Saturday, 20 April 2013 11:31

ኢህአዴግ በሁሉም የምርጫ ቦታ አሸንፌያለሁ ይላል

Written by 
Rate this item
(13 votes)

በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አሸንፈናል” - ተቃዋሚዎች ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የከተማ ምክር ቤቶች ምርጫ ኢህአዴግ ጊዜያዊ ውጤት በመጥቀስ በሁሉም ቦታዎች እንዳሸነፈ የገለፀ ሲሆን በምርጫው የተሳተፉ ተቃዋሚዎች በውጤቱ እርግጠኛ ባይሆኑም በጥቂት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ቦታዎች የምናሸንፍ ይመስለናል ብለዋል፡፡ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ “ህዝቡ ጥሩ ድምጽ እንደሰጠን እናውቃለን፡፡ ውጤቱን በተመለከተ ግን የምርጫ ቦርድ ይፋ ካደረገ በኋላ የምናየው ይሆናል” ብለዋል፡፡ አቶ አየለ አክለውም በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች እጩዎቻቸው አሸናፊ እንደሆኑ ነገር ግን የመጨረሻውን ውጤት በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የሚወሰን ስለሚሆን የምርጫ ቦርድ መግለጫ መጠበቅ የግድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ አየለ በሂደቱ ላይ የታዩ ብዙ ችግሮች እንደነበሩ ገልፀው፣ ከነዚህ መካከል የንብ ምልክት ብቻ በየጣቢያው መቀመጡ እንዲሁም በድምጽ ቆጠራ ወቅት የእነሱ ታዛቢዎች እንዳይገኙ መደረጋቸው ተገቢ አይደለም፤ ቅሬታችንን በወቅቱ ለምርጫ ቦርድ አቅርበናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፣ በምርጫው ውጤት እንዳልቀናቸው ማረጋገጣቸውን ጠቅሰው፣ ፓርቲያቸው በምርጫው መሳተፉን ይበልጥ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲተዋወቅ እንዳደረገው ገልፀዋል፡፡ የምርጫው አጠቃላይ ሂደትና ውጤት በተመለከተ ያላቸውን አቋምም በምርጫ ቦርድ ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ እንደሚያሳውቁ አቶ ተሻለ ገልፀዋል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ሊቀመንበር አቶ መሣፍንት ሽፈራው፤ በአዲስ አበባ በሶስት የምርጫ ጣቢያዎች ቢያሸንፉም አጠቃላይ ውጤቱን ለማወቅ የምርጫ ቦርድን መግለጫ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

ኢህአዴግ በበኩሉ በአዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ የአሸናፊነት ድምጽ አግኝቻለሁ ብሏል፡፡ በኢህአዴግ ጽ/ቤት የአደረጃጀትና የአጋር ድርጅቶች ዘርፍ ሃላፊ አቶ ተመስገን ጥላሁን በሰጡት ማብራሪያ፣ የምርጫው አጠቃላይ ውጤት የሚታወቀው በቦርዱ ይፋ ሲደረግ ቢሆንም አሁን ባለው ጊዜያዊ ውጤት ግን በሁሉም የምርጫ ወረዳዎች አሸንፈናል ብለዋል፡፡ ምርጫው ኢህአዴግ ባሰበው መንገድ ዲሞክራሲያዊ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ ተጠናቋል ያሉት አቶ ተመስገን፤ ነገ እሁድ የሚካሄደው የወረዳ ምርጫ ሲጠናቀቅና ምርጫ ቦርድ ውጤቱን ይፋ ሲያደርግ ምርጫውን በተመለከተ አጠቃላይ መግለጫ እንሰጣለን ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጌታሁን ገ/መድህን በበኩላቸው በምርጫው የተገኘው አጠቃላይ ውጤት ግንቦት 2ቀን 2005 ዓ.ም ይፋ ሲደረግ በአዲስ አበባ በየክልሉ የተገኘው ደግሞ ሚያዚያ 16 ቀን 2005 ዓ.ም ይፋ እንደሚደረግ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው ይታወቃል፡፡

Read 3574 times