Saturday, 13 April 2013 14:19

“ከ32 % በላይ እናቶች ለሞት ይዳርግ የነበረ ምክንያት...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

በአለም አቀፍ ደረጃ እድሜያቸው ከ15-24 አመት የሚሆኑት ወጣቶች ቁጥራቸው 1.2 ቢሊዮን ያህል ነው፡፡ በዚህ እድሜ የሚገኙት ታዳጊ ወጣቶች ሁል ጊዜ አዳዲስ ነገሮችን ለመፈተሸ እንዲሁም ለመሞከር የሚደፍሩ ሲሆኑ በዚህም ምክንያት ለተለያዩ የጤና ችግሮች ሊጋለጡ የሚችሉ ናቸው፡፡ የጤና ችግር ተብለው ከሚገለጹት መካከልም ካልተፈለገ እርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰት የስነተዋልዶ ጤና መጉዋደል ይገኝበታል፡፡ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በአመት ወደ 11 % የሚሆኑት ወሊዶች እድሜያቸው ከ15-19 በሚደርስ ወጣት ሴቶች ሲሆን ከዚህም 95% የሚሆነው በታዳጊ አገሮች የሚከሰት ነው፡፡

ወደ 2.5 ሚሊዮን ወይንም 14% ያህል ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥ የሚካሄደው በታዳጊ አገሮች እድሜያቸው ከ20 አመት በታች በሆኑ ሴት ልጆች ነው፡፡ Yohannes A. (Mekelle University, College of Health Sciences, Department of public health) ከላይ ለመግቢያ ያህል ያስነበብናችሁ ነጥብ ጽንስን በማቋረጥ ዙሪያ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ጠቋሚ ሀሳብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጽንስን በማቋረጥ ዙሪያ ህግ ወጥቶአል፡፡ ሆኖም ግን ምን ያህል ሴቶች በህጉ ይጠቀማሉ አይጠቀሙም የሚለው አነጋጋሪ ቢሆንም የህክምና ተቋማት ግን ህጉን መሰረት በማድረግ ብዙዎችን በመርዳት ላይ ናቸው ፡፡

ጽንስን ማቋረጥ በህጋዊ መንገድ በሚፈጸምበት ጊዜ ወደህክምና ተቋም መሄድ አስፈላጊ ሲሆን ለዚህም ተገቢውን እርዳታ ለማድረግ እንዲያስችል በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጎአል ፡፡ ስልጠናውን የሰጠው ማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የተሰኘው ድርጅት ሲሆን አሰልጣኞቹም ከፍተኛ ሐኪሞች ናቸው፡፡ ይህንን በሚመለከት ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ በማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮያ የክሊኒካል አገልግሎትና የጥራት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ውስጥ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1990 ዓ/ም ጀምሮ በስነተዋልዶ ጤና ላይ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ነው፡፡

የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግም ራቅ ባሉ አካባቢዎች በተለይም በገጠሩ ክፍል በራሱ ተቋማት አማካኝነት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ኢሶግ፡ ማሪስቶፕስ ኢትዮጵያ ጽንስን ከማቋረጥ ጋር በተያያዘ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠትን እንዴት አቀደው? ዶ/ር ብርሀኑ፡ በጽንስ ማቋረጥ ዙሪያ የአሰልጣኞች ስልጠና ለመስጠት የታቀደው በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስር አማካኝነት ሲሆን መስሪያ ቤቱ በመሪነት በአመታዊ እቅዱ በማካተት ስራውን ማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እንዲሰራው አድርጎአል፡፡ በእርግጥ ጽንስን በማቋረጥ ሂደት ላይ የሚሰጠውን አገልግሎት ከፍተኛ ሐኪሞች ካለችግር ሊያከናውኑት ይችላሉ የሚል እምነት ቢኖርም እነዚህ ከፍተኛ ሐኪሞች በማይገኙባቸው ተቋማት ሁሉ አገልግሎቱ በሚፈለግበት ጊዜ ሊሰጥ ስለሚገባው በተለያዩ መስተዳድሮች በየደረጃው ያሉ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ ተደርጎአል፡፡

የህክምና እውቀት አንድ ቦታ የማይቆም እና በተለያዩ አዳዲስ መሳሪያዎችና ጥናት ውጤቶችም የሚታገዝ ስለሆነ ሙያተኞች በየጊዜው እራሳቸውን በስልጠና እንዲያድሱ ይመከራል፡፡ የስልጠናውን ሂደትም በሚመለከት ውስን በሆነ የሰው ኃይል ብዙውን ቦታ ማዳረስ ስለማይቻል ከየክልል መስተዳድሩ አማራ ፣ትግራይ ፣ኦሮሚያ ፣ደቡብ ፣አዲስአባባ የተመረጡ ከአንድ እስከ አምስት የሚደርሱ አሰልጣኖች ስልጠናውን እንዲከታተሉ የተደረገ ሲሆን ወደየመጡበት አካባቢ ሲመለሱም እንደአስፈላጊነቱ ለሌሎች ባለሙያዎች እውቀቱን ያካፍላሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ስልጠናውን በመጠቀም ረገድ ለመንግስት ተቋማት ብቻም ሳይሆን ለማንኛውም የህክምና ተቋም ስለሚያገለግል ጥያቄው ባለበት ቦታና ወቅት ሁሉ የሰለጠኑት ባለሙያዎች ምላሽ ለመስጠት ይችላሉ፡፡

ኢሶግ፡ የህክምና ባለሙያዎቹ ስልጠናውን ሲወስዱ ቀደም ካለው እውቀታቸው ምን የተለየ ነገር ያገኛሉ? ዶ/ር ብርሀኑ፡ የህክምና ትምህርት አንድ ጊዜ በተሰጠ ስልጠና የሚቆም አይደለም፡፡ ሁልጊዜ ማንበብን ይጠይቃል፡፡ የተለያዩ ስራዎችን መስራት ካልተቻለም የነበረው እውቀት ይደበዝዛል፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና ሲባል ሰልጣኞቹም ወደሌሎች ሰልጣኞች በመሄድ እንዴት እንደሚያሰለጥኑ ዘዴው የተካተተበት ነው፡፡ የችግሩ መጠንና የእናቶች ሞት በኢትዮጵያ እና በአለምአቀፍ ሁኔታ መግለጽ ፣ ጽንስ ማቋረጥ የሚባለው በኢትዮጵያ ህግ ምን ይመስላል? ጽንስ ማቋረጥ ከሴቶች መብት አንጻር እንዴት ይታያል? ጽንስ ማቋረጥ በህግ የተፈቀደባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ መቋረጥ አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል የመጡ ሴቶች በምን መልክ አገልግሎቱን እያገኙ ነው? ጽንሱ በራሱ ጊዜ መቋረጥ ቢደርስበት እናትየው ላይ ጉዳት እንዳያስከትል በምን መንገድ ማከም ይቻላል? አሁን ሳይንስ በደረሰበት ደረጃ በምን መንገድ ጽንስን የማቋረጥ አገልግሎት እንደሚሰጥና ደንበኛዋ በአገልግሎቱ እንድትረካ ማድረግ እንዴት ይቻላል? የምክር አገልግሎትን በሚመለከት ለደንበኞች እንዴት ሊሰጣቸው ይችላል? ምን ምን አማራጮች አሉ? ከጽንስ መቋረጥ በሁዋላ ሴትየዋ በድጋሚ ማርገዝ ትፈልጋለች ...አትፈልግም የሚለው ተጣርቶ ማርገዝ የማትፈልግ ከሆነ ያልተፈለገ እርግዝናን አስቀድሞውኑ እንድትከላከል የሚያስችላትን አገልግሎት እንድታገኝ ማድረግ ፣ ሕክምናው በሚሰጥበት ጊዜ ምን ያህል እናቶች ችግር ደርሶባቸዋል ?ወይንም ችግር እንዳይደርስባቸው የሚያስችል የህክምና እርዳታ አግኝተዋል...ወዘተ የሚሉ ይገኙበታል፡፡

እውቀት ያላቸውን ሰዎች ለማሰልጠን በምን ዘዴ መጠቀም እንዳለባቸው፣ ስልጠናው ከተሰጠ በሁዋላ የአገልግሎቱን ደረጃ ለመለካት እንዲያስችል በሂደቱ ላይ ግምገማ ማድረግ እና ሪፖርትን በሚገባ በመጻፍ እስከኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ድረስ ማድረስ ከስልጠናው ሂደት መካከል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህግ እንዳስቀመጠው ጽንስን ማቋረጥ የሚፈቀድባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፡- መደፈር ካጋጠመ፣ ከቤተዘመድ ከተረገዘ፣ ጽንሱ እናትየው ላይ ወይንም በራራሱ ሕይወት ላይ አደጋ የሚያስከትል ከሆነ፣ እርግዝናው ያጋጠማት ሴት በኢኮኖሚ ፣እድሜ፣ ከማህበራራዊ አኩዋያ እርግዝናውን ልትደግፍ ካልቻለች ጽንስ ማቋረጥን የኢትዮጵያ ህግ ይፈቅዳል፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች በተደረገ ጥናት አገልግሎቱን ለመስጠት ህጉ ምን እንደሚልና በምን ምክንያት እንደሚፈቅድ እና እንደሚከለክል ለመረዳት የእውቀት ክፍተት እንዳለ ለመመልከት ተችሎአል፡፡

ስለዚህ ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና ህጉን በሚገባ ባለሙያዎች እንዲረዱትና ተግባራዊ እንዲያደርጉትም ያስችላል፡፡ ኢሶግ፡ ከህብረተሰቡ ምን ይጠበቃል? ዶ/ር ብርሀኑ፡ በቅድሚያ በአስገዳጅ ሁኔታ ተደፍረው ከሚያረግዙት በስተቀር ሌሎች ሴቶች ያልተፈለገ እርግዝናን አስቀድሞውኑ መከላከል ይገባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጽንስን በማቋረጥ ረገድ የወጣው ህግ ምን እንደሚል ጠንቅቆ ማወቅና በእርሱም መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ህጉ ከመሻሻሉ በፊት ንጽህናውን ያልጠበቀ ጽንስን ማቋረጥ ከ32 % በላይ ለእናቶች ሞት ምክንያት ነበር፡፡ አሁን ግን ከ 6-14 % የሚሆን የተለያዩ ቁጥሮች የሚገለጽ ሲሆን ዞሮ ዞሮ ግን የተሻሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ስለዚህ ይህንን አገልግሎት በየደረጃው ህብረተሰቡ ዘንድ ማዳረስ የሚቻል ከሆነ ንጽህናውን ባልጠበቀ መንገድ ውርጃ አካሂደው የሚሞቱ ሴቶችን ቁጥር መቀነስ ያስችላል፡፡ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የሚያስችሉ ሶስት ዋና ዋና ነገሮች አሉ፡፡

1/ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በአግባቡ ህብረተሰቡ ጋ ተደራሽነት ቢኖረው እና ህብረተሰቡም አገልግሎቱን ተጠቃሚ ቢሆን ፣ 2/ ልጅ መውለድ ፈልገው ላረገዙ እናቶች ከእርግዝና በፊት በእርግዝና ጊዜና በወሊድ ወቅት አስፈላጊው አገልግሎተ በህክምና ሙያተኞች ከተሰጠ እና በጤና ተቋም ከወለዱ፣ 3/ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ንጽህናውን የጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት በህክምና ተቋማት ማግኘት፣ የሚሉት በጥናት ከተረጋገጡ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከሚያግዙ መንገዶች መካከል ናቸው፡፡

Read 5146 times Last modified on Monday, 15 April 2013 09:13