Monday, 08 April 2013 10:06

ፓርቲው በክርክር መድረክ እንዳልሳተፍ ተከለከልኩ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በሚያዚያው ምርጫ ለመወዳደር በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች እጩዎችን ያቀረበው የመላ ኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ለፓርቲዎች በተዘጋጀው የእጩዎች ማስተዋወቂያና የክርክር መድረክ ላይ እንዳልሳተፍ ተከልክያለሁ በሚል የአዲስ አበባ መስተዳድርን ወነጀለ፡፡ ባለፈው እሁድ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ለመራጩ ህዝብ የሚያስተዋውቁበት መድረክ ተዘጋጅቶ እንደነበር ፓርቲው ጠቅሶ፣ የምርጫ ህጎችንና የምርጫ ቦርድ ደንቦችን በሚጥስ ሁኔታ በመድረኩ ላይ እንዳይሳተፍ መከልከሉን ገልጿል፡፡ ፓርቲው በመድረኩ ላይ ለመሳተፍ ለከተማው አስተዳደር ምክር ቤት የአፈጉባኤ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ህጋዊ ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱንም አስታውቋል፡፡

የፓርቲዎቹ የጋራ ምክር ቤት ውስጥ ያልገቡ ፓርቲዎች በየክፍል ከተማው በሚዘጋጁ መድረኮች እንይሳተፉ መከልከላቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ታከለ አዱኛ በበኩላቸው “የምርጫ ስነምግባር ደንቡን ፈርመን፣ ኢህአዴግና ሌሎች 8 ፓርቲዎች በመሠረቱት የጋራ ምክር ቤት ውስጥ አባል እንድንሆን በተደጋጋሚ ጠይቀን ምላሽ አላገኘንም” ብለዋል፡፡ የጋራ ምክር ቤት አባል የሚሆንበት መስፈርት በግልጽ ተብራርቶ አለመቀመጡንም አክለው ገልፀዋል፡፡ ፓርቲው ለኢህአዴግና ለቀሪዎቹ የጋራ ምክር ቤት አባል ፓርቲዎች የተሰጠውን መድረክ እንዳይጠቀም መከልከሉን ያወገዙት አቶ ታከለ፣ ፓርቲያችን እጩዎቹን ለመራጩ ህብረተሰብ በአግባቡ ለማስተዋወቅ፣ እንዲሁም አላማና ፕሮግራሙን ለመግለጽ አልቻለም ብለዋል፡፡

የመወዳደሪያ ሜዳው ለሁሉም እኩል መሆን ሲገባው፣ አድልዎ መፈፀሙ አግባብ አለመሆኑን የጠቀሱት አቶ ታከለ፣ የእጩዎች ማስተዋወቂያና የክርክር መድረኩ በመንግስት ሃብት የተመቻቸ ሆኖ ሳለ፣ ለኢህአዴግና የፋይናንስ ድጋፍ ለሚሰጣቸው ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል ምርጫው በተቃረበበት ወቅት ፓርቲው ላይ አድልዎ ቢፈፀምበትም፣ ፕሮግራሙን በመገናኛ ብዙሃን የአየር ሰአት አላማውንና እጩዎችን ለህዝብ እያስተዋወቀ መሆኑን አቶ ታከለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ፓርቲው ላቀረበው አቤቱታ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አቶ ወልደገብርኤል አብርሃ በበኩላቸው፤ ፓርቲው ጥያቄውን አቅርቦ እንደነበር አስታውሰው፤ ይሄም ሆኖ ግን ውሳኔ መስጠት የምክር ቤቱ ተግባርና ሃላፊነት አለመሆኑን በወቅቱ አሳውቀናቸዋል ብለዋል፡፡

Read 2704 times