Monday, 15 April 2013 07:47

ተፈናቃዮች የጉዳት ካሣ ይከፈላቸዋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(10 votes)

በቅርቡ ከቤኒሻንጉል ክልል ያሶ ወረዳ ተፈናቅለው ፍኖተሠላም ከተማ መጠለያ ውስጥ የቆዩትና ወደነበሩበት እንዲመለሱ የተደረጉት የአማራ ክልል ተወላጆች፣ የገንዘብና የሞራል ካሣ ሊከፈላቸው ይገባል ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ናስር በበኩላቸው፤ ክልሉ በአሁን ሰዓት ተፈናቃዮቹን በማረጋጋት ላይ እንዳለና የጠፋ ንብረት፣ የአካል ጉዳትና መሰል ችግሮች ካሉ ከመንግስት ጋር በመመካከር ካሣውን እንደሚከፍል ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ዓለምአቀፍ የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማሪያም፤ በዜጐቹ ላይ የተደረገው ህገወጥ የማፈናቀል ድርጊት ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን ጠቁመው፤ ለጠፋው ንብረት፣ ለደረሰባቸው መጉላላትና ለጤናቸው መታወክ ተመጣጣኝ ካሣ ሊከፈላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

“ጉዳዩ የክልል መንግስት ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ ካለ ተሣስቷል፡፡ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደመሆኑ የፌደራል መንግስትንም በቀጥታ ይመለከተዋል” ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤ የካሳ አከፋፈሉም ላይ ቢሆን የክልልም ሆነ የፌደራል መንግስት በጋራ ማከናወን እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ “የካሣ ክፍያው ለጠፋባቸው ንብረት ብቻም ሳይሆን ለሞራላቸውም ሊሆን ይገባል” ይላሉ ዶ/ሩ፡፡ “አንድ ሰው ከሞቀ ቤቱ ሲነቀልና ሲባረር ምን ያህል ኑሮው እንደሚስተጓጐልና ሞራሉ እንደሚነካ ሁሉም ያውቀዋል” ያሉት የህግ ባለሙያው፣ ለደረሰው ጥፋት ካሣው አስፈላጊ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ሁሉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ ወንጀሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን የተናገሩት የህግ ባለሙያው፤ በአለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት፣ በአፍሪካ የሰብአዊና የህዝቦች መብት እና በተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩ ቢታይ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት ካሣ የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

“በአለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት አንድ ሰው ለደረሰበት ሰብአዊ ጉዳት በዳዩን መቅጣት ብቻ ሳይሆን ተበዳዩም ካሣ እንዲከፈለው ያዛል፤ የቤኒሻንጉል ተፈናቃዮች ለደረሰባቸው እያንዳንዱ ጉዳት ካሣ የማግኘት መብት አላቸው” ብለዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ደህንነት እንዲሰማቸው ምን መደረግ እንዳለበት ባለሙያው ሲያስረዱም “አንድ መንግስት ተቀዳሚ ስራው የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ነው ሰዎቹን ቀደም ብለው ያፈናቀሏቸው አመራሮች መልሰው ሊያጉላሏቸው ስለሚችሉ፣ በፌደራልም ሆነ በክልል መንግስታት ደህንነታቸውም ሆነ ጤንነታቸው መረጋገጥ አለበት” ብለዋል፡፡ ለዚህም ከፌደራልም ሆነ ከክልሉ የተውጣጡ ፖሊሶች፤ የተፈናቃዮቹን ደህንነትና ሠላም በመከታተል ወደ ቀድሞ ኑሯቸውና መንፈሳቸው እስኪመለሱ ድረስ ጥበቃ ሊያደርጉላቸው ይገባል ብለዋል - ዶ/ር ያዕቆብ፡፡ በየጊዜው በየክልሉ ተመሳሳይ መፈናቀሎች መኖራቸውንና ለዚህ ዘላቂ መፍትሔ ስለሚሉት ጉዳይ የተጠየቁት ዶ/ር ያዕቆብ፣ “ከዚህ ቀደም ከደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ የተፈናቀሉት ዜጐች አሁን የት እንደደረሱ ብዙ የሚታወቅ ነገር ባለመኖሩ የቤኒሻንጉሎቹን ብቻ ሳይሆን የጉራፈሪዳዎቹንም መንግስት ሰብስቦ ከካሣ ክፍያ ጋር ወደ ቦታቸው መመለስ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

“የተጀመረው የማፈናቀል አዝማሚያ በእንጭጩ ካልተቀጨ ለዜጐች ችግርና ስጋት ሆኖ ይቀጥላል፤ ለአገርም መፍረስ ምክንያት ይሆናል” ያሉት ዶክተሩ፤ “ኢትዮጵያ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አሏት እየተባለ አንዱ ብሔር ሌላውን ‘አካባቢዬን ለቀህ ውጣ’ ካለው ምን አገር አለ?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ይህን አይነት ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙት የቤኒሻንጉል ባለስልጣናት ከፍተኛ ቅጣት መቅጣት ለሌላው ትምህርት እንደሚሆን ጠቁመው ጥፋተኞቹ በቸልታ ሊታለፉ እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ “ወንጀል እንዳይደገም ከሚደረግባቸው መንገዶች አንዱና ዋናው ወንጀለኛን በመቅጣት ሌላውን ማስተማር ነው” ያሉት ዶክተሩ፣ ሌላው መንገድ አጥፊን በመቅጣት ህብረተሰቡን መካስ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ “ወንጀሉን የፈፀሙት የቤኒሻንጉል ባለስልጣናት ብርቱ ቅጣት ቢቀጡ የሌሎች ክልሎችም ሆነ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ሁለተኛ እንዲህ አይነት ወንጀል አይፈጽሙም” ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ዋና አስተዳደር አቶ አህመድ ናስር በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮቹ ወደተፈናቀሉባቸው አራት ቀበሌዎች በመመለስ ላይ መሆናቸውን ገልፀው፣ ሲፈናቀሉ እህልና ንብረታቸውን ጥለው የሄዱት ሰዎች በአገሬው ሰው ጥበቃ የቆያቸው በመሆኑ እየተመለሰላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ንብረታቸው የጠፋባቸውና ችግር ላይ ያሉ ካሉ የተመደበው አመራር በጉዳዩ ላይ መክሮና አጣርቶ መደረግ ያለበትን ሁሉ እንደሚያደርግ አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡ “አሁን በዋናነት ትኩረት የሰጠነው በማረጋጋቱ ሥራ ላይ ነው” ያሉት አቶ አህመድ፤ የሞራል ካሣን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ተፈናቃዮቹን አሰባስበው እንዳናገሯቸውና ምንም አይነት የሞራል ችግር እንዳልደረሰባቸው እንደገለፁላቸው ተናግረዋል፡፡ “ሰብስበን ባወያየናቸው ወቅት ለወደፊቱም ምንም ችግር እንደማይገጥማቸው አረጋግጠንላቸዋል” ብለዋል አቶ አህመድ፡፡

ተፈናቃዮቹ ለዓመታት ከአገሬው ጋር የኖሩ በመሆናቸው “ሊመለሱ ይችላሉ” በሚል ንብረታቸውንና ቤታቸውን ጠብቀው እንዳቆዩአቸው መመልከታቸውን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ ይህን አልፎ የአካል ጉዳት፣ የንብረት መጥፋትና መባከን የደረሰባቸው ካሉ ጉዳዩ ተጣርቶና ከመንግስት ጋር በመካከር አስፈላጊውን ካሣ እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡ በክልላቸው እንዲህ አይነት ስህተቶች እንዳይደገሙ ምን እርምጃዎች እንደሚወስዱ የተጠየቁት አቶ አህመድ፣ መጀመሪያውኑም ማንኛውም ዜጋ የትኛውም ቦታ ሄዶ ሰርቶ የመኖር መብት እንዳለው እንደሚታወቅ ገልፀው “እኛ የምንለው ከእለት ወደ እለት እየበዛ የመጣው ፍልሰት፣ አካባቢን የመመንጠርና ህገወጥ ሠፈራ ይቁም ነው” ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡ የአማራ ክልል ተወላጆች ከ20 እና ከ30 ዓመት በፊት ጀምሮ በክልሉ ከተወላጁ ጋር አብረው መኖራቸውን የገለፁት ሃላፊው፣ “የአማራ ክልል ተወላጆች ወደ ክልላችን መምጣታቸው ጠቀመን እንጂ አልጐዳንም፡፡ በክልላችን ያለው የስራ ባህል ደካማ በመሆኑ የህዝቡን ህይወት መቀየራቸውን አንክድም” ብለዋል፡፡ እንደሃላፊው ገለፃ፤ ከጊዜ ወደጊዜ እየበዛ የመጣው ጫካን የመመንጠርና አካባቢውን ለበረሃማነት የማጋለጥና የማራቆት ተግባር ግን አሁንም መቆም አለበት፡፡

በአሁኑ ሰዓት አዲስ የመሬት ፖሊሲ ፀድቆ ስራ ላይ እየዋለ እንደሆነ የገለፁት አቶ አህመድ፣ መሬት ተተምኖ ለአገሬው ከተሰጠ በኋላ የሚተርፈውን ረጅም አመት በክልሉ ለኖሩት የአማራ ተወላጆች አንድም ሄክታር ይድረሳቸው ግማሽ እንደሚያከፋፍሏቸው ተናግረዋል፡፡ “አሁንም ቢሆን አብረውን የኖሩትን የአማራ ክልል ተወላጆች ጥላቻ የለብንም” ያሉት ሃላፊው፣ ለተፈናቃዮቹ ችግር መንስኤ የሆኑትንም ሃላፊዎች ገምግመው እርምጃ እንደሚወስዱ አረጋግጠዋል፡፡ ሃላፊው አክለውም በህገ ወጥ መንገድ ጫካ መመንጠርና ህገ ወጥ ሠፈራ ማድረግ እንደሌለባቸው፣ ለጉልበት ስራ ዝውውር ግን መብት እንዳላቸው ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የሠብአዊ መብት ጉባኤ (ሠመጉ) የአድቮኬሲና የህግ ድጋፍ አገልግሎት ባለሙያ አቶ ቴዎድሮስ ያለው ሲናገሩ፤ በአፍሪካ ከ2012 ዲሴምበር ጀምሮ ስምምነቱን በፈረሙ የአፍሪካ አገሮች ስራ የጀመረው “ካምፓላ ኮንቬንሽን” አንቀፅ 12 ላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀደመ ቦታቸው ተመልሠው የመስራት፣ በተፈናቀሉ ጊዜ የደረሠ ጉዳት ካለ የሞራልም የማቴሪያልም ካሣ የማግኘት መብት እንዳላቸው ህጉ መደንገጉን አብራርተዋል፡፡

“ምን ያህል ይከፈል የሚለው ነገር ግን የደረሠው ጉዳት መጠን ተጠንቶ የሚከናወን ነው” ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ማን ይክፈል የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ስምምነቱን የፈረመችው ኢትዮጵያ እንደመሆኗ በመጀመሪያ ሀላፊነቱን ፌደራል መንግስት ወስዶ አከፋፈሉ በኋላ የሚወሠን ይሆናል ብለዋል ባለሙያው፡፡ “በተደጋጋሚ በተለያዩ ጉዳዮች መፈናቅሎች እየደረሱ በመሆናቸው፣ ተፈናቃዮች እንዴት መስተናገድ አለባቸው የሚለውን እና የከለላን ጉዳይ የሚወስን የተፈናቃይ ፖሊሲ ኢትዮጵያ መቅረፅ አለባት” ያሉት ባለሙያው፤ በአሁኑ ሠዓት ግን እንዲህ አይነት መፈናቀል ሲከሠት ማን ምን ሀላፊነት እንዳለበት ለመለየት አስቸጋሪ በመሆኑ በመሀል ህዝብ እየተጐዳ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ዘርን፣ ቀለምን እና ፆታን ማዕከል ያደረጉ ማፈናቀሎች የሠብአዊ መብት ጥሠቶች በመሆናቸው ጉዳዩ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች መሠረት አድርጐ የተፈፀመ ከሆነ፤ ይህን የሠብአዊ መብት ጥሠት የፈፀሙት ግለሠቦች በአስቸኳይ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ብለዋል - አቶ ቴዎድሮስ፡፡ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) የህዝብ ግንኙነት ሀላፊና የኤዲቶሪያል ቦርድ አባል አቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ናስር “ችግሩ የተፈጠረው በወረዳው ሀላፊዎች ነው” ማለታቸው በጣም እንዳሣዘናቸው ገልፀው “ይሄ ሁሉ ግፍ ሲሠራ … ዜጐች በአይሱዙ እየተጫኑ ሲጋዙ ህፃናትና እናቶች እንግልት ሲደርስባቸው፣ ሀብት ንብረታቸው ሲባክንና ሲወድም አያውቁትም ነበር ማለት የዋህነት ነው” ብለዋል፡፡

አቶ ዳንኤል አክለውም ዜጐቹ ወደነበሩበት መመለሣቸው ግዴታ መሆኑን፣ ከቦታቸው ተፈናቅለው፣ ይሄ አገራችሁ አይደለም ተብለው የአዕምሮና የንብረት ጉዳት የደረሠባቸው በመሆኑ ተፈናቃዮቹ ከካሣ በተጨማሪ በአደባባይ ተሠብስበው በይፋ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ “ላለፉት 21 ዓመታት መፈናቀልና ስደት በከተማም በገጠርም ሲካሄድ ቆይቷል” ያሉት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው፣ ይህ ሁሉ ችግር የሚከሠተው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የሚከተለው ርዕዮተ አለም (አብዮታዊ ዴሞክራሲ) የብሄር የበላይነት እንዲጐላና ኢትዮጵያዊነት እንዲደበዝዝ የሚያደርግ መሠረታዊ የአስተሣሠብ ስህተት ያለው በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ “መንግስት የወረዳው ሠዎች ስህተት ሲሠሩ አያውቅም እንኳን ብለን ብናስብ አሁን ጉዳዩን ከሠማ በኋላ ጥፋተኞቹን በአስቸኳይ ለፍርድ ማቅረብ ይጠበቅበታል” ብለዋል አቶ ዳንኤል፡፡ መንግስት ለተፈናቃዮቹ የረጅምና የአጭር ጊዜ መፍትሄ እቅድ መተግበር እንዳለበት የገለፁት አቶ ዳንኤል፣ የአጭር ጊዜ እቅዱ ተፈናቃዮቹን ከነሀብትና ንብረታቸው ከካሣ ጋር ወደ ቦታቸው መመለስ ሲሆን፣ የረጅም ጊዜ መፍትሄው ግን በኢትዮጵያዊነት ላይ አለመደራደር መሆኑን አስምረውበታል፡፡ “የትኛውም ኢትዮጵያዊ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የመስራት መብቱ የተጠበቀ በመሆኑ ይህን መብቱን በመጠቀም ኢትዮጵያዊነቱን ለማንም በምንም አሣልፎ መስጠት የለበትም” ብለዋል፡፡

Read 3878 times