Saturday, 20 April 2013 11:39

“አድሮ ቁልቁል” የምርጫ ጉዞ

Written by  በጃፋር ባሌማ
Rate this item
(0 votes)

እድሜ ለሰጠው በየቀኑ ታሪክ ሲሰራ፣ ታሪክ ሲሻር አልያም ሲደገም ማየት የተለመደ ነው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ረጅም ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ውስጥ የሚነገረው ታሪክ (ተረክ) የሚነፃፀርበት ክንውን መብዛቱ አይቀሬ ነው፡፡ የምርጫ ታሪካችን ግን ውሱን ከመሆኑም ባሻገር የቅርብ ጊዜ ትውስታን የሚያጭር ነው፡፡ (የንጉሱና የደርግ ጊዜ የይስሙላ ምርጫዎችን ትተን ቢያንስ ካለፉት ሁለት አስርት ወዲህ የተካሄዱ የምርጫ ሙከራዎች በተለይ የ1997ት ዓ.ም ብሄራዊ ምርጫን ያስታውሷል)

“የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት (Process) ጊዜ የሚፈልግና ውጣ ውረዶችን ማለፈ ግድ የሚል ነው” ከሚሉት ወገን ነኝ፡፡ የአንድ ሀገር ግንባታን ያህል ሁሉም የተሳተፉበት፣ በአመለካከት የተቀየረ ማህበረሰብን የሚፈልግ፣ የዓላማ ፅናትና የትውልድ ቅብብሎሽን የሚሻ የታሪክ ክስተት ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ምርጫ “በፍፁም ዲሞክራሲያዊ መንገድ ተከናወነ” ለማለት አያስደፍርም፡፡ የአውሮፓና አሜሪካ (በመቶ ዓመታት በሂደቱ የተጓዙት) አገራት ሳይቀሩ ምርጫ ሊጭበረበርባቸው ይችላል፡፡ አወዛጋቢ የታዛቢዎች ሪፖርት፣ አልያም የተዛባ የሚዲያ ሽፋንና የውጤት መግለጫ ያጋጥማል፡፡

ምንም ቢፈጠር ግን ሁሉም ነገር በህግና ስርአት እንዲፈታ ከመደረግ አያልፍም፡፡ በእኛ ሀገር ብልጭ ብሎ “ድርግም” ካለው ምርጫ 97 ወዲህ ነገሮች ሁሉ በተንሻፈፈ መንገድ ለመሄዳቸው ማስረጃዎችን መዝዞ ማየት ተገቢ ነወ፡፡ ከፍ ካለ ደረጃ ተሽቀንጥሮ ሊንኮታኮት የቀረበውን የምርጫ ስርአታችንንም መታደግ ይኖርብናል፡፡ በመነጋገር፣ በመወያየትና ሁላችንም በመለወጥ! ያለ ተፎካካሪ እውን ምርጫ አለን? ሀገሪቱ የምትከተለው “ዴሞክራሲያዊ”፣ ፌደራላዊ ስርዓት፤ ስልጣን ከምርጫ ሳጥን በህዝብ ይሁንታ እንደሚገኝ በህገ መንግሥት ደንግጓል (አንቀፅ 54) በዚህ መርሁ ላይ በመመስረት “ያዝ ለቀቅ ቢሆንም” የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ድምፅ ለማሸነፍ እየተፎካከሩ ይታያሉ፡፡

በዚህም ቢያንስ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት “እየተጀመረ ነው” ተብሎ ነበር፡፡ በሀይሉ መንገሻ የተባለ አስተያየት ሰጪ፤ ምንም እንኳን የመቀናጀትና ህብረት የመፍጠር አቅማቸው ደካማ ቢሆንም ቀደም ባሉት ምርጫዎች እስከ 75 የሚደርሱ በምርጫ ቦርድ እውቅና ያገኙ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመፎካከር ይሞክሩ እንደነበር ያስታውሳል፤ ምርጫ 97 ላይ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ፓርቲዎች “ህብረትና ቅንጅት” በሚባሉ ከፍ ያሉ ጥምረቶች ተሰባስበው “ለአንድ ኢህዴግ አንድ ተቃዋሚ” የሚል የፉክክር መንፈስ መፍጠራቸው አማራጭ እንድናይ አስችሎን ነበር ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በቀዳሚነት ተፎካካሪ የሆኑ ፓርቲዎች ወይም ግለሰቦች ሊኖሩት ግድ ነው፡፡ አሜሪካዊው ዲፕሎማት Jeane kirrpatrick እንደሚለው “Democratic elections are not merely symbolic… They are competitive, periodic, inclusive…” (ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለይስሙላ የሚካሄድ ሳይሆን ውድድራዊ፣ በጊዜ የተገደበና ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት) በዚህ ሚዛን የዘንድሮን ሀገር አቀፍ የአካባቢና የከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤት ምርጫ ማየት ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ሦስተኛ ዓመት ተማሪው ወጣት በሃይሉ “አፎካካሪ ነበር” የሚያስብል ምርጫ አልነበረም ሲል በሙሉ አፉ ይናገራል፡፡ በአንድ በኩል የተሻለ ሊፎካከሩ የሚችሉ (ከነውስንነታቸውም ቢሆን) ፓርቲዎች አሳማኝ ባልሆነ ሁኔታ ከምርጫው ራሳቸውን አግለዋል፡፡ በሌላ በኩል በምርጫው ሊሳተፉ የሞከሩት ተፎካካሪዎች (መኢብን፣ ቅንጅት፣ ኢራፓ፣ አመአዴን…) አይነት ፓርቲዎች፤ እንኳን ደጋፊ እጩ ለማቅረብ የሚያስችላቸው አባል የሌላቸው “ዝቅተኛ ተቀባይነት” (Less acceptance) ያላቸው እንደሆኑ ያስረዳል፡፡

(አንዳንዶች ተለጣፊ እንደሚሏቸው ልብ ይሏል) በብዙዎቹ የምርጫ ክልሎች የተቃዋሚው ጐራ ባለመሳተፉ ኢህአዴግ ብቻውን ሮጦ እያሸነፈ ነው ይላል - በኃይሉ፡፡ በተሳተፉበት የምርጫ ክልልም ቢሆን ኢህአዴግ ለ30 ወንበር ሲወዳደር እነሱ ሁለት ወይም ሦስት እጩ እያቀረቡ፣ ፍፁም ተመጣጣኝና ተቀራራቢ ባልሆነ መንገድ የተፈፀመ የምርጫ ሂደት ነው፡፡ የኢዴፓ ፕሬዚደንት አቶ ሙሼ ሰሙ በቅርቡ ከቁምነገር መፅሄት ጋር ያደረጉት ቃለምልልስም፤ ተፎካክሮ ለማሸነፍ የሚያስችል ተስፋ ቆራጭነት የሚታይበት ነው፡፡ “…ኢህአዴግ የልማት ሠራዊት ብሎ ከገጠር እስከ ከተማ በሚሊዮኖች ያስተሳሰረውና በ1ለ5 ያደረጀው ሁሉ አሁን ወደ ምርጫ ሠራዊት ተቀይሯል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ተቃዋሚው ተበረታቶ፣ ህዝቡ ውስጥ የሚደርስበት መንገድ ዝግ ነው፡፡

ስለዚህም በዚህ ምርጫ በመወዳደር ገንዘብ፣ ጉልበትና ፖለቲካዊ ሞራልን ከማባከን ውጭ የሚገኝ ነገር የለም፡፡ ለዚህም ነው ለጨዋታው ህግ ለመገዛት ብቻ በአዲስ አበባ አንድ እጩ አቅርበን ሌላውን የተውነው…” ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ያለተፎካካሪ እየተካሄደ ያለ ምርጫ ፋይዳው ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ እዚያም፣ እዚያም መነሳቱ አይቀርም፡፡ “ለአሯሯጭነት አንገባም” የሚለው የአንዳንድ ተቃዋሚዎች ሽሽት ግን በራሱ በፉክክሩ መንፈስ ውስጥ ጋሬጣ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በደካማና አሰልቺ ቅስቀሳ የታጀበ ምርጫ አሳታፊ ነውን? ህዝብ ይመራኛል (ያስተዳድረኛል) ብሎ የሚመርጠው ፓርቲ የሚለካው በተግባሩ ወይም በፖሊሲ አማራጩ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በእኛ ሀገር ያሉ ፓርቲዎች (ከኢህአዴግ በስተቀር) ሁሉም ስልጣን ይዘው አልተፈተሹም፡፡ አሜሪካ ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካን፣ በእንግሊዝ ኮንዘርቫቲቭና ሌበር ፓርቲ፣ በሌላው የሰለጠነው ሀገርም ያሉት ሁለትና ሦስት ፓርቲዎች እየተቀያየሩ ወይም እንደ ድምፁ ሁኔታ በጥምር መምራት የተለመደ ነው፡፡ ይሄ ነገር “ጨለማ” በነበረው አፍሪካ ሳይቀር ሲጀመር ማየት ያስቆጫል፡፡ ለጊዜው የተግባር መለኪያው እንኳን ባይሳካ የፖለቲካ ድርጅቶች የበሰለ አማራጭ ይዘው ለህዝብ ለማቅረብ እየቻሉ አይደለም፡፡

ወ/ሮ አወጣሽ መንበሩ የተባሉ ነዋሪ፤ “አሁን ባለው ሁኔታ ከኢህአዴግ ውጭ የእገሌ አማራጭ የምንለው ፖሊሲ የለም” ይላሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቹ የኢህአዴግን አፈፃፀም ከመተቸት ባለፈ በይዘቱ የተለየና “ይሄ መገለጫችን ነው” የሚሉት ርእዮተ ዓለም (የፖለቲካ ፍልስፍና) ያለ መኖሩ አንድ ክፍተት ሲሆን ያላቸውን አማራጭ ለህዝብ ያለማቅረባቸውም ችግሩን አባብሶታል፡፡ “የዘንድሮው የአካባቢ ምርጫ ላይ ነባሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የተሰላቸ መስሏል፤ ወደ መድረክም አልቀረበም፡፡ አዳዲስ የፖለቲካ ተኪዎች የመጡ ቢመስሉም ሀገሪቱ የደረሰችበትን ደረጃና የህዝቡን ንቃተ ህሊና ያገናዘበ ሀሳብ ሲያቀርቡ አልተስተዋሉም የሚሉት ወ/ሮ አወጣሽ፤ ኢህአዴግ የተከተለው የቤት ለቤት ቅስቀሳና የቴሌቪዥን ቅስቀሳም ቢሆን ስርአት ያልነበረውና አሰልቺ ሆኖብኛል በማለት ይገልፃሉ፡፡ ከቅድሚያ ዝግጅት አንስቶ እስከ ድምፅ መስጫ እለትና ውጤት ማሳወቂያ ድረስ ሚዲያዎች (በተለይ የመንግሥቶቹ) በስፋት ዘግበዋል፡፡ ይሄ አንድ ነገር ሆኖ፣ በዘገባው ውስጥ የአንድ ወገን የሚመስል አቀራረብ መታየቱ፣ የፖለቲካ አማራጭ የሚፈልጉ ዜጐችም ሆኑ ፖለቲከኞች አለመካተት ሳቢነቱን ገድቦታል ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን ወደኋላ መልሶታል የሚሉም አሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ፓትሪክ ዊልሰም ከተባለው ካናዳዊ ፖለቲከኛ ሀሳብ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡

“Democracy is communication, people talking one another about their common problems and forging a common destiny. Before people can govern themselves, they must be free to express themselves” (ዲሞክራሲ በመነጋገርና ሀሳብን በነፃነት በማራመድ፣ የፈለጉትን በመደገፍና በመቃወም ለመስራት የሚችለው ምርጫ በመኖሩ ብቻ ሳይሆን ሀሳብን በነፃነት መግለፅ ሲቻል ነው) ይላል፡፡ ህዝቡ በምርጫ ቦርድና ሚዲያ ገለልተኛነት ላይ እምነት አለውን? ለአንድ ምርጫ፤ ነፃ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊነት የመሮጫ ሜዳው የተደላደለና አመቺ መሆን ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለዲሞክራሲ ምርጫ የሚጨነቁ መንግሥታት በቀዳሚነት የሚሰሩበት በህዝቡ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው የምርጫ ቦርድ፣ የህዝብ ሚዲያና ፍርድ ቤቶች መኖራቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ምቹ መደላድሎች በሂደት የሚመጡ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በየአምስት አመቱ ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ከቆሙ ግን ችግር እንዳለ ያመለክታል፡፡ በቅርቡ “መድረክ” የተሰኘው የተቃዋሚ ድርጅቶች ስብስብ “ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም” ሲል ይፋ መግለጫ አውጥቷል፡፡

“ይሄ ተመሳሳይ መዝሙራቸው ነው!” ለሚለው የኢህአዴግ ምላሽ ያቀረቡት ማስረጃ አለ፡፡ ኢህአዴግ፤ የምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በማድረግ በድፍረት የሰየማት ግለሰብ፣ ከአምስት አመት በፊት ለደብረብርሃን ምርጫ በእጩነት ያቀረቡትን ነው ይላሉ፡፡ በየምርጫ ጣቢያው የኢህአዴግ አባላት እጅ መኖሩ፤ በታዛቢ ብዛት ሙሉ በሙሉ ኢህአዴግ ማጥለቅለቁ ተሳትፎውን ገድቦታል ሲሉም ወቅሰዋል፡፡ ኢህአዴግም ሆነ ምርጫ ቦርድ ግን በዚህ ትችት አይስማሙም፡፡ ከሁሉም በላይ ህዝብ ያለው ግን መደመጥ አለበት፤ ፖለቲከኞች ህዝብ የሚሰጠው ምላሽ ሁሌ ትክክል ነው (Self Righteous) እንደሚሉት ማለት ነው፡፡ “የመንግሥት ሚዲያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (ከምርጫ 97 በኋላ) ሙሉ በሙሉ የመንግሥት ወገንተኛ ሆነዋል፤ የተቃዋሚው ትችትም ሆነ አማራጭ ሲቀርብ ፍፁም የማይታይበት ደረጃ ተደርሷል” ይላል በአንድ ሲቪክ ማህበር ሃላፊነት ላይ የሚገኘው አስተያየት ሰጪ፡፡ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ አጠራጣሪ ውሳኔ ያረፈበት የፖለቲካ ጉዳይ ተደጋግሞ ባይታይም፣ ፍርድ ቤቶችም ነፃና የህዝብ ተአማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ ግን ብዙ መሠራት እንዳለበት እሙን ነው፡፡ በምርጫው የህዝቡ ተሳትፎ ኮስሶ ነበር? ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳረጋገጠው፤ ከ31 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በመላው ሀገሪቱ ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ አውጥቷል፡፡ ይሄ ሊመርጥ ከሚችለው ህዝብ ብዛት አንፃር ሲታይ ትልቅ ቁጥር ነው፡፡ እውን ግን ሁሉም ድምፅ ሰጥቷል? በምርጫውስ ላይ በንቃት ተሳትፏ?

ስንል መጠየቃችን አይቀርም፡፡ በእለቱ በአዲስ አበባ 12 የምርጫ ጣቢያ እንደተዘዋወረ የገለፀልኝ የመንግሥት ጋዜጠኛ፣ “በምርጫ ታዛቢነት፣ አስመራጭነትም ሆነ መራጭነት ሲሳተፍ ያየሁት ድሃውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ህበረተሰብ ነው፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በኮንደሚኒየምና መሰል ወቅታዊ ስራዎች ከስርአቱ የተጠቀሙ የኢህአዴግ ደጋፊዎችም ይበዛሉ” ይላል፡፡ ምሁሩ፣ የመንግሥት ሠራተኛው፣ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ብዙ ሰው ግን ለምርጫው ትኩረት እንዳልሰጠ ግምቱን ሰንዝሯል፡፡ በእርግጥም በመገናኛ ብዙሃን (በቴሌቪዥን) ያየነው ይሄን ሃሳብ የሚያጠናክር ይመስላል፡፡ ያነጋገርናቸው አንዳንድ መራጮች ቅሬታቸወን የገለፁበት ሌላው ጉዳይ ኢህአዴግ ራሱ ያቀረባቸው እጩዎች ምን ያህል በተግባራቸው ተመዝነውና ህዝብ አምኖባቸው ነው? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፤ ለከተማና ለክፍለ ከተማ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡ አንዳንድ እጩዎች “አስተዳደሩ ከልቡ ለውጥ አለመፈለጉን አመላካች ናቸው” ይላሉ፡፡ በስነ ምግባር የሚወቀሱ፣ በኔትወርክና ቡድነኝነት በየጊዜው የተገመገሙ፣ በስመ “ነባር አባል” ስርአቱን የሚበድልና ህዝብ የሚያማርር ተግባር ከመፈፀም ወደ ኋላ የማይሉ እጩዎች፣ በህዝብ ሳይተቹ (ፎቶአቸው ብቻ ይፋ መደረጉ) የምርጫውን አሳታፊነት እንደገደበው ነው የሚያስረዱት፡፡

ለአዲስ አበባ አስተዳደር ቅርበት ያላቸው አንዳንድ ወገኖችም በም/ቤት እጩ ምልመላው ላይ ቅሬታ አላቸው፡፡ “እጩ የቀረበው ከብሄራዊ ድርጅቶች ነው፡፡ በብሄራዊ ድርጅቱ የምርጫ ኮሚቴ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከፖለቲካ ጥንካሬ፣ ስነምግባርና የህዝብ ተቀባይነት ይልቅ ትውውቅን ዋነኛ መስፈርት አድርገውታል” ሲሉ ይተቻሉ - ለዚህ ጥሩ ማሳያ በብአዴንና ደኢህዴን ውስጥ የታየው “መሳሳብ” እንደሆነ በመግለፅ፡፡ በድምሩ ሲታይ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርጊትም ሆነ የምርጫው አጠቃላይ ሂደት ለህዝብ ተሳትፎ የሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ ነበር በሚለው ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ኢህአዴግ ለምን “የምርጫ ስነምግባር ደንቡን” ዘነጋው? እስከ አሁን በተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ ኢህአዴግ ለአባላቱና ደጋፊዎቹ የሚያገለግል የምርጫ ስነምግባር ደንብ በማውጣት ይታወቃል፡፡ (አንዳንዶች በ97 የወጣው ደንብ እግር እጃችንን ይዞ ነበር ሲሉ ቢቃወሙም) ባለፉት ብሄራዊም ሆኑ የአካባቢና ማሟያ ምርጫዎች፣ ደንብና የምርጫ ስትራቴጂ ነድፎ ለአባሉና ለህዝቡ አሳውቆ ነበር ወደ ምርጫ የሚገባው፡፡ ከአምስት አመት በፊት እንኳን ጠንካራ የምርጫ ደንብና ስትራቴጂ አውጥቶ (አዲስ ራዕይ ጥር 2000 ላይ ታትሞ ነበር) ግልፅ ግብ አስቀምጦ ነበር የተንቀሳቀሰው፡፡ (ዘንድሮ የድርጅቱ መሃንዲስ ባለመኖራቸውም ይሆን የበፊቱን እንኳን ከልሶ አላመጣውም) ታዛቢዎች ግን ነገሩን በሌላ መልክ ያዩታል፡፡ “ኢህአዴግም ቢሆን ለምርጫው የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነወ፡፡ ተቃዋሚዎች ሰበብ አምጥተው ከምርጫው ራሳቸውን ሲያገሉ ቀደም ሲል የሚያደርገውን ያህል እንኳን ሆደ ሰፊነትና ውይይት ለማድረግ አልተነቃቃም፡፡ መጡም ቀሩም ልዩነት የለውም ነው ያለው፡፡

ባሉት ተፎካካሪዎች ላይ እምነት ባለማሳደሩም ለምርጫ ቅስቀሳ እንኳን አንድም ከፍተኛ አመራር ሳያቀርብ የተወው ምርጫ ነው” በማለት ገልፀውታል - የምርጫ ስነምግባር ኮድም ከዚሁ ቸልተኝነት እንደመነጨ በማስረዳት፡፡ እስከ አሁን ባለው መረጃ፣ በምርጫ ሂደቱ የተፈጠረ የጐላ የህግ ጥሰትና የስነምግባር ግድፈት አልተሰማም፡፡ ይሄ ደግሞ የምርጫ ስነምግባር ኖረም፣ ቀረም ችግር የለውም ሊያስብል ይችላል፡፡ አጠቃላይ ስርአቱ በህግና ስርአት፣ በፉክክር፣ በህዝብ ተሳትፎና በእኩል ሜዳ እንዲካሄድ ለማድረግ ግን የደንቡ መቀረፅ ወሳኝ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከዚህ በኋላስ ምን ይደረግ? (እንደማጠቃለያ) የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታን ለገዢው ፓርቲ፣ ለአንጋፋ ተቃዋሚዎች ወየም ለጥቂቶች ትቶ መቀመጥ ማንንም አያሳድግም፡፡ ወጣቱ፣ ባለሀብቱ በተለይ ምሁሩ ራሱን ከፖለቲካው ሂደት የማግለል ውሳኔና እርምጃ ከታሪክና ከህዝብ ብርቱ ወቀሳ (Public vilification) የሚያድነው አይደለም፡፡ ከግለኝነት ስነልቦና ወጥቶ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም፣ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመሰለፍ ምርጫ ወሳኝ መሆኑን ተገንዝቦ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲ (መንግሥት) ህገወጥነትና ፀረ ዲሞክራሲን ለመታገል ከከፈለው ዋጋ በላይ ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ መሰራት አለበት፡፡ በዚህ ፅሁፍ በተጠቀሱ ጥቂት መገለጫዎችና በሁለንተናዊ ገፅታው የምርጫ ጉዞአችን ወደኋላ የመመለስ ባህሪ ተላብሷል፡፡ ይሄን የሚናገር ኖረም አልኖረም (ዝምታን መርጦ) ሊካድ አይችልም፡፡

ካልሆነ ግን የመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታና የልማታዊ መንግሥት ርእዮት ፊት ለፊት የሚጋጩበት የተዘጋ መንገድ ፈጥጦ መታየቱ አይቀርም፡፡ በዘንድሮ ምርጫ 31 ሚሊዮን 6መቶ ዜጐች በመራጭነት ተመዝግበው፣ 90 በመቶ ድምፅ እንደሰጡ ምርጫ ቦርድ ገልጿል፡፡ አብዛኛው (87%) የኢህአዴግ የሆኑበት 3.5 ሚሊዮን እጩዎች ቀርበዋል፡፡ ከአንድ መቶ ሺ የማያንሱ የምርጫ ታዛቢዎችና ምርጫ አስፈፃሚዎችም ከምዝገባ እስከ ድምፅ ቆጠራ ለቀናት ደክመዋል፡፡ በግርድፍ ግምት (የምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል ከሚገልፀው ወጩ አንፃር) እስከ 100 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የሀገር ሀብት ወጥቶበታል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደቱ ላይ ያደረገው አስተዋፅኦ ምን ያህል ነው? እውን በየኮረጆው የገቡ የምርጫ ካርዶችስ ትክክለኛ የህዝብ ስሜት የታየባቸው ናቸውን? (በነገራችን ላይ ካርዱ ላይ ያልተገባ ነገር በመፃፍ፣ በመቅደድ፣ ደጋግሞ ምልክት በማድረግ ድምፅን ዋጋ ያሰጡ መራጮች በአዲስ አበባ መብዛታቸውን ከምርጫ ታዛቢዎች በቅርቡ መስማታችንን ልብ ይሏል) በአለም ላይ አሁንም ምርጫን የሚያካሂዱ ሀገሮች አሉ፡፡ ኤርትራ፣ ሰሜን ኮርያ፣ ቻይና (ለማስመሰልም እንኳን የሚደረግ ምርጫ የለም) ይጠቀሳሉ፡፡ አስመሳይ ዲሞክራሲ አራማጆች የሚባሉ የእስያና አፍሪካ ሀገራት ብዛትም ቀላል አይደለም፡፡

ያም ሆኖ አፍሪካ ውስጥ ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ ተስፋ ሰጪ የዲሞክራሲ ምርጫ ስርአት መላበስ የጀመሩ ሀገሮች ታይተዋል፡፡ እነጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አንጐላ፣ በቅርቡ ኬንያ፣ ዛምቢያና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ኢህአዴግን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ድርጅቶችና ምሁራን ዋጋ የከፈሉበት (በመቶ ሺዎች የተሰዋ፣ የተሰደደና አካሉ የጐደለ ትውልድ ለውጥ በመሻት በግራና ቀኝ ወድቋል) የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ህልም እንዳይጨልም ብዙ መስራት ይጠበቃል፡፡ ከሁሉም ሃይሎች፡፡

Read 1361 times