Monday, 15 April 2013 07:59

“የተናወጠች ዓለም” - የተናወጠ ደፋር “ተርጓሚ!”

Written by  ከዮሐንስ ገ/መድህን
Rate this item
(4 votes)

በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ የፕሬስ ውጤቶችና የትርጉም መፃህፍት ሕትመት የተጧጧፈበት ወቅት እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ነው፡፡ በተለይ ከትርጉም ሥራዎች ውስጥ የአጋታ-ክርስቲና የሲድኒ ሸልደን መፅሐፎች በገበያው ላይ ተጽዕኖ የፈጠሩና በብዙ አንባቢዎች እጅ የገቡ የትርጉም ሥራዎች ናቸው፡፡ 2004 ዓ.ም ማገባደጃን ይዞ አሁን እስካለንበት ወር ድረስ የሲድኒ ሸልደን መፅሀፎች በቀደምት ተርጓሚዎች ሳይሆን በሌላ ተርጓሚዎች ለገበያ ቀርበዋል፡፡ ከዚህ ቀደም “በሬ ካራጁ” በሚል ርዕስ ተተርጉሞ የነበረው “የደም ውርስ” በሚል፣ “የዕጣ ፈለግ” የሚለው “ጦሰኛው ማፊያ” በሚል፣ “ከእሣት የወጣች ነፍስ” ደግሞ የ“ተናወጠች ዓለም” በሚል ርዕስ ተተርጉመው ገበያ ላይ አግኝተናቸዋል፡፡

ከእነዚህም የትርጉም መፃህፍት ውስጥ ትርጉም ሊባል የማይችልና ድፍረት የተሞላበት “ትርጉም” የተባለ ሥራ በመመልከቴ ዝም ማለት አልቻልኩምና ብዕሬን አነሳሁ፡፡ ሲድኒ ሸልደን “Wind Mills of the God - በሚል ርዕስ የደረሰው መጽሐፍ ከዚህ ቀደም “ከእሳት የወጣች ነፍስ” አሁን ደግሞ “የተናወጠች ዓለም” በሚል ርዕስ በአቶ ብስራት እውነቱ አወቀ “ተተርጉሞ” ትርጉም ከተባለ ቀርቦልናል፡፡ ሲድኒ ሸልደን በዚህ መጽሐፉ ላይ ያስተላለፈውን አንኳር ሀሳብ ፈሩን ሳይስት “ከእሳት የወጣች ነፍስ” በሚለው የትርጉም ሥራ ላይ አይተን ነበር፡፡ ለአንባቢም ሆነ ለአድማጭ ግልፅ ይሆን ዘንድ መጽሐፉን በወፍ በረር ዕይታ መቃኘት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ተብለው የተጠቀሱት ፖል ኢንሰን፤ በሥልጣን ዘመናቸው አሳካዋለሁ ለሚሉት ግብ አጋዥ የሆነች ሜሪ ኤልሣቤጥ አሽሌ በምትባል የካንሳስ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር ላይ ዐይናቸውን ይጥላሉ፡፡

በምታዘጋጃቸው ጥናታዊ ፅሁፎችና በጋዜጦች ላይ በምታወጣቸው መጣጥፎች ለራዕያቸው አጋዥ ኃይል እንደምትሆን በመተማመን ለአምባሳደርነት ይመርጧታል፡፡ በተለይም ከሮማኒያ ጋር ያላትን የሽብር ግንኙነት ለማደስ በአያቷ ሮማኒያዊ የሆነችው ሜሪ አሽሌን ቁጥር አንድ ተመራጭ ያደርጋታል፡፡ ሜሪ አሽሌ ከዶክተር አሽሌ ጋር ትዳር መስርታ ቤቲና ቲም የሚባሉ ሁለት ልጆች አፍርታለች፡፡ በምታስተምርበት ዩኒቨርስቲና በምትኖርበት አካባቢ ስለ ሜሪ አሽሌ ግለ - ስብዕና ጥናት ይካሄዳል፡፡ የጥናቱ ውጤትም አጥጋቢ በመሆኑ፣ በሮማኒያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሆን ዘንድ ለመጠየቅ ከፕሬዚዳንቱ የተላኩ ሰዎች ወደ አለችበት ካንሳስ ያመራሉ፡፡ ሜሪ አሽሌ ለቀረበላት ጥያቄ ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ ምክንያቱም ሰላም ከሞላበት ኑሮዋና ከምትወደው ቧሏ ዶክተር አሽሌ መለየት አልፈለገችምና፡፡ ይህ ምላሿ ከተሰማ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ሲአይኤ ባቀነባበረው አደጋ በመሰለ ሁኔታ የምትወደው ባሏ ዶክተር አሽሌ ይገደላል፡፡ የሀዘን ጊዜዋን እንደ ጨረሰች በቀጥታ ከፕሬዚዳንቱ በቀረበላት ጥሪ አምባሳደርነቷን እንድትቀበል ይደረግና ወደ ሮማኒያ ታመራለች፡፡

በሲአይኤ ውስጥ ያሉ ሰዎች የፕሬዚዳንቱ ራዕይ እንዳይሳካና ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን እንዲለቁ የሚፈልጉት አነ ሮጀርስታንት በሮማኒያ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆነቺው ሜሪ አሽሌ ሥራዋን ለቃ ወደ አሜሪካ እንድትመለስ በረቀቀ ስልት ከፍተኛ ማስፈራሪያና ዛቻ አፈራረቁባት፡፡ አልተበገረችም፤ በመጨረሻም እንድትገደል ተወሰነ፡፡ እሷንና ሁለት ልጆቿን የሚያጠፋ በገንዘብ የተገዛ ገዳይ ከአርጀንቲና ይላክባታል፡፡ ድርጊት በድርጊት እየተፈራረቀ ሜሪ አሽሌና ልጆቿ እንዴት ከሞት እንደተረፉ የሚተርከው በሲአይኤ ውስጥ ያሉ ድብቅ ሰዎች ለሃላፊነታቸው ግድ ሳይሉ የሚያከናውኑትን ዕኩይ ተግባር ያሳያል፡፡ “የተናወጠች ዓለም” የሚለው የአሁኑ “ትርጉም” በፊት ለፊት ሽፋኑ ላይ መስከረም 11 በኒውዮርክ መንትያ ህንፃያዎች ላይ ጥቃት ሲደርስ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ይዟል፡፡ ሽፋኑን ገለጥ ሲያደርጉት ሲድኒ ሸልደን የሚለው የደራሲው ሥም በትልቁ ተጽፏል፡፡

የመጽሐፉ ርዕስ ደግሞ “widnd Mills of God” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ልብ ብላችኋል wind የሚለው widnd የተባለው እንደ ንግድ ምልክት ለማጭበርበር ይሆን? Sony የሚለውን sany፣ U.S.A የሚለውን USA እንደማለት? ከዚያ ወረድ ሲሉ ሌላ አስደንጋጭ ጽሑፍ ታያላችሁ “በእስላም አሸባሪዎችና በሲአይኤ መካከል በአፍጋኒስታን…” የሚል፡፡ ሲድኒ ሸልደን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለአፍጋኒስታንም ሆነ ስለአሸባሪ አንድም ቃል አልፃፈም፡፡ ከየት መጣ? ለምን? በዚህ መጽሐፍ ገጽ 15 ላይ ሜሪ አሽሌ የካንሰስ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር መሆኗን ይገልጽና፤ “አያቷ የተወለደው በአፍጋኒስታን ውስጥ ነው” ይላል፡፡ ደራሲው ያልፃፈውን! በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጡት አፍጋኒስታንን የሚመለከቱ ቦታዎችና ገፀ-ባህሪዎች የደራሲው የሸልደን ሳይሆኑ “የተርጓሚ”ው የአቶ ብስራት እውነቱ አወቀ የድፍረት ሥራዎች ናቸው፡፡ ከባድ ድፍረት ነው፡፡ ሚዛናዊ ለመሆን ስለፈለግሁ ከመጽሐፍ ላይ ባገኘሁት የስልክ ቁጥር ደውዬ አቶ ብሥራትን አገኘኋቸውና፣ ደራሲው ያልፃፈውን እንዴት ሊጽፉ እንደቻሉ ጠቅኋቸው፡፡ “በአሁኑ ወቅት እጅግ አስፈላጊ ወደሆነ ቦታ ቀይሬ በመፃፌ ልታደንቀኝ ይገባል” አሉኝ “ደራሲው ያላለውን መፃፍ አግባብ’ኮ አይደለም” “ቆይ አንተ ማን ነህ?...ምን አገባህ” አሉኝ እኔማ ተራ አንባቢ ነኝ፡፡ ደፋር “ተርጓሚ” ላሞኝህ ሲለኝ እምቢ የምል፡፡

ምን ላሉት ደግሞ ለሚሉት መልሴ ያገባኛል ነው፡፡ እንደ አንባቢ አጭበርብረውኛል፡፡ ስለዚህ ዝም ማለት አልችልም፡፡ የዚህን ደብዳቤ ግልባጭ ለደራሲያን ማህበር እልካለሁ፡፡ ከዚህም ሌላ በንባብ ላይ ትኩረት አድርገው ለሚሰሩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ተራ በተራ አደርሳለሁ፡፡ ዝም ማለት አልችልም፡፡ የደራሲያን ማህበር አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ፣ አሳታሚውንና ደፋሩን ተርጓሚ አቶ ብስራትን በህግ ፊት ለማቅረብ እገደዳለሁ፡፡ ያውም እንደእኔ መጭበርበርን የማይፈልጉ እጅግ ብዙ አንባቢዎችን ከጐኔ አሰልፌ፡፡ ሁሉም አንባቢ አሁን ባለንበት ዘመን ጥቅማቸውን ያስቀደሙ ልቅና ድፍረት የተሞላበት ዕኩይ ተግባር ሲፈጽሙ እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም፤ ዝም አንልም፤ አጭበርብረህ ሳይሆን ሰርተህ ብላ እንላቸዋለን!

Read 5342 times