Saturday, 20 April 2013 11:24

በመንገድ ጥገና ሥራ ለሙስና የሚያጋልጡ አሠራሮች አሉ ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

የፌደራል፣ የክልልና የከተማ መንገዶች ጥገናና ደህንነት ሥራ ላይ ለመሠማራት በአዋጅ የተቋቋመው የመንገድ ፈንድ ጽ/ቤት፤ የተለያዩ ክፍተቶች እንዳሉበትና ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚመሩ አሠራሮች መኖራቸውን መገንዘቡን የፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ የመንገድ ፈንድ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ራሺድ መሐመድ እና የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ ሰሞኑን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው፤ ጽ/ቤቱ በየዓመቱ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ የመንገድ ጥገናና የመንገድ ደህንነት ሥራዎችን ይሰራል፡፡

ጽ/ቤቱ የመንገድ ጥገና ደህንነት ሥራዎችን ለሚሰሩ የመንገድ ኤጀንሲዎች በማውረድ ክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በዚህ የአሠራር ሂደትም በርካታ ችግሮች በተቋሙ ውስጥ መኖሩን ለመረዳት መቻላቸውንና አሠራሩም ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚያመራ መሆኑን መገንዘባቸውን የፌደራል ሥነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ ውስጥ የሚታየውን የአሠራር ክፍተት በተመለከተ ጥናት ማካሄዱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ እነዚህን ክፍተቶች ለማስተካከል የሚችልና አማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦችን ያቀፈው ጥናት፤ መጠናቀቁንና ወደ ትግበራ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡

የመንገድ ፈንድ ጽ/ቤት በያዝነው ዓመት 1.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን የተናገሩት የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ረሺድ መሐመድ፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በነዳጅ ላይ ከተጣለ ታሪፍ ብቻ 749 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡ የከተማው መንገዶች በተሰሩ በአጭር ጊዜ ለብልሽት የሚዳረጉበትን ምክንያት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ፤ “ጽ/ቤቱ የሚመለከተው ተበላሽተው የሚጠገኑ መንገዶች እንጂ አዳዲስ መንገዶች አይደለም፡፡ እኛ ለሥራው በተመደበው በጀት መሠረት መንገዶች ሲበላሹ የመጠገን ኃላፊነት ነው ያለብን” ብለዋል - በተያዘው በጀት አመት 10.953.95 ኪ.ሜ መንገድ ጥገና መደረጉን በማከል፡፡

Read 1719 times