Saturday, 30 March 2013 14:11

“ዜጎችን ማፈናቀል መንግስትን በዓለምአቀፍ ህግ ሊያስጠይቀው ይችላል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ዜጎች አገራችሁ አይደለም፣ ልቀቁና ውጡ መባላቸው አሳፋሪ ነው! (የ“አንድነት” ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ) ነዋሪዎች ሲፈናቀሉ በህይወት የመኖር ህልውናቸውም አደጋ ላይ ይወድቃል ( ኢትዮጵያዊ ምሁር) የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ካስቀመጣቸው የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች መካከል፤የዜጐች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት አንዱ ሲሆን በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 32 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በህጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት” እንዳለው ተደንግጓል፡፡

በዚህ ድንጋጌ መሰረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ብቻ ሳይሆን የሌላም ሀገር ዜጋ በሀገሪቱ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ በማንኛውም አካባቢ መኖር ይችላል - ሃብትና ንብረት አፍርቶና ቤተሰብ መሥርቶ፡፡ በህገ-መንግስቱ ላይ በግልፅ የሰፈረው ሀቅ ይሄ ቢሆንም በየጊዜው ግን ድንጋጌውን የሚጥሱ ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከአማራ አካባቢ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በመሄድ ለአመታት ሀብትና ንብረት አፍርተው የኖሩ ዜጎች፣በየጊዜው የመፈናቀል አደጋ እየገጠማቸው ነው - መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፡፡

ከአመት በፊት በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ የተባለ ቦታ ላይ ለረጅም አመታት ኑሮ መስርተው ሲኖሩ የቆዩ የአማራ ተወላጆች “ቦታው የእናንተ አይደለም” በሚል በሃይል መባረራቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህን ዜጐችን የማፈናቀል ድርጊት በወቅቱ በርካታ ወገኖች ቢያወግዙትም ሰሚ ባለማግኘቱ፤ገበሬዎቹ ያፈሩትን ሃብትና ንብረት ትተው ወደየትውልድ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ተገደዋል፡፡ በዚያው በደቡብ አካባቢ በቤንች ማጂ ዞን ሸካ ወረዳ በርካታ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መሬታቸውን ተነጥቀው መባረራቸው ይታወቃል፡፡ በጋምቤላ፣ በአፋር እና በሌሎች አካባቢዎችም ከህገመንግስቱ ጋር በማይጣጣም መልኩ ዜጎች ከመኖርያ አካባቢያቸው መፈናቀላቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወሳል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ በተፈጥሮ ሀብቱ በሚታወቀው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኑሮአቸውን ያደረጉ የሰሜን ኢትዮጵያ ተወላጆች ለአመታት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ትተው በግፍ ከአካባቢው እንዲሰናበቱ መደረጉ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ተዘግቧል፡፡ እነዚህ ገበሬዎች በትውልድ ቀዬአቸው የእርሻ መሬት ባለማግኘታቸው፤ ወደክልሉ በመሄድ የሰፈሩ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የያሶ ወረዳ አስተዳደር “በህገወጥ መንገድ ስለገቡ ወደመጡበት መመለስ አለባቸው” በማለት ባለፈው ሳምንት ከአካባቢው እንዳፈናቀላቸው ይታወቃል፡፡ ከስድስት ሺህ እንደሚልቁ የተገመቱት እነዚህ ተፈናቃይ ዜጐች፤ በገዛ ሀገራቸው ለዳግም ስደት መዳረጋቸውን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ላለፉት 16 አመታት በዚምባቡዌና በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ሲያስተምሩ ቆይተው ወደ ሀገራቸው በመመለስ በግል ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ መልካምሰው ትዕዛዙ፤ለህገመንግስቱ ዘብ ቆሜያለሁ የሚለው አካል በህገመንግስቱ አንቀፅ 32 የተደነገገውን በመጣስ “ከሌላ ቦታ እየመጣችሁና እየሰራችሁ የአካባቢውን ተወላጅ ሰነፍ አደረጋችሁት” በሚል ዜጎች እንዲፈናቀሉ ትእዛዝ ማስተላለፉን ነቅፈዋል፡፡ “ይሄ የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ በነጮች ተይዞ የነበረውን የእርሻ መሬት በዘረኝነት ተነሳስተው ለጥቁር ዜጐች ለማከፋፈል ከመወሰናቸው በምን ይለያል?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

በዚምባቡዌ የመሬት ድልድል ላይ ከባልደረባቸው ጋር ጥናት ያደረጉት አቶ መልካምሰው፤በወቅቱ ሙጋቤ የወሰዱት እርምጃ ሀገሪቱን ለውስብስብ ችግሮች መዳረጉን ይናገራሉ፡፡ ሜካናይዝድ በሆነ የግብርና ቴክኖሎጂ በመታገዝ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን እያለሙ፤ ከሀገሪቱ አልፎ ለውጭ ገበያ የሚተርፍ የስንዴ ምርት ያቀርቡ የነበሩት ነጭ ገበሬዎች፤ መሬቱን ተነጥቀው ለጥቁሮች እንዲያካፍሉ ከተደረገ በኋላ፤ ጥቁሮቹ የግብርና ሙያ እና ባህሉ ስላልነበራቸው መሬቱን ፆም እያሳደሩ የሀገሪቱን የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ እንዳቀጨጩት የሚናገሩት አቶ መልካምሰው፤ምንም እንኳ በዚምባቡዌ የተፈፀመው እና በሀገር ቤት እየተፈፀመ ያለው መነሻውም ባህሪውም ለየቅል ቢሆንም መሰረታዊ የሰብአዊ መብትን ከመጣስ ባለፈ ምርታማነትን በማቀጨጭና ብዙ ተረጂዎችን በመፍጠር እንደሚመሳሰሉ ይገልፃሉ፡፡

“እነዚህ ተፈናቃዮች ቀድሞ ወደነበሩበት ምርታማ ያልሆነ አካባቢ ተመልሰው እንዲሰፍሩ ሲገደዱ በከፍተኛ የስነልቦና ስብራት የተረጂነት ስሜትን ስለሚላበሱ የሌላን አካል እጅ ጠባቂ ይሆናሉ፤አሊያም ከእጅ ወደ አፍ ወደሆነው የቀድሞ ህይወታቸው ይመለሳሉ” ብለዋል፡፡ በዚህ አግባብም ሀብት አፍርቶ የመኖር መብታቸው ከመጣሱም ባለፈ፤ በህይወት የመኖር ህልውናቸውም አደጋ ላይ ይወድቃል የሚሉት ምሁሩ፤ አንድ ዜጋ በሀገሩ በተደላደለ ሁኔታና በመረጠው አኳኋን የመኖር መብቱ ካልተረጋገጠ ደግሞ “አገር ማለት ሰው ነው” የሚለው የቀድሞው ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ “አስተምህሮት” ውሃ በላው ማለት ነው ብለዋል፡፡ “ሰው በሰውነቱ ብቻ መከበር ሲገባው፤በኢትዮጵያዊ ደም የሚተሳሰር የኢትዮጵያዊ ዜግነት ማረጋገጫ አርማን ያነገበ ዜጋ፣ የምትኖርበት መሬት ያንተ አይደለም፣ መሬትህን ፈልግ ከተባለ አገር ማለት ሰው መሆኑ ይቀርና አገር ቁስ አካል - መሬት ይሆናል” ያሉት አቶ መልካምሰው፤ይህ ሲሆን ደግሞ በፅናት እንከተለዋለን የተባለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ “አስተምህሮት” በወረቀት ላይ ብቻ እንደቀረው የህገ መንግሥቱ ቃል በአፍ ብቻ ይቀራል ሲሉ ስጋታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ከየአካባቢያቸው መልቀቂያ አምጥተውና መታወቂያ አውጥተው በመኖር ላይ የነበሩ ዜጎችን ይሄ አገራችሁ አይደለም፣ ልቀቁና ውጡ መባሉ አሳፋሪ ነው ያሉት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤለ ተፈራ በበኩላቸው፤ “ የኛ ዜጐች አሜሪካ አውሮፓ፣ ደቡብ አፍሪካና አረብ ሀገር ሄደው እንኳ እናንተ ባእዳን ናችሁ፣ ሀገራችሁ አይደለምና ለቃችሁ ውጡ ሳይባሉ፣ በገዛ ሀገራቸው እዚህ አካባቢ መኖር አትችሉም ተብለው እንዲወጡ መገደዳቸው፣ የኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ ያልገባቸው ትናንሽ አምባገነኖች በየአካባቢው በዘፈቀደ እየተፈጠሩ መሆኑን ያመለክታል” ብለዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ሀገራችን የት ነው? ሀገራችን ማን ናት? የሚሉትን ጥያቄዎች ያስነሳል የሚሉት የአንድነት ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ፤ “ዜጐች በኢትዮጵያዊነታቸው ከመመካት ይልቅ በብሄራቸውና በአካባቢያቸው ልክ ብቻ እንዲሰፉም ያደርጋል” ሲሉ የሚያስከትለውን ችግር ይገልፃሉ፡፡

ነዋሪዎችን የማፈናቀሉ ዘመቻ ከአመት አመት ተጠናክሮ መቀጠሉንና በህገመንግሥቱ የተቀመጠውን የመዘዋወር መብት አደጋ ላይ የሚጥል አደገኛ አካሄድ መሆኑን ያሰመሩበት አቶ ዳንኤል ፤ ሂደቱም ከዘመናዊ አስተሳሰብ የራቀ እና አግላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “ዛሬ የሰለጠኑት አውሮፓውያን፤አንድ እንሁን በሚል ጐጠኝነትን፣ ጐሰኝነትንና በሉአላዊ ሀገር መታጠርን አስቀርተው አንዲት አውሮፓን እያለሙ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ከሌላው አፍሪካዊ ወንድማችን ጋር መወዳጀቱ ቢቀርብን እንኳን፤ እርስ በእርስ ይሄ መሬት ያንተ አይደለም፣ ይሄኛው ያንተ ነው፣ ያኛው የእገሌ ነው መባባሉ በእርግጥም ዘመኑን ያልዋጀ ኋላ ቀርነት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ክልል የተፈፀመው ዜጐችን የማፈናቀል ድርጊትም ሆነ ከዚህ ቀደም ሲፈፀሙ የነበሩት መነሻ ምክንያታቸው ሁለት ጉዳዮች እንደሆኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ዳንኤል ይናገራሉ፡፡

“አንደኛው አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሚከተለው ቋንቋን መሰረት ያደረገው ፌዴራሊዝም ሲሆን ሁለተኛው ለስልጣን ማራዘሚያ ሲባል ብቻ ለግለሰቦች የሚሰጠው ፅንፈኛ ብሄር ተኮር አስተምህሮት የተሳሳተ መሆን ነው፡፡ ሰው ቋንቋው መደበላለቅ ሲጀምር አስቀድሞ በተማረው መሰረት ልዩነቱን ነቅሶ በማውጣት መቁጠር ይጀምራል፡፡ ያኔም በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መጠለል የሚለው ትርጉም ያጣና ቡድንተኝነቱ አይሎ ይወጣል፡፡ የመሰል ችግሮች ጥንስስም እዚያ ላይ ይቋጠራል፡፡

ይህ ደግሞ ሄዶ ሄዶ በገዛ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ ያለፓስፖርትና ቪዛ መኖር የማይቻልበት የታሪክ አጋጣሚ ላይ ሊያደርስ ይችላል፡፡” ብለዋል - የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፡፡ የአለማቀፍ ህግ ምሁሩ ዶ/ር ያዕቀብ ኃ/ማርያም በበኩላቸው፤ በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ላይም ሆነ ቤኒሻንጉል አካባቢ እንዲሁም በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዜጐች መፈናቀላቸው ህገ መንግሥቱንም ሆነ ኢትዮጵያ የተፈራረመቻቸውን አለማቀፍ ስምምነቶችን ይጥሳል” ይላሉ፡፡ በሀገሪቱ ህገ መንግሥትም ሆነ ስምምነት በተደረገባቸው አለማቀፍ ህጐች አንድ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ በሉአላዊ ግዛቱ በፈለገው ቦታ በመኖር ንብረት የማፍራት መብት አለው የሚሉት ዶ/ር ያዕቀብ፤ አሁን ባለው የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከተለያዩ አካባቢዎች የአንድ ብሄር አባል የሆኑ ሰዎች ከመሬታቸው እንዲፈናቀሉ ይደረጋል፡፡ ይሄ ደግሞ በአለማቀፍ ስምምነት ዘር ማጥራት (ethnic cleaning) ከሚለው ውስጥ የሚመደብ ሲሆን በሰው ልጅ ላይ የሚፈፀም አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ነው ብለዋል፡፡

ከሰባቱ የተባበሩት መንግሥታት አበይት የሰብአዊ መብት ሰነዶች መካከል አንዱ የሆነው፣ እንዲሁም ኢትዮጵያም ፈርማ በተቀበለችውና ማንኛውም የዘር መድልዎን ለማስወገድ በተደረገው አለም አቀፍ ስምምነት ላይም፤ በዘር ልዩነት ላይ የተመሰረተ የበላይነት ፍልስፍና ሳይንሳዊ መሰረት እንደሌለውና ከስነምግባር አንፃርም የሚወገዝ፣ ከማህበራዊ ኑሮ አንፃር ፍትህ የጐደለው፣ ትክክል ያልሆነና አደገኛ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በዚሁ የቃል ኪዳን ስምምነት ሰነድ በአንቀፅ 5 ንዑስ አንቀፅ “መ” ላይ፤ አንድ ዜጋ “በአገሩ የግዛት ክልል ውስጥ በነፃነት የመንቀሳቀስና የመኖር መብት” እንዳለው ተደንግጓል፡፡ (በኢፌድሪ ህገ መንግሥት በአንቀፅ 32 ላይ ከሰፈረው ጋር ተመሳሳይ አቋም ያለው አንቀፅ መሆኑን ልብ ይሏል) ከዚህ አንፃርም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ድርጊቱ መንግሥትን በአለማቀፍ ህግ ሊያስጠይቅ እንደሚችል አለማቀፍ የህግ ምሁሩ ዶ/ር ያዕቆብ ይናገራሉ፡፡

እንደሳቸው አባባል አንድ ዜጋ “በዚህ ዘርህ ወይም በዚህ ሃይማኖትህ ምክንያት እዚህ ቦታ መኖር አትችልም” ከተባለ የዘር ማጥራት ወንጀል ይባላል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ማስረጃ አሰባስበው የፀጥታው ምክር ቤት ቢያቀርቡት፤ ምክር ቤቱ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ምርመራ እንዲያደርግ ሊያዘው ይችላል የሚሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ፍርድ ቤት አባል ባትሆንም ይህን የፈፀሙ ግለሰቦች ሊከሰሱ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ዜጐችን የማፈናቀል ተግባር በየትኛውም የህግ አግባብም ሆነ ከሞራል አንፃር ተቀባይነት የለውም ብለዋል - ዶ/ር ያዕቆብ፡፡

Read 2624 times