Monday, 08 April 2013 08:57

የመብራት መቋረጥ መፍትሔ የሌለው ችግር ሆኗል!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“መብራት የሚቋረጠው በሀይል እጥረት አይደለም” ኤፕኮ በፕላስቲክ ፋብሪካ ውስጥ ለ11 ዓመታት እየሰሩ የሚገኙት አቶ ከበደ ይስማው፤ የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ የፋብሪካውን ሥራ እያወከ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በወር ውስጥ መብራት የማይጠፋበትን ቀን ማስታወስ ይቀላል ያሉት አቶ ከበደ፤ በቅርጽ ሥራ ላይ እያሉ መብራት ሲቋረጥ የተለያዩ ቅርፆች የሚወጣላቸው ምርቶች ለብልሽት እንደሚዳረጉና ያንን ለማስተካከል ከፍተኛ ጉልበትና ጊዜ እንደሚባክን ይናገራሉ፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና በአንድ የመንግስት ሆስፒታል ውስጥ ለ16 ዓመታት በቀዶ ጥገና ሀኪምነት ያገለገሉ አንድ ባለሙያ፣ በቀዶ ህክምና ስራ ላይ እያሉ በተደጋጋሚ መብራት እንደተቋረጠባቸውና ብዙ የድንጋጤ ጊዜያትን እንዳሳለፉ ያስታውሳሉ፡፡ “ደግነቱ ጀነሬተር መኖሩ እንጂ መብራት ሲጠፋ እጅሽ ላይ ሰው ሊሞት ይችላል” ይላሉ፡፡ በሌላ የግል ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ የቀዶ ጥገና ሃኪም ጓደኛቸው፤ ከአንድ ታማሚ በቀዶ ህክምና ዕጢ በማውጣት ስራ ላይ እያሉ መብራት ጠፍቶባቸው የገጠማቸውን ያስታውሳሉ፡፡

ሆስፒታሉ አውቶማቲክ ጀነሬተር ቢኖረውም በአጋጣሚ የዛን ቀን ቶሎ መነሳት እንዳልቻለና ጓደኛቸው በድንጋጤ ራሳቸውን ሊስቱ ደርሰው እንደነበር ገልፀዋል፡፡ “ሆኖም ነገሮች ሊበላሹ ክፍልፋይ ሠከንዶች ሲቀሩ መብራት መጥቶ ህክምናው በሠላም ተጠናቀቀ ብለዋል ሃኪሙ፡፡ በተለይ በሆስፒታሎች አካባቢ የሀይል መቆራረጥ ከህይወት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉም የህክምና ባለሙያው ያሳስባሉ፡፡ እንጀራ በመጋገር ለሆቴሎች እንደሚያከፋፍሉ የሚናገሩ አንድ አስተያየት ሰጪ፤ በፊት በፊት በቀን ከ300-500 እንጀራ ጋግረው ያከፋፍሉ እንደነበርና አሁን ግን ቶሎ ቶሎ ኤሌክትሪክ ስለሚቋረጥ የሚጋግሩት እንጀራ በቀን ወደ 120 ዝቅ ማለቱን ገልፀዋል፡፡ “ይሄንንም የምጋግረው ስራው ከሚቆም ብዬ ነው አሁን ያለው የመብራት ችግር በስራዬ ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሮብኛል” ሲሉ ያማርራሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት ኢትዮ ቴሌኮም ያስተዋውቀው አዲስ የ3ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት ባስዋወቁ ጊዜ የኢንተርኔት መንቀራፈፍን በተመለከተ የኢትዮጵያ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ ተጠይቀው፤ ለችግሩ ምክንያት ነው በማለት በግንባር ቀደምትነት የጠቀሱት የሀይል መቆራረጥን ነው፡፡ አንድ አዛውንት ስለመብራት መቆራረጥ ሲናገሩ “መብራት ሀይል ያልፈጠረው ችግር የለም፤ የትራንስፖርት ችግሩም ከመብራት ሀይል ጋር ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም” ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን የውስጥ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ገብረእግዚአብሔር ታፈረ፤ የሃይል መቆራረጥ በሁለት መንገድ እንደሚከሰት ይናገራሉ፡፡ አንድም በፕሮግራም አሊያም በድንገት፡፡ በፕሮግራም የሚከሰተው የሃይል መቆራረጥ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በጥገና እና ማስፋፊያ ወዘተ ሥራዎች ጊዜ ሥራው መሠራት ስላለበት ብቻ ለማህበረሰቡ በተለያዩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ ማስታወቂያ ተነግሮ እንደሚጠፋ ይናገራሉ፡፡

ድንገተኛ ተብሎ የሚጠራው የሃይል መቆራረጥ በራሱ ሌላ ሁለት ምክንያቶች እንዳሉት ሃላፊው ያስረዳሉ፡፡ “መኪና ፖል ሲገጭ፣ የጭነት መኪና የኤሌክትሪክ ገመድ ሲበጥስ፣ በዛፍ ቆረጣ ጊዜ ዛፍ ኤሌክትሪክ ገመድ ላይ ሲያርፍ፣ በኤሌክትሪክ ግራና ቀኝ መስመሮች ላይ አላስፈላጊ ግንባታዎችና በሌሎች ሥራዎች ምክንያት ህብረተሰቡም ሆነ ኮርፖሬሽኑ ሳያውቅ በድንገት መብራት ይቋረጣል፡፡” ሌላውና ሁለተኛው ድንገተኛ የሃይል መቋረጥ “ቴክኒካል” የሚባለው የሃይል መቆራረጥ ሲሆን ባረጁ መስመሮችና ፖሎች እንዲሁም ከአቅም በላይ በጫኑ ንዑስ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ችግር ሲደርስ የሚፈጠር የሃይል መቋረጥ መሆኑን የገለፁት ሃላፊው፤ ሌላው ለሃይል መቋረጥ አስተዋጽኦ የሚያደርገው የሃይል ብክነትና ሥርቆት ነው ይላሉ፡፡ ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ የተለያዩ ዘረፋዎችን እንደሚያካሂዱም ተናግረዋል፡፡

አንደኛው የተዘረጉ መስመሮች ላይ የሚካሄድ ዘረፋ ሲሆን ከወራት በፊት ወለንጪቲ ላይ የደረሰውንና በምስራቁ የሀገራችን ክፍል በተለይም በድሬዳዋ የተከሰተውን የመብራት መቋረጥ ጠቅሰዋል፡፡ የተዘረጉ መስመሮች ላይ ከሚደርስ ስርቆት በተጨማሪ የሃይል ስርቆትም ሌላው ችግር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ገብረ እግዚአብሔር፤ አንዳንድ ህገ-ወጥ ግለሰቦችና ድርጅቶች አንድም ሃይል ወደቆጣሪው ከመግባቱ በፊት ቀጥታ ጥቅም ላይ በማዋል፣ ቆጣሪው የተጠቀሙበትን እንዳያነብ ያደርጋሉ አሊያም ቆጣሪውን በመነካካት እንዳያነብ ያደርጋሉ ይላሉ፡፡ አንድ ድርጅት 60 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሃይል በመስረቅ ክስ እንደመሰረተበት በማስታወስ በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ ምን ያህል ኪሣራ እንደደረሰበት የተጠየቁት ኃላፊው፤ “ስርቆት በባህሪው በስውር የሚደረግ ነው፤ በዚያ ላይ በቴክኖሎጂ ካልታገዘ ይሄን ያህል ብር ማግኘት ሲገባን አጥተናል ለማለት እቸገራለሁ፤ ነገር ግን ብዙ ኪሣራ ደርሷል፤ ኪሣራው ደግሞ የኮርፖሬሽኑ ሳይሆን የሁሉም ማህበረሰብ ነው” ብለዋል፡፡

ፖል ተገጭቶ ሲወድቅ እና በማከፋፈያዎች ላይ ችግሮች ሲፈጠሩ ኮርፖሬሽኑ ቶሎ ምላሽ አይሰጥም በሚል የሚቀርብበትን ቅሬታ አስመልክቶ ሀላፊው ሲመልሱ፤ “አሁን ያለንበት የቴክኖሎጂ ደረጃ አንድ ቦታ ላይ ሆነን የት ቦታ ችግር እንደተፈጠረ ለመለየት አያስችልም፤” ችግሮች በሚፈጠሩ ጊዜ መረጃ ለኮርፖሬሽኑ በትክክል አይደርስም፤ ነገር ግን መረጃው በትክክል ከደረሠና የተከሠተው ችግር ለእሳት አደጋና ለሠው ህይወት አስጊ ሲሆን ከማዕከል መብራት ይጠፋል፡፡” ብለዋል፡፡ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መጠነኛ የአደረጃጀት ችግር እንደነበረ ያስታወሱት ሃላፊው፤ አሁን ግን ከማዕከላት ጀምሮ በሠው ሀይል፣ በማቴሪያልና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ብቻ በመደራጀት ለሚፈጠሩ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡ አጠቃላይ የመብራት መቆራረጥን ችግር ለመቅረፍ ኮርፖሬሽኑ በ138 ሚሊዮን ዶላር በጀት በአገር አቀፍ ደረጃ 19 ያህል የማከፋፈያ መስመሮች እየተሠሩ ሲሆን ከ8-10 ያህሉ በአዲስ አበባ እንደሚሠሩም ተገልጿል፡፡ የውስጥ ለውስጥ ኬብሎችንም ሆነ ከላይ ያሉትን አቅማቸውን ለማሳደግና ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሀላፊው ገልፀዋል፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ሃይል የሚቋረጠው ለጅቡቲ እየተሸጠ ነው ይላሉ፡፡ ይሄን በተመለከተ አቶ ገ/እግዚአብሔር ሲናገሩ፤ በአሁኑ ሠዓት የመንግስት ዕቅድ አቅጣጫ ሁሉም ዜጐች የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ በመሆኑ ከጫፍ እስከ ጫፍ ገጠር አካባቢዎች መብራት እያገኙ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለጅቡቲም የሚሸጠው ሀይል ከኢትዮጵያዊያን የተረፈ ነው ብለዋል፡፡ “በአገራችን ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል ከፍላጐት በላይ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ለጅቡቲ ሀይል እየተሸጠ ነው፡፡” ያሉት ሃላፊው፤ ሀይል መሸጡ በጅቡቲ እንደማይቆም፤ ለሱዳንና ኬንያም ለመሸጥ እቅድ እንደተያዘና እነዚህም አገሮች ሌሎች አገሮች እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ወደፊት እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በዚህም አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ታገኛለች ብለዋል - ሃላፊው፡፡ የማስፋፊያና የጥገና ሥራዎቹ እስኪጠናቀቁ ድረስ እንደ ሆስፒታል፣ ቴሌ፣ ውሀና ፍሳሽ እንዲሁም ሆቴሎችና ፋርማሲ ያሉ አገልግሎት ሠጪዎች ተጠባባቂ ጀነሬተር ሊኖራቸው እንደሚገባ ሃላፊው አሣስበዋል፡፡ በሌላ በኩል አሽከርካሪዎችም ሲያሽከረክሩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንዲሁም የመብራት መስመሮች የሚያልፉባቸውን አካባቢዎች ህብረተሠቡና የአካባቢው መስተዳድር ከህገ-ወጥ ዘራፊዎች መጠበቅና መንከባከብ አለባቸው ያሉት አቶ ገ/እግዚአብሔር፤ ችግሮች ሲፈጠሩም ፈጥነው ወደ ማዕከሉ እንዲደውሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Read 4135 times