Saturday, 16 March 2013 11:50

የጡት ካንሰር የወንዶችም ሥጋት ሆኗል!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

*የወንዶች የጡት ካንሰር ምልክቶች ምንድን ናቸው? *በየትኛው የእድሜ ክልል ያሉ ወንዶችን ያጠቃል? *መፍትሄው ምንድነው? ሃኪሞች ምን ይላሉ--- ካንሰር ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የህመም አይነቶች አጠቃላይ መጠሪያ ነው፡፡ በሽታው ከሌሎች በሽታዎች ተለይቶ የሚታወቀው ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ በማደግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሴሎችን ለመውረር በመቻሉ ነው፡፡ ካንሰር የተለያዩ አይነቶች ቢኖሩትም የሁሉም መነሻ ምክንያታቸው በሰውነት ውስጥ ያሉ ሴሎች ላይ የሚከሰት ያልተለመደ የሴሎች እድገትና መራባት ነው፡፡ ሴሎቹ ከተለመደውና ተፈጥሮአዊ ከሆነው የዕድገት መጠን ውጪ ልንቆጣጠረው በማንችለው ደረጃ እያደጉና እየተባዙ ይመጣሉ፡፡ ይህ የሴሎች ከቁጥጥር ውጪ ማደግና መባዛት በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ሊፈጠር ይችላል፡፡

ከእነዚህ ምክንያቶች መካከልም፤ ከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን፣ በተለያዩ ኬሚካሎች መጠቃት፣ ከፍተኛ ጨረር ባለባቸው አካባቢዎች ያለምንም መከላከያ መሠራት፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ሲጋራ ማጨስ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ ነገሮች የሰውነታችን ሴሎች ሲጠቁ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውና የሴሎችን ትክክለኛ ሥራ የሚቆጣጠረው ዲኤንኤ ይሞታል፡፡ ይህም የካንሰር ሴሎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡፡ እነዚህ የካንሰር ሴሎች ደግሞ እድገታቸውን የሚቆጣጠር ዲኤንኤ ስለሌላቸው ራሳቸውን ከሚጠበቀው በላይ በማባዛት፣ በደምና በሴሎች የሰውነታችን ፈሳሾች አማካኝነት በሰውነታችን ውስጥ በመዟዟር ችግሩ በመጀመሪያ በተነሳበት አካባቢ የህመም ስሜት ይፈጥራል፡፡ በዛሬው ጽሑፌ ትኩረት ያደረግሁት በወንዶች የጡት ካንሰር በሽታ ላይ ነው፡፡ የጡት ካንሰር በአብዛኛው የሚታወቀው የሴቶች ብቻ በሽታ እንደሆነ ነው፡፡ በሽታው ሴቶች በአብዛኛው ከሚሞቱባቸው የካንሰር ዓይነቶችም ዋንኛው ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን የጡት ካንሰር ከሴቶችም ባለፈ የወንዶች ሥጋት እየሆነ መጥቷል፡፡

በጊዜውና በወቅቱ ተደርሶበት ህክምና ካላገኘ በቀር ለሞት ሊዳርግ የሚችለው የጡት ካንሰር በሽታ ዛሬ በዓለማችን በርካታ ቁጥር ያላቸው ወንዶችንም እያጠቃ ነው፡፡ ከተፈጥሮአዊ የጡት አቀማመጥና አፈጣጠር አኳያ ሴቶች በጡት ካንሰር በሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ከወንዶቹ ላቅ ያለ ቢሆንም ወንዶችም በበሽታው ከመያዝ አላመለጡም፡፡ በዓለማችን በጡት ካንሰር በሽታ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚያዙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 25 የሚሆኑት ወንዶች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የወንድ የጡት ካንሰር በአብዛኛው የሚከሰተው ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ በሚሆኑ ወንዶች ላይ ሲሆን አልፎ አልፎ ግን በወጣቶች እና በታዳጊ ወንዶች ልጆች ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ የአሜሪካ የካንሰር ተጠቂዎች ማህበር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም በአሜሪካ ብቻ ቁጥራቸው 450 የሚደርስ ወንዶች በጡት ካንሰር በሽታ ሞተዋል፡፡ ይኸው መረጃ እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ይፋ እንዳደረገው፤ በዚሁ ዓመት ብቻ 1500 የሚሆኑ ወንዶች የጡት ካንሰር በሽታ ተጠቂ ሆነዋል፡፡

በአገራችን ይህንን በሽታ አስመልክቶ የተደረገ ጥናትም ሆነ በበሽታው የተያዙና ህይወታቸው ያለፉትን ወንዶች የሚያመለክት መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ይሁን እንጂ በሽታው በአገራችንም እንደሚገኝና ከጊዜ ወደ ጊዜም እየጨመረ እንደመጣ የሚያመለክቱ ሁኔታዎች መኖራቸውን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የወንዶች የጡት ካንሰር በሽታ እስከመኖሩም እምብዛም የሚታወቅ ባለመሆኑ በርካቶች በሽታው እንዳለባቸው ሳያውቁ እንኳን ህይወታቸው ሲያልፍ እንደሚታይ የነገሩን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ሰለሞን ዘርይሁን፤ ማንኛውም ዕድሜው ከ15 ዓመት በላይ የሆነ ወንድ ልጅ በጡቶቹ አካባቢ በተለይም በጡት ጫፍኛው ክፍል ላይ እብጠትና የቆዳ ቀለም መቀየር ሲያጋጥመው አስቸኳይ ምርመራ ማድረግ እንዳለበት ይገልፃሉ፡፡

ይህም በሽታው ሳይስፋፋና በሁሉም የሰውነት አካል ውስጥ ሳይዳረስ በጊዜ በመታከም ታማሚው ከበሽታው እንዲፈወስ ለማድረግ ያስችላል ይላሉ - ባለሙያው። በወንዶች ላይ በስፋት ከሚታዩት የጡት ካንሰር በሽታ ዓይነቶች መካከል አራቱ በብዛት የሚታወቁ ናቸው ያሉት ሃኪሙ፤ አራቱን የወንዶች የጡት ካንሰር አይነቶች እንደሚከተለው ያብራራሉ፡፡ “Paget disease of the Nipple” ወይንም ደግሞ “ኔፓል ፓጌት ዲዚዝ” በመባል የሚታወቀው የጡት ካንሰር ዓይነት ከሴቶች ይልቅ በብዛት በወንዶች ላይ የሚከሰት የጡት ካንሰር ነው፡፡ ይህ የሆነበትም ምክንያት የወንዶች ጡት ከሴቶች ጡት ይልቅ በመጠን አነስተኛ ስለሆነና ቦታው የሚያጠቃው የጡትን ጫፍ ክፍል በመሆኑ ለሴሎቹ መባዛትና መራባት የወንዶች ጡት ጫፍ ከሴቶቹ የበለጠ አመቺ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ የካንሰር ዓይነት ከጡት ውስጠኛው ሴል ተነስቶ ወደጡት ጫፍ በመውጣት በጡት ጫፍ አካባቢ ራሱን በማባዛት ያሰራጫል፡፡ እየበዛ ሲሄድ ወደ ጠፍጣፋውና ጠቆር ወዳለው የጡት ጫፍ ክፍል ይዛመታል፡፡ የዚህ አይነቱ የጡት ካንሰር ሲከሰት የወንዶች ጡት ጫፍ እብጠትና የመደደር ባህርይ ይኖረዋል፡፡ “Invasive Dactal carcinoma” ወይንም (ኢንቬሲቭ ዳክታል ካርሲኖማ) እየተባለ የሚጠራው የጡት ካንሰር አይነት ደግሞ ከወንዶች የጡት ካንሰር አይነቶች በወንዶች ላይ በብዛት በመከሰት የሚታወቅ ነው፡፡ 90 በመቶው የሆነውን ድርሻም ይይዛል፡፡

ካንሰሩ በወንዶች ውጫዊ የጡት አካል ላይ ከፍተኛ ወረራ በማካሄድ ህመም የሚፈጥርና ታማሚውን ለስቃይ የሚዳርግ የካንሰር ዓይነት ነው፡፡ Dactal Carcinoma (ዳክታል ካርሲኖማ) የተባለው ሌላው የጡት ካንሰር በወንዶች ላይ ከሚታዩ የጡት ካንሰር በወንዶች ላይ ከሚታዩ የጡት ካንሰር በሽታዎች ውስጥ ዋነኛው ቢሆንም በብዛት የሚከሰት አይደለም፡፡ ካንሰሩ የሚያጠቃው ፈሣሽ ሊያስተላልፍ የሚችለውን የጡት አካል ሲሆን ወደውጪኛው አካል መጥቶ የመባዛት ዕድሉ አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ካንሰር በቀዶ ህክምና የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ሌላኛው የጡት ካንሰር ዓይነት ደግሞ “Invasive lobelar carcinoma” (ኢንቬሲቭ ሎብለር ካርሲኖሚ) የሚባለው ሲሆን ይህ የጡት ካንሰር በወንዶች ላይ የመከሰት አጋጣሚው እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ከጡት ካንሰር ታማሚ ወንዶች መካከል ሁለት በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው በዚህኛው የጡት ካንሰር በሽታ የሚጠቁት፡፡ ካንሰሩ በባህርይው በስፋት የሚያጠቃው ወተት አምራቹን የጡት ክፍል በመሆኑ በሽታው በወንዶች ላይ የመከሰት አጋጣሚው እጅግ አነስተኛ ነው፡፡

ሆኖም በዚህ አይነቱ የጡት ካንሰር የሚጠቁ ወንዶች አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡ የወንዶች የጡት ካንሰር እንደሌሎቹ ካንሰሮች ሁሉ በወቅቱ ታውቆ ህክምናና ክትትል ከተደረገለት ሙሉ በሙሉ ሊድን የሚችል ቢሆንም ህመሙ በአብዛኛው ቶሎ የሚከሰትና ሊታወቅ የሚችል ባለመሆኑ፤ ከዚህ በተጨማሪም ወንዶች በጡት ካንሰር በሽታ ሊያዙ ይችላሉ የሚለው ግንዛቤ በህብረተሰቡ ውስጥ ባለመኖሩ በአብዛኛው በሽታው የሚታወቀው ሥር ከሰደደና ሥርጭቱ ከተስፋፋ በኋላ ነው፡፡ የወንዶች የጡት ካንሰር ምልክቶችን አስመልክተው ዶ/ር ሰለሞን ዘርይሁን ሲናገሩ፤ በሴቶች የጡት ካንሰር በሽታ ላይ የሚታዩ ምልክቶች ሁሉ በወንዶች የጡት ካንሰር በሽታ ላይም ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በጡት አካባቢ በተለይም በጡት ጫፍ እንዲሁም ጠፍጣፋውና ጠቆር ያለው ቦታ ላይ የመደደር፣ የጡት ጫፍ ቅርጽ መቀየር፣ ጫፉን ጫን ሲሉት እንደጐደጐደ መቅረት፣ በጡት አካባቢ በተለይም ጫፉ ላይ መሰነጣጠቅ መቅላት፣ ማሳቀቅና ማቃጠል፤ የጡት ጫፍ አካባቢ መድማት፣ ትናንሽ ፈሳሽ የያዙ እባጮች መኖር ለወንዶች የጡት ካንሰር በሽታ ዋንኛ ምልክቶች ናቸው፡፡ የሴቶች ብቻ በሸታ እንደሆነ ሲታሰብ የኖረው የጡት ካንሰር፤ አሁን አሁን የወንዶችም ሥጋት በመሆኑ ምልክቶቹ በታዩ ጊዜ አፋጣኝ ምርመራ ማድረጉ በሽታው ሥር ከመስደዱና ለማዳን አስቸጋሪ ከመሆኑ በፊት እንዲደረስበት ለማድረግ ያስችላል፡፡

Read 7045 times