Saturday, 16 March 2013 12:41

ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር

Written by  በተስፋ በላይነህ tes_bel@yahoo.com
Rate this item
(15 votes)

‹‹ታዲያ በዚህ አገር የፍቅር ማደሪያው የትኛው ልብ ነው?›› በተስፋ በላይነህ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. የጥበብን ሃይል የምናውቀው የተደበቀን ምስጢር ወደ ገሃድ ማውጣቱ፤ የተሰወረን አዚም፤ የጠፋን መንገድ በማመላከት መስመር ማስያዝ መቻሉ፤ በጦር በሰይፍ እንኳ የቀረበን ፍርድ ለእውነትና ለእውቀት ወግኖ መገኘቱ ከዛም ለትውልድ ቅርስ ሆኖ መዘከሩ ነው፡፡ ምንም እንኳ ጥቂት ሃጥአን ብዙዎችን የማጥፋት ሃይል ቢኖራቸውም፤ ጥቂት ወይንም አንድ እውነት አለምን እንደሚገዛም አይተናል፡፡

በዚህ እውነት ስር የሚወጡም በርካታ የጥበብ ስራዎች ብዙዎችን የመለወጥ ሃይል ይኖራቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ነገሮች ጠፍተውብን፤ መድረሻው ርቆብን፤ ማረፊያው በጠጠር ተደግፎ በአሜኬላ ታጥሮ፤ ፍጻሜው ታክቶን የምንንከራተት ስንቶቻችን ነን? ‹‹አፋልጉን›› የሚል ጩኸት የምናሰማ ብዙዎቻችን መሆናችንን ቤት ይቁጠረው፡፡ በዚህ የጩኸት ዓለም ውስጥ እውነትንና የጠራ እውቀትን ማግኘት ከባድ በሆነበት ዘመን፤ እውነትና እውቀት የለችም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ከሰውነት ተርታ የሚያስወጣን በመሆኑ መቼም ቢሆን ለእውነት መታገል ይኖርብናል፡፡ ‹‹አፋልጉን!›› እያሉ የመጮኽ ትግል የግድ ነው:: አሜሪካኖች ለየት ያለ የሙዚቃ አቀንቃኝ ብቅ ካለች /ካለ/ በአለማችን አስገራሚዋ/ው የሙዚቃ አቀንቃኝ ብለው መጮኽ ያዘወትራሉ፡፡

ሌላኛውን ዓለም ሳያዩ ፣ ሳይወዳደሩ በአለም አንደኛ! ማለት ይወዳሉ:: ይህም ትልቁ የንግድ ሴራቸው ነው:: እኔም በእነርሱ የንግድ አለም ሥርዓት አይደል ያደግሁት:: አዎ! “በአለም ረዥሙ ግጥም” በሚለው ጩኸት ርዕስ ስር የኤፍሬም ስዩምን ‹‹ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር›› የሚለውን የግጥም መድበል በአለም አንደኛ ረዥሙ ግጥም ለማለት ተገደድኩ፡፡ እውነት ነው በአለም ረዥሙ የግጥም ስንኝ ማነው ቢባል ማንም ይወራረደኝ “ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር” የሚለው ግጥም ነው፡፡ ኤፍሬም ስዩም “ሶሊያና”ን የግጥም ሲዲ በ 1998 ሲያቀርብልን ለግጥም የስነ ጥበብ ዘርፍ ከፍተኛ ትርጉምና ዋጋ ያሰጠበት ዓመት ነበር፡፡ ተፈጥሮ በለገሰችው ስርቅርቅ ጉሮሮ፤ ቅላፄ፣ ዐርምሞና ምሳጤ መሰረት የተለያዩ ሃሳቦችን በያዙ ግጥሞች ወደ ትልቅ ባህር በሚወስዱ ዜማዎች ታጅቦ አስከመኮመን፡፡ ግጥምን ልክ እንደ ሙዚቃ ስራ በቤተሰብ መሃል እያዳመጥን የምንወያይበትን መድረክ ከፈተልን፡፡ ግጥምን በድምፅ በማሰማት እነ ሎሬት ባለ ቅኔ ፀጋዬ ገ/ መድህን እና አበባው መላኩም ሞክረውልናል፣ ታገል ሰይፉም በዚሁ ሊካተት ይችላል፡፡

ሌሎችም… ሙዚ ቃል ( የብርሃን ክንፎች) ለኤፍሬም ቀጣይ ስራው ነበር፡፡ በ2004 ዓ.ም የለቀቀው ይኸው ስራ አሁንም ጥበብ የጋለ ብረቷን ለኩሳው በ 2005 ዓ.ም ለየት ባለ አቀራረብ፤ በሚስብ ይዞታ በሰማያዊ መደብ ሁለት ተበአትና እንስት የአዕዋፍ ፍጡራን በፍቅር ማዕድ ተቆላልፈው ተስለው፤ በነጭ ቀለም ዳርቻ ስር ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር የሚለውን መድበል እንኳችሁ አለን - ኤፍሬም:: የሽፉኑን ሥዕል አልፈን አንድ ገጽ ስንገልጥ፤ በጥቁርና ነጭ ቀለም የተጣለ የገጣሚውን ከደረት በላይ ምስል እናገኛለን፡፡ አንድ ፈላጊ የሚመስል ሰው አትኩሮ ይመለከትሃል፡፡፡ በመጠኑም ቢኾን እንደ ግጥም ለማንበብ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ይዘህ ልትቆይ ትችላለህ፡፡ ትገልጣለህ - “ተበረከተ” ለሶልያና የሚል ጽሑፍ ታገኛለህ፡፡

እዚህ ላይ ገጣሚው በሶልያና ፍቅር እንደተነካ በግልጽ ማየት ችያለሁ:: ፍቅር ደግ ነገር ነው! ከዛም ስትገልጥ ማውጫው ላይ በገጾች አምድ ስር ሀ፣ሐ፣ሠ፣ ኀ እና አ በሚሉ ፊደላት ለየት ያሉ ሃሳቦችን እናያለን፡፡ እስከዛሬ በብዛት የለመድነው በሮማን ቁጥር ሊሆን ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት የገጽ ቁጥሮችን በግዕዝ ቁጥር ማየት አልተለመደም፡፡ የይስማዕክ ወርቁ “የቀንድ አውጣ ኑሮ” የግጥም መድበል ላይ ገጾች በግዕዝ ቁጥር መፃፋቸውን አድንቄ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በፊደል ማየቴ ደስ አለኝ፡፡ ነገር ግን ሌሎች ገጾች በህንድ/አረብኛ ቁጥር (በ1 2 3) ተጽፈዋል፡፡ በግዕዝ ቁጥር ቢጻፉ ኖሮ የመድበሉን ውበት በጣም ሊያሳምሩት እንደሚችሉ አሰብኩ፡፡ ትገልጣለህ - የግጥሞቹ ማውጫ ያልቅና ባዶ ገጽ ታያለህ፡፡ የስነ-ጽሁፍ አድናቂ ፤ ፍልስፍናም ነካ የሚያደርግህ ከሆነ ባዶ ገፁን ልታነበው ትችላለህ፡፡ ባዶ መሆኑን ሳትገነዘብም ታልፍ ይሆናል፡፡ የምስጋናው ክፍል ይከተላል፡፡

ቤተሰቦችንም ለማመስገን ያቀረበውን ምክንያት በጣም ወድጀዋለሁ፡፡ ‹‹የእናንተን ለእናንተ መናገር ራሴን በራሴ ከማክበር እኩል ስለሚሆን በልብ ከልብ ለልብ›› ይላል፡፡ ለገፀ ሀ ደግሞ ከዛው ይህችን መድበል ሕይወት የዘራበትን ሰው ዘሚካኤልን ያመስግነዋል፡፡ እኔም በበኩሌ እጅጉን አመስግኜዋለሁ፡፡ እንዲህ ሰው በጠፋበት ዘመን ሰው ሲገኝ ያስደንቃል፡፡ “ዘ” ብድራቱን የላይኛው ይከፍልህ፡፡ ከዛም ስንገልጥ በገጽ ሠ ላይ የምናገኘውን የዚህን መጽሐፍ ትልቁን ክፍል ነው - “ጦማረ አሚን” ይላል፡፡ ‹‹ሁላችንም የግላችን የሆነ sound track አለን፤ ያ sound track ያለፈ ጊዜያችን የአሁን ማንነታችን ነው፡፡” እያለ ሕይወትን በሙዚቃ እያዋዛ እያመሳሰለ የህይወታችን መሰረት የሆኑትን አሁን ቅድም ዛሬ ትላንት አምና ካቻምናን ያስቃኘናል::

ያለፈው ሕይወታችን በአሁንና በነገ ማንነታችን ላይ ያለውን ተጽዕኖ ምላሽም ያስቃኘናል:: አራተኛው አንቀጽ ላይም “…ትናንሽ የሸክላ ጭረቶች የሙዚቃውን ጣዕም ይረብሹታል… ከሙዚቃ ሐዘንተኛ መንፈስ ይልቅ ባላዋቂ ጥፍሮች የተቧጨሩ የሸክላው ጀርባዎች…ዜማውን ያበላሹታል፡፡ አንድ ወዳጄ ውብ እኔነቱን ብዙ ምርጥ ዜማዎችን በማንነቱ ላይ እንደተሸከመ ራሱን በራሱ ለመስበር ሲሞክር፤ ሞክሮም ተሰባብሮ ስብርባሪው ተለቅሞና ታሸጎ ወደ ዘላለም ፀጥታ ሲጓዝ ተመልክቼአለሁ፡፡ በዚህም ከታላላቆች መሰበር የታናናሾች ጭረት እንዲጎዳ አስተውያለሁ፡፡” የምትለው አንቀጽ ውበቷ ጎልቶ ታይቶኛል፡፡ ቀሪውን ጦማረ አሚን /እውነተኛ-የታመነ ደብዳቤ/ ሃሳብና ይዞታ እስከ ገጽ ተ ድረስ ያንብቡ፡፡ ብዙ ይማራሉ፤ ብዙ ያስባሉ፤ ብዙ ይጠይቃሉ፤ ይመራመራሉ፡፡

ምናልባት ፀጥታ የሌለበት ስፍራ ወይንም ህሊናዎን ሰብሰብ አድርገው ካላነበቡት ምን ለማለት እንደፈተለገ ሊያገኙት ስለማይችሉ በትህትናና በትዕግስት እንዲያነቡት እመክራለሁ፡፡ ይቀጥላል - በ ኀ ገጽ ደግሞ ‹‹ዋዜማ›› በሚል ርዕስ ስር “ከደመና ልትቀዳ ተራራውን ወጣች የሚል የመዝገቡ ተሰማን አድባር ስዕል አስታወስኩት” በማለት ህልሙን ይነግረናል …ህልም…ከዛም የዮፍታሄን ስለት ጠቅሶልን ህልሙን ለመፍታት ሊተረጉምልን ይተርክልናል፡፡ ‹‹ቅደመ ታሪክ›› የሚል ግጥም ይጀምራል፡፡ ያንብቡት! በግርጌው ላይ በ29 -02 2004 ተጻፈ ይላል፡፡ ‹‹ታዲያ በዚህ አገር የፍቅር ማደሪያው የትኛው ልብ ነው?›› ብሎ በመጠየቅ በገንዘብና በቪላ ተደልላ ለሄደችበት ሴት የተፃፈ የሚመስል ረዥሙ የግጥም ወንዝ ይፈሳል፡፡

ገጽ 1 ‹‹ዕለተ ቅዳሜ ፒያሳና ቦሌ›› በቃ ከዚህ ጀምሮ እስከ ገጽ 100 ድረስ አንድ የግጥም ሃሳብ ያነባሉ:: ለዚህ ነው በአለም ረዥሙ ግጥም በማለት በአለም ድንቃድንቅ መዝገቦች ስፍራ የሸለምኩት፡፡ ከአንድ ታሪክ ከአንድ ቅዳሜ ተነስቶ አዲስ አበባን፤ የአዲስ አበባን ሰዎች- ወጣቶች ሴቶች፤ ልጆች፤ ኢትዮጵያን የምናይባቸው ግጥሞች ቀርበዋል:: በተለይ በመጀመሪያው ገጽ የቀረቡት ---- የቤት ልጅ (ፀጉሯን የምትሰራውን እፎይ ብላ ተቀምጣ ያረፈቸውን የፒያሳ ልጅ ከቦሌ ቀለማት ቆነጃጅት ጋር ያነፃፀረበትን ወገን ስቄበትም ተደንቄበትም አልፌዋለሁ፡፡) በአንዳንዱ ገጽ የተለያዩ ግጥሞች የሚመስሉ ስንኞች በተለያየ ርዕስ ስር ቢቀርቡም እርስ በርሳቸው የተያያዙና የተደጋገፉ፤ አንዱን ካላነበብን የሌላኛው የማይገባን ግጥሞች ናቸው፡፡

ምናልባት እንደ ሌሎች የግጥም መድበሎች ከመሃል አንድ፤ ከዳር አንድ እያደረግን የምናነበው ከሆነ አይገባንም፡፡ በአብዛኛው ሁሉም ማለት ይቻላል በ 21 -04-2004 እስከ 29 -04 2004 ባሉት ቀናት ውስጥ የተጻፉ መሆናቸውን በግርጌ ማጣቀሻቸው ማየት ይቻላል፡፡ ኤፍሬም ስዩም በዚህ የግጥም ስራው አንዲት የወደዳት ያፈቀራት፤ አብራው ትኖር የነበረችን ሴት እያስተዋወቀ ለሌላ ባል የተሰጠችውን ፍቅረኛውን የበለጠ ሃብት ፈልጋ ወደ ሌላ ወንድ ጋ ሄዳ የምታሳልፈውን ሕይወት ከጓደኛዋ፤ ከጎረቤት፤ ከሰራተኛ እና እራሱም ከሚያየው እየጠቀሰ ይተርክልናል፡፡ ምናልባት ትግስተኛ አንባቢ ካልሆኑ በዚህ ዘመን ደግሞ ‹‹ምን ያለ ፍቅር ነው›› ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ የዋዛ እንዳይመስላችሁ፡፡

በገጽ 87 ላይ በምናገኛት ‹‹ደባል ታቦት›› የግጥም ስንኝ ብዙ ልንማር፤ ብዙ ልናውቅ፤ ብዙ ልንለወጥ የምንችልበትን ሃሳብ በአዲስ ቀን 01-03-2003 ወደ ኋላ በመመለስ ያቀርብልናል፡፡ አዲስ ቀን ነው፡፡ ምናልባት ግን 2003 ዓ.ም በስህተት የተገለጸ ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ፡፡ ምክንያቱም በገጽ 87 የምናየው ‹‹መቼም›› የተሰኘችው ግጥም የተጻፈችው በ02-03-2004 በመሆኑ፡፡ በገጽ 91 “ስንብት” በሚል ያቀረበው ግጥም የዚህ ሁሉ ታሪክ መገባደጃ በመሆን “ቻዋ !!” ይላታል፡፡ ‹‹ሁሉም ከንቱ ነበር›› የሚለው ቀጣይ ግጥም በገጽ 92 ይቀርብልናል፡፡ አራት ጊዜ አንብቤዋለሁ፡፡ ወድጄዋለሁ! የመጣሁበትን ጉዞ ሁሉ አሳረፈኝ፣ አስተማረኝ፣ መከረኝ፣ እንድጠይቅ አደረገኝ፡፡ ተባረክ ኤፍሬም! ለዚህ ዘመን፣ ለዚህች አገር፣ ለዚህ ትውልድ፣ ለሽማግሌ ለነገስታት የተጻፈ ግጥም፡፡ ህልማችን መተኛት ህልማችን መጠጣት ተሰብስቦ ማውራት ማውራት ማውራት ማውራት-- --- አዎን በዚህ ሀገር ሁሉም ከንቱ ነበር፡፡

ሽማግሌው ማውራት ወጣቶቹ ማውራት ነገስታቱ ማውራት ማውራት ብቻ ጥበብ ሕይወት የሆነበት እርሷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ያንብቡት! ከዚያ በገጽ 97 ላይ “ሐያሲ” በሚል የግጥም ስንኝ የግጥሙ ፍሰት ይቋጫል፡፡ በ 30 - 02- 2004፡፡ በገጽ 101 “መውጫ ወዳሻችሁ” በሚል ርዕስ የተጻፈው ደብዳቤ ከምጠብቀው በላይ በእያንዳንዱ መስመር እፈልጋት የነበረችውን የመድበሏን ዋና ገጸ-ባሕርይ፤ ‹‹ምንም›› አጥብቄ እንድፈልግና ያቀረበበትን የአፋልጉኝ እርዳታ በምልክት ያስቀመጠበትን ‹‹ዘይቤ›› ከሚገባው በላይ ለመረዳት፤ ልጁንም በማድነቅ ምነው ፅሑፉ ባላለቀ አስብሎኛል፡፡ እነዚህ አራት ገጾች የጸሐፊውን ልዩ ችሎታ ያሳዩ ሃሳቦች የተሰነቁበት ልዩ ክፍል ነው፡፡

በዚህ ዘመን የምንፈልገው ጸሐፊ ከራሱና ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ እኛንም የሚያጣላን ውዥንብር ፍልስፍና ሳይኾን በብዙ መንገዶች በስነ-ጥበባዊ ወዝ እያዋዛ ራሳችንን፣ አገራችንን ፈጣሪያችንን ፈልገን ለለውጥ የምንነሳበትን ሀሳብ የሚጠቁመን ነው፡፡ ጥበብ ከሰይፍ ከጦር የበለጠ ሀይል አላት ያልኩበት ምክንያትም ይህ ነው፡፡ ጸሐፊዎች- ገጣሚዎች፤የስነ-ጽሑፍ ሰዎች ከዚህች ስራ ብዙ ሊማሩ ይገባል፡፡ አንባቢያን ከዚህ መጽሐፍ ብዙ ነገር ትፈልጋላችሁ፡፡ እናትን ፈልጎ ለማግኘት ቢያንስ ወደ እውነት ፍለጋ መንገድ የምትመራ ድንቅ መጽሐፍ፡፡ የራስን ፍለጋ ጨርሰህ እረፍትህን ሽተህ፤ ሌሎች ራሳቸውን እንዲፈልጉና እንዲያርፉ ለማድረግ መሞከርህ ያስመሰግንሃል፡፡ እውነትን እንድንይዝ ፤ እውቀትን ጥበብን እናገኝ ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን፡፡ እናታችን ጠፍታለች፤ ጭራሽ ደግሞ መገኛዋ ጠፍቶ ላትገኝ ስትዋትት ከማየት ፍለጋው ይጠንከር፡፡ በማንም እጅ ስር ተይዛ ሲያሻቸው ሊጨብጧት፤ ሲያሻቸው ሊገነጣጥሏት የሚሹ ሀይሎች አሉና ሁላችንም እንታደጋት፡፡ እናታችን ጠፍታለች፡፡ አፋልጉን፣ ከጠፋች ልክ 38 አመቷ፡፡ www.tesfabelaynehh.blogspot.com ቸሩ ቸር ያቆየን!

Read 9133 times