Monday, 15 April 2013 07:39

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ራሱን ከምርጫ አገለለ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(7 votes)

‹ከ200 በላይ እጩዎቻችንና ታዛቢዎቻችን ታስረው በምርጫ መሳተፍ ይከብደናል - ዶ/ር አየለ አሊቶ

‹‹ቀልዱን ብቻቸውን ይቀልዱ፤ ምርጫ የለም ንጥቂያ ነው›› - ኢንጂነር ሃይሉ ሻወል

‹‹የሲዳማ ዞን ህዝብ ወደ ምርጫው እንድንገባ ገፋፍቶኛል›› በሚል በምርጫው ላለመሳተፍ ከወሰኑት 33ት ፓርቲዎች በመነጠል የምርጫ ምልክት ወስዶ የነበረው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ ራሱን ከምርጫው ማግለሉን ይፋ አደረገ፡፡ ፓርቲው ከ200 በላይ እጩዎቼና ታዛቢዎቼ ታስረውብኛል በሚል ነው ነገ ከሚጀመረው የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫ ራሱን ያገለለው፡፡ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን በመቃወም ፒቲሽን ከፈረሙ 33 ፓርቲዎች መካከል አንዱ የነበረውና በኋላም ‹‹የሲዳማ ዞን ህዝብ ወደ ምርጫው እንድንገባ ገፋፍቶናል›› በሚል አውራ ዶሮ የምርጫ ምልክት ይዞ ወደ ምርጫ መግባቱን ያስታወቀው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር አየለ አሊቶ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት “የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ የክልል ጥያቄ ነው፣ ህዝቡ በምርጫው ተሳትፎ በካርዱ መብቱን ሊያስከብር ስለሚፈልግ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ወደ ምርጫው እንዲገባ በመወሰኑ፣ ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በላይ እጩዎችን ለከተማ፣ ለዞንና፣ ለወረዳ አቅርቦ ነበር፡፡

ሆኖም ከ200 በላይ ዕጩዎቻችንና ታዛቢዎቻችን ለእስር በተዳረጉበትና ቅስቀሳ ባላደረግንበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት ፋይዳ የለውም፡፡ በእስርና በክልከላ ህዝቡ እየተረረ ነው፡፡ “በደም ያገኘነውን፤ “በደም ብቻ ነው የምንለቀው” ብለው እየቀሰቀሱብን ስለሆነ ራሳችንን ከምርጫ ማግለላችን ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሳይሻሻሉና በምርጫው እንደማይሳተፉ ቀደም ብለው ያስታወቁት 33 ፓርቲዎች ባለፈው እሁድ በሰማያዊ ፓርቲ፣ በመድረክ፣ በመኢአድና በአንድነት ጽ/ቤት አዳራሽ ህዝባዊ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፣ የመኢአድ ሊቀመንበር ኢንጂነር ሃይሉ ሻወል፣ በእለቱ ከደጋፊዎቻቸው ጋር በወቅታዊ ጉዳዮችና ነገ በሚጀመረው የአካባቢና የአዲስ አበባ መስተዳድር ምርጫ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

“ለእኛ ምርጫው ቀልድ ነው፤ መሰረታዊ ጉዳዮች ሳይሻሻሉና በርካታ ውጥረቶች እያሉ በምርጫው ለመሳተፍ ይቅርና ስሙን ለመጥራትም አንፈልግም፡፡ ቀልዱን እነሱ ብቻቸውን ይቀልዱ፤ ምርጫ የለም ንጥቂያ ነው” በሚል ምሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ “ህዝቡ እናንተ ተነቃነቁልን ቢለንም እኛ ደካሞች ነን፤ ወጣቶችን አንቀሳቅሰን መነቃነቅ ነው ያለብን” ያሉት ኢንጂነር ሃይሉ፣ “ኢህአዴግ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ አጣሁ ይላል” ለሚለው ጥያቄ “ራሱ ወሳኝ፣ ራሱ ህዝብን አሰልፎ እንዲወጣ አድራጊ፣ ራሱ አስተዳዳሪ በሆነበት ሁኔታ የሚያወራውን አንሰማውም” ብለዋል፡፡

Read 2861 times