Print this page
Saturday, 16 March 2013 13:48

ለዓለማችን ሃብታም እግር ኳስ ተጨዋቾች ደረጃ ተሰጠ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በ2013 የእግር ኳስ ሃብታም ተጨዋቾች ደረጃ ላይ ለፓሪስ ሴንትዠርመን የሚጫወተው ዴቪድ ቤካም በ175 ሚሊዮን ፓውንድ የሃብት መጠን አንደኛ ሆነ፡፡ የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ በ115.5 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በ112 ሚሊዮን ፓውንድ ሃብታቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ብራዚላዊው ካካ በ66 ሚሊዮን ፓውንድ፤ ሮናልዲንሆ በ63 ሚሊዮን ፓውንድ፤ የራሽያው አንዚ ማቻካላ ተጨዋች የሆነው ሳሙኤል ኤቶ በ52 ሚሊዮን ፓውንድ፤የማን ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ በ50 ሚሊዮን ፓውንድ፤ የፓሪስ ሴንትዠርመኑ ኢብራሞቪች በ47 ሚሊዮን ፓውንድ፤ ሪቫልዶ በ45.5 ሚሊዮን ፓውንድ፤ የማን ዩናይትዱ ሪዮ ፈርዲናንድ በ42 ሚሊዮን ፓውንድ የሃብት መጠናቸው ከአራት እሰከ 10 ያለውን ደረጃ ወስደዋል፡፡ የእግር ኳስ ሃብታም ተጨዋቾች እስከ 50ኛ ያላቸውን ደረጃን በመስራት ከሳምንት በፊት ይፋ ያደረገው ታዋቂው የእግር ኳስ ዘጋቢ ድረገፅ ጎል ነው፡፡

ጎል የዓለም የእግር ኳስ ሃብታም ተጨዋቾች ለመጀመርያ ጊዜ ለማዘጋጀት የቻለው ተጨዋቾች ያላቸውን በይፋ የሚታወቅ ሃብትና ንብረት፤ በተለያዩ ኩባንያዎች በሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ፤ በደሞዝ ክፍያችው እና ቦነሳቸው እንዲሁም በማስታወቂያ እና በተለያዩ የንግድ ስራዎች የሚያገኟቸውን ገቢዎችን በማስላት ነው፡፡ በጎል ዶት ኮም የእግር ኳስ ሃብታም ተጨዋቾች ተብለው እስከ 50ኛ ደረጃ የተሰጣቸው በአጠቃላይ የሃብታቸው ድምር 1.7 ቢሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ በደረጃው ላይ ከሚገኙ ተጨዋቾች 22 በመቶ ያህሉ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ሲሆን የተቀሩት ከ18 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ ናቸው፡፡ ስምንት ፈረንሳዊያን፤ 6 ጣሊያናዊያን፤ 5 ስፔናዊያንና 5 ብራዚላውያን ገብተዋል፡፡ በደረጃው ሰንጠረዥ አራት ትውልደ አፍሪካዊ ተጨዋቾች አሉ፡፡

ባላቸው ሃብት እስከ 50ኛ ደረጃ ካገኙት ተጨዋቾች መካከል 37 ያህሉ እድሚያቸው ከ30 አመት በላይ ነው፡፡ ከ50ዎቹ ሃብታም የእግር ኳስ ተጨዋቾች የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከ25 በላይ ተጨዋቾች አስመዝግቦ 50 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ የስፔኑ ላሊጋ በ46 በመቶ፤ የጣሊያኑ ሴሪኤ በ42 በመቶ፤ የፈረንሳዩ ሊግ 1 በ24 በመቶ እንዲሁም የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ በ12 በመቶ ድርሻ ተወክለዋል፡፡ በደረጃው የገቡት ተጨዋቾች ከ10 በላይ ትልልቅ ዋንጫዎችን በአገር ውስጥ የሊግ ውድድርና በአህጉር ደረጃ ያገኙ ሲሆን 80 በመቶ ያህሉ በአማካይ እና አጥቂ መስመር የሚሰለፉ ናቸው፡፡ ከ50ዎቹ ሃብታም የእግር ኳስ ተጨዋቺች 26 በመቶው ለሪያል ማድሪድ፤22 በመቶ ለቼልሲ፤ 18 በመቶ ለኤሲ ሚላን፤ 16 በመቶ ለባርሴሎና እና ለማን ዩናይትድ እንዲሁም 14 በመቶ ያህሉ ለጁቬንትስ ክለብ ተጫውተዋል፡፡

Read 5897 times
Administrator

Latest from Administrator