Monday, 15 April 2013 08:24

የመታሰቢያ ድርጅቶች (ፋውንዴሽን) ከአፄ ምኒልክ እስከ መለስ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

         የመታሰቢያ እና በጐ አድራጐት ድርጅቶች የ85 ዓመታት ጉዞ

ከመላው ዓለም በፊዚክስና ኬሚስትሪ፣ በሕክምናና በሥነ ፅሁፍ እንዲሁም በሰላም ዙርያ የላቀ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰዎች ተመርጠው የሚሸለሙበት የኖቤል በጐ አድራጐት ድርጅት በተመሰረተ በ10ኛ ዓመቱ በኢትዮጵያም ተቀራራቢ ዓላማ ያለው “መታሰቢያ ድርጅት” ተቋቁሟል፡፡ አፄ ምኒልክ ከሞቱ ከአራት ዓመት በኋላ ልጃቸው ንግሥት ዘውዲቱ በ1910 ዓ.ም ለአባታቸው መታሰቢያነት አራት ኪሎ የሚገኘውን የበአታ ለማርያም ገዳም ቤተክርስቲያንን ማሰራት ጀመሩ፡፡

በግዛው ኃይለማርያም ተዘጋጅቶ የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ድርጅት በ1956 ዓ.ም ባሳተመው “ዳግማዊ ምኒልክ” የተሰኘ መፅሃፍ፤ የበጐ አድራጐት ሥራዎች በሦስት ዘርፎች ተከፍለው እንደሚከናወኑ ያመለክታል፡፡ የመጀመሪያው መታሰቢያቱን ማዕከል ያደረገው ነው፡፡ ግንባታው በተጀመረ በአስረኛ ዓመቱ በ1920 ዓ.ም የተጠናቀቀው የበአታ ለማርያም ገዳም ቤተክርስቲያን፤ የአፄ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱ፣ የንግሥት ዘውዲቱ፣ የብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ የልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ አስከሬንና የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶች መቀመጫ ሆኗል፡፡ መታሰቢያ ድርጅቱ፤ በሁለተኛ ደረጃ ተግባራዊ ያደረገው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ማቋቋም ሲሆን በ1925 ዓ.ም የተመሰረተው የአብነት ትምህርት ቤት፤ አገልግሎቱን ሳያቋርጥ እስካሁን በመቀጠል 80 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ሦስተኛው ተግባር የአረጋዊያን መርጃና የወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ነው፡፡ በንግሥት ዘውዲቱ ጠንሳሽነት የተመሰረተው የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ድርጅት፤ በተቋቋመበት ዓላማ መሰረት አገልግሎት እየሰጠ የቀጠለ ሲሆን እስከ 1967 ዓ.ም አስደማሚ ተግባራትን እንዳከናወነ የግዛው ኃይለማርያም መፅሃፍ ይገልፃል፡፡ ከአፄ ምኒልክ አድናቂና ወዳጅ ኢትዮጵያዊያን በተለገሱ መሬት፣ ገንዘብና ቁሳቁስ የበጐ አድራጐት ሥራውን የጀመረው የመታሰቢያ ድርጅቱ፤ በኋላ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ገቢ የሚያስገኙለት ይዞታዎች ባለቤት አግኝቶ ነበር፡፡ ፒያሳ ከመብራት ኃይል መሥሪያ ቤት አጠገብ የሚገኘው “ዘውዲቱ ሕንፃ” ከይዞታዎቹ ተጠቃሽ ነው፡፡ በ1967 ዓ.ም አብዮት ሲፈነዳ እነዚህ ገቢ የሚያገኝባቸው ይዞታዎች በደርግ መንግሥት ተወረሱበት፡፡ እንዲያም ሆኖ ድርጅቱ ከነአካቴው አልቆመም። እስካሁን ድረስ በሥራ ላይ የሚገኘው የመታሰቢያ ድርጅቱ፤ ችግርና ስጋት አጥልቶበታል፡፡

የመታሰቢያ ድርጅቱ በነሐሴ 2004 ዓ.ም ባሰራጨው ታሪክ ዘጋቢ ሲዲ ላይ በምስልና በቃለ መጠይቅ አስደግፎ ባቀረበው መረጃ፤ የአብነት ትምህርት ቤቱ ክፍሎች አርጅተው በመፈራረስ ላይ ሲሆኑ ችግረኞችን የመርዳት አቅሙም እየተዳከመ መምጣቱ ተጠቁሟል፡፡ ቤተመንግሥትን መነሻና ማዕከል አድርጐ የተቋቋመው ሁለተኛው የመታሰቢያ ድርጅት (ፋውንዴሽን) የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት ነው፡፡ በ1964 ዓ.ም “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት” ያሳተመው መፅሐፍ የድርጅቱን የሃያ አመት (ከ1945-1965 ዓ.ም) እንቅስቃሴ በስፋት ያስቃኛል - የንጉሡ የበጐ አድራጐት ሥራዎች ሕጋዊ መልክ ከመያዛቸው በፊትና በኋላ የተሰሩ ሥራዎችን በመዘርዘር፡፡ ንጉሡ፤ ገና ንግስናቸውን ሳያገኙም በበጐ አድራጐት ሥራዎች ላይ ይሳተፉ እንደነበር የሚገልፀው መፅሃፉ፤ በሐረር ከተማ ራስ በሚል ማዕረግ በሚጠሩበት ዘመን በደብረ ሊባኖስ ገዳም በየዕለቱ ለችግረኞች ምግብ ያቀርቡ ነበር ይላል፡፡ የበጐ አድራጐት ድርጅቱ በ1945 ዓ.ም በቻርተር ተቋቁሞ ሕጋዊ ከሆነ በኋላ፣ የመጀመሪያውን ገቢ የሚያስገኙ ተቋማት በልግስና ያገኘው ከራሳቸው ከንጉሡ ነበር፡፡ ለምሳሌ ቤተ ሳይዳ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሆስፒታል፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ የሐረር ልዑል መኮንን ሆስፒታል… የመሳሰሉት ከንጉሠ ነገሥቱ ወይም ከመንግሥት ለበጐ አድራጐቱ በቀዳሚነት የተሰጡ ተቋማት ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ የሚኖሩ የሕንድ ኮሚዩኒቲ አባላት መሉ ወጪውን በመቻል ያስገነቡትና በ1948 ዓ.ም ለበጐ አድራጐት ድርጅቱ ያበረከቱት ጋንዲ ሆስፒታልና ሌሎችንም በልግስና አግኝቷል፡፡ የበጐ አድራጐት ሥራዎቹ እየሰፉ ሲመጡም ገቢ የሚያስገኙለት ዘዴዎችን መንደፍ ጀመረ። የመጀመሪያ ተግባሩም በልግስና ያገኛቸውን ተቋማት ማስፋፋት ነበር፡፡ በመቀጠል በተለያዩ ቦታዎች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙለትን የግንባታ ሥራዎች አከናወነ፡፡ የሳር ቤት ጐጆዎች፣ አፍሪካ አዳራሽ አጠገብ የሚገኘው ኮከብ ሕንፃ፣ መርካቶ ውስጥ ምዕራብና አመዴ ገበያ የመሳሰሉት ሕንፃዎች የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት ያስገነባቸው ናቸው፡፡ የበጐ አድራጐት ድርጅቱ ሕሙማን በነፃ ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ፣ ጧሪ አልባ አረጋዊያንን በመንከባከብ፣ ወላጅ አልባ ሕፃናት ያለ ችግር የሚያድጉበትን ዘዴ በማመቻቸት፣ ለአካል ጉዳተኞች የትምህርት እድል በመፍጠር አያሌ መልካም ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በመጨረሻም በድርጅቱ ጥላ ሥር የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት በ1955 ዓ.ም በአዋጅ እንዲመሰረት ተደረገ። የሽልማት ድርጅቱ ከ1957-1966 ዓ.ም ባሉት ዘጠኝ አመታት ውስጥ 39 ብሔራዊ፣ 19 ዓለም አቀፍ እና 14 “የእቴጌ መነን” ሽልማቶችን ሰጥቷል።

ብሔራዊ ተሸላሚዎቹ እውቅ የጥበብ ሰዎችንና የንግድ ባለሙያዎችን የሚያካትት ሲሆን ሽልማቱን ከተቀበሉት መካከልም መርስኤ ሀዘን ወልደቂርቆስ፣ በቀለ ሞላ፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ተሰማ ሀብተሚካኤል፣ አፈወርቅ ተክሌ፣ ተካ ኤገና፣ ደስታ ተክለወልድ፣ ፀጋዬ ገ/መድህን፣ እስክንድር በጐሲያን፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ገብረየሱስ ኦዳ፣ ማህተመሥላሴ ወልደመስቀል፣ መንግሥቱ ለማ… ይገኙበታል፡፡ “የአፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ” በሚል ርእስ በበሪሁን ከበደ ተዘጋጅቶ፣ በ1993 ዓ.ም በታተመው መፅሐፍ ውስጥ ንጉሱ የሽልማት ድርጅቱን ያቋቋሙበትን ምክንያት ሲገልፅ፤ “አፄ ኃይለሥላሴ አገራቸው ኢትዮጵያ በትምህርት እንድታድግ፣ በሀብት እንድትበለፅግ ለማድረግ ሕዝባቸውን ከፊደል ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲ እንዲማር በማድረግ ብቻ ሳይወሰኑ፣ ዓለም አቀፍ የሆነ የሽልማት ድርጅት አቋቁመው በዓለም የሚጠቅም ታላላቅ ሥራ ለሰሩ ሰዎች እንዲሸለሙ አድርገዋል፡፡

ይኸንን የአደረጉበት ምክንያት ዝናን ለማትረፍ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሸላሚዎቹ ለመሸለም የበቁበትን ተረድቶ መንፈሳዊ ቅናት እንዲያድርበትና እነሱ የሰሩትን ሰርቶ አገሩንና ወገኑን እንዲጠቅም፤ እሱም ለሽልማት እንዲበቃ ለማድረግ ነው” ይላል፡፡ የ1967 ዓ.ም አብዮታዊ እንቅስቃሴ ለዳግማዊ ምኒልክም ሆነ ለኃይለሥላሴ የበጐ አድራጐት ድርጅቶች ጥፋት እንጂ ልማት አላመጣም፡፡ “የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ”ን መልካም ተግባር ያቀዛቀዘው የደርግ አብዮት፤ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የበጐ አድራጐትና የሽልማት ድርጅቶችን ደግሞ ከነአካቴው እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር መጋቢት 12 ቀን 2001 ዓ.ም ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ ስለዚሁ ሲናገሩ፡- “ደርግ ሁሉንም ነገር ሲወርስ ቆም ብሎ ማሰብ አልቻለም እንጂ ሽልማት ድርጅቱ ለአገር እድገት ቁልፍ የሆነ ተግባር ሰጪ ተቋም ነበር፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንደተባለው፣ ሽልማት ድርጅቱንም ብሔራዊ ወይም አብዮታዊ ብሎ ስሙን በመጠኑ በመቀየር ተግባሩን ማስቀጠል ይቻል ነበር፡፡ መዘግየት መፍጠኑ ለጊዜው ባይታወቅም፣ ያን መሰል የሽልማት ድርጅት በአገሪቱ መቋቋም ይኖርበታል” ብለው ነበር፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት፤ የኮሌጅ ተማሪዎችን ለማበረታታት “ደቂቀ ጠቢባን” በሚል ዘርፍ በጉብዝናቸው ከሸለማቸው ተማሪዎች መካከል የጀኔራል ዊንጌት ት/ቤት ተማሪ የነበሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይገኙበታል፡፡

ህይወታቸው ካለፈ ሰባት ወራት ገደማ ያስቆጠሩት አቶ መለስ ዜናዊ ባለፈው ሳምንት በስማቸው የመታሰቢያና የበጐ አድራጐት ድርጅት ተቋቁሞላቸዋል - “መለስ ፋውንዴሽን” የሚል፡፡ ይሄም በአገሪቱ በመሪ ደረጃ የተቋቋመ ሦስተኛ ፋውንዴሽን ያደርገዋል፡፡ በፋውንዴሽኑ ምስረታ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአቶ መለስ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ “የመለስ ፋውንዴሽን መገለጫ ግኡዝ ከሆነው ድንጋይና እምነበረድ ድርድር በላይ አስተሳሰቡና ራዕዩ ትውልድ ተሻጋሪ ኃያልነትን እንዲጐናፀፍ ማስቻል ነው” ብለዋል፡፡ ከዜሮ የመጀመር አባዜያችን በዚህ ታሪክ ውስጥም ይታያል፡፡ የተጀመሩ መልካም ተግባራትን ማስቀጠል ባይቻል እንኳን፤ ቀድሞ ለተሰሩና ለተሞከሩ ነገሮች ክብር፣ ምስጋናና አድናቆት መስጠት፤ ዛሬ እንደ አዲስ ለሚጀመሩት ሥራዎች ቀጣይነት ዋስትና ያስገኛል፣ ተስፋን ያለመልማል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለመከባበርና ለመመሰጋገን ጊዜው አልረፈደም፡፡

Read 3823 times