Monday, 15 April 2013 09:04

የበቅሎ የማንነት ቀውስ (የአህያ የበታችነት ስሜት)

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(4 votes)

አዲስ የጋማ እና የቀንድ ከብቶች በሽታ አገሪቱ ውስጥ ፈሷል፡፡ ለእያንዳንዷ መንደር አንድ አንድ ሰው ተመርጦ፣ ጥሩምባ ታጥቆ ገበሬው በጋጣ ውስጥ ያሉትን ከብቶቹን ሁሉ እንዲያስከትብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፤ ልመና ተነግሯል፤ ማስጠንቀቂያ ተላልፏል፡፡ ሲማልድ ሁሉም ገበሬዎች የጠዋት ቡናቸውን ፉት ሳይሉ፣ ቆሎዋቸውን ሳይቆረጥሙ፣ ለዚሁ ተብለው በየቀየው ወደተተከሉት ድንኳኖች እያመሩ ነው፤ የኑሮዋቸው ዋስትና የሆኑትን ከብቶቻቸውን ሊያስከትቡ፡፡ ገበሬዎቹም ከብቶቹም በቅጡ ከእንቅልፋቸው አልነቁም፡፡ በተለይ ከብቶቹ ግራ ተጋብተዋል፡፡ ሰዓቱ ማልደው ለስምሪት የሚወጡበት አልነበረም፡፡ ደግሞም ዛሬ ጋጣቸውን ከፍቶ ወደ መስክ እየነዳ ያወጣቸው ተወዳጁ እረኛቸው አይደለም፤ አሳዳሪዎቻቸው እንጂ፡፡ ሰሞኑን ጐህ ሊቀድ ሲል ጥሩንባ ሲነፋ እያንጐላጁ ሰምቷል፡፡ ለዘመናት ሲሰሙ እንደኖሩት “እከሌ የሚባል ሰው አርፏልና ወደ ጉድጓዱ ሸኙት” የሚል ጥሪ ነው ብለው ጆሮ አልሰጡትም፡፡ አሁን ነው ወዴት እንደሚሄዱ ጌቶቻቸው ሲያወሩ የሰሙት፡፡

ሰሞኑን እየቀነጠቡ ወይ እየጋጡ ወይ እያመለኩ እዚያው ፍንግል የሚሉ ጓደኞቻቸው ቁጥር በዝቶ ግራ ተጋብተው ነበር፡፡ አሁን አወቁት፡፡ በሽታ ገብቷል፡፡ ክፉ ነው አሉ በሽታው፡፡ መድሃኒቱም ውድ ነው። በብድር ነው የተገኘው፡፡ የቀንድ ከብቶቹ ወደፊት በቆዳቸው ይከፍሉታል ተብሎ ታስቧል፡፡ ክትባት ፈርተው ተደብቀው የሚያመልጡ ብልጣብልጥ ከብቶች እንዳሉ ተገምቷል፡፡ ብልጥ ሆንኩ ብሎ አንድ ከብት ሁለቴ ሊያስከትብ የሚሞክር ገበሬም አይጠፋም ተብሏል፡፡ ከታቢዎቹ ለዚህ ዘይደዋል፡፡ እያንዳንዱ የተከተበ ከብት በቀላሉ የማይለቅ ምልክት ይታተምበታል፡፡ ምን ይሄ ብቻ እያንዳንዱ ከብት የሚታከመው ስሙን ከነ አባቱ እያስመዘገበ ነው፡፡ ተጀምሯል፡፡ መጀመሪያ ላሜ ቦራ ቀረበች፡፡ አብራት የመጀመርያ ጥጃዋ ቡሬ አለች፡፡ “ስም?” አለ ቀጭኑ፣ ቀጫጫው፣ መላጣው ሐኪም፡፡ “ላሜ ቦራ፡፡” አለች፡፡ “ያባት ስም?” አሳዳሪዋን አየችው፡፡ አገዛት፡፡ “ዳለች፡፡” ላሜ ቦራ ዳለች ተብሎ መዝገቡ ላይ ተፃፈ፡፡ ተከተበች፡፡ ምልክቷን ቀኝ ታፋዋ ላይ አሳትማ ፈንጠር ብላ ቆመች፡፡ የመጀመሪያዋ ተከታቢ ስለሆነች በፍርሃት ይሁን በጉጉት ወደሚጠብቁት ጓደኞቿ በኩራት ገልመጥ አለች፡፡ ቡሬም ተከተበች፡፡

እሷም እንደ እናቷ እኩዮቿን እያየች ሳቀች፤ እምቧ አለች፡፡ የላሜ ቦራ ጐረቤት ቀጠለ፡፡ ብሎ ነው፡፡ ባለቤቱ፣ ፍቅረኛው የሚኮሩበት፤ እሱም በራሱ የሚኮራ ፈረስ ነው፡፡ “ስም ከነአባት?” “ቡሎ ታጠቅ፡፡” ተከተበ፡፡ ምልክት ተደረገበት፡፡ ሌሎች ፈረሶች ተከታተሉ፡፡ ክትባቱ እና ምልክቱ ልዩነት የለውም፡፡ የሚወጉት ፈሳሽ በእድሜ እና በፆታ ከመብዛት ከማነሱ ውጪ፡፡ ትንሽ የሚገርመው የከብቶች ስም ነው፡፡ አብዛኞቹ ፈረሶች ወይ ታጠቅ ወይ መቻል ወይ ኮስትር ወይ ቃኘው ናቸው፡፡ በእለቱ በከብቶች መሃል ለቀጠሉት ሳምንታት አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው ነገር የተከሰተው ኩንስንስ የተባለችው በቅሎ ለክትባት የቀረበች ጊዜ ነበር፡፡ “ስም?” “ኩንስንስ፡፡” “የአባት ስም?” እንደ ማሰብ አይነት አቀረቀረች፡፡ አፍታ አለፈ፡፡ ቀና ብላ አሳዳሪዋን አየች፡፡ የላሜ ቦራ አሳዳሪ ሲያግዛት አይታዋለች፡፡ አሁን አልሆነም፡፡ ያባቷን ስም ለከታቢው እንደመናገር ስታው ያያታል፡፡ ወደ ፈረሶች አየች፡፡

አያዩዋትም፡፡ እየቀፈፋት የጐረቤታቸውን ጐምቱ አህያ አየችው፡፡ አንገቱን አቀረቀረ፡፡ ብዙ አፍታዎች አለፉ፡፡ “የአባት ስም?” ደገመላት፤ ጥልማሞት የመሰለው ከታቢ፡፡ ድንገት ፊቷን አዙራ በኋላ እግሮቿ አናቱን ኳ ብታደርግለት ተመኘች፡፡ ደግሞ አጭር ስለሆነ ብትዘል መሃል አናቱን እንደምታገኘው ታውቋታል፡፡ “መጨፍለቅ ነበር፡፡” አጉረመረመች፡፡ “አልሰማሁሽም፤ ማነው ያልሽው?” አሁንም ዝምታ፡፡ “እየሰማሽኝ ነው? ያባትሽ ስም ማነው?” ተበሳጫቷል ከታቢው፡፡ የጥያቄውን መደጋገም ሰምተው፣ የኩንስንስን ግራ መጋባት አይተው ሁሉም ተከታቢዎች ወሬያቸውን አቋርጠው ወደ ሁለቱ እያፈራረቁ ያያሉ፤ አንዴ ወደ ኩንስንስ አንዴም ወደ ከታቢው፡፡ በመጨረሻም ንዴት እና ለቅሶ በተቀላቀለ ድምጽ፡፡ “አጐቴ ፈረስ ነው፡፡” አለች ኩንስንስ፡፡ ከታቢው ፊት ላይ የአግራሞት ቀለም ተደፋ። ለቅጽበት ሁሉ ነገር ፀጥ አለ፡፡ አየር ሁሉ የቆመ መሰለ። በዚህ ነብስ የዘራ ፀጥታ ውስጥ መጀመሪያ የአንዲት ፍየል ሳቅ ተሰማ፡፡ ያለ ሌላ ማስጠንቀቂያ ያን ሁሉ ፀጥታ የሳቅ ጐርፍ ወሰደው፡፡ ሳቁ በረደ ሲባል እየታደሰ ማቆሚያ የሌለው መሰለ፡፡ ከብቶቹ ብቻ አልነበረም የሚስቁት፡፡ ከታቢውም በሳቅ ሲንከተከት ዛር የሰፈረበት ቃልቻ መሰለ፡፡ ሳቁ እንደ አሜባ እራሱን እየበጣጠሰ ተባዛ። ሁሉንም ከብቶች ዝም ለማሰኘት እና ሥርዓት ለማውረድ ጊዜ እና ጥረት ጠየቀ፡፡ የአሳዳሪዎቻቸውን ዝም በሉ ጥሰው የሳቅ ክምችታቸውን አንጠፍጥፈው ሳቁ፡፡ ዝምታው በሀዘን፣ በፀፀት፣ በግራ መጋባት ሲተካ ለውጡ የታወቃቸው አልነበሩም፡፡

የቀረቻቸውን ሳቅ በከንፈራቸው አቅፈው ኩንስንስ ወደነበረችበት ቢያዩ የለችም፡፡ በሁካታው መሀል እብስ ብላለች፡፡ ከዛን ቀን በኋላ ኩንስንስን አየሁ የሚል አልተገኘም። የላሜ ቦራ ቤተሰቦች እና ሌሎችም ተከትበው የጨረሱ ቤተሰቦች የመልስ ጉዞ ሆነ፡፡ ኩንስንስ ለክትባት ቀርባ እያለ በነበረው ጥያቄ እና መልስ የፈነዳው ሳቅ እስካሁን እያሳቃት ቡሬ እየሳቀች ነው፡፡ የከታቢውን ጥያቄ የኩንስንስን መልስ ሰምታለች፡፡ ሲስቁ ባትሰማ ግን አትስቅም፡፡ አሁንም የሳቁ መወለጃ አልገባትም፡፡ የሳቁ ትዝታ ብቻ እያሳቃት መልሳ መላልሳ ትስቃለች። አሳዳሪዎቿ ወደኋላ ቀረት ሲሉ እና እናቷ ቆም ስትል ብቻ ሳቋን ጥላ የእናቷን ጡት ትጐርሳለች፡፡ በእድሜ ገፋ ያሉት ከብቶች ግን ሳቃቸውን ጨርሰውታል፡፡ ፊታቸው ላይ የሚታየው የሳቅ እላቂ ሳይሆን የሀዘን፣ የፀፀት ጅማሮ ነው፡፡ በተለየ አህዮች አንገታቸውን ደፍተዋል፡፡ ፈረሶች ነጠል ብለዋል፡፡ በቅሎዎቹ ወደኋላ ቀርተዋል፡፡ ፍየል እና በጐች ናቸው ከክትባቱ ቦታ ይዘው የመጡት ስሜት ያልነበራቸው፡፡ ላሜ ቦራ የጥጃዋን በእያንዳንዱ እርምጃ በሳቅ እየቦረቀች ወዲያ ወዲህ ማለት አልወደደችላትም፡፡ “ምን አስሬ እንደ ፍየል ታስካኪያለሽ? ምን ያስቅሻል?” ተቆጣች፡፡ “ኩንስንስ ናታ!” እየሳቀች አሁንም፡፡ “ኩንስንስ ምኗ ያስቃል?!” በርግጥም አሁን ቡሬ ግራ ተጋባች፡፡ ምን ነበር ያሳቃት? ግር አላት፡፡ መጫወቻው የጠፋበት ህፃን መሰለች፡፡ በዚያ ላይ መነሻውን ያላወቀችው የእናቷ ቁጣ አስደንግጧታል፡፡ በዙሪያዋ ያሉትን ሁሉ አየቻቸው፡፡ ሁሉም አንድ አይነት የስሜት ረግረግ ውስጥ እየሰመጡ ነው፡፡ ጨርሶ የሰመጡም አሉ፡፡ ላሜ ቦራ ቡሬ በድንጋጤ ኩስስ ብላ ደፋ ደፋ ስትል ራሷን ወቀሰች፡፡

ያኮረፈቻትም መሰላት፡፡ ቡሬ ከእናቷ ራቅ ብላለች፡፡ “ነይ ወዲህ!” አለች ላሜ ቦራ መፀፀቷን ሊደብቅ በሚሞክር ድምጽ፡፡ እናቷ ተቆጥታ ያበቃች መስሏት ነበር ቡሬ፡፡ ይኸኛው ቁጣ ክፍል ሁለት እንደሆነ ገመተች፡፡ “አቤት?” “ለምን እንደምትስቂ አልነገርሽኝም፡፡” አሁን እናቷ ድምጽ ውስጥ ቁጣ እንደሌለ ለየች፡፡ ተረጋጋች፡፡ “ቆይ እናንተ ሁላችሁስ ለምን ሳቃችሁ?” ላሜ ቦራ ጥጃነት የተጫነው የቡሬ መልስ ያመጣውን ሳቋን አስቀረችው፡፡ “መጀመሪያ የተጠየቅሺውን መልሺ!” “እኔ የሳቅሁት እናንተ ስለሳቃችሁ ነው፡፡” “ሌላው ሲስቅ ታይቶ ብቻ ይሳቃል እንዴ?” “ታዲያ ሌላ እንዴት ይሳቃል?” እንዲህ አይነት ጥያቄ መኖሩ ራሱ ገረማት ቡሬ፡፡ “አይ የጥጃ ነገር፡፡” አለች ላሜ ቦራ በልቧ፡፡ ቀጠለች ቡሬ፡፡ “ቆይ እማ አንቺም ስትስቂ ነበር፤ ሌሎቹ ሁሉ ሲስቁ ነበር፡፡ እናንተ ሌላው ሲስቅ አይታችሁ ካልሆነ እንዴት ሳቃችሁ?” “በከታቢው ጥያቄና በኩንስንስ መልስ ሃራምባ እና ቆቦ መሆን፡፡” “ሃራምባ እና ቆቦ ምንድነው?” ላሜ ቦራ ቡሬን እንዴት እንደምታስረዳት ግራ ገባት፡፡ “እንዲገባሽ አያቴ ያንቺ ቅድመ አያት ስለአንድ ጠንጋራ የነሱ እረኛ ስለነበረ ልጅ የነገሩኝን ልንገርሽ። እንደምታያቸው ፍየሎች አንድ ቦታ ረግተው ቅጠል አይቀነጥሱም፡፡

ቀልቃሎች ናቸው፡፡ በተለይ ሰብል በደረሰ ወቅት የሚበላ ሳይጠፋ ዘለው የሰው ማሳ ውስጥ መግባት ይቀናቸዋል፡፡ ታዲያ አንዴ…እ…ቆይ…የአቶ ከን እርሻ ታውቂዋለሽ አይደል?” “አዎ፡፡” “የአቶ ቀንስ?” “አቃለሁ እሱንም፡፡ ከአቶ ከእርሻ ፊት ለፊት ወንዙን ተሻግሮ ያለው አይደል?” “አዎ፤ ልክ ነሽ፡፡ እና አንድ የተንቀለቀለች ፍየል የአቶ ከ እርሻ ውስጥ ገብታ ያላረሰችውን ትሸመሽማለች፡፡” “እሺ፡፡” አለች ቡሬ እየሳቀች፡፡ የፍየሏ ተንኮል እና ድፍረት አስቀንቷት፡፡ “የተናደደው እረኛ ቅዝምዝሙን ወደ አቶ “ቀ” ማሳ ወረወረልሽ፡፡ አቶ “ከ” ማሳ ውስጥ ያለችውን ፍየል ሊሰብር መሆኑ እኮ ነው፡፡” እናት እና ልጅ አብረው ሳቁ፡፡ “እማ የዚህን እረኛ ታሪክ ሰምቻለሁ፡፡ አሁን አንቺ እንደምትይው ግን ጠንጋራ መሆኑን አልሰማሁም ነበር።” “ኧረ ለኔም ሲነግሩኝ ጠንጋራ ነው አላሉኝም፤ ግን እንዲህ አይነት ስህተት የሰራው ጠንጋራ ጥንግርግር ቢሆን እንጂ ብዬ ነው፡፡” “መቼስ እማ ፍየል ሁሉ እረኞቻቸው ጠንጋራ ቢሆኑላቸው ይመኛሉ አይደል?” “ፍየል ከዚህ የተሻለ ነገር ተመኝቶ አያውቅም።

አሁን ወደ ጥያቄሽ ልምጣና የአቶ ከን ማሳ ሀራምባ በይው የአቶ ቀን ቆቦ፡፡ አሁን ገባሽ ሀራምባና ቆቦ ምን ማለት እንደሆነ?” “ገባኝ፡፡” አለች ቡሬ፡፡ ከድምጿ ይልቅ የጥጃ አይኗ በደንብ እንደገባት ይናገራል፡፡ “ይኸውልሽ ከዛን ጊዜ ወዲህ ሰዎች የነገር መነሻ መድረሻው አልገናኝ ሲላቸው ‘ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ’ ይላሉ፡፡ ጠንጋራ እረኛ ወዲህ ክልፍልፍ ፍየል ወዲያ ማለት ይቀል ነበረ፡፡ ለውጥ ሲፈልጉ ‘ሀራምባና እና ቆቦ’ ይላሉ እልሻለሁ፡፡” “አሁን በጣም ገባኝ፡፡ ከታቢው የጠየቀው የአባት ስም፣ ኩንስንስ የመለሰችው ፈፅሞ የተለየ ነገር ነበር ማለት ነው፡፡ ኩንስንስ ግን ጠንጋራ መሆኗን አላውቅም ነበር፡፡” ላሜ ቦራ ሳቋን መቆጣጠር አልቻለችም፡፡ ቡሬም ተከትላት ሳቀች፤ በምን እንደሳቀች ባይገባትም።

ለመሳቅ የሚስቅ ፊት ከማየት ሌላ ምክንያት እንደሚያስፈልገውም የሰማችው ዛሬ ነው፡፡ “አይ! ኩንስንስ ጠንጋራ አልነበረችም፡፡” አሁን የላሜ ቦራ ድምፅ ሀዘን ነፍሶበታል፡፡ ዝም ተባባሉ። ቡሬ ነገሮችን ለማገናኘት ሞከረች፡፡ ሊገባት አልቻለም። የሆነ የተደበቃት ነገር አለ፡፡ ከፊት፤ ከጐን፤ ከኋላዋ የሚሄዱትን ከብቶች ሁሉ አየቻቸው፡፡ ማንም ወደ ማንም አያይም፡፡ ሁሉም አቀርቅረዋል፡፡ “እሺ እማ ኩንስንስ ጠንጋራ ካልሆነች ለምን እንዲያ አይነት መልስ መለሰች? ፈረሶች፤ በቅሎዎች እና አህዮችስ ምን ሆነው ነው እንዲህ ያዘኑት? አንቺስ መንገዳችን ላይ ስስቅ ለምን ተቆጣሽ? ኩንስንስ የት ገባች?” ላሜ ቦራ ወዲያው መልስ አልሰጠቻትም፡፡ “የዚህን ሁሉ ምክንያት በኋላ ብቻችንን ስንሆን እነግርሻለሁ፡፡” ከክትባት ሲመለሱ ሰዓቱ ረፍዷል፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ጥጆች ከላሞች ጋር ጌቶቻቸውን በየመዳረሻው ይጠብቁት ለነበሩት እረኞች ለስምሪት የተተውት፡፡ በስንት ጊዜ አንዴ የሚገኝ እድል ስለሆነ የጥጆች ደስታ ልክ አልነበረውም፡፡ ለወትሮው የእናታቸው ግት እስኪነጥፍ ጥጆች ጓሮ አጥር ላይ ታስረው፣ ላሞች ስምሪት ነበር የሚውሉት፡፡ ቀትር ላይ ከብቶች ሁሉ በወገናቸው በየጥላው አርፈዋል፡፡

ላሜ ቦራ ከቡሬ ጋር የዋርካ ጥላ ስር ጋደም እንዳለች፡- “እማ?” አለቻት ቡሬ፡፡ “እህ?” አለች ላሜ ቦራ፤ ነገሩ ገብቷታል፡፡ “ጠዋት ብቻችንን ስንሆን እነግርሻለሁ ያልሽኝን ንገሪኝ፡፡” “አንቺ መቼም ጡትና ነገር ከያዝሽ አትለቂም፡፡” “እራስሽ አይደለሽ ብቻችንን ስንሆን እነግርሻለሁ ያልሽኝ?” “እሺ እንግዲህ፡፡ የሚገርመው አሁን ስለኩንስንስ እያሰብኩ ነበር፡፡ ዛሬ ብትሰወር ጫካውን ጭር አደረገችው፡፡ ምስኪን ኩንስንስ… አያቴ አያቷ ከአያታቸው ሰምተው የነገረችንን ነው የምነግርሽ፡፡” “ምን ብለው ነገሩሽ?” “ያኔ በአያቴ አያት አያት ጊዜ ነው አሉ፡፡ አንድ ፈርጣማ፣ ጉልበታም፣ ተወዳጅ አህያ ነበር፡፡ እሱን መሳይ አህያ ተፈጥሮም አያውቅም ብለውኛል፡፡ በአካባቢው በፍቅሩ ያልከነፈች አህያ አልነበረችም። በተለይ አገር ያስመረረ ጅብ በአንድ እርግጫ ከገደለ በኋላ፣ በተፈጥሮ ሞገሱ ላይ ጀግንነነቱ ተደርቦ ጐፈር የቀረው አንበሳ ሆነ፡፡ ሴት አህዮች ሁሉ በፍቅሩ አበዱ፡፡ ፈጣሪ መቼስ ሲሰጥ አይሰስትም - ከጉልበቱ፣ ከውበቱ፣ ከድፍረቱም በላይ ደግሞ በፍቅር ጨዋታ አዋቂነቱ የሚስተካከለው አልነበረም፡፡ በቀበሌው ያሉትን አህዮች ትተሽ ከሩቅ ሀገር ስንት አህዮች ዝናውን ሰምተው ልጆቻቸውን ትተው በወጡበት ቀርተዋል መሰለሽ? ግና ምን ያደርጋል ኋላ ክብሩ ሁሉ እንዳይሆን ሆነ፡፡” ላሜ ቦራ ወሬዋን አቋርጣ ሩቅ የምታይ መሰለች። “ምን ሆነ?” “ትእቢት ወጠረው፡፡ ውሎውን ቀየረ፡፡ የአህያ ዘር አያሳየኝ አለ፡፡ ውሎው ሁሉ ከፈረሶች ጋር ሆነ፡፡ በኋላማ ጉድ አመጣ፡፡ ከጐረቤቶቻቸው ባዝራ ፍቅር ያዘኝ ማለት ያዘ፡፡

አገር ጉድ አለ፡፡ በዚያ ላይ ፈረሷ የምትወደው ጓደኛ አላት፡፡ በኋላ ሁኔታው አላምር ሲላት ትርቀው ጀመር፡፡ ይህ ደግሞ የሱን እልህ አባባሰው፡፡ አንድ ቀን ብቻዋን አግኝቷት ካልሳምኩሽ ይላታል፡፡ እምቢ አለችው፡፡ ትእግስቱ አልቆ ነበርና አንቺ ከማን በልጠሽ ነው እምቢ የምትይው ይላታል። እሷም የዋዛ አልነበረችም አሉ፡፡ ምን እንዳለችው ታውቂያለሽ?” “እንዴት አውቃለሁ? ምን አለችው?” “ጥያቄውማ መሆን የነበረበት ማን ከማን ጋር እኩል ነው ብላው አረፈች፡፡” “ትእቢተኛ አይደል፤ ‘አህያ ከፈረስ ጋር፡፡’ ብሎ መለሰላት” “እሺ ከዚያ በኋላስ?” አለች ቡሬ ምልልሱ ጥሟት፤ በቦታው ኖራ ቢሆን እየተመኘች፡፡ “በኋላ አህያነቱን የሚያስጠላ መልስ ሰጠችዋ፡፡ ‘አህያ እና ፈረስ መቼ ነው እኩል ሆኖ የሚያውቀው? ካልክስ አይቀር ፈረስ ሲበላሽ መጋዣ ይሆናል፡፡ መጋዣ ሲበላሽ ያው መጋዣ ነው፡፡ የተበላሸ መጋዣ ተበላሽቶ ሲበላሽ ምናልባት ከአህያ እኩል ይሆን ይሆናል፡፡’ስትለው ንዴቱን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ በእርግጫ ጥርሷን አወለቀው፡፡” “አቤት እንዴት ባለጌ ነው!” አለች ቡሬ፡፡ “ብልግናው በዚህ ቢበቃማ ደግ ነበር፡፡ እርግጫ ያለ ነገር ነው፡፡ እሱ ግን እርግጫው አልበቃ ብሎት እስከ ዛሬ የፈረሶችንም የአህዮችንም አንገት ያስደፋ ስህተት ሰራ፡፡ ዛሬ ጠዋት ኩንስንስ ለቀረበላት ጥያቄ መልስ አጥታ መሳቂያ ሆና የጠፋችውም ያ ወደል አህያ በፈፀመው ስህተት ነበር፡፡” ዝም አለች ላሜ ቦራ፡፡

ለቀረበላት ጥያቄ መልስ አጥታ መሳቂያ ሆና የጠፋችውም ያ ወደል አህያ በፈፀመው ስህተት ነበር፡፡” ዝም አለች ላሜ ቦራ፡፡ “ምን አደረገ?” አለች ቡሬ፡፡ “ለጥጃ የሚነገር አይደለም፡፡” “ላትጨርሽ ለምን ወሬውን ጀመርሽልኝ ታዲያ?” ተበሳጭታለች ቡሬ፡፡ አሰብ አደረገች ላሜ ቦራ፡፡ “እሱስ እውነትሽን ነው፤ ከጀመርኩ አይቀር ልጨርሰው፡፡ ላንቺም ትልቅ ትምህርት ይሆንሻል፡፡ ምድር ስትፈጠር ጀምሮ በሰዎች እንጂ በከብቶች መሃል ተደርጐ የማያውቅ ስህተት ፈፀመ፡፡ ይኸው ዳፋው ለዘር ማንዘሩ ተረፈ፡፡ አሳቻ ሰዓት ጠብቆ ያቺን ፈረስ ደፈራት፡፡ ሲያመጣው ልክ የለው አይደል፤ አረገዘች። ይህንን የሰሙ ወገኖቹ ይመኩበት እንዳልነበር አይንህን ለአፈር አሉት፡፡ አንድ ጠዋት እንደወጣ ቀረ። ፈረሶቹ ጥቃቱ አንገብግቧቸው ነበር። ሱባኤ ገቡ፡፡ ‘አንዴ የተረገዘው ይወለድ፤ እሱ ግን ፍሬ አይኑረው።’ ብለው ፀለዩ፡፡ ይኸው በቅሎ አይኗን በአይኗ ለማየት አልታደለችም፡፡ በዚያ ላይ የማንነት ቀውስ ያሰቃያቸዋል፡፡” “የማንነት ቀውስ ምንድን ነው?” ጠየቀች ቡሬ፡፡ “የማንነት ቀውስ ማለት አህያ ሆኖ ከፈረስ ጋር ፍቅር ያዘኝ ማለት ወይም በቅሎ ሆኖ የአህያን አባትነት መካድ ነው፡፡ ኩንስንስ እንዲህ አይነት ችግር ነው ያጋጠማት። አየሽ እናቷ ገና በልጅነቷ ሁሉን ነገር ልትነግራት ይገባ ነበር፡፡ ያ ሆኖ ቢሆን፤ ትክክለኛውን መልስ ብትናገር ይሄ ሁሉ ነገር ባልተፈጠረ ነበር፡፡” “ትክክለኛው መልስ ምን ነበር?”

“የአባቷን ስም መንገር ነዋ!” “አባቷ ማን ነው?” “የአቶ ሠ አህያ ጉራች ነው፡፡” “እንዲህ አይነት ቀላል መልስ እያለ ነው ኩንስንስ እንዲያ መሳቂያ የሆነችው?” “አየሽ መልሱ እንዲህ ቀላል ነው፡፡ የሚከብደው እራስን ካልተቀበሉ ነው፡፡ በአያቷ ስህተት መሃን መሆኗ አንሶ የአባቷን ስም ለመጥራት እንዲያ አይነት ችግር ውስጥ ራሷን ከታለች፡፡ ያ ነው የማንነት ቀውስ። ኩንስንስ ኩንስንስ ናት አባቷ ጉራች እንደሆነ ሁሉም ያውቃል፤ ያ ግን ለማንም ቁብ አይሰጠውም። ሁሉም ኩንስንስን ይወዷታል፡፡ ማንም በቅሎ፣ ማንም ጥጃ፣ ማንም ቡችላ አባቱን የመምረጥ እድል የለውም። የሆነውን መቀበል ነው፡፡ ኩንስንስ የጉራች ልጅ መሆኗን እያወቀ ሁሉም ይወዳታል፡፡ እሷ እራሷን ጠላች እንጂ፡፡” “እራስን መጥላት ይቻላል እንዴ?” ጠየቀች ቡሬ ገርሟት፡፡ ዛሬ ተገርማ አላባራ ብላለች፡፡ “እንክት አድርጐ ነዋ!” “እንዴት?” “እራስን መካድ፤ እራስን ካለመቀበል እራስን ከመጥላት ይጀምራል፡፡ እራስን ከሌላው ጋር ማነፃፀር ሲጀምሩ ደግሞ የከፋ በሽታ ይሆናል፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻ እኮ የአህያ ነው፡፡ እሱ እንደውም መሳይ ያልነበረው ፈርጣማ፣ ጐበዝ፣ ቆንጆ ነበር፡፡ ብጤዎቹ በፍቅሩ ሲከንፉ የንቀት ፈሱን እያንዛረጠባቸው የፈረስ ፍቅር ፍለጋ ሄደ፡፡ እሷም በንቀት አሽካካችበት፡፡

ያው የነገርኩሽ ውርደት በራሱም፣ በልጆቹም አመጣ፡፡ አህዮች እኮ ከዚያ ወዲህ ነው ወገባቸው እስኪታጠፍ ሲጭኗቸው፣ አጥንታቸው እስኪሰነጠቅ ሲመቷቸው እማያንገራግሩት፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ስህተቱን የሰራ አሁን አጥንቱ አመድ የሆነ አህያ ነው፡፡ እነሱ የእሱን ውርደት ተሸክመው የሚኖሩበት ምክንያት የለም፡፡ “ይኸውልሽ ቡሬ ጥጃዬ፤ ለመኖር የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ እራስን መቀበል ነው፡፡ እራስን ከሌላው ጋር ማወዳደር፣ መለካት አያስፈልግም፡፡ ይህ የልብም የአእምሮም ነቀርሳ ያመጣል፡፡ እኔ እናትሽ ሁሌ ላም አድርጐ የፈጠረኝን አምላክ አመሰግናለሁ፡፡ አንዴ የሆነ ነገር ሆኖ ከተፈጠረ በኋላ ይህን ብሆን፣ ያንን ብሆን የሚለው ለማንም አይበጅም፡፡ ሌላው ይቅርና ሰዎች እራሱ እራሳቸውን ተቀብለው ይኖራሉ፡፡ አሁን እስኪ ሰው አድርጐ ቢፈጥረን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር?” የመጨረሻው አረፍተ ነገር ቡሬን አስደነገጣት፡፡ ዞር ብላ ከእነሱ በቅርብ እርቀት ጥላ ስር ያለውን እረኛቸውን አየችው፡፡ “እውነት አሁን ሰው ሆነን ተፈጥረን ቢሆንስ” ብላ አሰበች፡፡ ሳቋ ጫካውን ሞላው፡፡

Read 2852 times