Saturday, 16 March 2013 11:25

ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው የታወሱበት መድረክ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

“ነፍስና ስጋውን ለልጆች መፅሐፍ የሰጠ ሰው ነበር” ስለ አገራችን ልጆች፣ ትምህርት ቤቶችና የትምህርት አሰጣጥ የተለያዩ ሃሳቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲሰነዘሩ ይሰማል፡፡ በአንድ ወገን አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች የልጆች አፍ መፍቻ ቋንቋ እንግሊዝኛ እንዲሆን በመመኘት ለዚህ የሚጥሩ ወላጆችና ትምህርት ቤቶች እየተበራከቱ መሆኑ አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ በሌላ ጐን የአገሪቱን የትምህርት ሥርዓት የሚተቹ ወገኖች ለችግሩ ጥሩ ማሳያ ነው ብለው ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች አንዱ በዩኒቨርስቲዎች ስማቸውን በእንግሊዝኛ መፃፍ የማይችሉ ተማሪዎች እንዳሉ በማስረጃ አስደግፈው ለማቅረብ ሲጣጣሩ ይታያል፡፡

ይህ መሟገቻ ሃሳብ ከአንዳንድ የውይይት መድረኮች አልፎ በፓርላማ ደረጃ መነሳቱን፤ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 30 ቀን 2005 ዓ.ም በጣይቱ ሆቴል በተሰናዳ አንድ የመፃህፍት ምረቃ መድረክ ላይ ተወስቷል፡፡ በእለቱ “Munas Monkey” እና “The Giant Pineapple” በሚል ርእስ በዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው የተዘጋጁ ሁለት የልጆች የተረት መፃህፍት ይመረቁ ነበር፡፡ በመስከረም ወር 2005 ዓ.ም በ45 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ዶ/ር ማይክል፤ አሁን ለምርቃት የበቁትን ጨምሮ 38 በእንግሊዝኛና ሁለት በአማርኛ ቋንቋ በድምሩ 40 የተረት መፃህፍትን ያዘጋጁ የልጆች ባለውለታ ናቸው፡፡ የፓርላማው ገጠመኝና ክርክር የተጠቀሰውም ዶ/ር ማይክልና መሰል የአገር ባለውለታ ብዙ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ የማያውቁ ባለስልጣናት መኖራቸውን ለመግለፅ ነበር፡፡

ስለ ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸውና ስራዎቻቸው ምስክርነት ከሰጡት ሰዎች አንዱ የባለታሪኩ ጓደኛ አቶ ተስፋዬ ገ/ማርያም ናቸው፤ የፓርላማውን ገጠመኝ ያነሱት፡፡ ፓርላማው ውስጥ በትምህርት ስርአቱ ላይ ውይይት ሲደረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደካማ መሆናቸው የውድቀቱ ምልክት ነው ለሚለው አስተያየት ምላሽ የሰጡ የትምህርት ሚኒስቴር ባለስልጣን፤ “ለልጆች የሚሆን መፅሐፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚያዘጋጁ ፀሐፍት በአገራችን የሉም” ይላሉ፡፡ ይህ ምላሽ አስገርሞኝ ለዶ/ር ማይክል ስነግረው “ተዋቸው ባክህ” የሚል ምላሽ ሰጠኝ ያሉት አቶ ተስፋዬ ፤ ቀጥሎ ስለሆነው ነገር ሲናገሩ “ትንሽ ቆይቶ ለሕፃናት የሚሆኑ መፃህፍት አዘጋጅተው ያሳተሙ ሰዎችን ማፈላለግ ያዘ፡፡ ያገኛቸውን የ10 ደራሲያን ስምና የመፃህፍቶቻቸውን ዝርዝር በማዘጋጀት ለሕዝብ አሰራጨ” ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ ገ/ማርያም በቅርብ ስለሚያውቋቸው ዶ/ር ማይክል የሥራ ሰው መሆን፣ ሰው አፍቃሪነት፣ ለቀጠሮና ሰዓት ስለሚሰጡት ክብር… አንስተው በተለይ አብሮ የመሥራት ፍላጐታቸውና የመሪነት ሚናቸው ላቅ ያለ እንደነበር የገለፁ ሲሆን በማሳያነት ያቀረቡትም ዶክተሩን ጨምሮ 10 አባላት የነበሩትን ስብስብ ነው፡፡

የዶ/ር ማይክል አለመኖር ለመበታተናቸው ምክንያት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፤ቡድኑ እንዴት እንደተሰባሰበ፣ ምን ተግባር እንደፈፀመና በቀጣይነት ሊሰሩት ያቀዱት ሥራ ለምን እንደተስተጓጎለ ተናግረዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ለቡድኑ መገናኘትና መተዋወቅ ምክንያት የሆናቸው አንድ የስልጠና መድረክ ነበር፡፡ ስልጠናውን ከጨረሱ በኋላ ያገኙትን እውቀት ምን እንስራበት ብለው ሲወያዩ ለልጆች የሚሆን የተረት መፃህፍትን እያዘጋጁ ሊያሳትሙ ይስማማሉ፡፡ ለዚህም አላማ 10 ሆነው በጋራ መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ስምንት የተረት መፃህፍትም ማሳተም ቻሉ፡፡ የመፃህፍቱን ቁጥር 10 የማድረስ እቅድ ነበራቸው፡፡ ከዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው ሞት በኋላ ስብስቡ እንደወትሮው መገናኘት አልቻለም፡፡

“ይህንን ሳስተውል” አሉ አቶ ተስፋዬ ገ/ማርያም “እንደ ሲሚንቶ አጣብቆ የያዘን ዶ/ር ማይክል ነበር ብያለሁ፡፡” ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን ታምራት ባደረጉት ንግግር፤ በ“ፊደል አሳታሚ” ታትመው የቀረቡት ሁለቱ መፃህፍት ዶ/ር ማይክል ታማሚ ሆነው አልጋ በያዙበት ወቅት የመጨረሻ ቅርፃቸውን የያዙና በእርሳቸውም የህትመት ይሁንታ ያገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ አፍሪካን መርዳት መነሻ አድርጐ አህጉሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ሥራ በመስራት ላይ ከሚገኘው “አፍሪካ ራካይ” ከሚባል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የመጡት ሚስ ኩሩሚ ሺራቶሪ በበኩላቸው፤ በዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው መፃህፍት ላይ በስዕል ሙያ ስለተሳተፉ ጃፓናዊያንና ከደራሲው ጋር እንዴት ተዋውቀው ምን እንደሰሩ ንግግር አድርገዋል፡፡ “የማይለወጥ ሰብእና ነበረው፡፡ ነፍስና ስጋውን ለልጆች መፅሐፍ ዝግጅት የሰጠ ሰው ነበር” በማለት አድንቀዋቸዋል፡፡

የዶ/ር ማይክል ታላቅ ወንድም ዶ/ር አብይ ዳንኤልም ስለ ወላጆቻቸው፣ ስለ እህት ወንድሞቻቸው፣ ስለ የልጅነት ህይወታቸው አንስተው፤ ዶ/ር ማይክል በዩኒቨርስቲ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለማጥናት የወሰኑት በኋላ የሰሩትን ሥራ ተግባራዊ እንደሚያደርጉት አርቆ ከማሰብ መሆኑን መስክረዋል፡፡ በ1977 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተዋወቅን ጀምሮ ጓደኝነታችን ቀጥሏል ያሉት አቶ ተድላ ኃይሌም፤ ስለ ዶ/ር ማይክል ዳንኤል የሚያውቁትን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ “ዶ/ር ማይክል በራሱ ገንዘብ ነው መፃህፍቱን የሚያሳትመው፡፡ ላመነበት ነገር ገንዘብ ከመመንዘር ወደኋላ አይልም፡፡ በአንድ ወቅት በጣሊያን ሮም ከተማ በተደረገ አለም አቀፍ የገጣሚያን መድረክ ላይ ተገኝቶ የራሱን ግጥም ለማንበብ የራሱን ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ሄዷል፡፡ ደሀ ሆኖ ለሚያስብ ሰው የዶ/ር ማይክል ጉዞ የሚታመን አይደለም፡፡ እንዴት እንዲህ ያደርጋል - ብለናል በቅርቡ ያለን ሰዎች፡፡ እሱ ግን ለሥነ ፅሁፍ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረው እስከዚህ ድረስ ዋጋ ከፍሎበታል፡፡ “የልጆች የተረት መፃህፍትን የሚያዘጋጀው ከሚሰማቸው ወይም በህይወት ሂደት ከሚያያቸው ገጠመኞች በመነሳት ነው፡፡ 10ሺህ ኮፒ ድረስ ታትሞ የተሰራጨ መፅሐፍ አለው፡፡ ብዙ የተለዩ ሊባሉ የሚችሉ ድርጊትና አቋሞች ነበሩት፡፡

ለምሳሌ የሠርጉ እለት በግል ቮልስዋገን መኪናው ነው ሙሽሪትን ወደ ቤቱ ያመጣት፡፡ ምነው ሲባል ‘ልጆቼ ሲያድጉ ወላጆቻችን የተሞሸሩት በኪራይ ሳይሆን በራሳቸው መኪና ነው’ እንዲሉ እፈልጋለሁ ነበር ያለው፡፡ “አባቱ ሲሞቱ አንድ ጓደኛው ማምሻውን ጋቢ ደርቦ ለአዳር መምጣቱን ያስተዋለው ዶ/ር ማይክል፤ የምትተኛበት ቦታ የለም ብሎ መልሶታል፡፡ በዚያው ሰሞን አንዲት ዘመዳቸው ለቅሶውን ልትደርስ ከውጭ አገር ስትመጣ ዶ/ር ማይክል ሊቀበላት ቦሌ ሄዶ ከተገናኙ በኋላ እየተጨዋወቱ ሰፈር ይደርሳሉ፡፡ ቤት ሲገቡ ልጅቱ እዬዬዋን ስታቀልጠው ያየው ዶ/ር ማይክል “የምርሽን ነው? እስካሁን ስትጫወቺ አልነበረም ወይ? አሁን ምን ነካሽ?” ብሏታል፡፡

ዶ/ር ማይክል በውስጡ የተሰማውን ስሜት ከመናገር ወደ ኋላ የማይል ግልፅ ሰው ነበር፡፡” አቶ ተድላ ኃይሌ በዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው የሥራና የህይወት ታሪክ እንዲሁም ገጠመኞች ዙሪያ ካነሱት ሌላኛው “በተማሪዎቹ በጣም የሚወደድ አስተማሪ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መሀል ሰዓት አክባሪነቱና ሥራውን አክብሮ ሁልጊዜም በቦታውና በጊዜው መገኘቱ ነው፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልክ ወደ አገራችን ከገባ በኋላ ዘግይቶ የሞባይል ስልክ ባለቤት የሆነው ዶ/ር ማይክል፤ በየካቲት ወር 2004 ዓ.ም ስልኩን እንዲያወጣ ያስገደደው ህመሙ እየጠነከረበት ስለመጣ ነበር” ብለዋል፡፡

የዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው ሁለት የተረት መፃህፍት ምርቃት ምክንያት በማድረግ በተሰናዳው መድረክ ላይ ንግግር ያቀረቡት ባለቤቱ ወ/ሮ ፋሲካዊት አያሌው፤ የባለቤታቸው ሥራዎች “ቤተሰቦቻቸውና ልጆቻቸውን እንዲፅናኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌሎች ሥራዎቹን ለማስተዋወቅ ኃላፊነት እንዲሰማን አድርጐናል” ካሉ በኋላ ለባለቤታቸው የገጠሙትን ግጥም አንብበዋል፡፡ እኔም ቅኝቴን በዚሁ የወ/ሮ ፋሲካ ግጥም እቋጫለሁ - ነበረ ችኮላው ፍጥነቱ የበዛ ለካስ ታይቶት ነበር መጠራቱ እዛ እኔ ነኝ መስካሪ እረፍት ለማጣቱ መፅሐፉን ለልጆች ለማቅረብ መጣሩ በአጭር ቢቋጭ እንኳን ዘመኑ ቢያበቃ እጅግ ብዙ ሰርቷል ማዘናችን ይብቃ ምን ብዬ ላስረዳ እንዴትስ ልናገር በትዝታ መርከብ ከመዋለል በቀር ግድየለም ይሁና ልቤ ተቀበለው ስራና ልጆቹን ቀሪ ስላረከው፡፡

Read 2505 times