Saturday, 20 April 2013 11:22

ለንግዱ ማኅብረሰብ ዘመናዊ አሠራር የሚያስተምር ጉባኤ ተዘጋጀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

የንግዱን ማኅበረሰብ ከተለመደው ባህላዊ አሠራር አላቅቆ ዘመናዊ ዘዴን እንዲከተል ለማድረግና ወቅታዊ በሆኑ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ትልቅ ጉባኤ ማዘጋጀቱን “ፓወር ሃውስ ዊኒንግ ስትራተጂ ሴንተር” አስታወቀ፡፡ በመጪው ሐሙስ በሸራተን አዲስ በሚካሄደው ውይይት፣ በግል ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ከተለመደው አሠራር ወጥተው በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየጊዜው የሚለዋወጠውን የንግድ አሠራር፣ አስተሳሰብና ዕድገት በመረዳት ከሚያጋጥመው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ማጣጣም፣ መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀምና መጥፎ ሁኔታዎችን መቋቋም በሚችሉባቸው ስልቶች ላይ ምሁራዊ ትንታኔ እንደሚቀርብ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል በምትሆንበት ጊዜ፣ ተጠቃሚውና የንግዱ ማኅበረሰብ መንግሥት ስለሚኖራቸው ተጠቃሚነትና የሚያጋጥማቸውን ችግሮች እንዴት መወጣት እንዳለባቸው ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ፤ የቢዝነስ ማኔጅመንት ስትራቴጂ ጽንሰ ሐሳብ በመረዳትና ተግባራዊ በማድረግ ምርትና አገልግሎቱን በጥራት በማቅረብ እንዴት ተጠቃሚና ተመራጭ መሆን እንደሚችል ውይይት ይደረጋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በጉልህ ጠቀሜታው በአንዳንድ ድርጅቶች ተግባራዊ እየተደረገ ስላለው የካይዘን ጥበብ ምንነትና አሠራር ገለጻ የሚደረግ ሲሆን፤ ስኬታማ የንግድ መሪዎች ሥራ ፈጣሪዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ምሁራን… ተሞክሯቸውን እንደሚያቀርቡ የውይይቱ አዘጋጅ ድርጅት አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ በካውንስሊንግ ክፍሉ ቢዝነስ ነክ ጉዳዮችን ለማማከር፣ ቢዝነስና ስትራቴጂያዊ ፕላኖችን ለመሥራት፣ አጫጭር የቢዝነስ ሥልጠናዎችና ሴሚናሮችን ለመስጠት የተቋቋመ መሆኑን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡

Read 1583 times