Saturday, 20 April 2013 11:43

“አዛኝ ሞግዚት ልሁንላችሁ“ የሚል መንግስት፤ “ጨካኝ አምባገነን” ለመሆን የተዘጋጀ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ1994 እስከ 1999ዓ.ም የነበረው ኢህአዴግ፣ ካፒታሊዝም የህልውና ጉዳይ ሆኖበት የቢዝነስ መሰናክሎችን አስወግዷል ከ2000 እስከ 2005 ዓ.ም ያለው ኢህአዴግ፣ ሶሻሊዝም የእምነት ጉዳይ ሆኖበት በርካታ መሰናክሎችን በዘመቻ ተክሏል ባለፉት አስር አመታት በኢህአዴግ ላይ ካየናቸው ሁለት ተቃራኒ ባህርያት ጋር የሚመሳሰል በአንድ ሰው እውነተኛ ታሪክ ላካፍላችሁ። ተራ ታሪክ አይደለም። የስመጥር ገናና ሰው ታሪክ ነው። በጊዜው ብዙ የተነገረለትና አለምን አጃይብ ያሰኘ ታሪክ! ታሪኩ ከእንግሊዝ ስኮትላንድ የሚጀምረው አስደናቂ ታሪክ፣ ወደ አሜሪካ ኢንዲያና የሚዘልቀው በታላቅ ክብር ነው - አወዳደቁም በዚያው ልክ “እጅግ ታላቅ” ሆነ እንጂ። በዚሁ ታሪክ ውስጥ ነው፤ “አዲስ ህብር (new harmony)” የተሰኘች ከተማ የተፈጠረችው።

“በሰማዬ ሰማያት በኤዶም ገነት” ውስጥ ምን አይነት ህይወትና ማህበረሰሰብ ሊኖር እንደሚችል፣ ብዙ ብዙ መላምቶች እየተሰነዘሩ ብዙ የምናብ ምስሎች መፈጠራቸው ይታወቃል። “አዲስ ህብር” ግን እዚሁ ምድር ላይ ነው - የሰማየሰማያት የገነት ህይወትን፣ እዚሁ አለም ውስጥ በእውን ለማሳየት የተፈጠረ አዲስ ከተማ! አዲስ ፕሮጀክት! አዲስ የህይወት አቅጣጫን የሚያውጅ፤ ለአዲስ አለማቀፍ ስርዓት የማንቂያ ደወል የሚያስተጋባ የእኩልነት ማህበረሰብ በምናብ ብቻ ሳይሆን፣ በአካል እውን የሚሆንበት ጊዜ ደረሰ። የዚህ ራዕይ ባለቤት ሮበርት ኦውን ይባላል። እንግሊዛዊ የኢንዱስትሪ ባለቤትና አንቱ የተባለ ሃብት ነው - ሮበርት ኦውን። ጊዜው 1817 ዓ.ም ነው - ብዙዎች የሚናፍቁት የ“ገነት ሕይወት” እዚሁ ምድር ላይ እውን የሚሆንበት አመት። ብዙም ሳይቆይ ነው፣ የሮበርት ኦውን አድናቂዎችና ተከታዮች፣ ለዚህ ግሩም ራዕይ መጠሪያ ያወጡለት፤ ሶሻሊዝም ብለው ሰየሙት። ካፒታሊስቱ ትርፋማ የቢዝነስ ሰው በስኮትላንድ የተቋቋመውና የተስፋፋው የኦውን ኢንዱስትሪ፣ በዘመኑ እጅግ ስመጥርና ታዋቂ ነበር፤ በዝና የሚስተካከለው አልነበረም።

አዳዲስ የምርት ማሽኖችን በማዘጋጀትና ስልጡን የአመራረት ዘዴ በመፍጠር እጅግ ትርፋማ ለመሆን የበቃው የኦውን ኢንዱስትሪ፣ ለባለንብረቱ በሃብት ላይ ሃብት ደርቦለታል። ለሰራተኞቹም አስገራሚ ለውጥ አስገኝቷል። የኦውን ሰራተኞች እንደሌሎች ሰዎች፣ ከንጋት እስከ ምሽት አይለፉም። በድካም እስኪዝሉ ድረስ አይሰሩም። ውጤታማ ስራ የሚያከናውኑት ለተወሰነ ሰዓት መሆኑን በመገንዘብ፤ የስራ ሰዓት እንዲገደብ አድርጓል። ሰራተኞች ሲታመሙ፣ ደሞዝ አይቆረጥባቸውም። ቶሎ አገግመው ወደ ስራ መመለስ የሚችሉት መታከሚያ ገንዘብ ሲኖራቸው ነውና። ሁለት ሺ ለሚደርሱ ሰራተኞቹም በወቅቱ እጅግ አስደናቂ የሚባሉ ባለሶስት ፎቅ የመኖሪያ ቤቶችን አሰርቷል። ታዲያ ነዋሪዎቹም በኮንዶምኒየም ቤቶቹ ውስጥ ለመኖር የድርጅቱን ደንቦች ማክበር ይኖርባቸዋል። ደረቅ ቆሻሻ በስርዓት መያዝና በትክክለኛው ቦታ መድፋት፣ የገላና የልብስ ንፅህናን መጠበቅ፤ ልጆችን ማስተማር… አለመስከር ወዘተ። ዝናው ከዳር እስከ ዳር ቢናኝም ኦውን በዚህ አልረካም። ራዕዩን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ወደ አሜሪካ ተጓዘ።

ያኔ አሜሪካ፣ ገና ሃምሳ አመት ያልሞላት አዲስ አገር ነች - መሬት እንደ ልብ የሚገኝባትና በጥንታዊ ባህሎች ያልተተበተበች። አዲስ ራዕይን ለመሞከር ትመቻለች። በእርግጥም፤ የኦውን ዝና እጅጉን የደመቀ በመሆኑ፣ ራዕዩን ለማስተዋወቅ አልተቸገረም። የአሜሪካ ፕሬዚደንት በተገኙበት፣ የአገሪቱ ከፍተኛ የህግ አውጪ አካላት (ኮንግረስና ሰኔት) በጋራ ስብሰባ ተጠርቶ፣ ኦውን ራዕዩን አስረዳ። ራዕዩን በተግባር ለማሳየትም፣ በኢንዲያና ግዛት በድንቅ ህንፃዎች የተገነባች ትንሽ ከተማ በራሱ ገንዘብ ገዛ። ሶሻሊስቱ የህዝብ አገልጋይ በኢንዲያና የጀመረው የ“አዲስ ህብር”ፕሮጀክት ከቀድሞው የስኮትላንድ ሙከራ በእጅጉ ይለያል። አዲስ ህብር፣ ሙሉ ለሙሉ “እውነተኛ የእኩልነት ማህበረሰብ” እንዲሆን የወሰነው ኦውን፤ የሚያምሩ 160 ህንፃዎችን ያካተተ ከተማና በዙሪያ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ ለም መሬት ገዝቶ አዘጋጀ። እናም “አዲስ ህብር” የተሰኘ ማህበረሰብ ለመመስረት የሚፈልጉ ሰዎች እንዲመጡ ጋበዘ። አላሳፈሩትም። ጥሪውን የሰሙ 800 ሰዎችና ቤተሰባቸው ወደ ከተማዋ ጎረፉ። በተለይ ደግሞ፣ በሶሻሊዝም ሃሳቦች የተማረኩ ምሁራን እንዲሁም በእውቀትና በችሎታ የመጠቁ ሰዎች፣ እጅጉን ደስተኞች ነበሩ። “ተስማሚ መጠለያ” ለሁሉም በነፃ ተሰጠ። “ትምህርት” ለሁሉም በነፃ ተጀመረ። ማንም ሰው በምግብ አይቸገርም ተባለ - ደግሞም ለእርሻ የሚሆን ለም መሬት ሞልቷል፤ ማንም አርሶ እህል ማምረት ይችላል። ራዕዩ እውን መሆን ጀመረ - “የገነት ማህበረሰብ” እዚህችው ምድር ላይ ሀ ብሎ ተጀመረ።

እንዲያም ሆኖ፤ ኦውን ገና የልቡ አልደረሰለትም። ሁሉም ነገር በነፃ የሚዳረስበት የእኩልነት ማህበረሰብ ሙሉ ለሙሉ ያለ አንዳች እንከን እውን ሆኗል ብሎ ለመናገር ጥቃቅን እንቅፋቶች ነበሩ። የከተማዋ ነዋሪዎች በየግላቸው እያረሱ ነበር ለየግላቸው እህል የሚያመርቱት። የቤት ቁሳቁስም እንዲሁ። ለዚህም ነው፤ ኦውን ከሁለት አመት በኋላ፤ የግል ንብረት የሚባለውን ነገር ጨርሶ ማጥፋት አለብን ያለው። የከተማዋ ነዋሪዎች አልተቃወሙም። በሆታ ደገፉት እንጂ። “ሁሉም ምርትና ንብረት፤ የሁሉም የጋራ ምርትና ንብረት ይሁን” ተብሎ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተወሰነ። የአዲሱ ራዕይ ዋነኛው ቁልፍ፣ የግል ምርትና ንብረት ማጥፋት ነው። እናም፤ የሁሉም ሰው ምርትና ንብረት ወደ፣ “የአዲስ ህብር ምርትና ንብረት ሆኗል” ተባለ። እህሉ፣ ከብቱ፣ እንጨቱ፣ ምጣዱ … ሁሉም ነገር ይሰበሰብና ለህዝቡ እኩል ይከፋፈላል። ያኔ ሁለት ችግሮች ተፈጠሩ። ሳይውል ሳያድር የሰዎችን ውሎ የሚቀይር አንደኛው ችግር፤ “ሁሉም ነገር የህዝብ ሆኗል፤ በእኩልነት ይከፋፈላል” በተባለ ማግስት፣ ከመጀመሪያው ክፍፍል አንስቶ የተፈጠረ ችግር ነው። የከተማዋ ነዋሪዎች የዘወትር ውሎ ተቀየረ። ዋነኛ ስራቸው፣ ለወረፋ ተሰልፎ መዋል ሆነ። ጨው ለማግኘት ሰልፍ፤ ቲማቲም ለማግኘት ሰልፍ፣ የኩራዝ ዘይት ለማግኘት ሰልፍ፣ ስንዴ፣ እንጨት… ከአንድ ሰልፍ ወደ ሌላው ሰልፍ ሲሯሯጡ መዋል! ከዚሁ ጋር አብሮም መቧደንና መጋጨት ተጀመረ።

“ለኔ ጅማት የበዛበት ስጋ ተሰጠኝ”፣ “ለጎረቤቴ ግን ቅልጥም ተሰጠው”፣ “በትውውቅ፣ በአድልዎ፣ በሙስና ተበደልኩ” … ወገን ለይቶ መሻኮትና መደባደብ መጣ። እንዲህም ሆኖ “አዲስ ህብር” ወዲያው አልፈረሰም። “ራስወዳድነት”ን የሚያወግዙና “ከራስ ጥቅም በፊት ለሌላው ሰው ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል” በማለት ነዋሪውን የሚገስፁ ፖሊሲ አውጪ ምሁራን ሞልተዋል። አብዛኛው ነዋሪም ያጨበጭባል። እንዲሁም፤ አዳዲስ የራሽን ክፍፍል ዘዴዎችን የሚቀይሱ ፖሊሲ አውጪ ምሁራን ሞልተዋል። ክፍፍሉን የሚያከናውኑ “የህዝብ አገልጋይ ቢሮክራቶችም” በየጊዜው እየተሻሩ ይመደባሉ። እናም ማህበረሰቡ በኑሮው ቀጠለ። የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ፈንጠዚያ ድራሹ ቢጠፋም፤ “ለሱ ከቀይ ስጋ፣ ለኔ ከልፋጭ፤ ለሱ ከሽንጥ ለኔ ቅንጥብጣቢ” እያሉ መጣላት እየቀረ መጣ። ስጋ ጠፋ። “ለሱ ነቀዝ የበላው ስንዴ፤ ለኔም እንክርዳድ የበዛበት ስንዴ” በሚል መጣላት መጣ። ይሄኔ ነው፤ ሁለተኛው ችግር አፍጥጦ የወጣው። ለካ እስካሁን አላስተዋሉትም እንጂ፤ ነገሮች ቀስ በቀስ እየተለወጡ መጥተዋል። ከከተማው ጎተራ እህል ለመከፋፈል የሚሰለፍ ሰው እንደወትሮው ብዙ ነው። እህል አምርቶ ወደ ከተማው ጎተራ የሚያስገባ ሰው ግን ቀስ በቀስ እየተመናመነ ከነጭራጩሹ መጥፋት ጀምሯል። ኦውን ያቋቋማቸው የጨርቃ ጨርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የእንጨት ወዘተ ፋብሪካዎችም ከአጀማመራቸው አልሆኑም። የደሞዝ ክፍያ ስለሌለ፣ “ታመምኩ፣ ቆረጠኝ፣ ፈለጠኝ” ብሎ የሚቀር ሰው በዛ።

በችሎታቸው ይታወቁ የነበሩ ሰራተኞችም፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከፋብሪካው ብቻ ሳይሆን ከከተማዋም ጠፍተዋል። እናማ፤ ምግብና ቁሳቁስ ፍለጋ የሚሰለፍ፣ የክፍፍል ፖሊሲ አርቃቂዎችና ውሳኔ ሰጪዎች፤ አስፈፃሚ ቢሮክራቶችና ሹመኞች አሉ፤ የሚከፋፈል ምርት እና አምራቾች ግን የሉም። ለካ፤ ብዙ ሰው በሆዱ ይዞ ዝም እያለ ነው እንጂ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማዋ የነዋሪዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል። በታታሪነታቸው ይታወቁ የነበሩ ጎበዝ ሰራተኞችና አምራቾች ከተማዋን ጥለው ሲሄዱ ከርመዋል። ሳይሰሩ ለመብላት የሚፈልጉ አጨብጫቢዎች፣ ቢሮክራቶችና ፖሊሲ አውጪዎች ብቻ ናቸው የቀሩት። ቅሬታ፣ ሃሜታ፣ ትችት ከየአቅጣጫው ቢሰነዘርም፣ ሮበርት ኦውን አንዳቸውንም ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም። በእርግጥ፤ ሰዎች ምንም አይነት ትችት እንዳይሰነዝሩ መከልከልና ማሰር አይችልም። አሜሪካ ውስጥ የማይቻል ነገር ነዋ። የመንግስት ስልጣን ቢኖረው ኖሮ፣ ችግሩን በቀላሉ ማስወገድ ይችል ነበር - ሶሻሊስት መንግስታት እንዳደረጉት ትችት የሚሰነዝሩ ሰዎችን ማሰርና በስፋት ፕሮፓጋንዳ ማካሄድ ነዋ። ኦውን ግን፣ ለእንዲህ አይነት አምባገነንነት “አልታደለም”። ቢሆንም ዝም አላለም። ልጆቹ ሳይቀሩ፤ “ይሄ ነገር ተበለሻሽቷል፤ ይሄ ነገር አያዋጣም” ቢሉትም፤ “በጭራሽ! ትልቅ እመርታ እያስመዘገብን ነው፤ ድል እየተቀዳጀን ነው፤ ሁሉም ነገር በታቀደለት አቅጣጫ እየሄደ ነው። አንዳንድ የአፈፃፀም ችግሮች ቢኖሩም፣ በቀላሉ በህዝቡ ሙሉ ተሳትፎ እንፈታቸዋለን” … የሚሉ አይነት ምላሾችን እያቀረበ ትችቶችን ውድቅ አድርጓቸዋል።።

“የአፈፃፀም ችግሮችን ያስወግዳሉ” ተብለው በህዝብ ተሳትፎ የተተገበሩ ከደርዘን በላይ መፍትሄዎች ግን፣ አንዳችም ውጤት አልታየባቸውም። በየወሩ ሲፐወዝ የቆየው ቢሮክራሲና እንደ አዲስ ሲዋቀር የከረመው የክፍፍል ስርዓት መፍትሄ አላስገኘም። ለ7 ጊዜ የተለወጠው የከተማዋ የሶሻሊዝም መተዳደሪያ ሰነድም ለውጥ አላመጣም። “እመርታ እያስመዘገብን ነው” በማለት እውነታውን ሲክድ የከረመው ሮበርት ኦውን፤ በዚህ ፕሮፓጋንዳው መቀጠል አልቻለም። አብዛኛው ነዋሪ፣ ከተማዋን ጥሎ ሄዷል። ግን “ስህተት ሰርቻለሁ” ብሎ አላመነም። የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ሶሻሊስታዊ ራዕይ መስዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኝነት የጎደላቸው ራስወዳዶች ናቸው ብሎ ወነጀላቸው። እሱ በሚያዛቸው መንገድ እንዲሰሩ ሊያስገድዳቸውና ሊያስራቸው አይችልም።

ለመላው አለም አዲስ ራዕይን ይፈነጥቃል የተባለውና “አዲስ ህብር” የተሰኘው የሶሻሊዝም ማህበረሰብ ሶስት አመት ሳይሞላው ፈራረሰ። በመላው አለም ዝነኛ ለመሆን የበቃ ታላቁ የኢንዱስትሪና የቢዝነስ ጥበበኛ ሮበርት ኦውን፤ በአንዲ ትንሽ ከተማ ውስጥ ተሸነፈ። የተለያዩ ቁሳቁሶችን በጥራትና በቅናሽ እያመረተ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ደንበኞች እያደረሰ ትርፋማ ለመሆን የቻለ፤ ከሁለት ሺህ ለሚበልጡ ሰራተኞች ከፍተኛ ደሞዝ እየከፈለ የቤተሰባቸውን ህይወት እንዲያሻሽሉ እድል የከፈተ ታላቅ ሰው ነው - ትርፋማውና ካፒታሊስቱ የቢዝነስ ሰው ሮበርት ኦውን። “አዲስ ህብር” በተሰኘው ማህበረሰብ ውስጥ፣ ግን ለዚያውም በርካታ ምሁራንና አዋቂዎች ከጎኑ ተሰልፈው እያሉ፣ አንድ ሺህ የማይሞሉ ቤተሰቦች ደህና ኑሮ እንዲመሩ ማድረግ ተስኖት ጉዞው በአጭር የተጨበት ደካማ ሰው ሆነ - ሃብት ንብረቱን መስዋዕት ያደረገ ሶሻሊስቱ የህዝብ አገልጋይ ሮበርት ኦውን።

Read 2920 times