Saturday, 16 March 2013 11:15

ስሜት፣ ሙዚቃና ድምፅ በስነ- ግጥም!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)

“ገጣሚያን ለሰው ልጆች ነፍስ አዲስ መስኮት ከፍተዋል” ደረጀ በላይነህ ስለ ኪነ ጥበብ አጠቃላይ መልክ ስናወራና ስንተርክ ብፌው ሙሉ ዥንጉርጉር መሆኑ የግድ ነው፡፡ ነጣጥለን ሳይሆን ህብረ -ቀለማዊነቱን ጠብቀን ነው፡፡ በልባችን እያቀማጠልን፣ዜማ አውጥተን ስናቀነቅነው እንደ ተለያየ ቅርንጫፍ ግን በአንድ ግንድ እንዳለ ውበት ነው፡፡ ውበቱም በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት ነውና!! ታዲያ እነዚህ ዥንጉርጉሮች ከሌሉ የሰው ልጅ ህይወት ፈጽሞ ሙሉ ሊሆን አይችልም፡፡ እያንዳንዳቸው የሚሞሉት የሰው ልጅ ክፍተት አለ፡፡ ሰው መንፈስ፣ ስሜት፣ዕዉቀትና ፍቃድ ስላለውም ከሌሎች ፍጡራን የተለየ ስነ ልቡናዊ መዋቅርና ፍላጎት አለው፡፡ በኔ እምነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኪነ-ጥበብ ውጭ መኖር አይችልም፡፡ እነዚህ የጥበብ ቤተሰቦች፣ ማለትም ስዕል፣ቅርጽ፣ቅብና ሙዚቃ ወዘተ ናቸው፡፡

የእነዚህ ባለቤት ለመሆን ደግሞ ተሰጥዖ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ በዋናነት ላወራበት የፈለግሁት የጥበብ ቤተሰብ ግጥም ነው፡፡ በስሜት ነበልባሉ ድምቀትና በጉዞው ችኩልነት ግጥምን ነጠል አድርገን ስናይ “ግጥም እንደ ጽጌረዳ፣ሙዚቃና ፍቅር ጥልቅ ደስታ ነው --ይላሉ ሚለርና ስሎቴ፡፡ ይህ ማለት ግን ደስታ ብቻ ነው ማለት አይደለም- እንደ ለውረንስ ፔረኒ አተያይ፡፡ ሁሉም ነው- ግን ሁሉን ወደ ውበት መቀየር ይችላል፡፡…ግጥም ራሱ ግጥም ለመሆን ስሜት ወደ ሙዚቃና የሚታይ ወለል ያለ ውብ ምስል መቀየር አለበት! ወደ ስሜት ስንመጣ ስሜት በግጥም ውስጥ ጥበባዊ ያልሆነ ቅርጽ ሲይዝ ፣ውጤቱ ግጥም ሳይሆን እንደሚያስተጋባ የገደል ማሚቱ አይነት ነገር ነው፡፡ ስሜት ፈጽሞ ግጥም አይደለም፤ግን የግጥምን ብብት የሚኮረኩር ጣት ሊሆን ይችላል፡፡

ስሜታዊ ገለጻ ግጥም ሊሆን የሚችለው ውብ ቅርጽ ሲኖረው ብቻ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በሊሪክ ግጥሞች ውስጥ፡፡ ጥበብ የገጣሚው የስሜት መግለጫ እንጂ የተጨባጩ ዓለም ወካይ አይደለም፡፡ ማለትም ለገጣሚው በአፍቃሪ ፈንታ ሲሆን ፣ባህር አብሮት ፈገግ ይላል፤ንፋሱ የውድ ፍቅረኛውን ስም እያፏጨ ይዘምርለታል፤ክዋክብት በፍቅር አይን ይገረምሙታል፡፡ በሌላ ስሜትም ሲሆን ተገላቢጦሹ ይሆንበታል፡፡ አሪፍ ገጣሚ የሚባለውም የሰውን ልጆች ስሜትና የልብ ትርታ አዳምጦ ስሜታቸው በጥልቀት የሚሰማው፣ልቡን እንደ ጨርቅ የሚያውለበልበው፣እርሱም በዚያው መነካት የሌሎችን ልብ እንደ ክራር ክሮች መንዘር የሚችል ነው፡፡ ልቅሶና ሳቁ የሰው ልጆች ሁሉ የሆነ ገጣሚ ዘመን ያልፋል፤ሞትን ይዘልላል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የሼክስፒር ልብ ከመላው የሰው ልጆች ልብ የተሰራ፣አንደበቱ የመላው ሰው ልጆች ንግግር የተማረ፣ሲቀመጥና ፈገግ ሲል ግን እንደ … ተቀምጦ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የስሜት ማስተጋባት የሚቀሰቅሰው ስሜትን አይደለም፤ የስሜትን ጥላ፣ራሮትን እንጂ!! ባብዛኛው ጥቅም-የለሽ -የውሃ ሽታ አይነት፡፡ በምድር ላይ አይረቤ ስም ያለው ሰው ማለት ቃሎቹን ከንፈሩ ላይ አንጠልጥሎ ወደ መቃብር የወረደ ሰው ነው፤ ይላሉ፡፡

ላምቦርን እንደሚሉት የሰው ልጆች ሁሉ ገጣሚ ነን፤ሁላችንም የሚነካ ማንነት አለን(feeling) ስሜት፣እንዲሁም ስሜታችንን ከሌሎች ጋር የምናጋባበት መንገድ አለን፤ይሁንና ገጣሚያን ግን ከኛ የላቀና የጠለቀ የስሜት ምጥቀትና ልቀት አላቸው፤ ስሜታቸውንም ከኛ በላቀ ሁኔታ ይገልጣሉ፣ ሌሎች ላይ ስሜታቸውን ያጋባሉ፡፡ ሁላችንም ትንሽ አይኑ እንደሚያስቸግረው ሰው በጨፍጋጋው ብርሃን፣ውበትን በኮረብታ ወይም በደመና እናያለን፤ገጣሚው ግን ሊያስጮኸው የሚያስችል በፈንጠዝያ ያሸበረቀ ልቅሶ ያዘለ ደማቅ ብሩህ አድርጎ፣ እኛ ደግመን እንድናየው የሚያደርግ ሃይል ነገር ይታየዋል፡፡ ስናደምጥም እኛ ትንሽ ትንሽ እንደሚሰማ ሰው፣ ሙዚቃውም እንደ ሚፈስስ ጅረት የገደል ማሚቶ ነው፤እርሱ ግን ሲያዳምጥ ጥርት ያለች ሜሎዲዋን የምትዳሰስ ያህል አቅርቦ ነው፡፡ እኛ.በጥሬው በክዋክብት ግርማ እንደነቃለን፤እርሱ ግን እንደ ካህን ጸሎት ከፍ ባለ ድምጽ እየጸለየ፣ በክዋክብቱ ፊት በግምባሩ ተደፍቶ ሁላችን እርሱን አጅበን ወደ ሰማዩ ጸጋ ዙፋን በመሄድ፣ የተናገራቸውን ብርቅ ቃላት ከርሱ ጋር እያስተጋባን እንድንል ያደርገናል፡፡

የሚሉት ጸሃፊ ግሪኒንግ ላምበርግ ናቸው፡፡ ገጣሚውና ሃያሲው ዊልያም በልተር የትስ ደግሞ “ገጣሚያን ለሰው ልጆች ነፍስ አዲስ መስኮት ከፍተዋል፡፡” ይላል፡፡ በላውረንስ ፔሬኒ አባባል ገጣሚ ሁሉ ገጣሚ አይደለም፤ የግጥም መጻህፍቱም ቢሆን በዓመት ውስጥ ከሚታተሙት ውስጥ ጥቂቱ፣ እጅግ በጣም ጥቂቱ ብቻ ናቸው ግጥም ተብለው ሊጠሩየሚችሉት፡፡…ታዲያ የሁለቱን ሰዎች ሃሳብ ስናቀናጀው ዊልያም በልተር የትስ የጠቀሳቸውና ክብር የሚገባቸው ገጣሚያን እጅግ እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ ግጥም የምጥና የጥልቅ ሃሳብ ስራ እንጂ የለብ-ለብ ሩጫ አይደለም፡፡ለዚያውም መወለድን ይጠይቃል፡፡ ግጥም ስዕል፣ግጥም ሙዚቃም ነው፤በርግጥም ግጥም ሙዚቃው በጆሮ ሲንቆረቆር የአእምሮ ዕውቀት አይተረጉመውም፤ስለዚህ የሚናገረው በተምሳሌት ሳይሆን በስዕል ነው፤ራሱ የሚነግረንን ነገር እንጂ የነገሩን ትርጉም አያብራራም፡፡ ሲያንስ፣በጆሮ ይለካል፤ግጥምን ልዩ የሚያደርገው አንዱ ዜማ ነው፡፡ እንደ ሎውረንስ ፔሬኔ አባባል፤ ዜማ ከልባችን አመታት ፣ከደማችን ዝውውር፣ከአተነፋፈሳችን ጋር ይመሳሰላል፤ምክንያቱም በተወሰነ ጊዜ መጠን ሳይቋረጡ የሚደጋገሙ ስለሆኑ ነው፡፡ ለማንኛውም ሙዚቃዊ ዜማ መሰረቱ ድግግሞሽ ነው፡፡

ስለዚህ የሙዚቃው ፍሰት መሪ ጆሮ ነው፡፡ ጆሮ አንቆርቁሮ ልብ እንዲያሸበሽብ ያደርገዋል፡፡ በመሰረቱ ግጥም አብሯቸው ከተወለደው ወንድሞቹ አንዱ ሙዚቃ ነው፡፡ በተለይ የእብራዊያኑ ግጥሞች መነሻ ሲታይ ከጨረቃ ፌስቲቫል ጋር የተያያዘ ጉድኝት አላቸው - በቅድመ ታሪክ ዘመን፤ማለትም ከሙሴ ህግ፣ከአብርሃም የኡር ምድር ጥሪ በፊት፡፡ ከብት አርቢዎች ስለነበሩ እጅግ በሚያቃጥለው የሲና ንዳድ ውስጥ ቀን ቀን መሄድ ስለማይችሉ ጨረቃ መጠበቅ ግድ ነበረና ፤ ጨረቃ ሲያዩ የሚያደርጉት ፌስቲቫል ዜማን ከግጥም ጋር አጣምሮ መውለዱ የአለማችን ግጥም አፈጣጠር ከፊል መልክ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ያነበብኩት አንድ መጽሃፍ እንደነገረኝ፣ዜማ በጆሮ ሲንቆረቆር የራሱ ቀለም አለው፡፡ ይህንን እውነት ስጠራጠር ደግሞ የሃገራችን የቀለም ተመራማሪ ጌታሁን ሄራሞ እንዲህ ብሎኛል፤ “ዜማና ድምጽ ምንጫቸው አንድ ነው፤የድምጽና የቀለም ምንጭ የሚለየው ቀለም የብርሃን ሞገድ፣ድምጽ ደግሞ የድምጽ ሞገድ መሆኑ ነው፡፡”ብሏል፡፡ እያንዳንዱ ድምጽ ደግሞ ቀለም አለው፡፡ ለምሳሌ ቢጫና ነጭ ብርቱካንማ ቀለሞች ከፍተኛ ምት አላቸው፡፡ እንዲያውም በነአፍላጦን ዘመን ለእያንዳንዱ ቀለም ኖታ ይሰጠው ነበር፡፡ ይሁንና ወደ ሃገራችን ግጥሞች ስንመጣ የላቀ ዜማ ያላቸው፣ጠቢባኑ እንደሚሉት እንደ ልብ ትርታችን ድም ድም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ግራና ቀኝ እንደ ሰካራም እግሮች አፈንግጠው የሚሄዱ ሞልተዋል፡፡

ዜማ ላይ ገብረክርስቶስ ደስታ፣በድሉ ዋቅጅራ፣ታገል ሰይፉ…የመሳሰሉት የተሻለ አቅምና ዝንባሌ አላቸው ማለት ይቻላል ፤ይህ ሲባል ግን በላቁ ቃላት ሰማይ ባይቧጥጡ፣በዜማ ዳንስ ልባችን ላይ ባያፏጩም ተዓምረኛ ሃሳብ ያላቸው ግጥሞች ቀሽም ተብለው ይፈረጃሉ ማለታችን አይደለም፡፡ እነዚህ ሳይኖሯቸው ሰማይ የሚያስቧጥጥ ሃሳብ ይዘው የሚመጡ ገጣሚያን አሉ፡፡ ለምሳሌ ገጣሚ ዳዊት ጸጋዬ በዜማና ምቱ ብዙ ሳቢ አይደለም፤ግን ደግሞ ፍልስፍናዊ ሃሳቦችን የሚያይባቸው መንገዶች ያስደምማሉ፡፡ ግጥም ደግሞ አንድ ውበቱና ግሩምነቱ በተለየ አይን እያሳየ “ጉድ” ማሰኘቱ ነው፡፡

“ሰላም vs ጸጥታ” የሚለውን ግጥሙን እነሆ- ጩኸትና ረብሻ ስላልታየ፣ ቤትና ንብረት ስላልጋየ፣ ዓመጻና ሁካታ ዋይታና ኡኡታ ስለሌለ፣ “ሰላም ነው”ተባለ፡፡ ኧረ ተው! ሕዝቦች በፍርሃት ጸጥ ስላሉ፣ ጸጥታ ሰላም ነው አትበሉ፡፡ ምናልባት ይህ የዳዊት ግጥም ከሌሎቹ በዜማው ሻል ያለ ነው ተብሎ ሊገመት ይችላል፤ግና በአብዛኛው ግጥሞቹ በሃሳብ ልቀት እንጂ በዜማ ተአምራት አንገት የሚያስነቀንቁ አይደሉም፤ይሁንና ጥቂት የማይባሉ የግጥም ሃያስያንና ተመራማሪዎች በዚህ ውበት ይስማማሉ፡፡ የአፍንጫ ጎራዳ ደመ-ግቡ እንደምታምር ሁሉ የሃሳብ ልቀትም ውበት ነው ይላሉ፡፡ የሚቃወሙም ግን አሉ፡፡ ሃሳብማ ብቻ ግጥም አይደለም፤ለዚህ ለዚህማ ምርጥ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሞልተው የለ! የሚሉ!!... እኛ ግን ከብዙዎቹ ወገን ቆመን አንዱ ያጎደለውን ሌላው ይሙላ እያልን ግጥማችንን እናጣጥማለን፡፡

Read 4630 times