Saturday, 30 March 2013 13:53

ሻዕቢያ የሚረጨው “የጥላቻ መርዝ”

Written by  ቦጋለ ንጋቱ (Bogal@gmail.com)
Rate this item
(2 votes)

ዘመንና ሁኔታዎች ቢቀያየሩም ታሪክን እንደፈለጉ መለዋወጥ አይቻልም፡፡ በእርግጥ ታሪክን የምናይበት የፖለቲካ መነፅር ነገሮችን ለዋውጦና አቀያይሮ (አንሸዋሮ) ሊያሳየን ይችል ይሆናል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ማንሳት የፈለግሁት ከ25 ዓመታት በፊት በነበረችው ኢትዮጵያና በዚያ መዘዝ ዛሬ የታሪክ ከዳተኞች በሚፈፅሙት ደባ ዙሪያ ነው፡፡ የዛሬ 25 አመት፣ በ1980 ዓ.ም የመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ በሰሜን ቀይባህር አውራጃ የደርግ መንግሥት ጦር ከፍተኛ ሽንፈት ገጥሞት ነበር፡፡ ደርግ እጅግ ከሚተማመንበት ክፍለ ሠራዊት መካከል “ናደው ዕዝ” በሚባለው ማእቀፍ የሚመራው 20ሺ ገደማ ጦር አፍአበት ላይ እንዳይሆኑ ሆኗል፡፡

በርካታ የመካናይዝድ መሳሪያዎችም በጠላት ወድመውበታል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሻዕቢያ የበለጠ ሞራሉን ያነቃቃበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነበር፡፡ ይህን ጉዳይ እንዳስታውስ ያደረገኝ ከሰሞኑ በኤርትራ ቴሌቪዥን ተደጋግሞ እየቀረበ ያለው “የድል ፕሮግራም” ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም የኤርትራ “ተጋድላዮች” በከፈሉት ከፍተኛ መስዋእትነትና ተጋድሎ ደርግና የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደተበታተነ በምስል ተደግፎ ሲቀርብ ሰንብቷል፡፡ የአፈአበት ድል ደርግ ከሚመካበት ከፍተኛ የጦር ሃይሉ ዋነኛው የተደቆሰበትና ኤርትራውያን አሸናፊነትን የተጐናፀፉበት ክስተት መሆኑን ደጋግሞ እየዘከረው ይገኛል - ሻዕቢያ፡፡ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ወገን የነበሩ መኮንኖች ግን የአፍአበቱ የናደው ዕዝ ሽንፈት ምክንያቶች ሌላ እንደነበሩ ይዘረዝራሉ፡፡

ኮሎኔል አምሳሉ ገብረዝጊ “የኤርትራ መዘዝ” በሚለው መፅሃፋቸው የተሳተፉበትን ውጊያ እንዲህ ያስታውሳሉ፤ “…ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሁአሰን በጐበኙበት ወቅት በውሸት ክስና ህግና ስነስርአት ሳይከተል በአዛዡ በብ/ጄ ታሪኩ አይኔ ላይ የተወሰደው ህገወጥ እርምጃ በናደው እዝ ስር የተሰለፈውን ጦር ሞራል ጐድቷል፡፡ ጦሩ በአዛዡ በግፍ መገደል የተሰማውን ጥልቅ ቅሬታ በልቡ ይዞ በሞራል መዋጋት አልቻለም፡፡ በነበረበት ቅሬታ ሞራሉ ወድቆ፣ የውጊያ ብቃቱም ቀንሶ ታይቷል” ከዚህም በተጨማሪ ጠላት ያለ የሌለ ሃይሉን ማሰለፉ፣ የናደው እዝ ጦር እርዳታ ሲጠይቅ አለማግኘቱና ጠላት እንደሚያጠቃ በቂ መረጃ እያለ ከግንባሩ አንድ ክ/ጦር እንዲነሳ መደረጉን ለናደው ዕዝ ሽንፈት በምክንያትነት ዘርዝረዋል፡፡ የሆነው ሆኖ እውነቱን ታሪክ ያረጋግጠዋል፡፡ ሻቢያ በወቅቱ ማሸነፉና በድል ተንበሽብሾ አጠቃላይ ትግሉን ከዚያ ወዲህ እያፈጠነ መሄዱ ግን የማይታበል ታሪካዊ ሃቅ ነው፡፡ናደው ዕዝ ከመጋቢት 8 - 11 ቀን 1980 በተደረገ ውጊያ ሲደመሰስ “19ኛ፣ 21ኛ እና 22ኛ ክፍለ ጦሮችና መካናይዝድ ብርጌድ፣ልዩ ልዩ ክፍሎችን እንደያዘ ነበር፡፡ በዚህም 20ሺ የሚደርስ ጦር፣ 40 ታንኮች፣ 60 መድፎች፣ በርካታ ተሽከርካሪና መጠባበቂያ ጥይት ከነማዘዣ ጣቢያው ተማርኳል ወይም ወድሟል፡፡ የዕዙ ጥብቅ አዛዥ የነበሩት ብ/ጄ ውበቱ ፀጋዬ በህይወት ቢተርፉም በርካታ አዛዦች ተማርከዋል፣ተሰውተዋል፡፡

ሦስት የሶቭየት ህብረት ከፍተኛ አማካሪዎች ሲማረኩ አንዱ ሞቷል፡፡ ይሄን ነው እንግዲህ ዛሬ ሻዕቢያ “ሓምድ ድብ ናደው ቅያ መቐየሯ” ሲል የሚዘክረው፡፡ የፅሁፉ ማጠንጠኛ የናደው ሽንፈት ወይም የሻዕቢያ ድል አይደለም፡፡ ይልቁንም የኤርትራ መንግሥት የዚህን ድል 25ኛ አመት ለመዘከር ሰሞኑን እያደረጋቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች ላይ ነው፡፡ የኤርትራ መንግሥት ሌላ አጀንዳ የሌለው ያህል አብዛኛውን ጊዜ እያሳለፈ ያለው ድል በመዘከር ነው (በታሪክ ይኖር ይመስል!) ይህ መሆኑ ባልከፋ ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ ከኃይለሥላሴ እስከ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ለኤርትራ “ጥላት” እንደሆነ መስበኩ ግን አደጋ ነው፡፡ ሻዕቢያ አሁን ላለውና ለመጪው ትውልድ ትምህርት ለመስጠት እንደሚዘክረው በገለፀው የድል በአል ላይ፤ ለምን የአሁኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አፈአበት ላይ ከተሸነፈው የቀድሞ መንግስት አመራር ጋር እንዳመሳሰለው ግራ ገብቶኛል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ድርጅትም ሆነ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ለኤርትራ ህዝብ ነፃነት አጋር እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ገና ከትጥቅ ትግሉ አንስቶ የወታደራዊውን የደርግ ስርዓት የጭቆና ቀንበር ለመጣልም ሆነ፤ከድል በኋላም ኤርትራውያን በፍላጐታቸው የፈቀዱትን እንዲወስኑ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡

እነሆ እስከአሁን ድረስ “አሰብ ይገባናል” የሚሉ ወገኖችም ሆኑ አንቀፅ 39 “የማይዋጥላቸው” የግዛት አንድነት የሚሹቱ እየተቹትም ቢሆን ኢህአዴግ በኤርትራ ህዝብ ጥያቄ ላይ ፅኑ አቋም እንደያዘ ነው፡፡ በእርግጥ እ.ኤ.አ ከ1998-2000 ዓ.ም በሁለቱ ሀገራት በድንበርና ሌሎች ፖለቲካዊ ግጭቶች ሳቢያ የተፈጠሩት አሰቃቂ ጦርነቶች በመንግሥታቱ መካከል ከፍተኛ መሸካከርን መፍጠሩ አይካድም፡፡ ያም ሆኖ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል የነበረውን ወንድማማችነት ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀላል የማይባሉ ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኛ ወጣቶች፤ ነፃ የዩኒቨርስቲ ትምህርት እድል ሰጥቷል፡፡ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ (በየኮንደሚኒየም ሳይቶች በንግድ የተሰማሩትን ይመለከቷል) ከመፍቀዱም ባሻገር ኤርትራውያን ስደተኞች ወደፈቀዱበት ሀገር እንዲሄዱ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው፡፡ በየስደተኛ ካምፑ ያሉት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችም የፀጥታ ስጋት እንዳይገጥማቸው መደረጉና በአለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች በኩል መሰረታዊ ፍላጐቶቻቸው እንዲሟሉላቸው መመቻቸቱ እንደቀላል ነገር የሚታይ አይደለም፡፡

የሻዕቢያ ተቃዋሚ ጐራን የተቀላቀለው ሃይልም “ከእጅ አይሻል ዶማ” ሆኖ እንጂ የተለያዩ ድጋፎች ሲደረግለት ነበር፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለኤርትራ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይሰፍን ዘንድ እገዛ እንደማድረግ የሚቆጠር ነው፡፡በእርግጥ ሻዕቢያ ካለፈው የድንበር ግጭት ወዲህም ሆነ በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ ስር የሰደደ ጥላቻ ሲያራምድ ነበር፡፡ ገና ከደርግ መፍረስ ጀምሮ የተመላሽ ኢትዮጵያዊያንን ሀብት ከመዝረፉም በላይ የጣት ወርቅ ለመውሰድ እጅ ሁሉ ሲቆርጥ እንደነበር ታሪክ አይዘነጋውም፡፡ በፈሪ አሸናፊነት በእሩምታ ተኩስ የጨረሰው ትጥቅ የፈታ ጦርም ሆነ ምርኮኛውን በግፍ አያያዝ እንዲማቅቅ በማድረግ እኩይ ተግባሩም የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትችት አስተናግዷል፡፡ከ”ነፃነት” በኋላም ኤርትራ ውስጥ አማርኛም ሆነ ኦሮሚኛ ሙዚቃ ማዳመጥ ያሳስር እንደነበር ይታወቃል፡፡ በ”ጥገኛ” አካሄድ ሊያልባት የተመኛትን ኢትዮጵያን (ሀብቷን ፈልጐ) ህዝቧን ግን በጠላትነት የፈረጀውም ቀድሞ ነበር፡፡ በጥላቻና ስድብ ፕሮፓጋንዳ የበላይነቱን ከመስበክም ባሻገር ድንበር አልፎ በሃይል ለመውረር ያደረገው የእብሪት ሙከራ መነሻም የንቀት አስተሳሰቡ ነው፡፡ ልማደኛው “የእናት ጡት ነካሽ” የሆነው ሻዕቢያ፤ለቀሪው ኤርትራዊ ትውልድ አሁንም እየረጨ ያለው የናዚ መርዝ አይነት አጥፊና ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ ነው፡፡

“ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ለመላቀቅ አንድ ትውልድ ገብረን ነፃነታችን ካረጋገጥን ሁለት አስርት ዓመታት ብናስቆጥርም አሁንም ከጠላቶቻችን ለአፍታ ልንዘናጋ አይገባም” እያለ በመስበክ ላይ ይገኛል - ኢሳያስ የሚመሩት የሻዕቢያ መንግሥት፡፡ ግጭቱን ከመንግሥታት ጋር እንኳን ሳያደርግ መላው ኢትዮጵያን የኤርትራ ህዝብ ጠላት በማድረግ መርዙን እየረጨ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአውሮፓ ጉዳይ አስተባባሪ አምባሳደር ዶ/ር ፅዮን ሲናገሩ፤ “ኃይለሥላሴም፣ መንግሥቱም አልፈዋል፣ አሁን ያለው ስርዓት ግን አድፍጦ ለጥቃት ይጠብቃል…” ብለዋል፡፡ ይሄ እንግዲህ “እኔ ከሞትኩ---” አይነት አስተሳሰብ የሚያመጣው ውጤት ነው፡፡ በተመሳሳይ ባለፈው ሰሞን “የፈንቅል ትውስታ” በሚል የምፅዋ ድላቸውን ሲዘክሩ አሳዛኝ ነገር ተመልክቼ ነበር፡፡ ራሱ ሻዕቢያ መላውን የምፅዋ ከተማ ህዝብ በቅርብ ርቀት በመድፍ መጨፍጨፉን ሁሉ ዘንግቶት (የታደሰ ቴሌ ሳልቫሮ “ኧይ ምፅዋን” ያስታውሷል) ሜዳ ላይ የተረፈረፈ የሲቪል አስከሬን እያሳየ “የቅኝ ገዢዎች ጠላቶች ደባ ያስከፈለን ዋጋ” በማለት ማራገቡ አዲሱ የኤርትራ ትውልድ ጭንቅላት ውስጥ ምን ሊቀርፅ እንዳሰበ ክፉኛ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው፡፡ ሻዕቢያ እስከ አሁን ድረስ ያገጠጠ መሬትና ምድረ በዳ ኤርትራን ይዞ፣ ከወደብ ኪራይና ከማዕድን ሽያጭ የሚያገኛትን እንኳን ለልማት ማዋል አልቻለም፡፡

ለዚህ ጥሩ ማሳያው ደግሞ የህዝቡ ጎስቋላ ህይወትና በየመድረኩ አዛውንትና ህፃናት (ወጣቶች የሌሉበት) ብቻ መታየታቸው ነው፡፡ እንግዲህ የሚበዛው ወጣት ወይ ሀገር ጥሎ ተሰዷል አልያም ነፍጥ ታጥቆ ድንበር ላይ አጥር ሆኗል፡፡ የመቃወም ዝንባሌ ያለውን እየሰበሰበም በየእስር ቤቱ አጉሮታል፡፡ እናም በስራ ላይ ያሉ አምራች ወጣቶችን መመልከት ብርቅ የሆነባት ምድር ሆናለች - ኤርትራ፡፡ እንግዲህ በዚህ ጊዜ ነው አቶ ኢሳያስ በሌላ የፍርሃት ሽብር (ጠላት ፈጥረው) ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ጋር ታሪካዊ ጠላት እንደሆኑ መስበክን ስራዬ ብለው የተያያዙት፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት የፊት ለፊት ውጊያውም ሆነ የማተራመስ ስትራቴጂው ሲነቃባቸው በትውልዱ ላይ “የጥላቻ መርዝ” መርጨቱን እንደ አማራጭ የያዙት ይመስላል፡፡ ታሪክ እንደሚፈርድባቸው ዘንግተው፤ የኢትዮጵያውያንን እስከአሁን የዘለቀ ውለታና ወዳጅነት ረስተው ለፖለቲካ ጥቅም ብቻ እየፈፀሙት ያለው ሴራ ግን ማንም ይቅር ሊለው የሚገባ ድርጊት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያንና መንግሥትም ቢሆኑ የአካሄዱን አደገኝነት ሊገነዘቡት የሚገባ ይመስለኛል፡፡

Read 4905 times