Monday, 15 April 2013 07:54

ኢህአዴግና ሰጐናዊ ባሕርዩ

Written by  ካሌብ ንጉሴ
Rate this item
(2 votes)

ሰጐን ትልቅ እንስሳ ናት፤ ሁለት እግሮችና ክንፎች ስላሏት ከአዕዋፍ ዘር የምትመደብ፡፡ ኢህአዴግም ትልቅ ፓርቲ ነው፡፡ “ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር” የሚባሉ ቃላትን ደጋግሞ ስለሚያወራም ዴሞክራትና የመልካም አስተዳደር ጠበቃ መስሎ ለመታየት ይሞክራል፡፡ ሰጐን የሆነ አደጋ ሲያጋጥማት አንገቷን ብቻ አሸዋ ውስጥ ትቀብራለች፡፡ ያ ግዙፍ ሰውነቷ ግን ለፈራችው ጥቃት መጋለጡን ልብ አትልም፡፡ ቢጋለጥም “ዓይኔ ካላየው የመጣው ይምጣ” የሚል ተፈጥሮአዊ ግብዝነት ያላት ትመስላለች፡፡

ለኢህአዴግ ስጋቱ ደግሞ የምርጫ ወቅት ነው፡፡ የምርጫ ጊዜ በደረሰ ቁጥር ረጅም አንገቱን ከህዝብ ውስጥ መቅበር ይፈልጋል፡፡ ለነገሩ እንዲህ ዓይነት የባህርይ ለውጥ ያመጣው መሠረቱን ክፉኛ አናግቶበት ካለፈው ከምርጫ 97 ወዲህ ነው፡፡ “ምርጫው እንከን አልባ እንዲሆን ኢህአዴግ ሌት ከቀን ይሠራል” ብሎ እንዳልተገዘተ ሁሉ እውነተኛውን የህዝብ ፍላጐት ሲረዳ ግን ምርጫው ሃገሪቱን በእጅጉ አጠይሟት አለፈ፡፡ ሁኔታው የተረጋጋ ሲመስልለት “ንስሐ ገብቻለሁና እባካችሁ ይቅር በሉኝ?” ብሎ ህዝቡን በየአዳራሹ በመሰብሰብ ተማፀነ፡፡ ይቅርታ ለመጠየቅ ሳይሆን ለስብከት የተላኩ የሚመስሉት ካድሬዎችም የታዘዙትን ፈጽመው ተመለሱ፡፡ ምርጫ 2002 ሲመጣም ኢህአዴግ ከመቸውም በላይ ስጋትና ፍርሃት ውስጥ በመውደቁ ካድሬዎቹ ሁሉ ሥራና ትምህርታቸውን እያቋረጡ ህዝቡን እንዲማፀኑ አዘዘ፤ በዚሁ መሠረትም በየቤቱ እየዞሩ “እባካችሁ እኛን ምረጡ?” በሚሉ ካድሬዎች ንዝንዝ ህዝቡ መውጫና መግቢያ አጥቶ ቆየ፡፡ “እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል” ሆኖበት እንጂ የሚያሰጋ ቀርቶ እዚህ ግባ የሚባል ተቃዋሚ ፓርቲ አልነበረም፡፡

ምን አልባት አለ ከተባለም የድሮው የህወሐት ጐምቱ አባላት ያሉበት መድረክ ብቻ ነበር፡፡ ቅንጅት የለም፤ ኦብኮ የለም፤ ኅብረት የለም፤ ሁሉም የለም፡፡ ያም ሆኖ የ1997 ምርጫ መንፈስ ከኢህአዴግ ልብና አዕምሮ ውስጥ ገና ስላልጠፉ እንደ ቀድሞው በህዝብ ላይ የሚሳለቅበት አቅም አልነበረውም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከምርጫው ውጤቱ በኋላ አድርገውት የማያውቁትን ኮፍያቸውን አውልቀው ትህትና ለማሳየት የሞከሩትና መስቀል አደባባይ ለተሰለፈው ደጋፊያቸው ዝቅ ብለው እጅ የነሱት፡፡ ይህ ትህትና በህይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳዩት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በያዝነው ወር ለሚካሄደው የከተማና ወረዳ ምርጫም ኢህአዴግ ያለፈውን ዓይነት ትህትና ለማሳየት እየሞከረ ነው፡፡ ወይም ሰጐናዊ ባህርዩን እያሳየን ነው፡፡

ለ22 ዓመታት ያልፈታውን ችግር በ”ፈጣን መንገድ” እፈታዋለሁ እያለ ይምልና ይገዘት ጀምሮአል፡፡ እድሜ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ካድሬዎች እንጂ በኢቴቪ የማይፈታ ችግርና የማይመጣ ዕድገት የለም። “ጤፉ ርካሽ ነው፤ መብራትና ውሃ በሽበሽ ነው፤ የትራንስፖርት ችግር የለም፤ ሥራ አጥነት በኮብልስቶን ተፈትቷል፤ የሴቶችና የሕፃናት ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዕልባት አግኝቷል፤ የሃይማኖት እኩልነት በሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መፍትሔ ተሰጥቶታል፤ ወዘተ” ሁሉ ሙሉ ሁሉም ዝግጁ ነው፡፡ ቴሌቪዥናችንን ስንዘጋ ብቻ ነው ያ ሁሉ ብልጽግና፣ ያ ሁሉ የኢህአዴግ በረከትና ረድኤት ህልም መሆኑን የምንገነዘበው፡፡ ኢህአዴግ በህዝብ ምርጫ ሳይሆን በጉልበቱ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ለድፍን 22 ዓመታት ሥልጣን ላይ ቆይቷል፡፡ በእኒህ ዘመናቱ ግን ትክክለኛ የሚመስል ምርጫ ለማከናወን የሞከረው በ1997 ዓ.ም ብቻ ነው፡፡ ያኔ እሱ ለራሱ የሚሰጠው ግምትና ሕዝብ ያሳየው እውነተኛ ምላሽ ተገቢውን ትምህርት የሰጠው ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም “ተጨባጭ ለውጥ አመጣለሁ” ብሎ መማልና መገዘት የጀመረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በእርግጥም ከምርጫ 97 በኋላ ኢህአዴግ የመላእክት ሳይሆን ሰዎች የተሰባሰቡበት ድርጅት መሆኑን ተገንዝቧል ባይ ነኝ፡፡

ቢያንስ የህዝብን ኃያልነት መቀበል ተገዶአልና! ገጠርን ማዕከል ያደረገውን ጉዞውን ወደከተማ በማዞር ቢያንስ አዲስ አበባ ላይ እንቅስቃሴ ጀምሮአልና፡፡ ሆኖም ሰጐናዊ ባህርዩ አልለቀቀውም፡፡ የምርጫ ጊዜ ሲደርስ ብቻ አንገቱን ከህዝብ ውስጥ ለመቅበር ይጣደፋል፡፡ የእሱ አሸዋ ሕዝብ ነው፡፡ ሰጐን አንገቷን አሸዋ ውስጥ ከቀበረች ሌላውን አካሏን ጅብ ቢዘነጥለው፤ ወይም አቦሸማኔ ቢበታትነው ጉዳይዋ አይመስልም፡፡ ኢህአዴግም ከምርጫ ሰሞን ጦስ የሚያወጣው የሚመስለው በምርጫ ዋዜማ ላይ ባህታዊ መስሎ ህዝብን መቅረብ መሆኑን ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ለነገሩ ቢጨንቀው ነው እንጂ ይህ አይነቱ የዳንኪሆቴ ጉዞ ባላስፈለገውም ነበር፡፡ የሰርቫንቲሱ ዳንኪሆቴ በሃሳቡ ጦረኞችን እየፈጠረ፣ ከነፋስ ወፍጮዎችና ከሌሎች ግዑዛን አካላት ጋር ይጨፋጨፋል፡፡ ኃይሉንም እንደ እራፊ ጨርቅ በዋዛ ሲጨርሰው እናስተውላለን፡፡ ኢህአዴግም እንዲሁ ነው፤ የሌለ ተቃዋሚ በሃሳቡ ይፈጥርና ሌትም ቀንም ሲዋትት ይኖራል፡፡ በተለይ በምርጫ ሰሞን አባላቱን እረፍት በመንሳት ህዝቡንም እረፍት እንዲነሱት ያደርጋል፡፡ በመሠረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ተቃዋሚ አለ ብዬ አላምንም፡፡ አንድም በኢህአዴግ ውትብትብ ድር በመጠለፋቸው፤ አለዚያም በራሱ በተቃዋሚው ልፍስፍስ ባህርይ የተነሳ አገራችን እንደ ሌሎች አገሮች (ኬንያን መጥቀስ ይቻላል) ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉ ፓርቲዎች የሉም፡፡ አሉ ከተባለም ከማርያምና ከሚካኤል ማህበራት የማይሻሉ አልቃሻ ስብስቦች ብቻ ናቸው፡፡

የእኒህ ስብስብ ደግሞ ኢህአዴግን ሊያሰጋው አይችልም፤ አይገባምም። ይልቁንም ሃገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ተጠቃሚ እንደሆነች ለጋሽ አገሮችን ማታለያ ዘዴ ሆኗል፡፡ ታዲያ ማንን ፈርቶ ነው ኢህአዴግ አድርጐት የማያውቀውን ትህትና ሰሞኑን ማሳየት የፈለገው? በየአዳራሹ ህዝብን እየሰበሰበ “ፈጣን ዕድገት፣ ፈጣን ለውጥ፣ ፈጣን ሎተሪ፣ ፈጣን ወዘተ” ሁሉም ሃሳቦቹ “ፈጣኖች” ናቸው፡፡ ሰሞኑን ዐበይት ካድሬዎቹ እናመጣለን ያሉትም “ፈጣን መፍትሔ” ነው። ግን እንዴት? መልስ ያልሰጡበት፣ ሊሰጡበት የማይችሉትም ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም ተዓምራዊ የሆነ “ፈጣን ለውጥ ይመጣበታል የተባለ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ተግባራዊ ላደርግ ነው” ብሎ በ1990ዎቹ ውስጥ ልባችንን ውልቅ ሲያደርገው ነበር፡፡ እንዲያውም “ከዚህ በኋላ በዋልጌ ቢሮክራቶች መንገላታት በቃ” የሚል ምሥራች ሁሉ ነግሮን ነበር፡፡ ለጉዳዩ ማስፈፀሚያ በየዘመናዊ ሆቴሎች ያልተካሄደ ስብሰባና ውይይትም አልነበረም፡፡ ያለቀው ወረቀት፣ ቀለምና ጊዜ ለታሪክ ቢተው ሳይሻል አይቀርም፡፡ ህዝቡም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሌት ቀን የሚረጩትን ፕሮፖጋንዳ ተቀብሎ “የዘመናት ችግሬ ሊፈታ ነው” የሚል ተስፋ አሳድሮ ነበር፡፡ ግን ገና ወሬው ከተጣደበት ሳይወርድ የወቅቱ አቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ፤ በተስፋ ሲያንበሸብሸን በነበረው በዚያው ቴሌቪዥን ብቅ ብለው “የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ መክኗል” ሲሉ መርዶአቸውን ነገሩን፡፡ ሰውየው ፊትለፊት ተናጋሪ በመሆናቸውና እውነቱን በወቅቱ ስለነገሩን ሊደነቁ ይገባል፡፡

ጥቂት ቆይቶም ኢህአዴግ “ቢፒአር” (መሠረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥ) ተግባራዊ አድርጌያለሁ ብሎ የተለመደ ዜማውን በመገናኛ ብዙኃኑ አማካይነት እስኪሰለቸን ድረስ ይነግረን ጀመር፡፡ እንዲያውም “የውልና ማስረጃ ጽ/ቤትና የኢሚግሬሽን ጽ/ቤት የአሠራሩ ውጤቶች ሆኑ” ተብሎ ሽልማት ሲበረከትላቸው በዚያው በኢቴቪ ተመልክተናል። እርግጥ ነው የአሠራር ሂደት ለውጡ እንደተጀመረ ቀበሌ ድረስ ሽርጉዱ በዝቶ ነበር፡፡ ግን የአንድ ሳምንት ሆይ ሆይታ ሆነና እሱም ወደ ነበር ተቀየረ፡፡ በቀልጣፋ ሥራቸው የተሸለሙት ተቋማትም ወደነበረው ቀርፋፋነታቸው ተመለሱ፡፡ መቸም ኢህአዴግ ስም የማውጣት ችግር የለበትም “ቢኤስሲ” (ባላንስድ ስኮር ካርድ) የሚባልና ተጠያቂነትን የሚያስከትል አሠራር አስፍኛለሁ” በማለት፡፡ እንደ ልማዱም ለአውደ ጥናትና ለልዩ ልዩ ስብሰባ እጅግ በርካታ ገንዘብ አባከነ፡፡ ቢፒአር ሲሰራማ እንዲያውም “ለልምድ ልውውጥ” እየተባለ በርካታ የሰው ኃይል ወደተለያዩ አገሮች በመላክ፣ “ከሰው ነፍስ በላይ ውድ የሆነው” ዶላር ባካነ፡፡ ወደ ውጭ እንዲሄዱ የተደረጉት ደግሞ በኮሚቴው ውስጥ የሚሰሩት ሳይሆን “አፋዳሾችና ለአለቃቸው የሚያቶከቱኩት” እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ይኸ ሁሉ የሚሆነው ታዲያ በገንዘባችን ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያሻው “ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሜሽን”ም ሆነ “ቢፒአር” እና “ቢኤስ ሲ” መልካም አስተዳደርን በማስፈን የህዝቡን ተጠቃሚነት ወይም እንደ ኢህአዴግ አባባል የፈጣን ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነበር፡፡ ሆኖም መልካም አስተዳደር ወሬው እንጂ ግብሩ አልታወቅ ብሎ ያው በእውር ድንብር እየተመራን ነው፡፡ ዋልጌትነትና ጉቦም በአዋጅ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ህዝቡን መድረሻ እያሳጣ ነው፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የኢህአዴግ ዘጠነኛ ድርጅታዊ ጉባኤም ሆነ ቀደም ብለው የተካሄዱት የአባል ድርጅቶቹ ጉባኤዎች ያረጋገጡትም ኢህአዴግን የሚጥሉት ተቃዋሚዎችም ሆኑ ሻዕቢያና አልሻባብ ሳይሆኑ የራሱ ሙሰኛ አባላት መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው ሰሞኑን አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ አቶ ተፈራ ደርበው፣ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤልና ቀደም ሲልም እነ አቶ ድሪባ ኩማ የአዲስ አበባን ህዝብ እየሰበሰቡ “ፈጣን ምላሽ የሚያሻቸው ጉዳዮች” እያሉ ብዙ ሲነገር፣ ሲደለዝና ሲሰረዝ በኖረ፤ እጅግ በሰለቸ ጉዳይ ላይ ሲፈክሩ የታዩት፡፡ ጉዳዩ ግልጽ ነው፤ የምርጫ ጊዜ ደርሷል፡፡ እናም ለ22 ዓመታት ያልተፈታውን ችግር በአንድ ሳምንት የሚፈታ መስሎ መቅረቡ የሰጐን ባህርዩን አጉልቶ አሳይቶበታል፡፡ ለዘመናት “ጆሮ ዳባ” ብሎት የኖረውን የትራንስፖርት፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ጣጣ እንዴት ነው በ “ፈጣን ምላሽ እፈታዋለሁ” ብሎ ህዝብን የሚደልለው? ባለሥልጣናቱ ቀን ህዝቡን ሰብስበው “በፈጣን ምላሽ እንፈታዋለን” ሲሉት የዋሉትና በተስፋ ተሞልቶ አጨብጭቦላቸው የተመለሰው ህዝብ እቤቱ ሲገባ የሚጠብቀው መብራትም ሆነ ውሃ ተዳፍኖበት ነው። ታዲያ ፈጣኑ ምላሽ መቼና የት ላይ ነው ተግባራዊ ሆኖ የሚታየው? ምን አልባት የሃይማኖት አባቶች እንደሚሉት፤ በሰማይ ቤት ይሆን የተሟላ መብራትና ውሃ የሚገኘው? ይህ ከሆነ ኢህአዴግ ከገዢ ፓርቲነቱ ይልቅ የሃይማኖት ተቋምነት ሊያዋጣው ይችላልና ፊቱን ወደዚያው ማዞር ይኖርበታል፡፡ የትራንስፖርት ችግር ሰውን መድረሻ አሳጥቶታል። ቁርሱን ሳይበላ ወጥቶ መንገድ ላይ ይሰለፋል፤ ሰብአዊ ክብሩንም ገንዘቡንም አጥቶ ቢሮው ሲገባ የህሊና ቢስ አለቆች ግልምጫና ስድብ ይጠብቀዋል፡፡ አለቅየው ከማርስ የመጣ ይመስል የሰራተኛውን ችግር መገንዘብ አይችልም፤ ወይም ነባራዊውን እውነት የሚገነዘብ በቂ ህሊና የለውም፡፡ ምክንያቱም ለእሱ ከእነቤተሰቡ ሁለትና ከዚያ በላይ መኪና ተመድቦለታል፡፡

ታዲያ የሚመራው ሰራተኛ እንደ ጅብ ሌሊቱን ሙሉ ሲሄድ አድሮ በሰዓቱ እንዲገባለት ቢሳደብ ከምን ላይ ነው ነውሩ?የሚቀብጥበት መኪና፣ የሚኖርበት ቤትና እንደ ፈለገ የሚንፈላሰስበት ገንዘብ የዚያ የሚላምጠው የብዙኃኑ ሠራተኛና የህዝብ ሃብት መሆኑን የሚገነዘብ አይመስለኝም፡፡ ቀን በአለቃ ግልምጫ፣ በታክሲ ወረፋ ጥበቃና በስራ ሲናውዝ ውሎ ወደ ቤቱ ሲገባ የሚጠብቀውም ውሃና መብራት አልቦ ጐጆ ነው፡፡ እናም ተነስቶ ውሃ ፍለጋ መኳተን ይጠበቅበታል፡፡ ሻማ ፍለጋም ሌላው ጣጣ ነው፡፡ ያለው አማራጭ ከተማ ውስጥ ቁጭ ብሎ በኩራዝና ከሰል እየተጨናበሰ ኑሮውን መግፋት ነው። ለነገሩ ኩራዝና ከሰሉም ከተገኘ ነው፡፡ አንዳንድ ሰፈርማ ልጆች ቁርስ የሚበሉት በተራ ነው ይባላል። ችግሩ የዚህን ያህል ጥልቅ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት አርጐ ነው ኢህአዴግ “በፈጣን ምላሽ” ይህን ችግር የሚፈታው? ሥራ አጥነት እየተባባሰ ነው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው የሰው ሃይል ቁጥር እጅግ አሳሳቢ ነው። ብዙ መሥራት የሚችል በርካታ ወጣት ኃይል ከተማዋን እያጥለቀለቃት ነው፡፡ መብራት የለም፤ ከ12 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ ስጋት እየሆነ መጥቷል፡፡ ባለስልጣናት አጃቢ ስላላቸው ላይፈሩ ይችላሉ፡፡ ህዝቡ ግን ስጋት ውስጥ ነው፡፡ ለዚህም “ፈጣን ምላሽ” ያስፈልጋል፡፡

ስደት ከምን ጊዜውም በላይ ተበራክቷል፤ የተማረው ብቻ ሳይሆን ምንም የማያውቁ የገጠር ሴቶች ለስደት ከተማዋን፣ በተለይ ደግሞ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን፣ ኢምግሬሽን ጽ/ቤትንና ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያን አጨናንቀውት ይውላሉ፤ ያድራሉ፡፡ ግን መቼ ነው ለዚህ ዓይነቱ ችግር “ፈጣን ምላሽ” የሚገኘው? መብራት ወደ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ እየተላከ (እየተሸጠ) ነው ይባላል፡፡ ዜጐች ግን በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፤ ባንኮችና በመረጃ መረብ ሥራቸውን ያስተሳሰሩ ተቋማት የዕለት ተግባራቸውን በአግባቡ መከወን አቅቷቸዋል፡፡ “ፈጣን ምላሽ” መቼ እንደሚሰጥ ኢህአዴግና አምላክ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ጉቦ ህጋዊ እውቀና ያገኘ መስሏል፡፡ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ ሆነ ቢሮ ሲሄድ የጉቦው መጠን ተወስኖ ይነገራል፡፡ ድሮ ጉቦ ወንጀል ነበር፤ አሳፋሪ ድርጊትም ነበር፡፡ አሁን የአዋቂነትና የጀግንነት መገለጫ እየሆነ ነው፡፡ ኢህአዴግም የአታላዮች መደበቂያ ጐሬ እየሆነ ይመስላል፡፡ ውስጡን ማጥራት አለበት፡፡ ከአምስት ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት ይናገራል፡፡ ግን ምን ያህሉ ነው ለትግል የገባው? ምን ያህሉስ ነው በድርጅት ጥላ ስር ለመዝረፍ የተጠጋው? መጠየቅ አለበት፡፡ ምርጫ ሲካሄድ “ለምን እኔ አልተጠቆምሁም” ብሎ የሚያኮርፍ አባል እየበዛ እንደ ሆነ ይነገራል፡ ግን ለምን? ለትግል የገባ ከሆነ ከእሱ የተሻለ የትግል ጓድ ቢመረጥ ምን አለበት? ይህ የሚያመለክተው የድርጅቱ ጉዞ አቅጣጫውን እየሳተ መሆኑን ይመስለኛል፡፡

ለዚህም “ፈጣን ምላሽ” ያሻል፡፡ ዜጐች በገዛ አገራቸው ላይ እንደ ልባቸው ተዘዋውረው የመሥራት መብታቸው እየተገደበ ነው፡፡ እየተገደበ ብቻ ሳይሆን በህገ ወጥ መንገድ ንብረታቸውን እየተዘረፉ በአገራቸው ላይ ስደተኛና ተመጽዋች እየሆኑ ናቸው፡፡ ይህን ወንጀል የሚፈጽሙትም የኢህአዴግ ካድሬዎች ናቸው፡፡ ከደቡብ ኢትዮጵያ የተባረሩትንና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተባረሩትን የአማራ ተወላጆች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የየክልል ባለስልጣናት ለምን እንዳባረሯቸው ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ “በህገ ወጥ መንገድ ገብተው ደን ሲጨፈጭፉ አገኘናቸው” የሚል ነው፡፡ ህገ ወጥነትን በህገ ወጥነት መቋቋም ግን የአንድ ህጋዊ ተቋም ድርጊት ሊሆን አይገባም፡፡ እንደተባለው አጥፍተው ከሆነ መጀመሪያ ማስተማር፤ ከዚያም መብቱ ወደሚፈቅድለት የህግ አካል አቅርቦ ማስቀጣት እንጂ እንዴት በጅምላ ከአገሩ ላይ ውጣ ይባላል? ኢትዮጵያ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ሃብት ናት። ይህ በአግባቡ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ (በሰብአዊ መብት ላይ የሚፈፀመው ጥሰትና በህገ መንግስቱ ተግባራዊነት ላይም “ፈጣን ምላሽ” ያሻል፡፡ ለነገሩ ኢህአዴግ ቅንና ትጉህ መስሎ የሚታየው ምርጫ ሲቃረብ እንጂ ሌላ ጊዜማ ያው ኢህአዴግ ነው፡፡ እናም በምርጫ ዋዜማ ላይ ብቻ አንገቱን የሚቀብርበትን ህዝብ መቼም ቢሆን ሊያስበው፣ ሊያከብረውና በፍቅር ሊመራው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ አለዚያ ውጤቱ የሚያምር አይሆንም፡፡

Read 1756 times