Saturday, 20 April 2013 11:27

ርዕዮት አለሙ በተለያዩ ህመሞች እየተሰቃየች ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

በሽብር ወንጀል ተከሳ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የአስራ አራት አመት ጽኑ እስራት ከተፈረደባት በኋላ በይግባኝ ቅጣቱ ወደ አምስት አመት ዝቅ ተደርጎላት በማረሚያ ቤት የምትገኘው ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙ፤ ለህመሟ ተገቢውን ህክምና ማግኘት ባለመቻሏ እየተሰቃየች መሆኑን አባቷና ጠበቃዋ አቶ አለሙ ጐቤቦ ለአዲስ አድማስ ተናገሩ፡፡ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት (CPJ) ለፍትህ ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ፣ ጋዜጠኛዋ ተገቢውን ህክምና የምታገኝበት መንገድ እንዲመቻችላት ጠይቋል፡፡ ርዕዮት በሶስት አይነት ህመሞች እየተሰቃየች ነው ያሉት አቶ አለሙ፤ በአፍንጫ ህመም (ሳይነስ)፣ ከባድ የጨጓራ ህመምና የጡት እጢ ህመሞች ተገቢውን ህክምና ማግኘት አለመቻሏን ተናግረዋል፡፡

ዓምና ክረምት ላይ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በአንደኛው ጡቷ ውስጥ የነበረው ጠጣር ነገር እንደወጣላት የተናገሩት አባቷ፤ ህክምናው ክትትል ስለሚያስፈልገው የሶስት ወር ቀጠሮ ተሰጥቷት እንደነበር፣ ነገር ግን ማረሚያ ቤቱ በተባለው ጊዜ ሳይሆን ሶስት ሣምንት አሳልፎ በመውሰዱ የህክምና መስተጓጐል በፈጠረው ችግር እስካሁን ድረስ በህመሙ እየተሰቃየች ትገኛለች ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ርዕዮት ማረሚያ ቤት ሆና ለሁለተኛ ድግሪዋ በርቀት ትምህርት ለመማር ከማረሚያ ቤቱ ቀደም ብላ ፈቃድ ማግኘቷን የሚናገሩት አቶ አለሙ፤ ቅድስት ማርያም ኮሌጅ በፖለቲካል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ 26ሺህ ብር በመክፈል ተመዝግባ የነበረ ቢሆንም ለትምህርቱ አስፈላጊ የሆኑ ሞጁሎች (የመማሪያ ሠነዶች) እንዳይገቡላት ማረሚያ ቤቱ በመከልከሉ ከትምህርቷ መስተጓጐሏን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

የትምህርቷንና የጤንነቷን ጉዳይ በተመለከተም ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አቤቱታ ለማቅረብ እየተዘጋጁ መሆኑን አባቷና ጠበቃዋ አቶ አለሙ ተናግረዋል፡፡ ርዕዮት ተገቢውን ህክምና አለማግኘቷና ትምህርቷ መስተጓጐሉ ሳያንስ ማረሚያ ቤቱ የዲሲፕሊን ክስ አቅርቦባታል ያሉት አቶ አለሙ፤ “የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር አታከብሪም፣ ትሳደቢያለሽ፣ ታንጓጥጫለሽ፣ ስራችሁን በሚዲያ አጋልጣለሁ እያልሽ ታስፈራሪያለሽ” በሚል ለቀረቡባት ክሶች የህግ ጠበቃዋን አማክራ ለማረሚያ ቤቱ ቃሏን መስጠቷን አቶ አለሙ ገልፀዋል፡፡ የዲሲፕሊን ክሱ ላይ የማረሚያ ቤቱን ውሣኔ በመጠባበቅ ላይ መሆኗን የተናገሩት አቶ አለሙ፤ ጥፋተኛ ከተባለች ከሚበየኑባት ቅጣቶች መካከል ለብቻዋ በአንድ ክፍል መታሰርን ጨምሮ፣ በዘመድ እንዳትጠየቅ እና ለሌላው እስረኛ የሚቀርቡ ጥቅማጥቅሞችንም እንዳታገኝ ልትታገድ እንደምትችል ሙያዊ ግምታቸውን ገልፀዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ የማረሚያ ቤቱን ሃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በእስር ላይ የምትገኘው ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙ፤ሰሞኑን ዩኔስኮ ተሸላሚ አድርጐ እንደመረጣት የሚታወቅ ሲሆን የሽልማት ሥነስርአቱም ሚያዝያ 25 ቀን 2005 ዓም በኮስታሪካ ይካሄዳል፡፡ ጋዜጠኛዋ ከዚህ ቀደም ተመሣሣይ ሽልማቶችን ከተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት ማግኘቷ ይታወሳል፡፡ የውድድሩ ተመልካቾች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

Read 4029 times