Monday, 07 November 2011 13:30

ሃቃኒ - አልቃይዳን የተካ አደገኛ አሸባሪ

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(1 Vote)

አሸባሪነት እየተስፋፋና በዓለም ላይ አሳሳቢ ችግር እየሆነ ባለበት በዚህ ዘመን፣ አሸባሪዎች በሚፈጽሙት ተግባር ፖለቲካዊ ውዝግቦችንና ጠላትነትን አስከትለዋል፡ ሰዎች ለዘራቸው፣ ለብሔራቸው ወይም ለጎሳቸው ያላቸው ታማኝነት ብዙውን ጊዜ አንዳቸው በሌላው ላይ እንዲነሱ አሊያም በመንግስታት መካከል መከፋፈል በመፍጠር እንዲጋጩ ምክንያት ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ በ1914 ዓ.ም ጋቭሪሎ ፕሪን ትሲፕ የተባለ አንድ ግለሰብ የአስትሮ ሃንጋሪን ጭምር መንግስት አልጋ ወራሽ የነበረውን አርክዱክ ፍራንሲስ ፈርዲናንድን እንዲገድል ያነሣሣው የዘር ኩራት ነበር፡ በአልጋ ወራሹ ላይ የተፈፀመው ግድያም የአንደኛው የዓለም ጦርነትን በማስነሳቱ ሚሊዮኖችን ለሕልፈት ዳርጓል፡፡

ከ25 ዓመታት በኋላ በተነሣው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጀርመን ናዚ ፓርቲ ዝቅተኛ ዘር እንደሆኑ በፈረጃቸው የአይሁድ፣ የጂፕሲ እና የስላቭ ዝርያዎች ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽሟል፡፡ በተለይም ከዝርያቸው በተጨማሪ በሃይማኖታቸው ልዩነት ምክንያት ስድስት ሚሊየን አይሁዳዊያን አሠቃቂ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ 
በ20ኛው ክ/ዘመን የነበረው የዘር ማጥፋት ግድያ ዛሬም በዚህ ዘመን ከሚካሄደው የሽብር ጥቃት ጋር ይመሳሰላል፡፡ የሽብር ጥቃት የሚፈጽሙ ግለሰቦች በሃይማኖታቸው፣ በብሔራቸው እንዲሁም በዘራቸው ላይ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት ፈጽመዋል ወይም እየፈፀሙ ናቸው በሚሏቸው አገራት ላይ የፍትህ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ራሳቸውንም እንደ አሸባሪ እንደሆኑ ሳይሆን የነፃነት ተዋጊዎች እንዲሆኑ ይቆጥራሉ፡፡ ሽብርተኝነት በየትኛውም ማህበረሰብ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ቢሆንም ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን አንዳንድ አገራት ፖለቲካዊ ጥቅማዠውን ለማስጠበቅ እንዲሁም ለእነርሱ ጠላት እንደሆኑ የሚያስቧቸውን የጐረቤት አገራት ሕልውና ለማናጋት ሽብርተኞችን እንደመሣሪያ ይጠቀማሉ፡፡
በአሜሪካ መስከረም 11/2001 ዓ.ም የሽብር ጥቃት በኋላ፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ “ወይ ከእኛ ጋር አለበለዚያ ከአሸባሪዎች ጋር ቁሙ” በማለት ለመላው ዓለም ያስተላለፉት መልዕክት የአሸባሪዎች ወዳጅ ለሆኑ አገራት የሚመለከት ግልፅ መልዕክት ነበር፡፡
በወቅቱ አብዛኛው አገራት ሽብርተኝነት በማውገዝ ከአሜሪካ ጐን የተሰለፉ ሲሆን በተለይም ፓኪስታን አሜሪካ በከፈተችው የፀረ-ሽብርተኝነት ዘመቻ ከአሜሪካ ጐን ከመሰለፏ በተጨማሪ አልቃይዳ የተስፋፋበትን ቦታ ለአሜካ ወታደራዊ ኃይሎች መረጃ በመስጠት እና ወታደራዊ ኮንቮዮተ በፓኪስታን በኩል ወደ አፍጋኒስታን እንደገቡ በመፍቀድ ትልቁን ሚና ተጫውታለች፡፡ በዚያን ጊዜ የአሜሪካው የስለላ ድርጅት (ሲ.አይ.ኤ) እና የፓኪስታኑ የስለላ ድርጅት (Pakistan’s Inter-Service Intelligence) መረጃ በመለዋወጥ በጋራ በመስራት ጥብቅ ወዳጅ ነበሩ፡፡
የፓኪስታን ወዳጅነት የተመቻቸው ጆርጅ ቡሽ በወቅቱ የፓኪስታን ፕሬዝዳንት የነበሩትን ጀነራል ፔርቬዝ ሙሻራፍን በተለያዩ ጊዜያት ወይት ሃውስ በመጋበዝ አብረው ይዝናኑ ነበር፡፡ መንግሥታቸው በፀረ-ሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ላሳየው ትብብርም ከዚህ በፊት ያኙ የነበረውን መጠነኛ እርዳታ ዳጐስ በማድረግ እንዲሰማቸው ከጆርጅ ቡሽ ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ ሙሻራፍ ከስልጣን ከወረዱም በኋላ ቢሆን አሜሪካ ለፓኪስታን የምትሰጠው እርዳታ ሳይቋረጥ ቢላደን ፓኪስታን ውስጥ እስከተያዘበት ቀን ድረስ አሜሪካ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ለፓኪስታን ለግሳለች፡፡
ቢላደን ፓኪስታን ውስጥ ከተገደለ ከአንድ ወር በኋላ፣ የፓኪስታን የገንዘብ ሚኒስቴር አብዱልሃፌዝ ሻይክ፣ ፓኪስታን ያለባትን የውጭ እዳ ለመክፈል አስመልክቶ በአይ.ኤም.ኤፍ የተገባላትን የ11 ቢሊዮን ደላር እርዳታ ቢየንስ 4 ቢሉዮን ዶላሩን ለማስለቀቅ ወደ ወሽንግተን አቅንተው ነበር፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴሩ ዋሽንግተን እንደደረሰ በአሜሪካና በአይ.ኤም.ኤፍ ባለስልጣናት ቀዝቃዛ አቀባበል የተደረገላቸው ከመሆኑም በላይ ፓኪስታን ከጠቅላላው የታክስ ስርዓት 10 በመቶ ብቻ መሰብሰቢን እንደምክንያት በጥቀስ አይ.ኤም.ኤፍ ሚኒስቴሩን ባዶ እጃቸውን ሸኝቷቸዋል፡፡
አሜሪካ አትጨክንም በሚል ተስፋ ወደ ዋሽንግተን ያቀኑት ባለስልጣኑ እርዳታውን የተከለከሉት በታከስ ጉዳይ አለመሆኑን ለማወቅ ብዙ ማሰብ አያሻቸውም፡፡
መቼም ፍቅር ሲቀዘቅዝ ወይም ሲጠፋ አይጣል ነው፡፡ አሜሪካና ፓኪስታን እንደዚያ ወዳጅ የነበሩትን ያህል፣ አሁን ሁሉም ነገር ያከተመለት ይመስላል፡፡ ቢላደን በፓኪስታን ውስጥ በአሜሪካ ልዩ ኮማንዶ ኃይሎች መገደል በኋላ የተጀመረው ጥላቻና መወነጃጀል ባፈው መስከረም ወር ደግሞ ሃቃኒ የተባለው አሸባሪ በአፍጋኒስታን ውስጥ የአሜሪካ ኤምባሲና በሌሎች የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ በወሰደው ጥቃት የፓኪስታን የስለላ ድርጅትን ጠንካራ ድጋፍ ያገኛል በሚል አሜሪካ መግለጿ ይታወሳል፡፡ የአሜሪካ ጀይንት ቺፍ ኦፍ ስታፍ አዛዥ የሆኑት አድሚራል ማይክ ሙለን፣ የፓኪሰታን የስለላ ድርጅትና ሃቃኒ የጠበቀ ግንኙነት የላቸው ከመሆኑ በላይ በአሜሪካ ላይ ለሚፈፀመው የሽብር ጥቃት የስለላ ድርጅቱ አመራር እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡ በእርግጥ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስቴር የሱፍ ራዛ ጂላኒ የአሜካን ውንጀላ መሰረተ ቢስ በማለት ማጣጣላቸው ይታወሳል፡፡
ሰሞኑን ለንንባብ የበቃው The Economist መፅሄት ደግሞ Snake country በሚል ርእስ የሃቃኒን ማንነትና የፓኪስታንን ሚና አስመልክቶ ሰፊ ዘገባ አቅርቧል፡፡
ሃቃኒ የተባለው አሸባሪ ቡድን የዛሬ 30 ዓመት በአፍጋኒስታን ሲደራጅ፣ ማንኛውንም የውጭ ወሪሪ ኃይል ለመዋጋት ዓላማ አድርጐ የተነሳ ቡድን ነበር፡፡ ሃቃኒ ተስፋፍቶ የሚኘው በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን ድንበር መካከል በሆነው በዋዛሪስታን አውራጃ ውስጥ ነው፡፡ የአሜሪካ ወታደራዊ ባለስልጣናት የዋዛሪስታን ዋና ከተማ ሚራናሻ የሃቃኒ አሸባሪዎች እንደልብ የሚርመሰመሱባት እንደሆነ ይናገራሉ በተጨማሪም በዚህች አካባቢ የፓኪስታኑ የስለላ ድርጅትም የላቀ ሚና እንዳለው ይገልፃሉ፡፡
ሃቃኒን ከ30 ዓመት በፊት ያደራጀው ደግሞ፣ ጃላሉዲን ሃቃኒ የተባለው የአፍጋን ሽምቅ ተዋጊ ኮማንደር ነበር፡፡ ጃላሉዲን ሃቃኒ እ.ኤ.አ በ1979 ሶቭየቶች አፍጋኒስታንን ሲወሩ፣ ከሙጂሃዲኖች ጋር በመሆን የሶቭየትን ጦር ከአፍጋኒስታን በማውጣት ይታወቃል፡፡ የሶቭየት ባላንጣ የነበረችው አሜሪካ በወቅቱ የሶቭየት ጦር ከአፍጋኒስታን ለቆ እንዲወጣ ሙጂሃዲኖችን ረድታለች፡፡ ሃቃኒ ላሳየው የጦር ብቃትም አድናቆትን ቸራቸለች፡፡ በዚያን ቢላደን ወዳጇ እንደነበረ ሁሉ ጃላሉዲን ሃቃኒም የሲ አይ ኤን ድጋፍ ያገኝ ነበር፡፡
የ60 ዓመቱ ጃላሉዲን ሃቃኒ በዋዛሪስታን እጅግ የተከረ ሰው ነው፡፡ በታሊባን የአስተዳደር ዘመን የአካባቢው የበላይ ገዢ በመሆኑ፣ የሚፈጠረውን የጐሳ ግጭት በመሸምገል ይታወቃል፡፡ ሃቃኒ የውጭ ወራሪዎችን አጥብቆ የሚቃወም ቢሆንም፣ በመንግስታት የሚታደኑ እስላሚክ ሚሊሺያዎችን ወይም አክራሪ ኃይሎችን መጠለያ ሰጥቷቸዋል፡ ከ20 ዓመት በፊት ቢላደን ወደዚያ ያመራው የሃቃኒ እንግዳ ተቀባይነት እንደሆነም ይነገራል፡፡
ሃቃኒ በአሁኑ ወቅት በሕመም ላይ የሚገኝ ቢሆንም ሱራጁዲን ሃቃኒ የተባለው ወንድ ልጁ የሃቃን ቃል አቀባይ በመሆን የሽብር ቡድኑን ይመራል፡፡
ሃቃኒ የሚለውን የሽብር ቡድን በራሱ ስም የሰየመውም ድርጅቱ ሲያቋቁም ነበር፡፡
ሃቃኒ ወደ 5000 የሚጠጉ አሸባሪዎች ያቀፈ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ በአጥፍቶ መጥፋት የሽብር ጥቃት በደንብ የሰለጠኑ ናቸው፡፡
ሃቃኒ አሁን ካሉት አባላቱ በተጨማሪም 20.000 ተዋጊዎች በሃቃኒ ውስጥ እንዲሳተፉ በዋዛሪስታን ለሚኖሩ ጐሳዎች ጥሪ አቅርቧል፡፡
ቢላደን ባለፈው ሚያዚያ ወር ከተገደለ በኋላ በአካባቢው ያለው የአልቃይዳና እንቅስቃሴ በጣም መዳከሙን የሚገልጹት የአሜሪካ ባለስልጣናት በተቃራኒው ሃቃኒ ግን በጣም እየተስፋፋና የጥቃት ደረጃው እየጨመረ እንዲመጣ ገልፀዋል፡፡
ትኩረቷን ከአልቃይዳ ወደ ሃቃኒ ያደረገችው አሜሪካ፣ ሰው አልባ በሆኑ አውሮፕላኖች ተደጋጋሚ ጥቃት አድርጋለች፡፡ ሰው አልባ የሆኑ አውሮፕላኖች የሚካሄደው ጥቃት ንፁሀንንም አንድ ላይ እያጠፋ በመሆኑ ሲ.አይ.ኤ ለፀረ ሽብር ተግባር ብቻ በተለየ ሁኔታ የሰለጠኑ ፓራሚሊተር ወታደሮችን ከልዩ ኮማንዶ ኃይሎች ጋር እየተጠቀመ ይገኛል፡፡
ከሃቃኒ ጋር ግንኙነት አላት በሚል የቀረበባትን ክስ ውድቅ ያደረገችው ፓኪስታን የስለላ ድርጅት በዋዛሪስታን አካባቢ የሚንቀሳቀሰውም ከሃቃኒ ጋር ግንኙነት ስላለው ሳይሆን ጠላቴ ከምትላት ከሕንድ ጋር ግንኙነት አላቸው የምትላቸውን የሁዝቤክ፣ የታጂክ እና የሃዛሪያስ ነዋሪዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እንደሆነ ትገልፃለች፡፡
በሌላም በኩል አሜሪካ አፍጋኒስታናዊያንን በማሰልጠን ታደራጅ ብኛለች የሚል ጥርጣሬ እንዳላት በመግለጽ የስለላ ድርጅቷ ይህንን ሁሉ ለመከታተል በዋዛሪስታንን ይንቀሳቀሳል ትላለች፡፡
ፓኪስታን የሚቀርብባትን ክስ በተደጋጋሚ ብታጣጥልም ከተለያዩ አሸባሪዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አላት፡፡
በተለይም ባላንጣዋ ከሆነችው ከሕንድ የሚደርስባትን ጥቃት በመፍራት በሕንድ ላይ አደጋ የሚያደርሱ አክራ ኃይሎችን የስለላ ድርጅቷ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ለምሳሌ በ2008 በሕንድ ሙምባይ ውለታ በታጅ ማሃል ሆቴል ውስጥ ለደረሰው ጥቃት ፓኪስታን የስለላ ድርጅት ጋር ግንኙነት እንዳለው ሕንድ ገልፃለች፡፡ በቅርቡ ክስ የቀረበባት ሃቃኒም ቢሆን ከፓኪስታን ጋር የቆየ ግንኙነት አለው፡፡
እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም ጃላሉዲን ሃቃኒ እና የፓኪስታን የስለላ ድርጅት ወዳጅነት የመሠረቱበት ጊዜ ነበር፡፡
በዚያኔ በአፍጋኒስታን በስልጣን ላይ የነበረው ታሊባንም የፓኪስታን ወዳጅ ነበር፡፡ ነገር ግን ለአሜሪካ መስከረም 11/2001 ዓ.ም የደረሰው የሽብር ጥቃት ፓኪስታን አሰላለፏን ከአሜሪካ ጋር በማድረጓ ከአክራሪዎቹ ጋር ያላትን ግንኙነት አቋረጠች፡፡ ከታሊቢያን ጋር እስካሁን እንደተቆራረጠች ብትቀርም ከ2008 በኋላ ግን ከሃቃኒ ጋር ወዳጅነት መጀመሯን የአሜሪካ የስለላ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡
የቢላደን ለአምስት አመት ያህል በፓኪስታን ውስጥ ተሸሽጐ ሲኖር ማውቀው ነገር የለም በማለት የገለፀችው ከሃቃኒም ጋር ግንኙነት የለኝም በማለት ሁለቱንም ክሶች ውድቅ ብታደርግም አሜሪካዊያን ግን በቀድሞ ወዳጃቸው መከዳታቸውን ሙሉ በሙሉ አምነው ተቀብለዋል፡፡
በቅርቡ በአሜሪካ በተካሄደ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አፈጉባኤ የሆኑት ጂን ቦህነር ሲናገሩ “20 ቢሊዮን ዶላርና ወታደራዊ ድጋፍ ያደረግንላት ፓኪስታን ከእኛ ምንድነው የምትፈልገው? ከእኛ ጠላቶች ጋር ወዳጅ የምትሆነው ለምንድነው?” በማለት ለራሳቸውም ግራ የገባቸው ነገር ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበው ነበር፡፡
የፓኪስታን የስለላ ድርጅት ከመንግስት በጀት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚያገኝ በመሆኑ በፓኪስታ ብቻ ሳይሆን ከፓኪስታን ውጪ ያለውን በተለይም በአፍጋኒስታንና በሕንድ ያለውን ፀረ ፓኪስታን እንቅስቃሴ እየተቆጣጠረ ቢላደን ፓኪስታን ውስጥ እንደነበር አላውቅም ነበር ማለት ለማመን አስቸጋሪ ነው፡፡ በሌላ በኩል ቢላደን በተገደለበት አቡታባድ ውስጥ የፓኪስታን የጦር አካዳሚና የጦር አዛዥ መኖሪያ እዚያው አቡታባድ ውስጥ ነው የሚገኙት፣ ይህም ፓኪስታን መረጃ የለኝም ነበር ማለቷ ከእውነት የራቀ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ፓኪስታኖች እንዳሉት አላወቁም ተብሎ ቢባል እንኳን ወዳጃቸው የነበራቸውን አሜሪካንን ላለማስቀየም ሲሉ፣ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ መግለጽ ይችሉ ነበር፡ ነገር ግን የፓኪስታን መንግስት የቢላደን መገኘት ሳይሆን ሉዓላዊ ግዛታቸው መጣሱን በማንሳት ነበር የተቃወሙት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሱፍ ራዛ ዷላኒ ከታይም መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲናገሩ፣ “ሕዝቡ በአሜሪካን ላይ ቁጣውን ሲገልጹ ከሕዝቡ የተለየ አቋም መያዝ የለብኝም”፣ በማለት የበለጠ የሚያሻክር ንግግር ተናግረዋል፡፡ ለፓርላማቸውም ባቀረቡት ንግግር አሜሪካ ግዛታቸውን መጣሷን በመግለጽ አገራቸው ማንኛውንም የውጭ ወራሪዎች የመመከት ኃይል እንዳላት ተናግረዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሽብር ጥቃትን እያጠናከረ የመጣው ሃቃኒ በአፍጋኒስታን የተዳከመውን አልቃይዳ ጋር ባለው ወዳጅነት አልቃይዳም እንደገና እንዲያንሰራራ ሃቃኒ ሊረዳው እንደሚችል የአሜሪካ ባለስልጣናት ስጋት ነው፡፡ የበለጠ አደገኛ የሚሆነው ደግሞ የፓኪስታን የስለላ ድርጅት ሁለቱንም ለማጠናከር የሚያደርገው ድጋፍ ነው በማለት ይናገራሉ፡፡
ፓኪስታንና አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ሆድና ጀርባ በመሆናቸው ሁለቱም አገራት አካባቢውን ከሽብርተኞች ለመጽዳት በጋራ የነበራቸው የረጅም ጊዜ እቅድ ዳር ሳይደርስ ሊከሽፍ ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ የሁለቱም መቃቃር ለሽብርተኞች የበለጠ ጥሩ አጋጣሚን የሚፈጥርና ለመስፋፋት የሚያመች በመሆኑ አካባቢውን የአሸባሪዎች መፈንጫ ሊያደርገው እንደሚችል ይታወቃል፡፡
አሜሪካ በአካባቢው ያሉትን አክራሪ ኃይሎች ለመደምሰስ ከፓኪስታን የተሻለ አጋር አገር እንደማታገኝ ስለምታውቅ ምናልባት ከፓኪስታን ጋር የላትን ግንኙነት እንደገና እንደምታጤነው አንዳንድ ፖለቲከኞች ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል ፓኪስታን ያለባትን የውጭ ዕዳን ለመክፈልና የኢኮኖሚ ችግሯን ለመቅረፍ የአሜካ አጋርነት የግድ ያስፈልጋት በማለት አስተያየት ይሠጣሉ፡፡

 

Read 6041 times Last modified on Monday, 07 November 2011 13:34