Monday, 25 March 2013 15:21

“የጦር ዕቅድና ብልሃት ከአባቶች እስከ እኛ ዘመን”

Written by  ብዕር ጂ.
Rate this item
(0 votes)

“ወታደር የተማረና ያወቀ መኾን አለበት”

ከግራዚያን ጭፍጨፋ፣ ከጣሊያን ወረራ …

የውጊያ ስልት ጨምቆ ያወጣ መጽሐፍ

ለዚህ ጹሑፍ መነሻ የኾነኝ፣ ጣሊያን ለቀድሞ የጦር አበጋዟ ለማርሻ[ል] ግራዚያኒ ሐውልት በማቆሟ ሳቢያ፣ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን መቆጣታቸውን፣ ተቆጥተውም ለሰልፍ መውጣታቸውን፣ ሰልፍ ወጥተውም በኢሕአዴግ ሕግ አስከባሪዎች መታገታቸውንና ብሎም መታሰራቸውን ስስማ የተፈጠረ የተሳከረ ስሜት ነው ማለት ይቻላል፡፡ “እንዴት አሉ?” እንዴት ማለትማ ጥሩ ነው፡፡ ከዛሬ 65 ዓመት በፊት መታተሟን የምትገልጥ አንዲት አነስተኛ አሮጌ መጽሐፍ መንገድ ላይ ተዘርግታ ሳያት አንሥቼ እንዳደረሰኝ መሀከል ላይ ገለጥኋት - ገጽ 48 - “በጦርነት ያለቀው ሕዝባችን÷ በግራሲያኑ አደጋ በመላው ኢትዮጵያ ያለቀው ህዝብ÷ አካላቸው የጐደለው÷ ለመሣሪያ ወጪ የተደረገው÷ ንብረቱ ጠፍቶ ያልተቋቋመው÷ በአርበኝነትና በስደት ያለቀው ሕዝብ ይህ ሁሉ አብሮ ሲቆጠር ኢትዮጵያ በሚሊዮን ገብቶ የሚታሰብ ሕዝብ ሞቶባታል ለማለት ይቻላል” የሚለውን ሣነብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ሢያንስ ነው? እስከ ማለት ደረሥኩ፡፡ የግራዚያኒን ጭካኔ በሉት ጀብድ ለማንበብ ካለኝ ተነሣሽነት ብቻ ሣይሆን፣ ሠላማዊ ሠልፍ ወጥተው “ግራዚያኒ ለምን ሐውልት ተሠራለት?” ብለው ለመጠየቅ የወጡ ሰዎች መታሠራቸውን በመስማቴ ጭምር ይመስላል ይኼን አሮጌ መጽሐፍ በውድ ገዝቼ ማንበቤን ቀጠልኩ፡፡ “የጦር ዕቅድና ብልሃት፡፡

ከአባቶች እስከ እኛ ዘመን፡፡” የሚለው ባለ 95 ገጹ መጽሐፍ፣ ምን ያህል አርቆ አሣቢ ዜጐች እንደነበሩ ያሥተነትናል፡፡ በሻምበል ተስፋ ደስታ የተፃፈው ይኼ የጦር ዕቅድ መጽሐፍ፣ ከአገራዊ የውጊያ ሥልት እስከ የወቅቱ ዓለማቀፋዊ የውጊያ ብቃት ድረሥ ሂሣዊ በሆነ መንገድ ተንትኗል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር፣ ከ65 ዓመት በፊት የነበረበትን አቋምና ደረጃ ያመለክታል፡፡ ወታደርነት፣ በጦር መሣሪያ እያሥፈራሩ ያሻቸውን የሚያደርጉበት የጉልበት ሞያ በሚመሥልባት በዛሬዋ ዓለም፣ ከውትድርና ጀርባ ሊገነባ ሥለሚገባው የእውቀት ሀብት ያሥረዳል፡፡ ወታደር የሚባለው ስም በምን በምን ጊዜ እንደተለመደና ወታደርም ይህን ሥም ያገኘበት ጊዜ መቼ እንደሆነ ማወቅ አስፈላጊ ሲሆን÷ በአሁኑ ጊዜ “ገና ተመርምሮ ያልታወቀ ምስጢር” መሆኑን መጽሐፉ ይጠቁማል፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጅ፣ የሻምበል ተስፋ እውቀት፣ ጥንቃቄና ብልህነት ጐልቶ በሚታይበት በዚህ የጦር ዕቅድ ሠነድ÷ “ወታደር” የሚለው ቃል፣ ከሁለት ሀገራዊ የአገላለጽ ዘልማድ የመጣ ሊሆን እንደሚችል በትሕትና ያስተነትናል፡፡ በመጀመሪያ፣ “ወታደር÷ ከወጥቶ አደር የተገኘ ቃል ይመስላል፡፡ ይህም የታዘዘውን ሥራ ከግቡ ሳያደርስና ሐሳቡን ከቁርጥ ነገር ላይ ሳይቆም የማይመለስ፣ እንደወጣ የሚቀር፤ ወጥቶ አደር” ማለት ሊሆን እንደሚችል ይገልፃል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ “ወታደር÷ ከዋቶ አደር የተገኘ ቃል ይመስላል፡፡ ደክሞና ተቸግሮ÷ በዱር በገደል÷ በበረሐ በሐሩር ÷ ከመከራ ጋር የሚተናነቅ የሚዋትት ማለት” ሊሆን እንደሚችል ያሥረዳል፡፡ መጽሐፉ፣ የቀድሞ የጦር አበጋዞችንና የነገሥታቱን ሀገር በቀል የውጊያ ሥልት ይመረምራል፡፡

የመጽሐፉ መነሻ ማዕቀፍም ይኸው የጦረኞቹ አያቶቻችን የጦርነት ገድልና ሥልት ነው፡፡ “የሀገራትን ታሪክ ብንመረምር ኢትዮጵያ ታላላቅ ተዋጊዎችና የጦር መሪዎች÷ አገር ቆርቋሪዎች÷ ወሰን ጠባቂዎች ነገሥታት ወልዳለች” በማለት በየዘመናቸው ታላላቅ ጦርነቶችን ያሸነፉ መሪዎችን ይዘክራል፤ በርግጥ በየዘመናቸው ታላላቅ ጦርነቶችን ሥለማሸነፋቸው አይገልፅም፡፡ በዚህ መፅሐፍ÷ በውጊያ ሥልታቸው፣ በጀግንነታቸው ሚዛን ደፍተው ለመዘከር የበቁት፣ አፄ ካሌብ፣ አፄ ላሊበላ፣ አፄ ሰርፀድንግል፣ አፄ ዳዊት፣ አድያም ሰገድ ኢያሡ፣ አፄ ሱስንዮስ፣ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስና አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ ቅድሚያ ተሠጥቷቸው የተሠውትን ነገሥታት ሥንመረምር፣ በየዘመናቸው ከወራሪ ሀገሮች ጋር ታላላቅ ጦርነቶች በማድረጋቸው የተመረጡ ይመሥላል፡፡ በተለይ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስና አፄ ምኒሊክ ከውጭ ወራሪዎች ጋር ህይወት እስከ መክፈል የሚያደርስ የጦርነት አውድማዎች ላይ መገኘታቸውን የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ይነግረናል፡፡ መጽሐፉ ከዛሬ 65 ዓመት በፊት ሢታተም፣ ምን ያህል የቀደሙ ሀሣቦችን ይዞ እንደተነሣ የምንገምተው፣ “በሀገራችን እንደተለመደው ሁሉ ወታደር ትምህርት አያስፈልገውም” የሚሉ ሀሣቦች በእውቀት እየሞገተ ወታደርም ትምህርት እንደሚያሥፈልገው ያፀናበትን አቋም ሥናነብ ነው፤ “ወታደር የተማረ÷ ያወቀ መሆን አለበት፡፡

የጦር መኮንን ደግሞ ከሞያው ሌላ የፖለቲካና የቁጠባ፤ ያሥተዳደርን ዘዴ ያወቀ መሆን አለበት” በማለት ኢትዮጵያችን በትምህርታቸና በብቃታቸው የሚያኮሩ፣ ከፍ ያሉ የጦር መኮንኖች ከታላላቅ ትምህርት ቤቶች እንደሚመጡላት ይመሰክራል - ከየትኞቹ ትምህርት ቤቶች እንደሆነ ግን በዝርዝር አይጠቅስም፡፡ ኢትዮጵያውያን በጽሑፍ ተከትቦ የተቀመጠ መረጃ ባይኖረንም፣ አባቶቻችን በዝና ከሚታወቀው በግማሽ ጨረቃ ቅርጽ የማጥቃት ስልት ውጭ የጦርነት ዕቅድና ብልሃት አያውቁም፣ አልነበራቸውም ማለት ታላቅ ድፍረት እንደሆነ ደራሲ ሻምበል ተስፋ ያሥረዳል፡፡፡ ቀጥሎም፣ “የንጉሠ ነገሥት ሠርፀድንግል ታሪክ ፀሐፊ አባ ባሕይርና የንጉሠ ነገሥት ሱስንዮስ ታሪክ ፀሐፊ አዛዥ ጢኖ በጻፏቸው ታሪኮች ውስጥ ንጉሡ ከእከሌ ጋር ተዋግቶ ድል አደረገው” እንጂ የሚለው የጦርነቱን እቅድና ብልሃት በፍፁም አያሥረዱም በማለት ይጠይቃሉ፡፡ መጽሐፉ፣ ከሀገር በቀሉ የውጊያ ሥልት በኋላ የውጮችን የጦር ስትራቴጂ በሂሥ ዐይን ይቃኛል፡፡ የነናፖሊዮንን፣ የነሒትለርን ወዘተ. የጦርነት ስትራቴጂዎች ሢያወሣ፣ በሀገርኛ የጦርነት ልምድና ባህላዊ እሳቤ እያዋዛ መሆኑ ይገርማል፤ ተጨባጭ ሀገርኛ ምሣሌዎች እየተጠቀመ ማብራራቱ ደግሞ የመጽሐፉን ብቻ ሣይሆን የትውልዱንም መሠረተ እውቀትና ብቃት የሚያሣይ ይመስለኛል፡፡

Read 2844 times