Monday, 15 April 2013 08:47

የ“ፖለቲካዊ ፍልስፍና” መጽሃፍ ለዛና ቁምነገር!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)

ሰሞኑን እጄ ገብቶ ያነበብኩት መጽሃፍ “ፖለቲካዊ ፍልስፍና” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን የ“ኢቦኒ” መጽሄት ዋና አዘጋጅ በሆነው በቃል ኪዳን ይበልጣል የተዘጋጀ ነው፡፡ መጽሃፉ በዓለማችን የታወቁ ታላላቅ ፈላስፎችን ታሪክና ስራ የያዘ ሲሆን ፍልስፍና ምንድነው? ፍልስፍና ለምን? የፍልስፍና ታሪክ፣ ዐበይት የፍልስፍና ክፍሎች፣ ሌሎች የፍልስፍና ዘርፎች፣ ነገረ ፖለቲካዊ ፍልስፍና…ወዘተ በሚሉ ክፍሎች ተከፋፍሏል፡፡ ዐበይት የፍልስፍና ክፍሎች በሚለው ርዕስ ስር ዲበአአካል፣ሥነ ዕውቀት፣ሥነ ምግባር፣ሥነ ውበት፣ሥነ አመክንዮ እያለ አስቀምጧቸዋል፡፡ ከአምስቱ በተጨማሪ ራሳቸውን የቻሉ ናቸው ተብሎ እንደ ቅርንጫፍ የሚታዩትን የአዕምሮ ፍልስፍና፣የቋንቋ ፍልስፍና፣የትምህርት ፍልስፍና፣የሃይማኖት ፍልስፍና በሚል ዘርዝሯቸዋል፡ መጽሃፉ ከጉዳዮች ቅደም ተከተልና የጽሁፉ ፍሰት ጀምሮ እጅግ ደስ የሚያሰኝ፣ማራኪና ዕውቀት ሰጪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የብዙ ጸሃፊዎች ችግር ስለጉዳዩ ዕውቀት እያላቸው እንዴት አድርገው እንደሚጽፉ ያለማወቃቸው ነው፡፡ እኔ ደግሞ ጥሎብኝ ውበት አደንቃለሁ፡፡ ፍሬነገሩ ብቻ አይማርከኝም፡፡

ውበት መፍጠርም ውድ ተሰጥዖ ነው፡፡ የተመኘ ሁሉ አያገኘውም፡፡ መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ እንኳ ነቢዩ ኢሳያስ በዘይቤ ያበዱ ቅኔዎችን ሲጽፍ፣ ሁሉም ያንን አላደረጉትም፡፡ ሉቃስ ወንጌሉን በምሳሌያዊ ንግግሮች ሲያጅብ፣ ሌሎቹ ያን ያህል አላስጌጡትም፡፡ የቃል ኪዳን “ፖለቲካዊ ፍልስፍና” ከጠበቅሁት በላይ ስለነበር ታክሲ ውስጥ ሆኜ ነው ያገባደድኩት፡፡ መጽሃፉ ውስጥ ምናልባት የምናውቃቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ይሁንና የማናውቃቸውን አዳዲስ ነገሮች ይጨምርልናል፡፡ የጥንቱን ፈላስፎች እነ አፍላጦንን፣ አርስጣጣሊስን ጨምሮ ኒኮሎ ማኪያቬሌን፣ጆን ሎክን፣ኤድመንድ በርክን፣ ዣን ዣክ ሩሶን ወዘተ ትውልዳቸውን፣ ዕድገትና ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን ያሳየናል፡፡ ሌላው ትልቁና ጥሩው ነገር ጸሃፊው ሰበካ ውስጥ ሳይገባ ሃሳቡን ለአንባቢ መተው ነው፡፡ አንብቦ ይህ ጥሩ ነው- ይህ መጥፎ ነው የሚል እድል ለአንባቢው ትቷል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ብዙዎቻችን በማኪያቬሌ ሃሳብ በጣም እንበሳጫለን፤እንራገማለን፡፡

ምናልባትም ሊከብደን ይችላል፡፡ በተለይ እዚህ መጽሃፍ ውስጥ ያልተካተተውና እንግሊዝኛው መግቢያ ላይ ያለው ስለ (inspiration)ወይም በአማርኛ የነገረ መለኮት ምሁራን እንደሚሉት “አፊዎት” የሚናገረው ነገር በጣም ያስጠላል፡፡ ጸሃፊው ይህንን ያለመጥቀሱን አድንቄያለሁ፡፡ ምክንያቱም አንባቢውን ይገፋልና! ከማኪያቬሌ ሃሳቦች ውስጥ ጥቂት ላንሳ መሰለኝ፡፡ እንዲህ ይላል፡- “የሰዎች ባህርያት በተለያዩ ስሜቶች ሊቀረጹ ይችላሉ፡፡ ኑሮ የተመቻቸውም ያልተመቻቸውም አዲስ ነገር ይፈልጋሉ፡፡ የለውጥ ፍቅር የትም ቦታ ለሚከሰት ፈጠራ መለኮሻው ነው፤ ስለዚህ ሰው በብዙሃን እይታ አዲስ ወይንም እንግዳ መስሎ ከታየ ሃሳቡ እርባና ያለውም የሌለውም ቢሆን በስኬት መሰላል ወደ ላይ መመንጠቁ ይገመታል፡፡ሌሎች ብርቱ ስሜቶቻችን ድርጊቶቻችንን ይወስናሉ፡፡ ፍቅርና ፍርሃት፡፡ ሰዎች እንዲፈሩት የሚያደርግ ፤ሰዎች እንዲወዱት የሚያደርገውን ያህል ተጽእኖ መፍጠር ይችላል፡፡ ቶማስ ጀፈርሰን እንዲህ ቢልም “…and not to blast the confidence we have inspired of proof that a government of reason is better than one of force.” ጥልቅ ምኞትም በማንነታችን ላይ ከፍተኛ ጉልበት አለው፡፡

ሰዎች የቱንም ያህል ቢያድጉ ከቁመታቸው የሚልቅ ምኞት በልባቸው ውስጥ ይኮተኩታሉ፡፡ የምኞት ሃይል የተመኘነውን ስናገኝ ከሚሰማን እርካታ ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ምኞት ተጨማሪ እየጠየቀ ዘወትር ከጉያችን አይጠፋም፡፡ ሰዎች የነጻነት ፍላጎትም ኣላቸው፡፡ ነጻ ሆነው በማንም ሳይገደቡ ህይወታቸውን እንዲመሩ፣ዝንባሌያቸውን እንዲከተሉ፤ጥሩ ነው የሚሉትን እንዲያባርሩ ይሻሉ፡፡ ነጻ መሆን (በሌሎች እስር ወይም ጥገኝነት ስር ላለመዋል)ያለው እርግጠኛ መንገድ ሌሎችን ጥገኛ ማድረግ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ሰው የበላይ መሆንን ያፈቅራል፡፡ እንደ ማኪያቬሌ እምነት በዚህ ፍላጎት መነሻነት በህዝብና መንግስት መካከል ፍልሚያ ሊኖር ግድ ነው፡፡ የማኪያቬሌ ሳይንስ ደግሞ ፖለቲካል ሳይንስ ነው- በቅርቡ እንደሚጠራበት ስያሜ፡፡ ምክንያም ፖለቲካል ሳይንስ የሚያጠናው፤ መንግስት በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ተግባር ነውና!...የፖለቲክስ ኤንድ ሶሳይቲ ጸሃፊ ሚካኤል ሩሽ እንደሚሉት “political science is therefore the study of the function of the government in society. ማኪያቬሌ ፖለቲካዊ ስልጣን በህዝብ ፈቃደኝነት ላይ የሚመሰረት ነው ይላል፡፡ በዚህ ሃሳብ ደግሞ አብርሃም ሊንከን፣ ቶማስ ጀፈርሰንና ሌሎችም የአውሮፓና የአሜሪካ ፖለቲከኞች ይስማማሉ፡፡ ይሁንና ማኪያቬሌ ይህንን ፍቃደኝነቱን እንደ ህጻን አባብሎ ከህዝብ ጉያ መንጠቅ ይቻላል ብሎ ያምናል፡፡

እንዲህ፡-ህዝብ ክብሩ፤ንብረቱ እና ደህንነቱ ከተጠበቀለት ስለ ፖለቲካዊ ፖሊሲዎች ፤ስለመንግስት ስርዓቶች እና ቅርጾች ጠልቆ በመመራመር ራሱን አያደክምም፡፡ ደስ እያለው ፈቃዱን ይቸራል፡፡….እያለ ይቀጥላል፡፡ ይህንን መርህ ደግሞ ብዙ የአፍሪካ መሪዎች እንደሚጠቀሙበት አይተናል፡፡ የኛም ሃገር መሪዎች ከምንወዳቸው ይልቅ እንድንፈራቸው ስላደረጉን፣ ስናማቸው እንኳ ግራና ቀኝ ተገላምጠን ነው፡፡ ካለበለዚያ መታወቂያና ሽጉጥ አውጥቶ “የህዝብ ደህንነት ነኝ” ቢል የማን ያለህ ይባላል፡፡ አያድርስ እንጂ!...እግዜር የምንፈራው ሳይሆን የምንወድደውን መሪ ይስጠን! እኔ ተቃዋሚዎቹም ከዚህ የተለዩ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ የተከበብነው በጉልበተኞች ነው፡፡ ከራሱ ሃሳብ በስተቀር የሌላውን የተለየ ሃሳብ የማያስተናግድ ፕሬስም አምባገነን ነው፡፡ ጠመንጃ ከያዘማ…አለቀልን፡፡ አምባገነንነት የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ምናልባት እነዚህ ሰዎች ስልጣን ቢይዙ የዛሬውን ያህል እየታሰሩም መጻፍ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሁላችንም ውስጥ አምባገነንነት አብሮ ሳያድግ አልቀረም፡፡ ማኪያቬሌ የሚለውን አንድ ሃሳብ ልበል መሰለኝ - ባልደግፈውም፡-“ሁለት አይነት የፍልሚያ ስልቶች እንዳሉ ማወቅ አለባችሁ፡፡አንደኛው በህግ ሌላኛው በሃይል፡፡ የመጀመሪያው ዘዴ የሰዎች ነው፤ሁለተኛው የአራዊት፡፡ ግን ቀዳሚው መንገድ ሁልጊዜም በቂ ስለማይሆን ሁለተኛውን መተግበር የግድ ይሆናል፡፡

ቀጣዩ ቶማስ ሆብስ ነው፡፡ ይህ ሰው የዴሞክራሲን አስተሳሰብ የሚያጣጥልና ባላባታዊውን አገዛዝ የሚደግፍ እንደሆነ መጽሃፉ ያሳያል፡፡ ሆብስ ስለ ሳቅ የሚለው ነገር ትንሽ ለየት ይላል፡፡ “ሳቅም ሆነ ጨዋታ አንድም በኣንዳች ዘርፍ የበላይነት በማግኘት ለራስ የሚሰጥ ዕውቅና እና ሙገሳ ነው፡፡ ወይንም በሌሎች ላይ እንከን ውድቀትን ማየት የሚፈጥረው የደስታ ስሜት ነው፡፡ ሆብስ ስለ ሰዎች ልዩነት የሚናገረው ቀለል አድርጎ ነው፡፡ ለምሳሌ እንዲህ ይላል፡-“ተፈጥሮ ሰዎችን በአዕምሮና በአካል ዘርፎች እኩል አድርጋ ነው የሰራቻቸው፡፡ ምንም እንኳን ለሌሎቹ በአካል ገዝፎ የሚታይ ወይንም በአእምሮ ደከም ብሎ የሚስተዋል ባይጠፋም፤በጥቅሉ ሲመረመር በሰውና በሰው መካከል ያለው ልዩነት እምብዛም ነው፡፡ የሚበልጥ የመሰለው ሰው ብልጫው ከሌሎች የተሻለ ዕድል ተጠቃሚ የማያደርገው ነው፡፡ ሆብስ እንዲህ ይላል የሰውን ልጅ አስመልክቶ፡፡…ሰው በአንድ ወቅት ይኖር የነበረው ያለ መንግስት ነው፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሯዊው የአኗኗር ሁኔታ ያ ነው፤ ነገር ግን ይህ “ተፈጥሯዊ የነገሮች ሁኔታ”ወይ ሊከሰት የማይቻል ወይንም የማይመች ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ስለሆነም በተወሰነ ወቅት ላይ የተፈጥሯዊው ሁኔታ ኗሪዎች ተሰባሰቡና በንቁ ልቦናቸው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተቋማትን ለመመስረት ተስማሙ-- ይልና መንግስት የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ ሲናገር፡-“በማህበር ከመሰባሰባቸው በፊት ተፈጥሯዊው የሰዎች ሁኔታ ጦርነት ነበር፤ ቀላል ጦርነት ሳይሆን ሁሉም ሰዎች ከሁሉም ሰዎች ጋር የተፋጠጡበት ጦርነት፡፡” መንግስት እንዲቀጣ መኖር አለበት የሚል ሃሳብ አለው፡፡ ይህ ደግሞ በዘመናችን ካለው legitimate -/position/ power ከሚለው ጋር የሚመሳሰል ይመስላል፡፡ ይህ ስልጣን ሌሎችን የመቆጣጠሪያ፣ የማስተዳደሪያ መሳሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ መምህር፣ፖሊስ፣ወዘተ መንግስት መኖር ግድ ያለው የሰው አውሬያዊ ጠባይ ነው- እንደ ሆብስ አባባል፡፡ የዚህ ተቃራኒ ደግሞ ሄነሪ ዴቪድ ቶሩ የተባለው ፈላስፋና ጸሃፊ ነው፡፡ ቶሩ ፈጽሞ መንግስት መኖር የለበትም ነው የሚለው፡፡ ጥሩ የሚባል መንግስት የለም ባይ ነው፡፡ የሰዎችን ነጻነት ነጥቆ ህይወታችውን ይረብሸዋል ይላል፡፡…ይህ ሰው በነኤመርሰን ዘመን የነበረ የቅርብ ዘመን ሰው ነው፡፡ ዣን ዣክ ሩሶ ሌላው የመጽሃፉ እንግዳ ነው፡፡ ሩሶ የካልቪን እምነት ተከታይ(ፕሮቴስታንት) እንደ ነበረ ይገልጻል፡፡ ሩሶ በርግጥም የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በቀጥታ ቃል በቃል ባላስታውሰውም እምነቱን የተወበት ምክንያት ጥቅም ሳይሆን ፣ክርስትና ለነጻነት ትግል አያመችም በሚል እሳቤ ነው፡፡ ያ ብቻ አይደለም ፤ሩሶ ፈላስፋ ነው፣ወይስ አይደለም የሚሉ ሁለት ጎራዎችም አሉ፡፡..የሩሶን ጉዳይና ህይወት በሚያትተው ጽሁፉ ጸሃፊው ቃል ኪዳን ግልጽ ያላደረገልን ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡

ምናልባት ልክ የሌለውንና ወደ ግብዝነት ያዘመመውን ጨዋነታችን(ትህትና) አስፈርቶት ይሆን?…እንዲህ የሚለው ነገር አልገባኝም፡-“…የሩሶ እናት ትዳር ከመመስረትዋ በፊት የፍቅር ግንኙነት መጀመሯ በሌላ በማንኛውም ቦታ ያንን ያህል ተጋንኖ ሊታይ የማይችል ጉዳይ ቢሆንም ጄኔቫ ውስጥ ግን ተሰምቶ የማይታወቅ ዓይነት ቅሌት ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡” ምናልባት የግብረ ስጋ ግንኙነት ፈጽማ ነበር ለማለት ይሆን? የዚህ ዓይነቱ ነገር ቢነገር ምን ጣጣ አለው!...ምላስ ላይ ሳይሆን ተግባር ላይ መጠንቀቅ ይሻል ይመስለኛል፡፡ ንግግሩን ጠልቶ ነገሩ ላይ ከበረቱ በእግዜርም በሰውም ፊት ዋጋ የለውምና ህዝቡም ይህንን ቢለምድ ደስ ይለኛል፡፡ ራስን ማታለል አይጠቅምም፡፡ ያፈጠጠ ጸያፍ ካልሆነ ስንሸፋፍነው ሃሳቡን ያዛባልና ቃልኪዳን --- ግድ የለህም በለው፡፡ ወደ ማጠቃለያ ከመምጣቴ በፊት ፖለቲካዊ ትግልን ከሰላማዊ ትግል ጋር አጣምሮ የሚያስበውን ጋንዲን መጥቀስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ጋንዲ ጆርጅ ዉድ ኩክ በጻፉለት የህይወት ታሪክ መጽሃፍ ውስጥ እንዲህ ተጠቅሷል፡፡…who did not fear to be violent, but chose deliberately to be non violent and to fight by power of truth rather than by the power of body. ይሁን እንጂ በዚህ ሰላማዊ ትግሉም እስርና ጉስቁልና አልቀረለትም፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ደራሲ እንዲህ ይላሉ በመጽሃፋቸው፡-“Gandhi entered yeravda prison, near poona, with a great deal of composure. he is already familiar with the predictable routines of prison life,~ ሰዎች ይህንን እንደ ተጋነነ ቢቆጥሩትም ጋንዲ እስር ቤቱን እንደ እረፍት ስፍራ ይቆጥረው ነበር፡፡ በርግጥም ከላይ እንደ ተጠቀሰው እስር ቤት መግባት ለርሱ ተደደጋጋሚ የህይወት ጎዳና ነበር፡፡

በሰለጠነው ዓለምና በሰለጠነ ህዝብ መሃል ሰላማዊ ትግል በጣም የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ የዚህ ቀማሪና ጀማሪ ደግሞ መንግስት አያስፈልግም ባዩ ሄነሪ ዴቪድ ቶሩ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግም ይህንኑ ተከትሎ ውጤት አስገኝቶበታል፡፡ ምንም ቢሆን ሰላማዊ ትግል ከመገዳደል የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ይህንን እንደ ማታለያ ወስደው የሚሸቅጡ መንግስታት ቢኖሩም አንድ ቀን ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብሎ መቀበል የተሻለ ነው፡፡ ወደ ማጠቃለያ ስመጣ የ“ኢቦኒ” መጽሄት አዘጋጅ የሆነው ቃል ኪዳን ይበልጣል “ፖለቲካዊ ፍልስፍና” በሚል መጽሃፉ እጅግ በጣም ጥሩ ስራ እንደሰራ ሳልናገር አላልፍም፡፡ አንዳንድ ቦታ በጣም በአጋጣሚ ጥቂት ስህተት ከማየቴ ውጭ (ለምሳሌ ገጽ 44 ላይ ስለክርስቲያናዊ ፈላስፎች የሚያወራበት ቦታ ‹በአጭሩ ሰው ሀጥአን ነው፡፡ ብሏል፡፡ ሀጥዕ- መባል ሲገባው! በዚሁ ገጽ “የፖለቲካ ቲዮሪስትነቱ” የሚለው አልተመቸኝም፡፡ ምክንያቱም በአማርኛና በእንግሊዝኛ መሃል ተንጠልጥሏል፡፡ ካልሆነ ዶክተር ፈቃደ እንደሚለው “ትወራ” ቢለው ይሻላል፡፡ እርሱም የአማርኛ ቋንቋን የሚገድል አካሄድ በመሆኑ አይመችም፡፡ ከዚህ በቀር በቋንቋ አጠቃቀም፣በጽሁፉ ፍሰት፣በቅደም-ተከተላዊ ትረካው እጅግ የሚመስጥና የሚስብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን ዕውቀት ለጠማቸው ሁሉ የሚያስጨብጠው ስንቅ አለ፡፡ እኔ ደስ ብሎኝ አንብቤዋለሁ፡፡ ውበትና እውቀትን አይቼበታለሁ፡፡ ቃልኪዳን ይበልጣል ተሰጥዖም ጥረትም አለህ በርታ - አሪፍ ነው!!

Read 5116 times