Monday, 15 April 2013 07:49

ተቃዋሚዎች የአቶ መለስ ፋውንዴሽን በአዋጅ ሊቋቋም አይገባውም አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የመንግስት ጣልቃ ገብነትንም ኮንነዋል

 የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ “ፋውንዴሽን”፤ እንደማንኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መቋቋም ሲገባው በመንግስት ጣልቃ ገብነት በአዋጅ ፀንቶ መቋቋሙ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለፁ፡፡ የኦሮም ህዝቦች ኮንግረስ ሊቀመንበርና የመድረክ አመራር አባል ዶ/ር መራራ ጉዲና በሰጡት አስተያየት፤ “ሲጀመር ፋውንዴሽኑን ለምን በአዋጅ ማቋቋም አስፈለገ” የሚለው ጥያቄ እንደተፈጠረባቸው ገልፀው፤ ፋውንዴሽኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለማቋቋም በወጣው ደንብ መሠረት መቋቋም እንደነበረበትና በአዋጅ መቋቋሙ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት (አረና) ሊቀመንበርና የመድረክ አመራር አባል አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፤ በአዋጅ መቋቋሙ ከህግ አንፃር ምን አንድምታ እንዳለው ባይገነዘቡም ከፖለቲካ አንፃር ትክክል እንደማይመስላቸው ይናገራሉ፡፡ “ኢህአዴግ ስልጣን በመያዙ ሁሉንም አዋጅ በማውጣትና በማስፈፀም ላይ ይገኛል፤ ይህም ከዚያ ባህሪው የመጣ ነው” የሚሉት አቶ ገብሩ፤ ፋውንዴሽኑ የተቋቋመው በቤተሠቦቻቸው፣ በደጋፊዎቻቸውና በባለውለታዎቻቸው ቢሆን ተቀባይነት ይኖረው ነበር ብለዋል፡፡

መንግስት እጁን ያስገባው መለስ የሃገር ባለውለታ መሆናቸው ታስቦ ከሆነም በትግሉ ለተሰውት ሃውልት ነው የቆመላቸው ያሉት አቶ ገብሩ፤ “ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል ከ54 ሺህ በላይ ታጋዮች ተሠውተዋል፤ በቀይ ሽብርም በርካቶች ተሠውተዋል፤ እነዚህስ የሃገር ባለውለታነታቸው እንዴት ነው የሚመዘነው” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ እስከዛሬ “የመለስ ሌጋሲ” የሚባለው ብዙ ጥያቄ የሚነሣበት መሆኑን የገለፁት አቶ ገብሩ፤ “በተለይ በመልካም አስተዳደር በሙስና፣ በዲሞክራሲና በህግ የበላይነት ላይ የመለስ ሌጋሲ የተጫወተው ሚና ምንድን ነው የሚለው እንደ ትልቅ ጥያቄ የሚነሣ ነው” ብለዋል፡፡

የአቶ መለስ ልጅ ሰመሃል መለስ መንግስት በፋውንዴሽኑ ላይ ያለውን ሚና መቃወሟን አስመልክቶ አስተያየት የተጠየቁት አቶ ገብሩ፤ እሷ የተቃወመችው ከምን አንፃር እንደሆነ ግልፅ ባይሆንላቸውም፣ ተቃውሞው ተገቢ መሆኑን ጠቁመው ፋውንዴሽኑ የፖለቲካ ውሣኔ ያለበት መሆኑ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ “አሁን እየተደረገ ያለውን ስንመለከት አቶ መለስ የህዝብ ሳይሆኑ የመንግስት ናቸው” ያሉት አቶ ገብሩ፤ “የህዝብ ናቸው ለመባል የግዴታ ፋውንዴሽኑ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ወጥቶ በህብረተሠቡ የተለያዩ አካላት መቋቋም ነበረበት” ብለዋል፡፡ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር እንዲሁም የመድረክ አመራር አባል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ፋውንዴሽኑ ተቀባይነት የሚኖረው በመንግስት አዋጅ ሣይሆን በህዝቡ ቢቋቋም እንደነበር አመልክተዋል፡፡ እንዲህ አይነት ፋውንዴሽን ለመሪዎች መቋቋሙን የደገፉት ዶ/ር ነጋሶ፤ ነገር ግን ከመንግስት ገለልተኛ ሆኖ በቤተሠብ፣ በአድናቂ እና በተለያዩ የህብረተሠብ ክፍሎች መቋቋም እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡ የፋውንዴሽኑ መስራች ጉባኤ ቅዳሚ መጋቢት 28 ቀን 2005 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዲሱ አዳራሽ ሲካሄድ የአቶ መለስ የመጀመሪያ ልጅ ሰመሃል መለስ “በአዋጁ ላይ የመንግስት ሚና መጉላቱ ስህተት ነው፡፡ ፋውንዴሽኑ የአስተሣሠብ ምንጭ ይሆናል ብለን ነው ያሠብነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ፋውንዴሽኑ ላይ ያለው ሚና ትክክል አይደለም ባይ ነኝ” ብላለች፡፡ የመለስ ፋውንዴሽን በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 2455 times