Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 12 November 2011 07:27

“ኮተቤ ኮሌጅ ላይ የቀረበው ትችት፤ ቅንነት የጎደለውና የተዛባ ትችት ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በኮተቤ ኮሌጅ ለምዝገባ ዘግይተው አንድ ቀን ያለፈባቸው ተማሪዎች አላግባብ እንደተጉላሉ የሚገልፅ ፅሁፍና ትችት ባለፈው ሳምንት በአንድ ተማሪ መቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፤ ትችቱ ቅንነት የጎደለውና የተዛባ ነው በማለት ኮሌጁ አስተባብሏል።ፅሁፉ የተዛቡ መረጃዎችን የሚያቀርበው ከመጀመሪያው አረፍተነገር አንስቶ ነው ብለዋል - የኮሌጁ የሪጅስትራል ክፍል ሀላፊና የአካዳሚክ ም/ዲን ተወካይ አቶ ዘለቀ በየራ። በፅሁፉ የመጀመሪያ አንቀፅ የሰፈረው ሃሳብ እንዲህ ይላል...“...የምዝገባ ቀን ጥቅምት 4 እና 5 መሆኑን፤ ኮሌጁ በማስታወቂያ አስነግሯል...፡፡ ብዙዎችም በእነዚሁ ቀናት ተመዝግበዋል፡፡

አንድ ቀን ያለፈባቸውና ያልተመዘገቡ ተማሪዎችስ?”በሶስተኛውና በአራተኛው አንቀፅ ደግሞ፤ በአገር ውስጥና በውጭ አገር፤ የዩኒቨርሲቲዎችን የምዝገባ አሰራር ምን እንደሚመስል በመግለፅ እንዲህ ይላል - የኮተቤ ኮሌጅን በመተቸት።
“በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ በመደበኛ የምዝገባ ቀን መድረስ ለማይችሉ ተማሪዎች፤ ከመጠነኛ ቅጣት ጋር ተጨማሪ የመመዝገቢያ ጊዜ ይሰጣቸዋል - ከ2 እስከ 5 ቀን፡፡ በህመም ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ሌላ ችግር፤ በጊዜ ያልተመዘገበ ተማሪ ከመጣም፤ ... በከፍተኛ ችግር ሳቢያ እንደዘገየ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለማቅረብ የቢሮክራሲ ፈተናዎችን መጋፈጥ ባይቀርለትም የተወሰነ ተጨማሪ የምዝገባ እድል ያገኛል”
“እንኳን የትራንስፖርትና የመረጃ አቅርቦት ባልተስፋፋባት አገራችን ይቅርና፤ በበለፀጉት አገራትም፤ እንዲህ አይነት አሰራር የተለመደ ነው። ታዲያ፤ ይህንን እውነታ ላለማየት አይኑን የሚጨፍን የኮሌጅ አስተዳደር እዚሁ አገራችን ውስጥ ብታዩ አይገርምም? አንድ ቀን ያለፈበት ተማሪ እንዳይመዘገብ በዘፈቀደ የሚወስን አስተዳደር ቢያጋጥማችሁስ? ካጋጠማችሁ፤ ኮተቤ ግቢ ውስጥ ገብታችኋል ማለት ነው”
ትችቱ ቅንነት የጎደለውና የተዛባ ነው የሚሉት አቶ ዘለቀ፤ ኮሌጁ የምዝገባ ቀናትን በማስታወቂያ አስነግሯል። የምዝገባ ስርአቱም ካለፉት አመታት ምንም የተለወጠ ነገር የለውም ብለዋል። ጥቅምት 4 እና 5 መደበኛ የምዝገባ እንደሆነ በማስታወቂያ መነገሩ እውነት ነው ያሉት አቶ ዘለቀ፤ ነገር ግን በመደበኛው የጊዜ ሰሌዳ ላልተመዘገቡ ተማሪዎች ጥቅምት 6 ቀን በቅጣት የመመዝገቢያ ቀን እንደሆነ በዚያው ማስታወቂያ መነገሩንና በተግባርም ጥቅምት 6 ቀን ምዝገባ መካሄዱን ገልፀዋል። ትችት የሰነዘሩት ፀሃፊ ይህን መረጃ አዛብተዋል በማለት አቶ ዘለቀ ጠቅሰው፤ አላግባብ ትችት ለመሰንዘር በማሰብ፤ የቅጣት የምዝገባ ቀን በማስታወቂያ እንዳልተነገረና ምዝገባም እንዳልነበረ አድርጎ ማቅረብ ከቅንነት የራቀ ነው ብለዋል።
ሁለት መደበኛ የምዝገባ ቀናት እና አንድ የቅጣት መመዝገቢያ ቀን፤ ላለፉት አመታት ስንሰራበት የቆየ አሰራር እንጂ አዲስ አሰራር አይደለም ያሉት አቶ ዘለቀ፤ በህመምና በሃዘን አጋጣሚዎች ወይም ከአቅም በላይ በሆኑ ሌሎች ችግሮች ሳቢያ ዘግይተው የሚመጡ ተማሪዎችም፤ አሳማኝ መረጃ እስካቀረቡ ድረስ የምዝገባ እድል እንዲያገኙ የኮሌጁ ደንብ ይፈቅዳል ብለዋል። ጥቅምት 7 እና ከዚያ በኋላ ለመጡ ተማሪዎችም፤ ይህንን የአሰራር ደንብ በማስረዳት፤ መረጃ ካላቸው ይዘው እንዲመጡ ገልጨላቸዋለሁ ያሉት አቶ ዘለቀ፤ ከአንድ ተማሪ በስተቀር ሌሎቹ መረጃ የለንም የሚል ምላሽ ስለሰጡኝ፤ የኮሌጁ ደንብ ከማስረዳት ውጭ ማንንም አላጉላላሁም ብለዋል።
የተዛባ ትችት የተሰነዘረው፤ በአንድ በኩል ድክመት ያለበትን ሰው አላግባብ ለማዳነቅ ሊሆን ይችላል የሚሉት አቶ ዘለቀ፤ በሌላ በኩል የተማሪዎችን ችግር እየፈታ ትምህርታቸው የተሳካ እንዲሆን የኮሌጁን ደንብ ተከትሎ የአቅሙን ያህል የሚጥር ሰውን ለማሳጣት የታሰበም ሊሆን ይችላል ብለዋል።
የምዝገባ ጊዜ ያለፈባቸው ተማሪዎች ወደ የበላይ ሃላፊ አመልክተው፤ “ችግራቸው ታይቶ ይመዝገቡ” የሚል ምላሽ እንዳገኙ የባለፈው ሳምንት ፅሁፍ ይገልፃል። ተማሪዎቹ እንዲመዘገቡ በበላይ ሃላፊ ከተፈቀደ በኋላ ለምን እንዳይመዘገቡ ተከለከሉ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዘለቀ፤ ይሄም የተዛባ መረጃ ነው። የኮሌጁ ዲን አቶ ሣህሉ ክፍሉ በተማሪዎቹ ማመልከቻ ላይ የፃፉት ምላሽ ከዚህ የተለየ እንደሆነና የተማሪዎቹ ጥያቄ በኮሌጁ ደንብ መሰረት ይስተናገድ የሚል እንደሆነ አቶ ዘለቀ ጠቅሰው፤ በኮሌጁ ደንብ መሰረት ከሆነ ደግሞ፤ ተማሪዎቹ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር እንደዘገዩ የሚያሳይ መረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በእርግጥ ተማሪዎቹ “እንድንመዘገብ በኮሌጁ ዲን ተፈቅዶልናል” በማለት በወቅቱ ቅሬታ አቅርበዋል። ይህንኑም ለማረጋገጥ ዲኑን ደውዬ አናግሬያቸዋለሁ ይላሉ አቶ ዘለቀ። በፅሁፍ የደረሰኝ ተማሪዎቹ በኮሌጁ ደንብ መሰረት እንዲስተናገዱ የሚል ነው፤ ወይስ በቀጥታ እንዲመዘገቡ ተፈቅዷል? ይህን ጥያቄ ለዲኑ አቅዳቀረቡ የገለፁት አቶ ዘለቀ፤ በፅሁፍ ከደረሰኝ ሃሳብ የተለየ ምላሽ አላገኘሁም ብለዋል። ስለዚህ፤ “ችግራቸው ታይቶ ይመዝገቡ” የሚል ውሳኔ ከኮሌጁ ዲን አግኝተናል በሚል የቀረበው መረጃ ከእውነት የራቀ መረጃ ነው ብለዋል - አቶ ዘለቀ።
ተማሪዎቹ በመጨረሻ ጥቅምት 13 ቀን መመዝገባቸውን አቶ ዘለቀ ጠቅሰው፤ በኮሌጁ ደንብ መሰረት መረጃ አቅርበውና ታይቶ ነው የተመዘገቡት። ከጥቅምት 7 ጀምሮ ስነግራቸው የነበረውም ይህንኑን ነው፤ የመደበኛና የቅጣት የምዝገባ ቀናት ያለፈበት ተማሪ፤ መረጃ በማቅረብ መመዝገብ ይችላል። በዚሁ መሰረትም ሰርተናል ብለዋል - አቶ ዘለቀ።

 

Read 3836 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 07:29

Latest from