Saturday, 06 April 2013 14:30

ለብለብ የጋዜጣ ፅሁፎችን “ ቅሸባ” !

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ዛሬ ማንም ጋዜጣ ላይ የጻፈ ሰው፤ ነገ መጽሃፍ ይዞ እንደሚመጣ እርግጠኛ እስከመሆን ደርሰናል፡፡ ይሄ ደግሞ “ደራሲ” የሚለውን ብርቅ ስም ያለአቅም ለመሸከም ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡ ፖለቲካ የጻፈው፣ ስለሳይንስ ያወራው፣ ሁሉም ከጋዜጣ ወደ መጽሃፍ መሸጋገሩ ተለምዷል፡፡ ይህ ልምድ ደግሞ የኛ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይ ያደጉት ሃገራት ደራሲያን ይህንን ሲያደርጉት ለመኖራቸው በጄ ላይ ያሉ መጽሃፍት እማኝ ናቸው፡፡ በጋዜጣ ላይ የወጡ ብቻ ሳይሆኑ በሬዲዮ የተተረኩና በቴሌቪዥን የታዩ ፕሮግራሞች ሳይቀሩ ታትመው ለህዝብ ቀርበዋል፤ይሁንና ውስጣቸው ሲታይ ግን እንቶ ፈንቶ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ዴቪድ ፍሮስት የተባሉ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የጻፉት መጽሃፍ ቀላልና ተራ ነገር የያዘ ሳይሆን ታላላቅ የአሜሪካ የኪነጥበብና የፖለቲካ እንዲሁም የህግና የሌላም ሞያ ባለቤቶችን ያካተተ በመሆኑ የሚሰጠው ዕውቀት ቀላል አይደለም፤ለምሳሌ የማርቲን ሉተር ኪንግ ያልተነገሩ ነገሮች በጓደኛው አማካይነት ተጽፈው ቀርበዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የተለያዩ ደራሲያን የጻፏቸው መጣጥፎች ተሰባስበው ታትመዋል፡፡

ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑን የፐርልስ በክና የሌሎች የስነጽሁፍ ምሁራን ስራዎች ናቸው፡፡ የተለያዩ ደራሲያንን ቃለምልልስ የያዘው የቻርልስ ሩአስ “conversations with American writers” የተሰኘ መፅሐፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ ወደ እኛ ሃገር ስንመጣ ግን እውነታው ሌላ ነው፡፡ በእርግጥ ጊዜ የማይሽራቸው ፣የታላላቅ ሰዎችን ታሪክ የያዙ ወይም ደግሞ እንደ ጲላጦስ “ፍልስፍና” ዓይነቶቹ በመፅሐፍ መልክ መታተማቸው ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚያ ጸሃፊው ደክሞ የሰራቸው ሃሳቦች በቀላሉ ዳግም ስለማይገኙ፣ የዚህ ዓይነት ስራዎችን ማሳተም ለትውልድ እንደማስተላለፍም ይቆጠራል፡፡ዕውቀት ሆነው ለትውልድ የሚተላለፉ ከሆነ ደግ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ከሃሜት ያልተለዩ ፅሁፎችን፣ በጥላቻና በቂምበቀል የተሞሉ ፖለቲካዊ የጋዜጣ ፅሁፎችን በመፅሐፍ ማሳተም ግን ጥጃዋ ለሞተባት ላም ፣ ጭድ የተወተፈበት ቆዳ በማቅረብ ወተት እንድትሰጥ እንደማታለል ነው፡፡

ላም እንስሳ ስለሆነች የሟች ጥጃዋን ቆዳ ገፍፈው ጭድ በመክተት ሲያቀርቡላት ጡትዋን ትሰጣለች ፤ እኛ ግን ሰዎች ነን - ለዚያውም አንባቢ! አንባቢ ደግሞ የተሻለ መመዘኛ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን አሁን ግን እኛ ጋ የአንድ ሰሞን የፖለቲካ ትኩሳት፣የሚያልፍ ገጠመኝ ወዘተ ይዘን “አረ ጎራው” እንላለን፡፡ ወይም ለሽቀላ እንነሳለን፡፡ እንደኔ እንደኔ በተለይ እንደበዕውቀቱ አይነት አዳዲስ ሃሳብ ብቅ የሚልባቸው ወጎችና ጽሁፎች እንዲታተሙ መፈቀድ ብቻ ሳይሆን ገንዘብ ያለው ጥበብ ወዳድ ቢኖርና ቢያሳትመው ደስ ባለኝ ፤ክፋቱ የኛ ሃገር ድርጅቶች ስፖንሰር የሚያደርጉት ምናልባት እግር ኳስን እንጂ ጥበብ ብዙም አይማርካቸውም፡፡ ለነገሩ ጥበቡም አላማረበትም፡፡ ውበት እየተረሳ ፣ ሽቀላ ብቻ እየነገሰ መጥቷል፡፡ ብር ከሰውም ከጥበብም ይልቅ ሃገር እየገዛና እየሸጠ ያለበት ዘመን ቢኖር ዛሬ ነው፡፡ አውጣን እያሉ ከመታገል ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡

ጋዜጠኞቻችን እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ለብ ለብ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሳምንታዊ ጋዜጣዎችን የሚያነቡ ስንት ናቸው ብትሉ እፍኝ አይሞሉም፡፡ ስለዚህ ስለንባብና ስለጥበብ ያላወቀ “ነጋዴ ጋዜጠኛ” ስነጽሁፍ ሲወድቅና ሲነሳ ምን ስሜት ሊሰጠው ይችላል? ቀድሞ ራሱ ወድቋልና፡፡ምናልባት እንደጋንዲ ያለ ሰው ያስፈልገን ይሆናል፡፡ ግን ከየት ሊወለድ ይችላል? ጋንዲ ያልኩት ጥበብ እንዲያሳድጉ የተሰጣቸውን ስልጣን፤ አዙረው ለሌላ ፖለቲካዊ ጥቅም ለመመንዘር የሚተጉ ሰዎችን ስላየሁ ነው፡፡ ጥበቡን ሸጠው እንጀራና ስልጣን የሚያሳድዱ ሰዎችን ማየታችን እንግዳ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው የጥበቡ ሰፈር ጭርታ የበዛበት! አሜሪካዊቷ የወግና መጣጥፍ ጸሃፊና ደራሲ ማርጋሬት ሲ ባኒንግ እንደሚሉት፤ በጋዜጣ ላይ የሚወጡ ተከታታይ ጽሁፎች ለፈጠራ ደንቃራ ናቸው፡፡ እንዲያውም በጋዜጣ ላይ በተከታታይ የሚታተሙ ልቦለዶች እንኳ የረዥም ልብወለድ (ኖቭል) እንጀራ ልጆች ናቸው፡፡

ጥበብ በሚገባ እንዳያድግ መንገድ የሚይዙ፡፡ እናም በስነጽሁፍ አለም ውስጥ ምንም አክብሮት አይሰጣችውም፤ወይም ግርማ የላቸውም ይላሉ - ደራሲዋ፡፡ እርሳቸው በሚጽፉበት የሴቶች ጉዳይ ላይ ያተኮረ መጽሄት፤ የዚህ ኣይነቱን ጽሁፍ ክፉኛ በመተቸቱ፣ አሁን አሁን አቅም እያጣ እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ እኛ አገር ግን ትችትና ሂስ እየተዳከመ በመምጣቱ ሁሉም የፈለገውን እየፃፈ የሚያሳትምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የጋዜጣ ላይ ጽሁፎች መጽሃፍ ላይ መታተማቸውን አስመልክቶ አንድ ጸሃፊ ከጥቂት ወራት በፊት የጻፉትን ጽሁፍ አንብቤ ነበር፡፡ ይሁንና ሙሉ ለሙሉ ተቃውሞ ብቻ ስለነበር ፣ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረና አሁንም “ሸቀጣዊ” አስተሳሰብ ያለው ስለመሰለኝ በአክብሮት ልቀበለው አልቻልኩም፡፡ በርግጥ ጽሁፉ የሚያሳያቸው እውነታዎች አሉ፡፡ ጥቅል ሃሳቡ የጋዜጣ ላይ ጽሁፎች ህትመት ሲበዛ፤ አንባቢው አዳዲስ ስራዎች አያገኝም የሚል ነው፡፡ የበዕውቀቱንና መሰል ፀሃፍትን ጽሁፎችም ጠቅሶ ነበር፡፡ ግና መስመር ያለማበጀቱ አናደደኝ፡፡ እንዴት ነው የበዕውቀቱ ወጎች ከሌሎች የጋዜጣ ጽሁፎች ጋር በጅምላ የሚተቸው?የእሱ ቀልዶች እኮ ሰማይ ቀድደው ያያሉ፡፡ “የአስተናጋጁ ማስታወሻ” ላይ ያነበብኩት አንድ ታሪክ ሁሌ ይገርመኛል፡፡

ሲቀልዱ ሰውን ማሳቅ ብቻ ሳይሆን በጥልቀት እንዲያስቡ ማድረግ እንደሚቻል በዕውቀቱ አሳይቷል፡፡ አንድ የቆሰለ ሰውዬ ቀይ ቀበሮ ቁስሉን ስትበላው አይቶ፣ ባለጠመንጃው ሊተኩስ ይሞክርና ቀይ ቀበሮ መሆንዋን ያያል፣ያኔ ጠመንጃውን መለስ ያደርጋል፡፡ ለካ እኛ ሃገር ቀይ ቀበሮ ከሰው ይልቅ ውድ ነው!... ደሃ ስለሆንን ከሰው ይልቅ ለሰው የሚያስፈልጉት ነገሮች ናቸው! እንዲህ መሰል ነገሮችን የጻፈው በዕውቀቱ፣ ደጋግሞ ቢጽፍና ቢያሳትም ከዳቦዬ ቆርሼ ከመግዛት ወደ ኋላ አልልም፤ አልቆጭም፡፡ ለአለማየሁ ገላጋይ ፅሁፎችም ያለኝ አመለካከት ከዚሁ ጋር የተመሳሰለ ነው፡፡ ውብ የቋንቋ አጠቃቀምና ጥሩ ሃሳብ የመምረጥ አቅም አለው፡፡ ስሜትና ወሬ ብቻ ይዞ አይጋልብም፡፡ አንዳንዴ ሊያነቅፈው ቢችልም ጎበዝን ሲሳሳት መታገስ ያስፈልጋል፡፡ ከሺህ “ኮተታሞች” አንድ ጥርት ያለ ይሻላል፡፡ የግጥሙ ሰፈር የተበለሻሸው በዚህ የተነሳ ይመስለኛል - ሺ “ኮተታሞች” አደባባይ ላይ ብዙ ሳይደክሙ መታየት ስለሚፈልጉና “መጽሃፍ አሳተመ” መባልን እንደ ገድል ስለሚቆጥሩት፡፡ አሁንም የጋዜጣ ጽሁፎች አንዱ ሩጫ ያልተወለዱበትን ተልዕኮ ለማሳካት የሚደረግ መታተር ነው፡፡ ያለመክሊት ስም መፈለግ!... አንዳንዶቹ ለንጹህ ሽቀላ ሲሆን፣ ሌሎቹ ለስም ነው - ”ደራሲ” ለመባል ያላቸውን ናፍቆት ለመወጣት፡፡ ተፈጥሮና ፈጣሪ ካልሰጡኝ ቢቀርስ!... በቃ መጣጥፍ ጸሃፊ ብሆን! ህሊና ሲኖር ይህ ይቻላል፡፡ አንዳንዶቹማ የሰዎችን ስም መጥራት ሲቀራቸው ስድባቸውን በመጽሃፍ ማሳተም ጀምረዋል፡፡

ምነው ጎበዝ! የሃገራችንን ስነጽሁፍ ክብር ይህንን ያህል ማዋረድ ይገባናል እንዴ? . ለሽሙጥና ግለሰቦችን ለመስደብ መፅሐፍ ከማሳተም ይልቅ አዝማሪ ቤት መክፈት አይሻልም ? እዚያም ቢሆን ግን ልክና ጨዋነትን ይጠይቃል፡፡እንደ እኔ እንደ እኔ የዚህ ዘመን አብዛኞቹ ጽሁፎች ቁም ነገር አዘል የማይሆኑት ካለማንበብ የተነሳ ነው፡፡ ምንም ሲጠፋ ከስድብ ውጪ በአፋችንም ሆነ በብዕራችን አይመጣም፡፡ ያልዘሩት አይታጨድምና! ብናነብ ግን የስነ ጽሁፍም ክብር ይገባን ነበር፡፡ ሚዛናዊነትን እንለምዳለን፤ ከመሳደብ ይልቅ ወደ መወያየት እንመጣለን፡፡ ትውልድን ላለማበላሸት ሃላፊነት ይሰማናል፡፡ ትውልድ ከሳንቲም ሽቀላ እንደሚበልጥ እንረዳለን፡፡ ሃገር መውደድና ለሃገር መታገል ትውልድን በጥላቻና በቂም ውስጥ እየዘፈቁ አይደለም፡፡ ለሆድ ሳይሆን በእውነት ለወገን በመቆርቆር ነው፡፡ አርቆ አሳቢ በመሆን! ብርን ብቻ መውደድ የቅርብ ቅዠት እንጂ የሃገር ህልም ሊሆን አይገባም፡፡ ቂምና ጥላቻን መዝራትም በሽታ ነው፡፡ ፈውስ የሚመጣው በቂም አይደለም፤ እውነትን በፍቅር በማስተላለፍ ነው፡፡

ሃገራችን በብዙ መልኩ ጥንካሬዎችዋን እያጣች የመጣች ይመስላል፡፡ ምናልባት ዓለማችንም ማለት ይቻላል፡፡ ሙዚቃው ለብለብ፣ ጽሁፉ ለብለብ፣ ምግቡ ለብለብ፣ ፖለቲካው ለብለብ እየሆነ ነው፡፡ የሃገራችንን ሁለንተና መለወጥ ያለብን እኛ ነን ብዬ አምናለሁ፡፡ እንግዲህ ያያችኋት ናት ሃገራችን - በጥበቡ ሰፈር፡፡ የገጣሚ ነቢይ መኮንንን “ሃገርህ ናት በቃ!” የምትል ግጥም አንብቡና ራሳችሁን ፈትሹ፡፡ ይቺው ናት ኢትዮጵያ ሃገርህ ናት በቃ! በዚች ንፍቀ-ክበብ፣ አይምሽ እንጂ መሽቶ፣ማታው ከጠረቃ የነቃም አይተኛ የተኛም አይነቃ፡፡ ይቺው ናት ዓለምህ፣ ብቻዋን የተኛች ከዓለም ተደብቃ!! አኪሯ ቀዝቅዞ፡- “ያንቀላፋች ውቢት” ያንተው የክት ዕቃ! ምን ትሆን እንግዲህ ሀገርህ ናት እሷ! ልቧን አታውልቃት አትጨቅጭቃት በቃ፣ አብረህ አንቀላፋ ወይ አብረሃት ንቃ!! ሁሉንም አወራን ባንል ትንሽ ነካካን፤ገናም ወደ ፊት እናወራለን፤ግን ሃገራችንን የምንሰራት እኛ ነን፤ማንም አይመጣልንም፡፡ ሽቀላ ብቻ አይደለም፤ ሃላፊነትም ሊሰማን ይገባል፡፡ በተለይ ጋዜጠኞቻችን እባካችሁ ክፉና ደግ ለመለየት እንኳ አንብቡ፡፡ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል፡፡

Read 2478 times