Print this page
Saturday, 16 March 2013 10:28

አፈጉባኤ ያልተዋጣለት ምክር ቤት

Written by  በእሳቱ ተነሳ
Rate this item
(1 Vote)

በአስር ክፍለ ከተሞችና በ116 ወረዳዎች የተከፋፈለችው አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናና የዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛም ናት። በዚህም ምክንያት ፈጣን እድገቷም ሆነ፣ ዘገምተኛ ጉዞዋ ከሀገር አልፎ የሌላውን ዓለም ትኩረት መሳቡ አይቀርም፡፡ ስለሆነም የከተማዋ አስተዳደራዊ መዋቅር በሁሉም ዘርፍ የተጠናከረና ከሀገር አልፎ አህጉራዊ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን (ተገልጋዩ፣ የውጭ ባለሀብት፣ ዲፕሎማትና ቱሪስት የመሆን እድልም ስላለው) ይፈለጋል፡፡

ለዛሬ በነፃ አስተያየት አምድ ላነሳው የፈለግሁት የአዲስ አበባ ምክር ቤትን የተመለከተ ነው፡፡ በተለምዶ “የኩማ ካቢኔ” የሚባለው አሁን ያለው የከተማዋ አስተዳደር እነሆ የስልጣን ጊዜውን አጠናቆ ለሚተካው አካል ለማስረከብ የቀናት እድሜ ነው የቀረው፡፡ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት አመታት ከባለአደራ የከተማዋ አስተዳደር ስልጣኑን ተረክቦ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑ ባይካድም፤ ውጤት ያላሳየባቸው (ጐታታ ለውጥ የታየባቸው ዘርፎች) ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ የከተማዋ ምክር ቤትን ሁኔታም ስናይ ከዚሁ የተለየ አይደለም፡፡ በተለይ በቻርተሩ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር እንዲሁም በህገ መንግሥቱ ከተደነገገው የህዝብ ምክር ቤቶች ተግባር አኳያ መመዘን ተገቢ ነው፡፡

ምንም እንኳን ምክር ቤቶች አስፈፃሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር፣ የህዝብ ቅሬታዎችን ተቀብሎ እንዲፈቱ ማድረግ፣ አዳዲስ ሊያሰሩ የሚችሉ ደንቦችና መመሪያዎችን ማውጣትና አፈፃፀማቸውን መከታተል የመሳሰሉት ተግባራት ቢኖሩትም የስራ ጊዜው ያለቀው ምክር ቤት ግን ውጤታማ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ በተለይም በቀዳሚዎቹ ሦስት አመታት ጥርስ የሌለው አንበሳ ብቻ ሳይሆን የራሱን ችግር ያልፈታ “ችግር ፈቺ” ሆኖ ነበር የከረመው፡፡ ለዚህ ችግር ተጠቃሽ የሚሆኑት ደግሞ ራሱ አስተዳደሩና የምክር ቤት አባላት ቢሆኑም ምክር ቤት ፅህፈት ቤቱን ጭምር የሚመሩት አፈ ጉባኤዎች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በአምስት አመታት ውስጥ ሦስት ዋና አፈጉባኤዎች ከመቀየራቸው ባሻገር፣ እስከአሁን በተለያዩ ድክመቶች የሚታወስ ቦታ ሆኗል፡፡

የመጀመሪያዋ አፈጉባኤ ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ ነበሩ፡፡ በስነፅሁፍ ትምህርት መስክ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከሚያስተምሩበት በአዴንን ወክለው ምክር ቤቱን የመሩት አፈጉባኤዋ፤ ከሃላፊነታቸው የተነሱት በግምገማ ነበር፡፡ በአንድ በኩል አቶ ኩማን ጨምሮ አስፈፃሚውን የማይቀበሉና ለችግሮች ተነጋግሮ በጋራ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ የተቆጣጣሪነት ሚናቸው መጐልበቱ አስተችቷቸው ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የግል ባህሪያቸው፣ በራስ መተማመናቸውና ተናጋሪነታቸው ወይም ግልፅነታቸው አብዮተኛ ቢያስብላቸውም በብዛት አምባገነንነት ይታይባቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ጋዜጠኞች ተሰብስበን፣ መግለጫ እንዲሰጡን ስንጠብቅ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ካልመጣ (ለመታየት ከነበራቸው ፍቅር) ብለው በትነውናል፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኝነት የተከበረ ሙያ መሆኑን ዘንግተው በማንኳሰስ ሰዎችን ሲዘልፉ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከስልጣን በወረዱ ሰሞን ከተገመገሙበት ነጥብ አንዱ ሰራተኞችንና ባለጉዳዮችን የሚያንጓጥጡ “ደርግ” በመሆናቸው ነው፡፡ ለነገሩ ምክር ቤት ፅህፈት ቤቱ ሊሰራ የሚገባውን ተግባር ሁሉ ክፉኛ ገድለውት ነበር፡፡

በከተማዋ ባሉት ሁሉም መዋቅሮች (በየደረጃው) ከ36ሺ የማያንሱ የምክር ቤት አባላት አሉ፡፡ እነዚህን አደራጅቶ፣ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ አድርጐ፣ በህዝብና መንግሥት መካከል ሚና ያላቸው የህዝብ ወኪሎች ከማድረግ አንፃር የጐላ ክፍተት ነበር፡፡ እንዲያውም የአንዳንዱን ም/ቤት አባል ቁጥርና ማንነት እስካለመታወቅ የደረሰ መዝረክረክ መታየቱ የፅ/ቤቱን የስራ ኃላፊዎች በመሉ ለማስቀየር አስገድዷል፡፡ (ከዚህም በላይ ወ/ሮ ስንቅነሽ በስማቸው ሦስት የመንግሥት ቤቶች ይዘው በመገኘታቸው በኪራይ ሰብሳቢነት መገምገማቸው የሚታወስ ነው) ምክር ቤቱ የነበረበት ክፍተት ተገምግሞ አፈጉባኤዋን ጨምሮ ሁሉም የስራ ኃላፊዎች (ም/አፈጉባኤ፣ ፅ/ቤት ኃላፊና ፀሐፊ) ሲቀየሩ የመጡት እነ ዶክተር አፀደ ናቸው፡፡ አፈጉባኤ አፀደ በኢኮኖሚክስና ቢዝነስ ማኔጅመንት የፒ.ኤች.ዲ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (አዳማ ዩኒቨርስቲና ቤዛ ኮሌጅ በመምህርነት በስራ ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡

በወቅቱ ምክር ቤቱን በኃላፊነት ሲረከቡ ለአለምአቀፍ ግንኙነትና ገፅታ ግንባታ ጭምር አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ቢታመንም እምብዛም ሊሳካ አልቻለም፡፡ በተለይም ምክር ቤቱ አስፈፃሚውን በመቆጣጠርና በመደገፍ ረገድ ቋሚ ኮሚቴዎች አፈፃፀማቸው በቂ አልነበረም፡፡ በዶ/ር አፀደ ጊዜ ሪፖርትና እቅድ ከመገምገም ባለፈ የወጡ ህጐችም እዚህ ግባ የሚባሉ አልነበሩም፡፡ ያ አልበቃ ብሎ ፅ/ቤቱ በፊት የነበረበት በሽታ አገርሽቷል፡፡ ሰራተኛውና አመራሩ ተቀናጅቶ ያለመስራት፣ አፈጉባኤዋም “ከከንቲባው በደረጃ እበልጣለሁ” ወደሚል በመርህ ላይ ብቻ በተመሰረተ (በአዲስ አበባ ሁኔታ የመጨረሻው ሰው ከንቲባው መሆኑ ቅቡል ሆኖ ያደረ ጉዳይ ነው) እሳቤ መናገር ጀመሩ፡፡ ይሄም አለመግባባትን ከመፍጠሩ ባሻገር የግምገማ ነጥብ እየሆነ መጣ፡፡

“በእንቅርት ላይ…” እንዲሉ በዚህ ውዝግብ መሃል ዶክተሯ መኪና በሚያሽከረክሩበት ወቅት አንድ የጐዳና ተዳዳሪ ገጩና ተከሰሱ፡፡ ይሄ ደግሞ የመከሰስ መብታቸውን የሚያስነሳ ስለሆነ ከሌሎች ቀደም ሲል ከተጠቃቀሱ ምክንያቶች ጋር ተደራርቦ ከሃላፊነታቸው አስነሳቸው፡፡ አጠቃላይ የምክር ቤት ፅህፈት ቤቱም ቢሆን አንዳንድ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንዳለበት አቅጣጫ አመላካች ነገሮች ተንፀባረቁ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ አፈጉባኤ ሲፈለግ የተገኙት የምክር ቤት አባል የቀድሞው ምክትል ከንቲባ አቶ ከፍያለው አዘዘ ነበሩ፡፡ (በነገራችን ላይ እርሳቸው በአሁኑ ወቅት በስደት አውሮፓ መሆናቸው ይታወቃል) ይሁንና በወቅቱ ሰውዬው ኃላፊነቱን ለመረከብ ፈቃደኛ አልሆኑም “አፈጉባኤነት እምብዛም የፖለቲካ ስልጣን የሌለውና የተዳከመ የሚቀመጥበት ነው” ስለሚባል ለቆዳቸው ሰስተው (የሰው አፍ ፈርተው ይሆን) ስራውን ሳይጀምሩ ቀሩ፡፡ በኋላ በለስ የቀናቸው ሰው የአሁኑ አፈጉባኤ “ዶክተር” ታቦር ገብረመድህን ተገኙ፡፡

በለስ የቀናቸው የምልበት ዋነኛ ምክንያት ቀደም ሲል ከነበሩበት የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ም/ኃላፊነት አንፃር የሚበዛባቸው ቦታ ስለሆነ ነው፡፡ ለነገሩ ከዚያም በፊት (በዲሞሽን በአማራ ክልል የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ እንደነበሩ ልብ ይሏል) በዚያ ላይ ምክር ቤቱን የተቀላቀሉት በማሟያ ምርጫ ከመሆኑ አንፃር የስድስት ወር እንኳን የምክር ቤት ልምድ ሳይኖራቸው ነው “ጉብ” ያሉበት፡፡ ለነገሩ የስራ ኃላፊው ያላቸው ልምድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን በመሆኑ ስራው ባይከብዳቸውም ከአመታት በፊት “የስርአቱ አደጋ” ተብለው ከኢቴቪ ም/ስራ አስኪያጅ የተባረሩ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ይህን ስያሜ ያሰጧቸው መገለጫዎችም በወቅቱ ከድርጅቱ አልፈው በግሉ ሚዲያ ለህዝብ መድረስ ችለው ነበር (በተለይ በሪፖርተር ጋዜጣ) በመሆኑም በበርካታ ሰራተኞች ላይ ጭካኔ የተሞላበት በደል በመፈፀም ቤታቸው እንዲፈርስ በማድረጋቸው፤ ባህርዳር ከተማ ከመሬት ሙስና ጋር በተያያዘ ጋዜጠኛ ልከው የተዛባ ዘገባ ለመሸፈን በመሞከራቸው፣ በቢሮ ውስጥ በአጉል ስነምግባር በመወቀሳቸው ጭምር ነበር፡፡

ምክር ቤቱ አዲስ አፈጉባኤ ከማግኘቱ በላይ የተሻለ የፖለቲካ አቅም ያላቸው ምክትል አፈጉባኤና ፀሐፊ ማግኘቱ ነቃ ብሎ እንዲንቀሳቀስ አድርጐታል። ከዚህም ባሻገር ቋሚ ኮሚቴዎችን የሚመሩ አመራሮች በቋሚነት በመመደባቸውና ፅ/ቤቱ በሰው ሃይልና በግብአት እየተሟላ በመምጣቱ፣ ከራሱ አልፎ እስከ ወረዳ ምክር ቤቶች ድጋፍና እገዛ ማድረግ እንደጀመረ ይነገራል፡፡ አፈጉባኤው ያሉበት ሁኔታ ግን አሁንም ከችግር የተላቀቀ እንዳልሆነ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይገልፃሉ። በተለይ ከስድስት ወር በፊት ያገኙት “የዶክትሬት” ማዕረግ ከንቲባውም ሆነ ሌሎች አካላት ሳያውቁት ተደብቀው አምስት አመታት በመማራቸው መሆኑ አስወቅሷቸዋል፡፡ (እርሳቸው ተደብቃችሁ ተማራችሁ ብለው ያባረሯቸው በርካታ ሰራተኞች እያሉ፤ አስተዳደሩ ለጊዜው ከፍተኛ ትምህርት ቆሞ ስራ ላይ እንረባረብ እያለ ሙሉ ጊዜያቸውን በድብቅ ለትምህርት በመስጠታቸው ስራው መውደቁ ይታወሳል፡፡

እንዲያውም ደካማ የኮሙኒኬሽን መዋቅር ተብሎ ባለፈው አመት በመገምገሙ በዚሁ መዘዝም የቢሮ ሃላፊው የነበሩትና ምክትል ከንቲባው አቶ ከፍያለው ለመባረር በቅተዋል፡፡ አፈጉባኤው ከሰሞኑ ለግምገማ ያበቃቸው ጉዳይ ደግሞ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተመደቡበትን የመረጃ ነፃነት ፅ/ቤት ካለአሳማኝ ምክንያት በመበተናቸው ነው፡፡ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ የከተማዋን መረጃ ለማስተካከል ድረገፆችን ለመስሪያ ቤቶች ገንብቶ የወረዳ ማዕከላትን አስከፍቶ፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ልዩ ልዩ ህትመቶችን በስታንዳርድ ይገኛል፡፡ ስለመረጃ ነፃነትም እስከ ሺ ለሚደርሱ (የመረጃና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ባለጉዳዮች)፣ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች፣ ህገ ደንቦችና መመሪያዎች በአጭር ጊዜ አዘጋጅቶ የተሻለ ውጤት እያሳየ ነው። በዚህም እምባ ጠባቂ ተቋም ሥራው አበረታች ጅምር እንደሆነ ከመገለፁ ባሻገር፣ ሌሎች ክልሎች (ትግራይና ድሬደዋ) ልምዱን ለማስፋት እንቅስቃሴ ጀምረው እንደነበር የመ/ቤቱ ሃላፊዎች በቅርቡ በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡ እንግዲህ እነዚህ ጅምሮች ባለቡት ሁኔታ አፈጉባኤው የስራ ሃላፊዎቹን ባልተገባ ምክንያት አንስተው ሠራተኛው እንዲበታተን ከማድረጋቸው ባሻገር ተቻኩለው ስራውን እንዲያስቀጥል በሚል የሹመት ሃላፊ (በግል የሚቀርባቸውና በአቅም ከሠራተኞችም ያለፈ) ሆኖ በመገኘቱ ከፍተኛ ወቀሳ አስነስቶባቸዋል፡፡

በተለይ የወሰዱት እርምጃ የስራ አመራር ቦርዱንም ሆነ ድርጅቱን ሳያሳውቁ በመሆኑ የኔትወርክ ስራ እንደሆነ ታውቆ ያስገመገማቸው ሲሆን የተሾመው ባለሙያም በከንቲባው እንዲሻር ተደርጓል፡፡ ጉዳዩም በአዲስ አበባ ኢህአዴግ ደረጃ እንዲታይ በመደረጉ አፈ ጉባኤው ወንበራቸው የተነቀነቀ መስሏል፡፡ ዶክተር ታቦር ከቀደሙት አፈጉባኤዎች የተሻሉ አይደሉም የሚያስብላቸው ሌላው ጉዳይ የሚያራምዱት የቡድነኝነት ዝንባሌ በግምገማ ጐልቶ መውጣቱ ነው፡፡ በብሄር ኦሮሞ (የአዲስ አበባ ዙሪያ ለገጣፎ ተወላጅ) ሆነው ረጅም ጊዜ በአማራ ክልል በመስራታቸው የብአዴን አባል ሆነዋል፡፡ በአጠቃላይ ያለፉት አምስት አመታት የበረው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጠንካራና የተሻለ አፈጉባኤ አላገኘም (ሦስት መቀያየራቸውን ልብ ይሏል) ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ በሚያዚያ በሚካሄደው ምርጫ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመወዳደራቸውም ባሻገር፣ ኢህአዴግም ቢሆን ከፍተኛ የሀገሪቱን ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ ምክር ቤት እያስገባ መሆኑን አይተናል፡፡ ስለሆነም ቀጣዩ የአዲስ አበባ ምክር ቤት በየጊዜው ከሚገመገምና ከሚቀያየር የፀዳ ብቁና ከተማዋን የሚመጥን አፈጉባኤ ታገኝ ዘንድ ብንመኝስ!!

Read 3152 times