Saturday, 16 March 2013 13:50

በአፍሪካ ደረጃ ለመሻሻል ምድብ ድልድል መግባት ወሳኝ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ክለቦች በአፍሪካ ደረጃ በሻምፒዮንስ ሊግ እና በኮንፌደሬሽን ካፕ በተሳትፎ እና በውጤታማነት ከፍተኛ ደረጃ ከያዙት የአህጉሪቱ ክለቦች ተርታ ለመግባት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው መረጃዎች አመለከቱ፡፡ ዘንድሮ በሁለቱ አህጉራዊ ውድድሮች ተሳታፊ የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ የምድብ ድልድል ለመግባት ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ስኬት ለኢትዮጵያ ክለቦች የአፍሪካ ደረጃ መሻሻል አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ በ2013 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም በ2ኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታውን ከማሊው ክለብ ዲጆሊባ ጋር ያደርጋል፡፡ በ2013 የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚሳተፈው ደደቢት በበኩሉ በ2ኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ በመጓዝ ከሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሼንዲ ጋር ይጋጠማል፡፡

የኢትዮጵያ ክለቦች በአፍሪካ ትልልቅ የክለብ ውድድሮች በነበራቸው የተሳትፎ ታሪክ ከማጣርያ ምእራፍ አልዘለለም፡፡ የኢትዮጵያ ክለቦች በአፍሪካ ያላቸውን ደረጃ ለማሻሻልና ያለባቸውን የፋይናንስ ችግርን ለመቅረፍ በአህጉራዊ የክለብ ውድድሮች የምድብ ድልድል መግባት ያግዛቸዋል፡፡ ይህ ስኬት ለአምስት አመታት በሚዘልቅ ውጤት ሲያጠናክሩ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን አሰራር መሰረት ነጥብ ያሰጣል፡፡ በአህጉራዊ ክለብ ውድድሮች በ3 ምእራፎች የሚደረጉ ማጣርያዎችን ለመቀነስም ወሳኝ ነው፡፡ በካፍ የውድድር አካሄድ መሰረት በሻምፒዮንስ ሊግ ሻምፒዮን መሆን አምስት ነጥብ፤ ሁለተኛ ደረጃ ማግኘት አራት ነጥብ፤ ግማሽ ፍፃሜ መግባት 3 ነጥብ፤ በምድብ ድልድል 3ኛ ደረጃ ማግኘት 2 ነጥብ እንዲሁም 4ኛ ሆኖ መጨረስ 1 ነጥብ ያስገኛል፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፕ ደግሞ ሻምፒዮን መሆን አራት ነጥብ፤ ሁለተኛ ደረጃ ማግኘት ሶስት ነጥብ፤ ግማሽ ፍፃሜ መግባት 2 ነጥብ፤እንዲሁም በምድብ ድልድል 3ኛ እና 4ኛ ሆኖ መጨረስ 1 ነጥብ ያሰጣል፡፡ በሁለቱ ውድድሮች በአምስት የውድድር ዘመናት በሚገኝ ውጤት የሚገኘው ድምር ነጥብ በአፍሪካ እስከ 12ኛ ደረጃ ካስያዘ በየውድድሮቹ ከአንድ በላይ ክለቦችን ለማሳተፍ ያስችላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከካፍ የሽልማት ገንዘብ ክለቦቹም ሆነ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ድርሻቸውን ያስገኝላቸዋል፡፡ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ ለምድብ ድልድል መድረስ ለክለብ ብቻ ሳይሆን ለሚወክለው ፌደሬሽንም የገንዘብ ጥቅም አለው፡፡ አንድ ክለብ በኮንፌደሬሽን ካፕ ሻምፒዮን ለመሆን ሲበቃ 625ሺ ዶላር ሲያገኝ የወከለው ፌደሬሽን 35ሺ ዶላር ይታሰብለታል፡፡ በሁለተኛነት ለክለቡ 432ሺ ዶላር ለፌደሬሽኑ 30ሺ ዶላር፤ በምድብ ሁለተኛ ሆኖ መጨረስ ለክለቡ 239ሺ ዶላር ለፌደሬሽኑ 25ሺ ዶላር፤ በምድብ በ3ኛ ደረጃ መጨረስ ለክለቡ 239ሺ ዶላር ለፌዴሬሽኑ 20ሺ ዶላር እንዲሁም በአራተኛ ደረጃ መጨረስ ለክለቡ 150ሺ ዶላር ለፌደሬሽኑ 15ሺ ዶላር ያስገኛል፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከሽልማት ገንዘብ ለፌደሬሽኖች ድርሻ ባይኖርም ለየአገሩ ክለቦች ደረጃ ማደግና ለተጨዋቾቻቸው የፕሮፌሽናል እድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ሻምፒዮን በመሆን ዋንጫ የሚያነሳ ክለብ በሽልማት 1.5 ሚሊዮን ዶላር ከማግኘቱም በላይ በዓለም ክለቦች ዋንጫ አፍሪካን ወክሎ መሳተፍ እድል ይችላል፡፡ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ በሁለተኛነት ደ 1 ሚሊዮን ዶላር፤ ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስ 700ሺ ዶላር፤ በምድብ 3ኛ ደረጃን ይዞ መጨረስ 500ሺ ዶላር እንዲሁም በአራተኛ ደረጃ ማጠናቀቅ 400ሺ ዶላር ያስገኛል፡፡

Read 5019 times Last modified on Saturday, 16 March 2013 13:52