Saturday, 30 March 2013 14:23

ልጆች እንዴት ቢማሩ ይሻላል ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

“በአሁኑ ዘመን ልጅን በቁንጥጫ ማስተማር አይመከርም!” ልጆችን ለማስተማር የሰለጠነው መንገድ የትኛው ነው? የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የስነ ትምህርት (Education) መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሃዋርድ ጋርድነር፤ መረጃን ለሌላው ወገን እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተላለፍ ይቻላል በሚለው ንድፈ ሃሳብ ዙርያ የሰሩትን ጥናት ውጤት ይዘው ብቅ ያሉት እ.ኤ.አ በ1983 ዓ.ም ነበር፡፡ ጋርድነር “መልቲፕል ኢንተሊጀንስ ቲዎሪ” በሚል የሠየሙት አስተምህሮት በአዲስነቱ ብዙም ተቀባይነት ባያገኝም፣ የኋላ ኋላ ግን በአንዳንድ ታዳጊዎች ላይ ባመጣው አስደናቂ ውጤት በአሜሪካ ብዙ ተከታዮችን ያፈራ የማስተማር ዘይቤ ሊሆን በቅቷል፡፡ የዚህ ንድፈ ሃሳብ ዋነኛ ማጠንጠኛ፣ ሠዎች በፈለጉት ወይም ምቾት በሚሠጣቸው መንገድ እውቀትን እንዲገበዩ ማስቻል የሚል ነው፡፡

ሁሉም ሠው የተለያየ አንጐል እንዳለው የሚገልፁት ፕ/ር ሃዋርድ ጋርድነር፤ አንዱ ጋ የሌለ የእውቀት አቀባበል ሌላው ጋ እንደሚኖር ያስረዳሉ፡፡ ለምሣሌ አዕምሮው በትክክል የማይሠራ ታዳጊ የመናገር ብቃቱ ደካማ ሊሆን ይችላል፡፡ በተቃራኒው ግን በስዕል እና በሙዚቃ ሃሣቡን በትክክል ሊገልፅና ሊረዳ ይችላል፡፡ ይህን የእውቀት አረዳድ መንገዱን ያገናዘበ የማስተማር ዘይቤ ተከትለን በነፃነት ስናስተምረው ብቻ ነው ሁሉም ነገር ግልፅ የሚሆንለት፡፡ ሪታ ዱን የተባሉ የዘርፉ ሊቅም “አንድ ህፃን አንተ በምታስተምረው መንገድ ካልተረዳህ፤ እሡ በሚፈልገው መንገድ አስተምረው” ሲሉ ይመክራሉ፡፡ ታላቁ ሣይንቲስት አልበርት አንስታይን በበኩሉ፤ “ሁሉም ሠው የምጡቅ አስተሣሠብ ባለቤት ነው፤ ነገር ግን አሣን ረጅም ዛፍ ላይ ውጣ ብትለው እድሜ ልኩን ቀሽም እንደሆነ ይሠማዋል” ይላል፡፡

በእነዚህ አስተምህሮቶች ላይ በማተኮር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ“መልቲ ስተዲስ ኤዱኬሽን” የማስተርስ ድግሪያቸውን ያገኙት መምህርት ቆንጅት ሞገስ እና መምህርት ገነት የማነ፤ በ“ኢንተርናሽናል ኮሚኒቲ ስኩል” በአስተማሪነት ከሚሰሩት ሥራ በተጨማሪ “መዲ ቱቶር” በተሰኘው ድርጅታቸው አማካኝነት ታዳጊ ተማሪዎች እንዴት ፍላጐታቸው ተጠብቆ መማር እና ማጥናት እንደሚችሉ ለወላጆች እና ለመምህራን ስልጠና ይሠጣሉ፡፡ ለተለያዩ ት/ቤቶች መምህራን በርካታ ስልጠናዎችን መስጠታቸውን የሚገልፁት መምህራኑ፤ በቅርቡ ቦሌ ድልድይ አካባቢ በሚገኘው ቲኬ ህንፃ 8ኛ ፎቅ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ለተማሪ ወላጆች ስልጠና ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ “ከዚህ ቀደም ወላጆችም ሆኑ መምህራን ልጆችን እነሡ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ እንዲማሩ፣ እንዲያጠኑ እና እንዲንቀሣቀሡ በቁጣና በተግሣፅ አለፍ ሲልም በልምጭ በመሸንቆጥ ባህሪያቸውን ለማቃናት ይጥሩ ነበር” የምትለው መምህርት ቆንጂት፤ ዛሬ ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ግን ይሄ የማይሞከር እየሆነ መምጣቱን ትናገራለች፡፡

መምህራኖችም ሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው የሚፈልጉትን መንገድ መከተል እንጂ ከልጆቹ ፍላጐት ውጪ ሃሣባቸውን ለመደፍጠጥ መሞከር የለባቸውም፡፡ “አንድን ተማሪ እኔ ባልኩት መንገድ ተማር ብለን በማስጨነቅ ተገቢውን እውቀት ሳያገኝ ከሚቀር፤ አንተ በምትፈልገው መንገድ አስተምሬህ የምፈልገውን እውቀት ያዝልኝ ብንለው ይሻላል” የምትለው ቆንጂት፤ አንድ ልጅ ተኝቶ ሲያነብ ወይም ቆሞ ሲማር ትምህርቱ የበለጠ የሚገባው ከሆነ “በስነ ስርአት ቁጭ ብለህ አጥና!” እያልን መነታረክ አይገባንም፤ እንዲያ ስናደርግ ልጁ የሚመቸውን መንገድ አልጠበቅንለትም ማለት ነው ትላለች፡፡ “ልጁ ቁጣውን ፈርቶ በስነ ስርአት ቁጭ ብሎ ቢያጠና እንኳን ምቾቱ ስላልተጠበቀለት ብቻ የሚያጠናው ነገር ሣይገባው ያልፋል፡፡ ካነበበው ውስጥ ጥያቄ መርጠን ብንጠይቀውም ላይመልስልን ይችላል፡፡ ያን ጊዜ ይሄ ልጅ ትምህርት አይገባውም ብለን እንደመድማለን፡፡ ይህ ከሚሆን ለምን የተማሪዎቹን የትምህርት አቀባበል መንገድ ተከትለን አናግዛቸውም” ስትል መምህርቷ ምክሯን ትለግሳለች፡፡

የዚህ አስተምህሮት አመንጪ የሆኑት ሃዋርድ ጋርድነር፤ ሠዎችን ከአዕምሮ እውቀት አንፃር በሰባት አይነት ክፍሎች ይመድቧቸዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በተምሮ ማስተማር በትምህርት ቤቶች የሚንፀባረቁ ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ በአብዛኛው ከጥበባዊ (Arts) ክህሎቶች ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ በግላዊ የአዕምሮ እውቀት ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ምሁሩ ይገልፃሉ፡፡ በመጀመሪያው ምድብ የሚገኙት “ሊንጉስቲክ ኢንተሊጀንስ” ያላቸው እንደሆኑ የሚያስረዱት ምሁሩ፤ እነዚህ ሰዎች መረጃን በመናገርና በመፃፍ ሲለዋወጡ የበለጠ መረዳት የሚችሉ ሲሆን በቋንቋ ችሎታቸውም ምጡቅ እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ ለዚህም ጥሩ አብነት የሚሆኑት ሼክስፒር እና አብርሃም ሊንከን ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጡት “ሎጂካል-ማቲማቲካል ኢንተሊጀንስ” በሚለው ምድብ የሚካተቱ ሲሆኑ እነዚህኞቹ ወደ ሣይንሣዊ ምርምሮች እና እውቀቶች የሚያዘነብሉቱ ናቸው፡፡ ነገሮችን በዚህ መንገድ እንዲረዱ በማድረግም ውጤታማ የመረጃ ልውውጥ ማካሄድ እንደሚቻል ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም አልበርት አንስታይንን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የሚቀመጡት ደግሞ “ሚዩዚካል ኢንተሊጀንስ” ያላቸው ናቸው፡፡

እነዚህኞቹ ነገሮችን የበለጠ በሙዚቃ ቅኝት የመረዳት ዝንባሌ ያላቸው ሲሆን ህይወታቸውም ከሙዚቃ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ በአራተኛ ደረጃ የሚጠቀሠው “ኬኔስቴቲክ ኢንተሊጀንስ” የሚባለው እንደሆነ የሚገልፁት ጋርድነር፤ የዚህ ፀጋ ባለቤት የሆኑ ሠዎች ከአካላዊ እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ ተግባቦት መፍጠር የሚችሉ ናቸው ይላሉ፡፡ “ስፓሺያል ኢንተሊጀንስ” ያላቸው ሠዎች ደግሞ ተግባቦትን ይበልጥ የሚፈጥሩት በስዕላዊ ጥበቦች ነው፡፡ “ኢንተር-ፐርሠናል ኢንተሊጀንስ”፣“ኢንትራፐርሠናል ኢንተሊጀንስ” እና “ናቹራል ኢንተሊጀንስ” የሚሏቸው እንዲሁ ከግላዊ የአዕምሮ እውቀት ጋር ተያያዥነት ያላቸው እንደሆኑ ጋርድነር ያስረዳሉ፡፡ እነዚህን የሠዎች ተፈጥሮአዊ ባህሪያት ጠንቅቆ በማወቅ፣ ሠዎች በሚቀናቸው መንገድ ተግባቦት መፍጠር ያስፈልጋል የምትለው ሌላዋ መምህርት ገነት የማነ፤ በተፈጥሮ የአንጐላችን አቀማመጥ የተለያየ መሆኑን ታስረዳለች፡፡

“አንዳንድ ሰዎች ወደ ቀኝ ያዘነበለ አንጐል ያላቸው ሲሆን ነገሮችን በሚገባ መረዳት የሚችሉትም አንድ ቦታ ተረጋግተው በመቀመጥ ሣይሆን እየተቅበጠበጡና አካላዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ከእንደነዚህ አይነት ሠዎች ጋር መረጃ ስንለዋወጥ ይህን ባህሪ ካልተረዳን ለምን ተረጋግተው አያዳምጡንም ልንል እንችላለን” የምትለው መምህርቷ፤እኒህ ሰዎች ሃሣብን በቀላሉ መረዳት የሚችሉት ከዝርዝር ሲጀመርላቸው ሣይሆን በቀጥታ ጉዳዩ ሲነገራቸው ብቻ ነው ባይ ናት፡፡ ወደ ግራ ያዘነበለ አዕምሮ ባለቤቶች ደግሞ ተረጋግተው ቁጭ ብለው መረጃ መለዋወጥ ካልቻሉ አይገባቸውም፣ በዚያው ልክ መረጃው በቀጥታ ከሚነገራቸው ይልቅ ከዝርዝር ቢጀመርላቸው የበለጠ ይረዳሉ፡፡ ይህን አስተምህሮት ይዘው ብቅ ያሉት ቆንጅት እና ገነት፤ወላጆችም ሆኑ መምህራን ልጆችን በእነዚህ መለኪያዎች እየመዘኑ ተስማሚ በሆነው መንገድ ማነፅ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

በአስተምህሮቱ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ ለመፍጠርም ለወላጆችና ለመምህራን እንዲሁም ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስልጠናውን በመስጠት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ መምህራኖቻቸው በ“መዲ ቱቶሪያል” እንዲሠለጥኑ ማድረጋቸውን የነገሩን የ“ስኩል ኦፍ ኔሽን” ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ታደለ፤ከዚህ ቀደም ለመምህራኖቻቸው ብዙ ስልጠናዎችን በሃገር ውስጥና በውጭ አሠልጣኞች እንደሠጡ ያስታውሳሉ፡፡ ከሁሉም ውጤታማ ሆኖ ያገኙት ግን የ“መዲ ቱቶሪያል” ስልጠና እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ስልጠናውን ለየት የሚያደርገው ምን እንደሆነ ሲናገሩም፤አሣታፊ እና አዳዲስ ፍሬ ሃሣቦችን የያዘ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡

Read 2516 times