ከዘንድሮም አመራር የነገው የበለጠ እየሆነ ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም ካለፈው ትግል ቀጣዩ ትግል ነው ከባድና ረቂቅ የሚሆነው፡፡ ከራሱ የበለጠ የአመራር አካል የማይፈጥር አመራር ሲመራ አልነበረም ማለት ነው፡፡

ጨረታ ሲገመግም ነበር ማለት ነው እንጂ ሲመራና ሰው ሲያፈራ አልነበረም ማለት ነው፡፡ አሁን ያልካቸው የተተኩ አንጋፋ አመራር የሚሰጋቸው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ላመኑበት ፖለቲካዊ ኘሮግራም በፅኑ እምነት የተሰለፉ ስለነበሩና አሁን በዚያኛው ፅናት ስለሚያምኑበት፣ ድርጅቱ በፈቀደው በሌላ መንገድና አግባብ ትግሉን እንደሚቀጥሉበት ያምናሉ፡፡ በእምነት ተገቢው ግለት የሌላቸው አንዳንድ አንጋፋዎች ካሉም /ያሉም አይመስለኝም/ ለማንኛውም የድርጅት ድክመት ተጠያቂ ስለሚሆኑ ተጠያቂነታቸው ይገፋፋቸዋል፡፡ ስለዚህ የሚያሰጋቸው ነገር ፍፁም የለም፡፡ ለነገሩ አንጋፋዎቹ ወኔያቸው ስለማያስተኛቸው ነው እንጂ፣ አዲሱም አመራር የተለመደውን ድርጅት የማጠናከር ኘሮጀክቱን ቀርፆ፣ የማያሰጋ ሁኔታ ራሱ ይፈጥራል፡፡ የአንጋፋ መሰለፍ ተጨማሪ ነው፡፡

Read 8008 times