Print this page
Saturday, 16 March 2013 10:51

ሁሉም ነገር ይለመዳል? እንደ ታክሲ ወረፋ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ፣ ውጤት እያስመዘገብኩ ነው አለ እንዴት ቢባል፤ የታክሲ ስምሪት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማካሄድ ነዋ ሌላ አዲስ አበባ ካለ ይነገረን፤ ነባሯ ከተማ ግን ታክሲ ተቸግራለች ገና ምኑን አይታችሁ? የትራንስፖርት ሚኒስትርም ያሰበው ነገር አለ ከከተማ ውጭ፣ ማታ ማታ የመኪና ጉዞ ክልክል ይሆናል ተብሏል በዚህም ውጤት ይመዘገባል - የትራንስፖርት እጥረትን የሚያባብስ ሜክሲኮ አካባቢ፣ የስራ መውጫ ሰዓት ላይ፣ ወደ ጦር ሃይሎችና ወደ አውቶቡስ ተራ ለመሄድ አዳሜ ይጋፋል።

ከወዲያ ማዶ፣ ወደ ሳሪስና ወደ ጎፋ፣ መዓት ሰው ይተራመሳል። ወዲህ ዞር ስትሉም፣ ወደ መገናኛ ለመሄድ የሚጠብቅ እልፍ ሰው ታያላችሁ። የታክሲ ስምሪት ከታወጀ በኋላ፣ የትራንስፖርት እጥረት ተባብሶ፣ ግፊያውና ግርግሩ ጨምሯል። ለዚህም ነው፤ በርካታ ፌርማታዎች ላይ ወረፋ የተጀመረው። እዚያው ሜክሲኮ አካባቢ በገሃር መስመር፤ ወደ አራት ኪሎ ታክሲ ለመሳፈር የሚፈልግ ከ150 በላይ ሰው በሁለት አቅጣጫ ተሰልፏል። ታክሲ ጠፋ! ለነገሩ “ታክሲ ጠፍቷል አልጠፋም” ለማለት ያስቸግራል።

ወረፋ ከሚጠብቁ ሰዎች አጠገብ ከአስር በላይ ሚኒባስ ታክሲዎች ተሳፋሪ አጥተው ቆመዋል። ግን ወደ ቦሌ መስመር የተመደቡ ናቸው፤ ከዚያ ውጭ ቢንቀሳቀሱ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። ምን የሚሉት ቅዠት ነው? ከመቶ በላይ ሰዎች ታክሲ አጥተው ለወረፋ ተገትረዋል፤ ከአስር በላይ ሚኒባስ ታክሲዎች ተሳፋሪ አጥተው በሰልፍ ቆመዋል። ወረፋ ጠብቀው አራት ኪሎ ሲደርሱም፣ ነገርዬው ተመሳሳይ ነው። ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳና ወደ መርካቶ ለመሄድ ብዙ ሰዎች ይሻማሉ - በታክሲ እጥረት። ዞር ብለው ሲያዩ ግን፣ ከአራት ኪሎ ወደ አምባሳደር መስመር የተመደቡ በርካታ ሚኒባሶች፣ ተሳፋሪ ጠፍቶ አፋቸውን ከፍተዋል።

ተሳፋሪ ወደሚበዛበት ቦታ ሄደው መስራት አይችሉማ። በደርግ ዘመን የነበረውን የታክሲ ስምሪት እንደገና ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ ያስተላለፉ ባለስልጣናት፤ ገና ከጅምሩ መዘዙን ማሰብ አይችሉም ነበር? ይችሉ ነበር። ሰው ናቸው። ደግሞም፣ እነሱ ባይችሉ እንኳ፣ አስቦ የሚመክር አልጠፋም ነበር። ለምሳሌ፣ የስምሪት ቁጥጥር በግንቦት 2003 ዓ.ም ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በአዲስ አድማስ የወጡ ፅሁፎችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። የታክሲ ስምሪት የትራንስፖርት እጥረትን በማባባስ አሁን የምናየውን አይነት ቅዠት እንደሚፈጥር በግልፅ ተንትኖ የሚያቀርብ ፅሁፍ በአዲስ አድማስ መቅረቡን አስታውሳለሁ (የካቲት 26 ቀን 2003 ዓ.ም የአዲስ አድማስ እትም)። “በየአቅጣጫውና በየመስመሩ፤ የትራንስፖርት ፈላጊዎች ብዛት እንደእለቱና እንደሰአቱ፣ እንደወቅቱና እንደሁኔታው ይለያያል።

... የሰኞ፤ የአርብ፣ የቅዳሜና የእሁድ ተሳፋሪዎች ቁጥር ተመሳሳይ አይሆንም። ማለዳ 11 ሰአት፤ ጥዋት ሁለት ሰአት፤ ረፋዱ ላይ፣ ከቀኑ 11 ሰአት፤ ከምሽቱ ሶስት ሰአት በኋላ በዚያው መስመር የሚኖረው የተሳፋሪ ቁጥር… ይለያያል። በክረምት፤ በበአል ቀናት፣ በልዩ ዝግጅቶች፣ በሰርግ ወራትም እንዲሁ ለየቅል ነው። “...ታክሲዎች የራሳቸውን ገቢ ለማሳደግ ብዙ ተሳፋሪ ማግኘት ስላለባቸው፤ በእያንዳንዱ መስመር ላይ እንደሰአቱና እንደእለቱ፣ እንደወቅቱና እንደሁኔታው የሚለዋወጠውን የተሳፋሪ ቁጥር በማስተዋል (መስመራቸውን እያስተካከሉ) ለመስራት ይጣጣራሉ። ... በስምሪት ቁጥጥር ከተመደቡበት መስመር ውጭ እንዳይሰሩ ከተከለከሉ ግን ገቢያቸው ይቀንሳል፣ ታክሲ ፈላጊውም ይጉላላል” “በሆነ ሰአት፤ …ተሳፋሪ ከመብዛቱ የተነሳ፤ በዚያ መስመር ከተመደቡት ታክሲዎች አቅም በላይ ይሆናል። ... ብዙ ሰዎች በትራንስፖርት እጥረት ለሰአታት ይቆማሉ፤ ሌሎች ታክሲዎች መጥተው መስራት አይችሉም። …በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ተሳፋሪ ከማነሱ የተነሳ፤ በቦታው የተመደቡ ታክሲዎች ያለስራ ቆመው ጊዜ ያባክናሉ። በትራንስፖርት እጦት ብዙ ሰው ወደተጉላላበት ቦታ ሄደው መስራት አይችሉም። ከጥቂት ሰአታት በኋላ፤ ሁኔታው ይቀየራል። በመጀመሪያው ቦታ ተሳፋሪ ጠፍቶ ታክሲዎች ያለ ስራ ይቆማሉ። በሁለተኛው ቦታ ደግሞ፤ በታክሲ እጥረት፤ ተሳፋሪዎች ለረዥም ሰአት ይጉላላሉ።

” “…ተሳፋሪ አጥተው ያለ ስራ የሚቆሙ ታክሲዎችን እና ታክሲ አጥተው የሚንገላቱ ተሳፋሪዎችን ማበራከት ነው የቁጥጥሩ ውጤት። ቢሮክራቶቹ… የቁጥጥር ሱስ… የመጣው ይምጣ የሚያሰኝ እጅግ ሃይለኛ ሱስ ካልሆነባቸው በቀር፤ መዘዙን ያጡታል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል” እንዲህ እንደምታዩት፤ የስምሪት ቁጥጥሩ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ጠቃሚ ምክር ቢቀርብም፣ የሚሰማ ባለስልጣን አልተገኘም። ለነገሩ፣ ከአንዳንድ የታክሲ ባለቤቶችና ሾፌሮች በስተቀር አብዛኛው ሰው፣ የታክሲ ስምሪት ጠቃሚ እንደሚሆን ገምቶ ነበር - የትራንስፖርት ችግር የሚቃለልለት መስሎት። ለምን መሰለው? ታስታውሱ እንደሆነ፤ አንዳንድ የታክሲ ሾፌሮችና ባለቤቶች ቅሬታቸውን ሲገልፁ፤ “ስምሪቱን የሚቃወሙት፣ ጥቅማቸው ስለሚቀርባቸው ነው” ተባለ። የዚህ ትርጉም ምን እንደሆነ አስቡት። አሃ… “ባለታክሲዎችና ሾፌሮች ከተጎዱ፣ ተሳፋሪ ይጠቀማል” ማለት ነዋ። እንዴት እንዴት? በንግድ እና በቢዝነስ ዙሪያ የብዙ ሰው አስተሳሰብ በጣም የተዛባ ከመሆኑ የተነሳ፤ ሻጮችና ሸማቾች፣ ባለታክሲዎችና ተሳፋሪዎች… ተቀናቃኝ ባላንጣ ሆነው ይታዩታል። ስለ ታክሲ ሲያስብ፣ 5 ሳንቲም አሳልፎ የማስከፈልና 5 ሳንቲም አጉድሎ የመክፈል ጉዳይ ብቻ ጎልቶ የሚታየው ሰው፤ “አንደኛው ወገን ጥቅም የሚያገኘው በሌላኛው ጉዳትና መስዋእትነት ነው” ብሎ ያምናል።

እናም፣ “ስምሪቱ ባለታክሲዎችን የሚጎዳ ከሆነ፣ ተሳፋሪዎችን ይጠቅማል” ብሎ ይደመድማል። የሰዎች ኑሮ፣ ከአውሬዎች ሕይወት ብዙም የተለየ ሆኖ አይታየውም - እርስ በርስ እየተቦጫጨቁ መኖር። እውነታው ግን፣ የዚህ ተቃራኒ ነው። አንዱ የሚጠቀመው፣ ሌላኛው ሲጠቀም ነው። ባለታክሲው የሚጠቀመው መቼ ነው? በሆነ አቅጣጫ በክፍያ ለመጓዝ የሚፈልግ ተሳፋሪ ሲመጣለት። ተሳፋሪው የሚጠቀመውስ? ክፍያ ተቀብሎ ለማጓጓዝ የሚፈልግ ታክሲ ሲመጣለት። የባለታክሲው ጥቅም እየጨመረ የሚሄደው፣ ብዙ ተሳፋሪዎችን ፈልጎ ሲያገኝና ሲያስተናግድ ነው - ገቢው ያድግለታል። የተሳፋሪ ጥቅም የሚጨምረው ደግሞ፣ በርካታ ተሳፋሪዎችን የሚያስተናግዱ ታክሲዎች ሲመጡ ነው - በትራንስፖርት እጦት ተገትሮ አይውልም። አንደኛው ወገን ጥቅም የሚያገኘው፣ ሌላኛውም ወገን የሚጠቀም ከሆነ ነው። መሰረታዊው የቢዝነስ ቁምነገርም ይሄው ነው - አምስት ሳንቲም የማጉደልና የማሳለፍ ሳይሆን። የስምሪት ቁጥጥሩም፣ ይህንን መሰረታዊ ቁምነገር በማደናቀፍ ነው ባለታክሲዎችንና ተሳፋሪዎችን ለጉዳት የዳረጋቸው። ጉዳቱ ግን፣ ዛሬ የምናየው ቅዠት ብቻ አይደለም። የባለታክሲዎች ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመጣ ቁጥር፤ ወደ ቢዝነሱ የሚገቡ ሰዎችም ቁጥራቸው ይቀንሳል። በተቃራኒው፣ ከቢዝነሱ የሚወጡ ሰዎች ይበራከታሉ።

ለዚህም ነው፤ በአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ መደበኛ ሚኒባስ ታክሲዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየቀነሰ የመጣው። ከጥቂት አመታት በፊት ቁጥራቸው 12ሺ ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ቢገልፁም፣ አሁን ግን በስራ ላይ የሚገኙት 9ሺ አይሞሉም። አላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥር፣ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ ውሎ አድሮ መዘዙ የከፋ እንደሚሆን ከዚህ ቀውስ መረዳት እንችላለን። የታክሲ ወረፋ ባልነበረበት ከተማ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ… “የታክሲ ወረፋ” የኑሯችን አካል ሆኖ አረፈው። ተሳፋሪ ያጣ ታክሲ ተደርድሮ፣ ታክሲ ያጣ ተሳፋሪ ተሰልፎ የምናይበት የቅዠት ዓለም ውስጥ ገብተናል። ይህም አልበቃ ብሎ፣ ቅዠቱን የሚያጦዝ መግለጫ እንሰማለን። የአዲስ አበባ መስተዳድር የትራንስፖርት ቢሮ፣ ረቡዕ እለት በመንግስት ሚዲያዎች በኩል የሰጠውን መግለጫ አላዳመጣችሁም? በየጊዜው በምወስዳቸው እርምጃዎች መልካም ውጤቶችን እያስመዘገብኩ ነው ብሏል - የትራንስፖርት ቢሮው። ለምሳሌ ያህልም፤ የታክሲዎች ስምሪት ላይ ቁጥጥሩን ለማጥበቅ እርምጃ እንደወሰደ ቢሮው ሲገልፅ፤ አሁን አሁን ከተመደበበት መስመር ውጭ ውልፍት የሚል ታክሲ የለም ብሏል። ችግሩ ምን መሰላችሁ? አላስፈላጊው ቁጥጥር በተፈጥሮው መጥፎ ወይም ጎጂ ስለሆነ፣ ቁጥጥሩ በጥብቅ ተግባራዊ ሲደረግ ጎጂነቱ ይጨምራል እንጂ መልካም ውጤት ሊመዘገብ አይችልም። መልካም ውጤት የተመዘገበባትና ባለስልጣናት ብቻ የሚያውቋት ሌላ “አዲስ አበባ” ከሌለች በቀር፤ በነባሯ ከተማ ውስጥ የታክሲ ግርግርና ወረፋ ሲበራከት ነው የምንመለከተው።

የፌደራል ባለስልጣናት ደግሞ በበኩላቸው ሌላ ቁጥጥር ተግባራዊ ለማድረግ እንደተዘጋጁ ገልፀዋል። ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በማታ የሚደረጉ ጉዞዎች እንደሚታገዱ ለኢቴቪ የተናገሩ ባለስልጣናት፤ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የታሰበ እርምጃ ነው ብለዋል። ከከተማ ውጭ፣ በማታ በሚከናወን ጉዞ ላይ የትራፊክ አደጋ ይደርሳል ወይ? አዎ ይደርሳል። ነገር ግን፣ የከተማ ውስጥ እና የቀን ጉዞ ላይም የትራፊክ አደጋ ይደርሳል። ታዲያ፣ የትራፊክ አደጋ ለመከላከል አስበን፤ በከተማ ውስጥና ከከተማ ውጭ፤ በቀን እና በማታ የሚከናወኑ የመኪና ጉዞዎችን ለምን አናግድም? ለነገሩማ፤ አይነቱና መጠኑ ይለያያል እንጂ፤ በተፈጥሮው “አደጋ” የማያሰጋው አንዳችም የሰው እንቅስቃሴ የለም። ፎቅ መስራት፣ ጉድጓድ መቆፈር፣ መንገድ መጥረግ፣ መሬት ማረስ፣ ቤት ማፅዳት… ሁሉም አይነት ስራ፣ ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ መስራት ሳይቀር፣ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገበት አደጋ ይደርሳል።

ለምሳሌ፣ ከፍተኛ አደጋ ከሚያጋጥማቸው ነገሮች መካከል፣ እርግዝናና ወሊድ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ምን ይሄ ብቻ? እንደአረማመዱና እንደአሯሯጡ፣ እንደአጎራረሱና እንደአጠጣጡ፣ እንደአስተኛኘቱና እንደአለባበሱ ሁኔታ ለአደጋ የሚጋለጥ ሰው ጥቂት አይደለም። እና፣ አደጋዎችን ለማስቀረት አርፎ መቀመጥና ሞቱን መጠባበቅ አለበት? በጭራሽ! ሰው፣ የስራውንና የእንቅስቃሴውን ምንነት ለማገናዘብ፣ በጥረቱ የሚያገኛቸው ጥቅሞችንና ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ለማመዛዘን የሚያስችል አቅም አለው - የአእምሮ አቅም። ጥቅሞቹን የሚያሳድጉ ዘዴዎችና አደጋዎችን የሚያስቀሩ ጥንቃቄዎች የሚፈጠሩትም፣ በሰዎች የአእምሮ አቅም ነው። ያለ ድካም በፍጥነት ከቦታ ቦታ መጓዝ እጅጉን ጠቃሚ እንደሆነ ትጠራጠራላችሁ? መኪና የተፈጠረውና የሚመረተው፣ አስፋልት የሚቀየሰውና የሚገነባው፣ ለሌላ ምክንያት አይደለም - ያለ ድካም በፍጥነት ለመጓዝ ነው። በእርግጥ አደጋዎች ያጋጥማሉ።

ግን ከጥቅሙ ጋር ሲነፃፀር፣ አደጋው በጣም ትንሽ ነው። መኪናና አስፋልት ባልነበረበት ዘመን፣ የሰዎች አማካይ የሕይወት ዘመን 30 አመት ገደማ ብቻ ነበር። አስፋልት ላይ ፈጣን የመኪና ጉዞ፤ የሰዎችን ሕይወት አሻሽሏል። ነገር ግን፤ ከጥቅሙ ጋር ሲነፃፀር አደጋው ትንሽ ነው በሚል፤ አደጋውን ቸል ማለት አለብን ማለት አይደለም። “አደጋ አለው” በሚል ሰበብ እርግዝናንና ወሊድን ለማስቀረት ማሰብ እብደት ቢሆንም፤ አደጋውን ለመቀነስና ለማስቀረት የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን ከመተግበር መቦዘንም “እብደት” ይሆናል። የመኪና ጉዞም ተመሳሳይ ነው። የትራፊክ አደጋ ተፈርቶ፤ የመኪና ጉዞን ማስቀረት የጤንነት አይደለም። አደጋውን በ“ፀጋ” መቀበልም እንዲሁ። ለዚህም ነው፤ የትራፊክ ደንቦችና ምልክቶች፤ የትራፊክ መብራቶችና የማሽከርከር ስልጠናዎች የተፈጠሩት። ይህም ብቻ አይደለም። አማራጮችን አመዛዝኖ፣ የመጓጓዣ አይነቱን፣ አቅጣጫውንና ጊዜውን መምረጥ ያስፈልጋል።

ለምሳሌ፤ ዋጋውንና አቅርቦቱን፣ የመጓጓዣውንና የአሽከርካሪውን ብቃት ማነፃፀር አስፈላጊ የመሆኑን ያህል፤ በጥቅሉና በአመዛኙ ሲታይ፤ በብስክሌትና በሞተር ብስክሌት ከመጓዝ ይልቅ በመኪና መጓዝ የተሻለ መሆኑንም ማገናዘብ ይቻላል። በማታ ከመጓዝ ይልቅ በቀን፤ በመኪና ከመጓዝ ደግሞ በባቡር፤ በባቡር ከመጓዝ ደግሞ በአውሮፕላን ይሻላል። ለምን በጥቅሉ አማካይ የአደጋ መጠናቸው አነስተኛ ስለሆነ። እንዲህም ሆኖ፤ የአውሮፕላን ጉዞ የተሻለ ስለሆነ የመኪና ጉዞን ለማገድ፣ ወይም የመኪና ጉዞ ስለሚሻል የሞተር ብስክሌትን መከልከል፤ አልያም የቀን ጉዞ ስለሚሻል የማታ ጉዞን መከልከል… ከእብደት አይለይም። መከልከልና ማገድ ይቅርና፤ “ብስክሌት አትጠቀሙ፣ በማታ አትንቀሳቀሱ” ብሎ መምከርም ስህተት ነው።

ጥቅሙንና ጉዳቱን፣ ሰዓቱንና አቅጣጫውን፣ መጓጓዣውንና አሽከርካሪውን እያመዛዘናችሁ ተጠቀሙ ነው መባል ያለበት። “አትጠቀሙ፣ አትንቀሳቀሱ” ከሚለው የተሳሳተ ምክር አልፎ፤ ወደ ክልከላና እገዳ መግባት፤ ከመሳሳት አልፎ የሰውን ነፃነት መርገጥ ይሆናል። አለበለዚያማ፤ “የመንቀሳቀስ ነፃነት” ተብሎ በህገመንግስት የሰፈረው ፅሁፍ ምን ትርጉም አለው? ባለስልጣናት በፈቀዱት ሰዓት ብቻ ነው መንቀሳቀስ የሚቻለው? በደርግ ዘመን የ”ይለፍ” ወረቀት ያልያዘ ሰው ከከተማ ከተማ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ከድሮው የደርግ ዘመን የሰዓት እላፊ አዋጅ፤ በከፊል ተቀንጭቦ ተግባራዊ ሊደረግ ነው ቢባል አይሻልም?

Read 4073 times
Administrator

Latest from Administrator