Print this page
Monday, 15 April 2013 10:08

በምድር ተሽከርካሪ በሰማይ በራሪ 100 ሰዎች በቅድምያ 10ሺ ዶላር ከፍለዋል

Written by 
Rate this item
(101 votes)

በሰማይ ላይ የሚበሩ ክንፍ ያላቸው አውቶሞቢሎች እውን የማድረግ ህልም ከዛሬ 82 ዓመት ገደማ ጀምሮ የተወጠነ የቴክኖሎጂ ትልም ሲሆን እስካሁን ግን እንደ ሳይንሳዊ ፊክሽን (ልቦለድ) ሲቆጠር የቆየ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በሳይንሳዊ ልቦለድነት የሚጠቅሳቸው ማንም አይኖርም፡፡ ለምን ቢባል? በቅርቡ ለገበያ ሊቀርቡ እንደሆነ እየተነገረ ነዋ! የሚበረው መኪና የመጀመርያ በረራውን ያጠናቀቀ ሲሆን በመጪው አመት Transition በሚል ስያሜ ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል፡፡ አውቶሞቢሉ ሁለት መቀመጫዎች፣ አራት ጐማዎችና የሚታጠፉ ክንፎች እንዳሉት ታውቋል፡፡ የክንፎቹ መታጠፍ አውቶሞቢሉ እንደ መኪናም በመሬት ላይ መሽከርከር እንዲችል ያደርገዋል፡፡ ባለፈው አመት Transition በ1ሺ 400 ጫማ ከፍታ ለ8 ደቂቃዎች እንደበረረ የሚታወቅ ሲሆን የንግድ ጀቶች በ35ሺ ጫማ ከፍታ ነው የሚበሩት፡፡

ገና ካሁኑ Transition የተባለውን በምድር ተሽከርካሪ በሰማይ በራሪ መኪና ለመግዛት 100 ሰዎች 10ሺ ዶላር በቅድሚያ ከፍለዋል፡፡ የአውቶሞቢሉ አምራች ኩባንያ Terrafugia inc. በመጪው ሳምንት አዲሱን በራሪ መኪና በኒውዮርክ ለህዝብ እይታ የሚያቀርብ ሲሆን ከዕይታው በኋላ የገዢው ቁጥር እንደሚጨምር ተገምቷል፡፡ ሆኖም ግን Transition በየመንገዱ ላይ እንደልብ የሚታይ አውቶሞቢልም አይደለም፡፡ ለምን ቢሉ? 279ሺ ዶላር ያወጣል ተብሎ ይገመታል - ባለ ክንፋሙ አውቶሞቢል! ይሄን አውቶሞቢል በምድር ላይ እያሽከረከራችሁ ሳለ በትራፊክ ብትጨናነቁ ምንም ማድረግ አትችሉም፡፡

ምክንያቱም ከመሬት ወደ አየር ለመነሳት ማኮብኮብያ ሜዳ ያስፈልገዋል፡፡ የሚበር መኪና በአሜሪካውያን ምናብ ውስጥ ልዩ ቦታ ነበረው፡፡ ከ1930ዎቹ ዓመታት ጀምሮ የፈጠራ ባለሙያዎች ይሄን አውቶሞቢል ለመስራት ሲታትሩ ቆይተዋል፡፡ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ተንታኝ የሆነው አሜሪካዊው ሮበርት ማን እንደሚለው፤ የሚበሩ አውቶሞቢሎችን እውን ከማድረግ አንፃር እንደ Terrafugia ኩባንያ እጅግ የቀረበ ማንም የለም፡፡ ኩባንያው ለአውቶሞቢሎቹ ልዩ ጐማዎችንና ለተለመዱት መኪኖች ጥቅም ላይ ከሚውሉ መስተዋቶች ቀለል ያሉትን ለመጠቀም ለመንግሥት ጥያቄ አቅርቦ ተፈቅዶለታል፡፡ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ተንታኙ ሮበርት ማን እንደተናገሩት፤ ከዛሬ አምስት አመት በፊት በፌደራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን ውሳኔ ኩባንያው የተለየ ቀላል የስፖርት ኤርክራፍት ስታንዳርድ በመፍጠር እገዛ ተደርጐለታል፡፡ ስታንዳርዱ የኤሮፕላኑን መጠንና ፍጥነት እንዲሁም የፓይለቶች የፈቃድ መስፈርቶችን የሚወስን ነው፡፡ ኩባንያው እንደሚለው፤ የመኪናው ባለቤት የሚሰጠውን ፈተና ማለፍ ያለበት ሲሆን Transition የተባለውን አውቶሞቢል ለማብረር የ20 ሰዓታት በረራ ማጠናቀቅ የግድ ይላል፡፡

አውቶሞቢሉ በመሬት ላይ በሰዓት 70 ማይል የሚፈተለክ ሲሆን በአየር ላይ 115 ማይል ይበራል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአጠቃላይ የአቪዬሽን ገበያው እያሽቆለቆለ መምጣቱን የሚናገሩት ተንታኙ፤ ለዚህም ምክንያቱ ከፍተኛ የነዳጅ ወጪና በአምራቾቹ ላይ የሚያርፈው የወጪ እዳ ነው ይላሉ፡፡ ሌላው ችግር የበረራ ትምህርት የሚወስዱ ሰዎች ጥቂት መሆናቸው ነው፡፡ “ይሄ ለማምረትም ሆነ ለገበያ ለማቅረብ እርካሽ የሚባል ኤርክራፍት አይደለም” የሚሉት ሮበርት ማን፤ “አዲሱ በራሪ መኪና አንዳንድ ለየት ያሉ ነገሮች አሉት፤ እናም ጥቂት ሽያጮች ያገኛል፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ምርቱ ትርፋማ ሊሆን ይችላልን? የሚለው ነው፡፡ ተንታኙ ባለሙያ እንደሚሉት ለዚህ ባለክንፍ አውቶሞቢል የበጠ የገበያ ስፍራ የሚሆነው የአሜሪካ ምዕራባዊ ክፍል ነው፡፡ ለምን ቢሉ? በዚያ አካባቢ ሰዎች ረዥም ርቀት ከማሽከርከር ይልቅ መብረርን የሚመርጡ በመሆናቸው ነው፡፡

Terrafugia በበራሪ መኪናዎች ላይ መስራት ከጀመረ ስድስት ዓመት ገደማ ይሆነዋል - ከ2006 ዓ.ም አንስቶ ማለት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በጋ ላይ ኩባንያው ምርቱን በ2011 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ለማቅረብ የገባውን ቃል ለማዘግየት ተገዶ ነበር - በዲዛይን ተግዳሮቶች እና የመለዋወጫ እቃዎች አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ማለት ነው፡፡ በራሪው ተሽከርካሪ በኒውዮርክ ለእይታ ሲቀርብ የደንበኞችንና የኢንቨስተሮችን ዓይን እንደሚስብለት ኩባንያው ተስፋ አድርጓል፡፡ “ራሳችንን ለአውቶሞቲቩ ዓለም እንደ አዋጭ ኩባንያ እያስተዋወቅን ነው” ብለዋል - የኩባንያው ቃል አቀባይ፡፡

Read 17296 times
Administrator

Latest from Administrator