Saturday, 20 April 2013 11:14

የስነተዋልዶ ጤና በታዳጊ አገሮች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የስነተዋልዶ ጤና ምንነት በአለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ቢሆንም ምክንያቶቹ ግን በታዳጊ አገሮች በአብዛኛው የተለዩ ናቸው፡፡ በታዳጊ አገሮች የሚገኙ እናቶች በ 5/ማይል እርቀት የጤና ጣቢያ ካገኙ ደስተኞች ናቸው፡፡ በታዳጊ አገሮች የሚገኙ እናቶች ጤና ጣብያው ምንግዜም በስራ ላይ ሆኖ ከቆያቸውና ለታካሚዎች በቂ ምላሽ የሚሰጡ ሙያተኞች እንዲሁም የተሟላ አቅርቦት በጤና ተቋሙ ካለ ደስተኞች ናቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከላይ የተጠቀሱት ሁነቶች ተሟልተው የሚገኙ ባለመሆኑ የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት የተጉዋደለ ይሆናል፡፡ በታዳጊ አገሮች የተለያዩ መሰረተ ልማቶች...ለምሳሌ...እንደ መንገድ የጤና ተቋም በቅርበት አለመኖር የትራንስፖርት ችግር የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች የመሳሰሉት ካልተሙዋሉ እናቶች ወደ ጤና ተቋም በጊዜው ሄደው እርዳታ እንዳያገኙ ያደርጋቸ ዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የስነተዋልዶ ጤና በሴትና በወንድ በባልና ሚስት መካከል ባለው መቀራረብና ለውይይት መገባበዝም ሁኔታው እንደማሻሻል ሙያተኞች ይመሰክራሉ፡፡ ቀጣዩን የተሳታፊ መልእክት ታነቡ ዘንድ እንጋብዛለን፡፡

.....እህ የምትኖረው በደብረማርቆስ ከተማ ሲሆን በህመም ምክንያት ባልተቤቷ ወደ እኔ ማለትም ወደአዲስ አበባ ይዞአት መጣ፡፡ ሁኔታዋን ከተመለከትኩ በሁዋላ ለባልተቤቷ ጥያቄዬን ሰነዘርኩ፡፡ ጥ: ባልተቤትህ ምንዋን ነወ ያመማት? መ: እኔ እንጃ... ጥ: እንዴት እኔ እንጃ? ሚስትህ ምንዋን እንደሚያማት አታውቅም እንዴ? መ: አረ እኔ አላውቅም... ጥ: አልጠየቅሀትም? መ: እኔም አልጠየቅሁዋት...ብጠይቃትም አትነግረኝ... በባልተቤቷ አመላለስ በጣም ተበሳጨሁና...ፊን ወደእህ መለስኩ፡፡ ጥያቄየን ገና ሳልጀምር ...ና ተነስ አብዬ...አለችኝ እና ወደጉዋሮ ተያይዘን ሄድን፡፡ ጥ: ፈልገሽኝ ነው አልኩዋት... መ: እናስ...እንዴ...እሱ ፊት ምን ልትጠይቀኝ ነው ብዬ እኮ ነው? ጥ: እንዴ እኔ ምን እጠይቅሻለሁ...የመጣሽው ታምመሽም አይደል እንዴ? ምንሽን ነው የታመምሽው ነው የምልሽ? መ: አ...አ...ይ...ሕመሙንም ቢሆን ለሚስትህ ነግሬያት የለ...እሱዋ ትንገርህ...ዪ...እኔስ ምኑንም አላውቀውም... አለችኝ፡፡ እህን ከባለቤቴ ባገኘሁት መረጃ መሰረት ወደማህጸን ሐኪም ወሰድኩዋት፡፡

እዚህ ላይ ለመናገር የምፈልገው በተለይም በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በግልጽነት መነጋገር ስለማይችሉ ሕመማቸው ስር ከሰደደ በሁዋላ ወደሕክምና ይሄዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ካለውጤት ብዙዎች ይጎዳሉ፡፡ ተሳታፊ የስነተዋልዶ ጤና በታዳጊ አገሮች የሚለው ርእስ ሊያሳይ የፈለገው በመንግስት ወይንም ሌሎች በሚመለከታቸው አካላት ሊሟሉ የሚገባቸውን ነገሮች ሳይሆን ከዚያ ውጪ ህብረተሰቡ በልማድ የሚፈጽማቸውን ነገሮች ነው፡፡ ለዚህ ማብራሪያ የሚሰጡን ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ መምህርና የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ እንደ ዶ/ር ዳዊት ማብራሪያ በታዳጊ አገሮች የሚገለጹ ችግሮች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የተለያዩ ሲሆኑ ከነዚህም መካከል ትምህርት ማጣትና ድህነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አንዲት ሴት ትምህርትን የተቋደሰች ከሆነች በብዙ መልኩ በጤናዋ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን አስቀድማ መከላከል ትችላለች፡፡

ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል፣ ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥን ማስወገድ፣ ተላላፊ ኤችአይቪ የሆኑትን ሕመሞች ለመከላል የሚያስችሉ ነገሮችን አስቀድሞ ለማወቅ፣ በኢኮኖሚው ረገድ ጥገኝነትን ለማስወገድ እንዲረዳ አቅም የፈቀደውን ስራ መስራት፣ የግል ንጽህናን መጠበቅ ...ወዘተ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከስነተዋልዶ ጤና አኩዋያም ሆነ ለማንኛውም የአኑዋዋር ዘዴ ለማስተካከል እንዲቻል ትምህርት ወሳኝነት አለው፡፡ ድህነት ከስነተዋልዶ ጤና አጠባበቅ አንጻር ጎጂ የሚሆንባቸው መንገዶች የሚኖሩ ሲሆን በተለይም አስቀድሞውኑ ሕመሙ እንዳይከሰት ለማድረግ እና ከተከሰተም በሁዋላ በፍጥነት ወደሕክምና ተቋም ለመሄድ እንቅፋት የሚሆንበት አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡ በኢ ኮኖሚው በዝቅተኛ ደረጃ የሚኖሩ ሰዎች እራቅ ወዳለ አካባቢ ለመሄድ ለትራንስፖርት የሚከፍሉት ስለማይኖራቸው የሚከሰተውን ችግር መቀበልን ይመርጣሉ፡፡

ይህ ደግሞ በቀጣዩ የህይወት አቅጣጫቸው ላይ አንድ እክል እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ እንደ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የስነተዋልዶ ጤናን ከአገር ወደህብረተሰብ እንዲሁም ወደቤተሰብ ዘልቆ ገብቶ ሲታይ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ነገሮች ጫና የሚያሳድ ሩበት ሁኔታ ይታያል፡፡ የስነተዋልዶ ጤና ጉዳይ የሴቶች ብቻ ሳይሆን የወንዶችም ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ በአብዛኛው ሲጎዱ የሚታዩት ሴቶች ቢሆኑም ወንዶቹም የሚያጋጥማ ቸው ችግር እንደሚኖር እሙን ሲሆን በተለይም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመፍታት የወንዶች ተሳታፊን በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በሚፈጠሩ የጤና እክሎች ላይ በግልጽ መወያየት የአንድ ባልና ሚስት ተግባር መሆን አለበት፡፡ ሴቶችና ወንዶች ለሚያስፈልጉዋቸው ማናቸውም የኑሮ ሁኔታዎች በእኩል መወሰን መቻል አለባቸው፡፡ ሴቶች ከባሎቻቸው ጋር በተለይም ከስነተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ መወሰን የሚገባቸው እና በቀጥታ ከሕይወታቸው ጋር ተያያዥ የሆኑ ነገሮች ያሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል የሚወለዱ ልጆችን ቁጥር እና በምን ያህል የጊዜ ልዩነት መውለድ እንዳለባቸው አስቀድሞ መወሰን ይገኝበታል፡፡

አንዲት ሴት ልጅ የምትወል ድበትን ጊዜና ሊኖራት የሚገባውን የልጅ ቁጥር በወንዱ የገቢ አቅም ላይ ተመርኩዛ ብቻ ሳይሆን ከእራስዋም ጤና አንጻር ልትመለከተው ይገባታል፡፡ ይኼውም በላይ በላይና ብዙ ልጅ በመውለድ እየዋለ እያደረ የሚከሰተውን የስነተዋልዶ ጤና ችግር አስቀድማ ልትከላከል ትችላለች፡፡ የቤት ውስጥ ጥቃት ሌላው ለስነተዋልዶ ጤና ችግር የሚዳርግ ድርጊት ነው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያስረዱት 50 ኀ ሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ናቸው፡፡ የቤት ውስጥ ጥቃት ሲባል አካላዊ፣ መንፈሳዊ ፣ኢኮኖሚያው ተብሎ ሊከፈል የሚችል ሲሆን አካላዊ ጥቃት ከሚባሉት ውስጥ አስገድዶ መድፈር አንዱ ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ በሴቶች ላይ የስነአእምሮ እና የአካል ችግር ያስከትላል፡፡ በዚህ መንገድ የተጎዱ ሴቶች ባጠቃላይ እራሳቸውን ማግለልና ዝቅ ማድረግ ይታይባቸዋል፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚባሉት እንደ ጠለፋ ግርዛት እና በቤት ውስጥ ልጅን ማዋለድ የመሳሰሉት ሌሎች የስነ ተዋልዶ ጤናን የሚፈታተኑ ድርጊቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በቤት ውስጥ ሚፈጸሙ ሲሆኑ በቤት ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ሲቀየር ግን ችግሩም ሊቃለል እንደሚችል ይታመናል፡፡ ውፍረት ሴቶችን ለስነተዋልዶ ጤና ችግር ከሚያጋልጡ መካከል ናቸው፡፡ አመጋገብን ከመጠን በታችም ሆነ ከመጠን በላይ ማድረግ ጎጂ መሆኑ የተመሰከረለት ነው፡፡ ስለዚህ አካልን በተገቢው መንገድ እንቅስቃሴ በማድረግ መጠበቅ ጠቃሚ ነው፡፡

የግል ጽዳትን መጠበቅ የስነተዋልዶ ጤናን ከመጠበቅ አኩዋያ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ የመራቢያ አካልን እና አካባቢውን በተገቢው መንገድ አለማጽዳትም ሆነ ከተገቢው በላይ ማጽዳት ጎጂ መሆኑን አስቀድሞ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በመራቢያ አካል አካባቢ በተፈጥሮ የሚገኙ ባክሪያዎች ኢንፌክሽንን የሚከላከሉ ስለሆነ በኬሚካሎችና በመሳ ሰሉት በመጠቀም አለአግባብ ማስወገድ ለችግር ያጋልጣል፡፡ ዶ/ር ዳዊት በስተመጨረሻ እንደሚሉት የስነተዋልዶ ጤናን ሁኔታ ሰፋ አድርጎ ለመመልከት ቢሞከር በአገራችን ብዙ የተሸሻሉ ነገሮች አሉ፡፡ የእርግዝና ክትትል ማድረግ፣ በጤና ተቋም እና በህክምና ሙያተኛ እርዳታ መውለድ ፣ ከወለዱም በሁዋላ ክትትል ማድረግ፣ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ተጠቃሚ መሆን...ወዘተ ... ከላይ በተጠቀሱትና የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች በየአካባቢው መኖር እንዲሁም የጤና ጣቢያዎች መገንባት በመሳሰሉት ምክንያቶች መሻሻሎች የሚታዩ ቢሆንም ነገር ግን ገና ብዙ መሰራት ያለበቸው ነገሮች እንዳሉ ሁኔታዎች ያሳያሉ ብለዋል ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ፡፡

Read 3477 times