Thursday, 11 April 2013 09:46

ደብረ ጽሙና፤የዘንዶ ተራራ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት “ዲግኔ፣ ቅምብርሼ ዞጋ” እና “ብሉላ” የሚባሉ የአካባቢው ባላባቶች አምላካቸውን ማስደሰት ፈለጉና ወተትና ስጋ ይገብሩለት ጀመር፡፡ ወተቱ የጊደር፣ ሥጋውም የበኩር (የመጀመሪያ) ልጅ እንዲሆን ወሰኑ፡፡ ተግባራዊም አደረጉት፡፡ የሚመለከው ዘንዶም “ጣጋ” ከሚባል ወንዝ እየመጣ ግብሩን በመቀበል የአካባቢውን ሕዝብ አንቀጥቅጦ ገዛው፡፡ ይህ የተደረገው በደብረ ጽሙና ተራራ ነው፡፡ ደብረ ጽሙና በምስራቅ ጐጃም ዞን እነማይ ወረዳ ውስጥ ለዓባይ ሸለቆ በጣም ቅርብ የሆነ ምስራቃዊ ገዳም ነው፡፡ በ1297 ዓ.ም በአፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት የተመሠረተው ይህ ገዳም፣ ዙሪያውን በአስፈሪ ገደል የተከበበ የየብስ ላይ ደሴት ነው፡፡ ወደ ገዳሙ ለመግባት በሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ ያለውን አንድ ጠባብ በር ብቻ መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ከዚያ ውጭ ሲኳትኑ ውለው ቢያድሩ ደብረጽሙና ገዳም መግባት አይቻልም፡፡ ተራራው አናት ላይ ሲወጣ ለጥ ያለ ሜዳ ይገኛል፡፡

ሜዳው ግን ልሙጥ ሜዳ አይደለም፤ በወይራና በሌሎች ዕጽዋት የተዋበ፣ በሰንበሌጥ ሳር የተጀቦነ በመሆኑ በእርግጥም “የፀጥታ” እና “የሰላም ተራራ” ቢባል የሚዛበት አይሆንም፡፡ በዚህ ተፈጥሮ አቆናጅታ በቀረፀችው ተራራ ላይ ነው ያ አስፈሪ ዘንዶ ህጻናትን ሲሰለቅጥና የጊደር ወተቱን ያለ ከልካይ ሲጋት የኖረው፡፡ ግን የነበረው ሁሉ እንዳለ አይቀጥልምና “አባ ሲኖዳ” የሚባሉ መነኮስ ከወደ ሸዋ ድንገት ብቅ አሉ፡፡ የአካባቢው ህዝብ በፍርሃት የሚሰግድለትና ውድ ልጆቹን (ያውም የመጀመሪያቸውን) ሲገብሩለትም አስተዋሉ፡፡ አባ ደካማ መነኩሴ ናቸው፡፡ ያንን ሁሉ ሕዝብ ሲያስረግድ የኖረ ግድንግድ ዘንዶ እንዴት ሊያስወግዱት ይችላሉ? የብዙዎች ጥርጣሬ ነበር፡፡ ለነገሩ አባም “እገድለዋለሁ” ብለው አልፈከሩም፡፡ ግን ጸሎታቸውን ወደፈጣሪያችን ከማድረስ አልቦዘኑም፡፡

አባ ሶስት የመፀለያ ቦታዎችን አመቻቹ፤ “ደብረጋስና” ከሚባልና ረግረግ ካለበት ቦታ ሌሊቱን ሙሉ ተዘፍቀው ያድሩና ቀን ደግሞ “ብሔረ አንቀጥቅጥ” ከሚባል እጅግ አስፈሪ ገደል ላይ ሲጸልዩ ይውላሉ፡፡ አንዳንድ ቀን ደግሞ አሁንም ድረስ ለእማኝነት በሚመስል መልኩ ቆሞ ከሚገኝና ውስጡ ከተፈለፈለ የወይራ ዛፍ ውስጥ ገብተው ይጸልዩ ነበር፡፡ አንድ ቀን እንደ ልማዳቸው ከዚሁ ወይራ ዛፍ ውስጥ ገብተው መዝሙረ ዳዊት እየደገሙ ሳለ፣ መጽሐፈ ዳዊታቸው ላይ የሚንጠባጠብ ነገር አዩ፡፡ ቀና ሲሉ አንዲት መልኳ እንደ ፀሐይ የሚያበራ ልጅ አስተዋሉ፡፡ ለምን እንደምታለቅስ ቢጠይቋት “ለዘንዶ ግብር የቀረብሁ ነኝ፡፡ ዘንዶው እየመጣ ስለሆነ አባ እባክህ ከካባቢው በፍጥነት ራቅ” አለቻቸው፡፡ አባ ግን ዘንዶውን ከመፍራት ይልቅ ልጅቷን ያረጋጓት ጀመር፡፡

ብዙም ሳይቆይ ያ ግዙፍ ዘንዶ የሰንበሌጡን ሳር እያጥመሰመሰ የተዘጋጀችለትን ልጅ ሊውጥ ከተፍ አለ፡፡ ዘንዶው ግብር በሚቀበልበት እለት ሁልጊዜ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲመጣ የተዘጋጀለትን ህጻን ይውጥና በሰፊ የድንጋይ ገበታ ላይ የተከማቸለትን የጊደር ወተት ግጥም አርጐ ያወራርዳል፡፡ በዚያንለት ሊሆን የነበረውም ይኸው ነው፡፡ የተዘጋጀችለትን የምታምር ልጅ ለመዋጥ አፉን ሲያዛጋ አባ ሲኖዳ በስመ አብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በመስቀል አማተቡበባት፡፡ ወዲያው ያ አደገኛ መርዙ አልጫ ሆነ፣ ተዝለፍልፎም በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘውና ለዓባይ ገባሮች አንዱ ከሆነው ጣጋ ወንዝ ላይ ወደቀ፡፡ ገድሉና የገዳሙ አባቶች እንደሚናገሩት፣ የዘንዶው ወርድ አራት ክንድ ሲሆን የቁመቱን ልክ ግን “እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያውቀው“ ልጅቱ ተሰቅላበት ነበር” የሚባለው ወይራና ዘንዶው “ወተት ይጠጣበት ነበር” የተባለው የአለት ገበታ ዛሬም ለእማኝነት አሉ፡፡ ግን ወይራው ደርቋል፤ አለቱም “በአካባቢው እሳት ተነስቶ ነበር” አሉ፣ ተሰነጣጥቋል፡፡ አካላቸውን ለማድከም ሲጸልዩ “ይሸከሙት ነበር” የተባለ ትልቅ ቆልማማ ድንጋይም ለአስረጅነት ተቀምጧል፡፡ ለዘንዶው ግብር የሚሆን ወተት ይከማችበት የነበረው እጅግ ትልቅ የአለት ገንዳ ለሁለት ተከፍሎ በክረምት ውሃ ይጠራቀምበትና ከፊሉ ለገዳማውያኑ መጠጥ፣ ሌላው ደግሞ ለልብስና አካላቸው ማጠቢያነት ያገለግላል፡፡

ችግሩ ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በትነትና በአገልግሎት ምክንያት ውሃው ሲያልቅ የሚከሰተው ጣጣ ነው፡፡ በአካባቢው የውሃ ዘር የለም፡፡ ቢኖርም ረጅምና አድካሚ ጉዞን ይጠይቃል፡፡ የገዳሙ የዜማ መምሕር ዳዊት ነቢይ እንደሚሉት፣ መነኮሳቱና መነኮሳያቱ አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡ ተራራው እንኳን ለመነኮሳቱ ለጐረምሳም እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ቦታውን ለማየት በሄድሁበት ጊዜ የታዘብሁትም ይህንኑ እውነት ነው፡፡ ካሜራዬንና ማስታወሻ ደብተሬን መያዝ አቅቶኝ፣ አንድ ትህትና የተሞላ የመምህር ዳዊት ደቀመዝሙር እያገዘኝ ነበር ያንን ትንፋሽ ቀጥ ሊያደርግ የሚችል ተራራ የወጣሁት፡፡ ክረምት ላይ በርከት ብለው የሚታዩ መነኮሳት፣ በውሃ ጥሙ ምክንያት በጋ ላይ የውሃ ሽታ ይሆናሉ፡፡ በሄድሁበት ጊዜ “አሉ” የተባሉት የመነኮሳት ቁጥርም ዘጠኝ ብቻ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ያን የመሰለ ፍጹም ፀጥታና ሰላም የሰፈነበት ገዳም፣ በውሃ ዕጦት ምክንያት የመነኮሳቱ ህይወት አለመረጋጋቱ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ ከዚያ ተፈጥሮው ድንቅ ከሆነ ተራራ ላይ ውሃ ማፍለቅ ባይቻልም፣ ከላይኛው ደብረ ጽሙና (ዮሐንስም ይሉታል) በቧንቧ መሳብ እንደሚቻል የውሃ ምህንድስና ባለሙያዎች አስረድተውኛል፡፡ ግን በምን አቅም? ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት “ቸርች ኤንድ ስቴት” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፣ ገዳሙ ከዲማና ደብረ ወርቅ ገዳማት ጋር አንድ ወቅት የተመሰረተ ነው፡፡

ግን የጥንታዊነቱን ያህል ገዳሙ ገና ብዙ ይቀረዋል፤ ቤተክርስቲያኑ በእጅጉ የተጐሳቆለ ነው፡፡ ከቤተክርስቲያኑ ይልቅ “ጻድቁ ዮሐንስ አሠሩት” የሚባለው ዕቃ ቤት የተሻለ ነው፡፡ የሰባ አንድ ዓመቱ አዛውንት ቄሰገበዝ ፀጋ ጥሩነህ እንደሚሉት፣ ገዳሙ የበቁ መነኮሳት የሚኖሩበት፣ ባህታውያን (ከሰው ተገልለው በብቸኝነት የሚኖሩ) ያሉበት በመሆኑ በረከትና ረድዔት ተለይቶት አያውቅም፡፡ እስካሁን የኖረውም በእነሱ ጸሎትና ትጋት ነው፡፡ ወደ ቀደመነገራችን እንመለስ፡፡ አባ ሲኖዳ ዘንዶውን ከገደሉ በኋላ ሕዝቡ “እሰይ ጠላታችንን፣ የልጆቻችንን ፀር ገደሉልን” ብሎ አላጨበጨበም፤ ይልቁንም “አምላካችንን ገደለብን፣ በውሃችን ተዘፍቆ እያደረም አረከሰብን” ብሎ ለወቅቱ ንጉሠ ነገሥት ሕዝበ ናኝ ክስ አቀረበ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አባ ሲኖዳ “አላዊው ንጉሥ ሕዝበ ናኝ ይወርዳል፤ በምትኩ ሃይማኖተኛ የሆነው ዘርዓያዕቆብ ይነግሳል” ብለው ትንቢት ተናግረው ነበርና ሸውከኛ ተነሳባቸው፡፡ ሕዝበናኝ ሰበብ ሲፈልግላቸው ነበርና፣ ጣና ሃይቅ ላይ ከሚገኘው ደቅ እስጢፋኖስ ደሴት ወስዶ አሰራቸው፡፡ ግን የታሰሩበት ሰንሰለት እየተበጠሰና ያሉበት ቤት በብርሃን እየተከበበ ጠባቂዎች ማድነቅ ስለጀመሩ ህዳር 12 ቀን 1414 ዓ.ም ቀኝ እጃቸውንና እግራቸውን ቆረጣቸው፡፡

ለሳምንት ያህል ደማቸው እየተንዠቀዠቀ፤ ግን ደግሞ ጸሎታቸውን ሳያቋርጡ ቆዩና ከላይ በተጠቀሰው ዓመት ህዳር 17 ቀን አረፉ፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ደብረ ጽሙናን ቸንፈርና ችጋር ክፉኛ መተው፡፡ ለሶስት ዓመታትም ዝናብ ጠብ ሳይል ቆየ፡፡ ከዚያ አንዲት የበቁ ሴት “የአባ ሲኖዳን አስከሬን ከደቅ አውጥታችሁ ደብረጽሙና ካልቀበራችሁት ዝናብ ለዘለዓለሙ ጠብ ሊል አይችልም” የሚል ህልም ተናገሩ፡፡ “መጀመሪያውኑም አባ ሲኖዳ ዕለተ ሞታቸው ሲቃረብ አጽሜን ከመሠረትሁትና ከምወደው ገዳሜ ደብረ ጽሙና አሳርፉት” ብለው ለተማሪዎቻቸው ተናዝዘው ስለነበር አጽማቸውን ማምጣት ግድ ሆነ፡፡ እናም አጽማቸው ከዲማና ከደብረ ጽሙና ድንበር ልዩ ስሙ “ፍቼና ጉልቴ” ከሚባል ቦታ ሲደርስ ሰማይና ምድር ታረቁ፡፡ በዕለቱም ያፈራ አለ፣ ለአጨዳ የደረሰ አለ፣ ቡቃያም የሆነ አለ” ይላሉ ቄስ ገበዝ ፀጋ ጥሩነህ ገድሉን ዋቢ አድርገው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ደብረ ጽሙና የበረከትና የቅድስና ገዳም መሆን ቻለ፡፡ ህዝቡም ክርስትናን በይፋ ተቀበለ፡፡ ግን የውሃው ችግር ለአገርና ለህዝብ ሰላም በሚጸልዩ መነኮሳትና መነኮሳይያት ህይወት ላይ ብርቱ ክንዱን ያሳረፈ በመሆኑ “የሃይማኖቱ ተከታዮችና በጐ አድራጊዎች ሊደርሱልንና ከጻድቁ በረከት ረድዔት እንዲሳተፉ በኃያሉ አምላክ ስም እንማፀናለን” ብለዋል መነኮሳቱ፡፡

Read 4898 times Last modified on Thursday, 11 April 2013 09:52