Print this page
Saturday, 09 March 2013 12:58

የጃኖ ባንድ ጠንሳሽ አዲስ ገሠሠ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

“ጅምሬ ወዴት እንደሚሄድ አውቀዋለሁ” ከትውልድህ እንጀምር የተወለድኩት ጎሬ/ኢሊባቡር ነው፤በእኛ ጊዜ ጠቅላይ ግዛት ይባል ነበር፡፡ እዛ ትንሽ ተምሬአለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ እዛ ነበሩ፡፡ ከዛም በተረፈ አዲስ አበባ ተምሬ ነው በ17 ዓመቴ ከኢትዮጵያ የወጣሁት፡፡ በምን ምክንያት ወጣህ? ዕድል፡፡ እርግጥ ቤተሰቦቼ ገንዘብ ኖሯቸው አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ወጥቼ ቺካጎ ገባሁ፡፡ ለብዙ ዓመት እዛው ኖሬያለሁ፡፡ በኋላ እናቴንም ወንድሞቼንም ወደዛው ለመውሰድ በቃሁ፡፡ አሜሪካ የኖርኩት ለ35 ዓመት ነው፡፡ እዚያ በመቆየቴ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ እንዴት? ተማርኩኝ - ቢዝነስ ማኔጅመንት፡፡ ሙዚቃ ውስጥ ያስገቡኝ ወንድሞቼ ናቸው፡፡ ከዛ በፊት ጎበዝ የኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ሙዚቃ አለም ውስጥ ከገባሁ ጀምሮ በጣም የተሳካ ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡

እንዴት ነው ወንድሞችህ ወደሙዚቃው ያስገቡህ? ወንድሞቼ ከሃገር የወጡት ቀይ ሽብርን ሸሽተው ነበር፡፡ ጅቡቲ እስር ቤት ከነበረ ወንድሜ ደብዳቤ ሲደርሰኝ በጣም ደነገጥኩ፡፡ በዛን ጊዜ ነው ወንድሞቼን ከኢትዮጵያ ያወጣሁትና ቺካጎ የመጡት፡፡ እኔ ሙዚቃ እንደሚጫወቱ አላውቅም ነበር፡፡ ሙዚቃ መቻላቸውን ሲነግሩኝ...በጣም ተገረምኩ፡፡ የኢስተርን ኢሊኖ ዩኒቨርስቲን ዲን ‹‹እነዚህ ወንድሞቼ ሙዚቀኞች ናቸው›› ስለው በየዓመቱ ፌብሪዋሪ ብላክ ሂስትሪ መንዝ (February black history month) የሚባል አለ፡፡ ያኔ ለተማሪዎች በጀት አለ ብሎ ነገረኝ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ለዩኒቨርስቲው ሾው እንዲያቀርቡ መሳሪያ ተከራይቼላቸው ነበር - ያን ጊዜ ነበር የወንድሞቼን ችሎታ ያየሁት፡፡

በህይወቴ ውስጥ ለለውጥ የተነሳሁበት ቀን ይሄ ነው፡፡ ምን ዓይነት ሙዚቃ ነበር ያቀረቡት? በአማርኛ፣ በአፍሪካ፣ በሬጌ ...ሙዚቃውን አቀረቡ፡፡ እነሱ በጣም ልምድ አላቸው፡፡ ሌለው ቀርቶ ጅቡቲ ከእስር ቤት ወጥተው ለትንሽ ጊዜ ቆይተው ነበር፤በዚያን ጊዜ ባንድ አቋቁመው ይጫወቱ ነበር፡፡ በጣም ጎበዞች ነበሩ፡፡ ሁሉን ነገር ትተህ ወደ ሙዚቃው አደላህ ማለት ነው? አዎ! ሙሉ በሙሉ ወንድሞቼ ቀየሩኝ፡፡ ሙዚቃ ህይወት ነው፡፡ ሙዚቃ ይለውጥሻል፡፡ እንደ አዲስ መፈጠር ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜ ልጅ ያደርጋል፡፡ ያን ደስ የሚል ስሜት ይዘን መከርን ከወንድሞቼ ጋር፡፡ የሙዚቃ መሳሪያ መግዛት አለብን አልኳቸው፡፡ አሜሪካ ከተሰራ፣ ከተማሩ፤ ጊዜን በአግባቡ ከተጠቀሙ በጣም ጥሩ አገር ስለሆነ፤ ሰው ይኮናል፡፡ እኔ ደግሞ ቺካጎ ስኖር ዘመድ የለኝም፣ ራሴን የማስተዳድር ነኝ፣ ትጉህ ሰራተኛና መልካም ባህሪ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ወንድሞቼ የኔን ፈለግ ተከትለው በየሳምንቱ ከምንሰራው ደሞዛችን ላይ ገንዘብ አጠራቅመን መሳሪያ ገዛን፡፡ እኔ ደግሞ በክሬዲት ቫን አምጥቼ በራፋቸው ላይ አቆምኩላቸው፡፡ ሊያምኑ አልቻሉም፡፡

አሜሪካን አገር...ገና በስድስት ወራቸው አዲስ መኪና..፡፡ ህልም ነው፤እኔ ግን እውን እንደሚሆን አሳየኋቸው፡፡ ዋሽንግተን ሄድን ለአበሻው የመጀመሪያ አንድ ትልቅ ሾው ስናሳይ ህዝቡ ደነገጠ፡፡ ከየት መጡ፤ እነዚህ የቺካጎ ልጆች ተባልን፡፡ ከዛ ካሊፎርኒያ ሄደን ሰራን፤ብዙ ገንዘብ፡፡ ያንን ለዓመት የትምህርት ቤት ክፍያ አዋልነው፡፡ በዓመቱ የቦብ ማርሊ ልደት ይከበራል፡፡

በዛ ላይ ለመሳተፍ በቀጥታ ደብዳቤ ፃፍን፡፡ አክቲቭ መሆን ነው የእኔ እህት (ሳቅ) ከዚያ ሪታ ማርሊ የአውሮፕላን ትኬት ከፍላ፤ ሆቴላችንን አመቻችታ፤ ወንድሞቼ መጡ ብላ በአጀብ ተቀበለችን፡፡ የመጀመሪያውን ሾው የቦብ ማርሊ ሙት ዓመትን በማስመልከት በተወለደበት ጃማይካ ሄደን አከበርን፡፡ ያ የነገሮች ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ በስንት ዓመት ምህረት ማለት ነው? እ.ኤ..አ በ1991ዓ.ም. ማለት ነው፡፡ እኔም ወንድሞቼ ወደ አሜሪካ ከመጡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እመጣለሁ የሚለውን ነገር ተውኩት፡፡ ለምን? ወንድሞቼ እንዲህ ተሰደው ከሃገር ከወጡ ትልቅ ችግር አለ የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ በዚያ መንግስት ኢትዮጵያ ለመምጣት አልፈለግሁም፡፡ በጭራሽ፡፡ አንድ ወንድሜ ሞቷል፤ ሌሎች ወንድሞቼ ተሰደዋል፡፡ “ለምን ኢትዮጵያውያን ሆነን ተፈጠርን” የሚል አይነት አስተሳሰብ ይዘው ነው የመጡት፡፡ ከኢትዮጵያ መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን እስር ቤት በነበሩ ጊዜም ብዙ ተሰቃይተዋል፡፡ ይህንን ሳይ እዚሁ አሜሪካ መኖር አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ ዲግሪ አለኝ ተምሬያለሁ፤ሪታ ማርሊ ጥሩ ገንዘብ ሰጥታን ወደ ቺካጎ ተመለስን፡፡

እኔን ግን በጎን ታባብለኝ ነበር፡፡ እንዴት---ምን ብላ? ከእኔ ጋር ስራ፤ጥሩ ወንድማችን ትሆናለህ በማለት፡፡ መጀመሪያ ብዙም ፍላጎት አልነበረኝም፤ በኋላ ግን ደስ አለኝ፡፡ አንድ እህት አገኘሁ፤ አፍሪካዊት ጃማይካዊት፣ ኢትዮጵያዊት..የሆነች እህት፡፡ እሷ ጋ ሄጄ መኖር ጀመርኩኝ፤ለአንድ ዓመት ያህል፡፡ አንድ ዓመት ስሰራ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረስኩኝ፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ እዛ መኖሩ አልታየኝም.. በጣም ከፍተኛ ደረጃ የደረስከው ሙዚቃ አብረሃቸው በመስራት ነው? የጃማይካ ባህል እንደኛው አገር ነው፡፡ የቦብ ማርሊ ልጆች ሃይስኩል እስኪጨርሱ ድረስ ነፃነት አልነበራቸውም፡፡

በአንዳንድ ካረቢያን ደሴቶች፤ትምህርት ቤት ሲዘጋ ደግሞ አሜሪካ አብረን ሄደን ሾው እንሰራለን፡፡ በኋላ ዚጊ ሃይስኩል ጨረሰ፤ሪታ ማርሊ ልጆቿዋን - ስቲቭን፣ ዚጊን፣ ሸረንና፣ ስዴላን ለእኔ ለቀቀቻቸው፡፡ ዚጊ ማርሊ “ዘ ሜሎዲ ሜከርስ” ተብሎ ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር ዳሎል ባንዱ ሆኖ ስራ ተጀመረ፡፡በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ግራሚ ከእሱ ጋ አገኙ፡፡ በከፍተኛ የአልበም ሽያጭ ጎልድና ፕላቲኒየም ሪኮርድም አገኙ፡፡ ለእኔ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ አንድ የድሃ ልጅ ...እኛ ምንም አልነበረንም፡፡ ቤተሰቦቼም እኔም ምንም አልነበረንም፡፡ ..ወጥተን በአለም ላይ፡፡ በጣም ትልቅ እድል ነው፡፡.

በሙዚቃ ሥራችሁ የት የት ዞራችሁ? የት አልዞራችሁም ብትይ ነው የሚቀለው የእኔ እህት...አሜሪካን ከዳር እስከዳር..አውሮፓ የቀረን አገር የለም..ወንድሞቼ ዘለቀ፣ ሙሉጌታ፣ ሩፋኤል፣ ደረጀ መኮንን (አሁን በቅርብ ጊዜ ያረፈው) በጣም ድንቅ ጊዜ ነበረን፡፡ በጣም ወጣት ነበርኩ፤እንደ አሁኑ ምርኩዝ አልያዝኩም (ረጅም ሳቅ) ህልም እውን ሲሆን ታውቂያለሽ...ትንሽ እንደሰራን ዚጊ ግፊት በዛበት.. ግፊት----ምን ዓይነት? ጃማይካ ውስጥ ሙዚቀኛ ጠፍቶ ነው ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር የሚጫወተው የሚል.. አለማቀፍ ግፊት ነው..የቦብ ማርሊ ልጅ እንዴት ከኢትዮጵያኖች ጋር ..የሚል ዓይነት ነበር፡፡ ግፊት ሲበዛ እኔን አማከረኝና የጃማይካውያን ሙዚቀኞች ባንድ መቋቋም አለበት ተባለ...ዳሎል ወደ ቺካጎ ተመለሰ፡፡

አሁን ከቦብ ማርሊ ቤተሰብ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? አሁንም እንጠያየቃለን..አሁንም ሪታ ማርሊ እህቴ፣ እናቴ፣ ጓደኛዬ ናት፡፡ ማኔጀርዋ ነኝ.. በጣም እንገናኛለን፡፡ በቀደም እዚህ መጥታ ነበር፤ የቦብ ማርሊ ሃውልት የተሰራ አለ፤ለሱ ጉዳይ ነበር የመጣችው---.ባለፈው ፌብሪዋሪ 6 ለማስመረቅ አስበን ነበር፤ጤንነትዋ ጥሩ ስላልሆነ ተመለሰች፡፡ ከቦብ ማርሊ ቤተሰብ ምን አገኘህ? መውደድን የተማርኩት ከእነሱ ነው፡፡ በጣም ጥልቅ ፍቅር ነው ያሳዩኝ፡፡ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላ ጃማይካዎች፡፡ ጃማይካ ውስጥ ---- ጌቶ ውስጥ ብትይ፣ አፕታውን ብትይ፣ የፈለኩበት ቦታ ብሄድ ---- ንጉስ ነኝ፡፡ በቅርቡ ሎሳንጀለስ ሄጄ፤ ከዚጊ ማርሊ ጋር ትንሽ ጊዜ አጥፍቼ ነው የመጣሁት፡፡ በጣም ጠንካራ የሆነ ግንኙነት አለን፡፡ እማልቀይረው፡፡

ዳሎል ባንድ ከቦብ ማርሊ ልጅ ጋ ከተለያየ በኋላ እጣ ፈንታው ምን ሆነ? ይሰራል፡፡ ወንድሞቼ ዘለቀና ሙሉጌታ እየሰሩ ነው፤እንደውም እኮ እዚህ አገር ናቸው አሁን፡፡ ከዛ በኋላ ግን ኒውዮርክ መጥቼ ቢሮ ከፈትኩ፡፡ ለ19 ዓመት ኒውዮርክ ነበር ቢሮዬ፤ እመላለሳለሁ በሳምንት፣ በወር ... ጃማይካ፡፡ የማኔጅመንት ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡ የኒውዮርክ እምብርት ላይ..ሆኜ ማኔጅ አደርግ ነበር - እነ ዚጊን፡፡ በዚህ መሃል የዛሬ 10 ዓመት ገደማ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ብቅ አለች፡፡ እስዋን ይዟት የመጣው ቶማስ ጎበና የተባለ ቤዝ ጊታር ተጫዋች ነበር፡፡ ከቤቴ ሁለት ብሎክ ላይ ሆኖ ስልክ ደወለልኝና- ‹‹አንድ ዘፋኝ ይዤልህ መጣሁ›› “የት ነው ይዘሃት የምትመጣው?” “ይህችን ልጁ አንተ ልታገኛት ይገባል..አለበለዚያ የትም አትደርስም...አንተ እንድታግዛት ነው” ብሎ ይዟት መጣ፡፡ ያኔ ጂጂን አላውቃትም ነበር፡፡ ጥሩ ድምፅ አላት፤ በጣም ጉጉ ናት፡፡ አወራኋት፡፡

ግቢዬ ውስጥ በጓሮ በኩል የሙዚቃ ቤት አለኝ..ገባንና ዝፈኝ አልኩዋት..ለቀቀችው፡፡ በጣም ተደነቅሁ፤ ደነገጥኩ፡፡ ማመን አልቻልኩም፤ ድፍረቷ፣ተሰጥዖዋ----በጣም ጎበዝ ልጅ! በዛን ወቅት የምትኖረው ሳንፍራንሲስኮ ነበር፡፡ ሳፍራንሲስኮ የሙዚቃ ከተማ አይደለም፤ ኒውዮርክ መምጣት አለብሽ አልኳት፡፡ ‹‹ብር የለኝም›› አለች፡፡ ‹‹ግዴለም እሱን ለእኔ ተይልኝ›› አልኳት፡፡ መጣች፤በጣም ጥሩ ቤት ተከራየንላት፡፡ ከትልቅ ኩባንያ ጋር አፈራረምኳት፡፡ አንዴም ድምጿን አልሰሙዋትም፤ በእኔ እምነት ነው የፈረሙት፡፡ በጣም ብዙ ገንዘብ አምጥቼ ሰጠኋት፤ አላመነችም፡፡ ጂጂን የማደንቃት ነገር ቢኖር ከዛ ገንዘብ ላይ ብዙውን ወደ ባህርዳር ቤተሰቦችዋ ጋ መላኳ ነው፡፡ በጣም ገረመችኝ፡፡ ገና ሳትደራጅ..ራስዋ በእግሯ ሳትቆም፡፡ በኋላ ቤላስዌልን አስተዋወቅኋት፡፡ ባለቤቷን ማለትህ ነው? ቤልን እንደ ጥላ ያመጣሁት እኔ ነኝ፡፡ አገባችው፡፡ በቃ አደገች፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ ቴዲ አፍሮ መጣ፡፡ እንደ ጂጂ ሁሉ የእርሱም በጣም የሚደንቅ ነበር፡፡ አላውቀውም፡፡ አንድ ዲጄ መንጌ የሚባል ልጅ አለ፡፡ “አንድ ጎበዝ ልጁ ተፈጥሯል አዲስ አበባ፤ እሱን ማኔጅ ማድረግ አለብህ” አለኝ.. “እኔ ጊዜ የለኝም” ብዬ አባረርኩት፡፡ የባለቤቴ ቅርብ ዘመድ ነው፡፡

እኔ ቱር ሄጄ ስመለስ ባለቤቴን በደንብ አድርጎ ሞልቷት፤እኔ ስመጣ የመጀመሪያ አጀንዳ ያደረገችው ቴዲ አፍሮ ነበር፡፡ በቃ እሽ አልኩ፡፡ እዚህ መጣሁና አገኘሁት፤ወደ ቺካጎ ይዤው ሄድኩኝ..ባንድ አዘጋጀሁለት..እኔ እዛ ክለብ ነበረኝ፤ ከዘለቀ ጋር ‹‹ዋንቴር›› የሚባል የታወቀ ክለብ ውስጥ ቀን ከሌት እንዲለማመዱ አደረግሁ --- ለአንድ ወር ተኩል፡፡ ሙዚቀኞች አያውቁትም ነበር፤እሱም አያውቃቸውም.. እኔም የዚህን ልጅ ስራ ብዙ አላውቅም፤ተገናኝተው ሲሰሩ ስሰማ በጣም ተደነቅሁ-----ሶስት ሙዚቃ ሰምቼ በአራተኛው ላይ ታክሲ ይዤ ለሌላ ስራ ወደ ኤርፖርት ሄድኩ፡፡ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ሾው አቀረብን፤ታሪክ ነው የተሰራው፡፡ ከሌሎች አለማቀፍ ዘፋኞችስ ጋር--- ከሎረን ሂል ጋር ትንሽ ጊዜ ሰርቻለሁ፤“አርዝ ዊንድ ኤንድ ፋየር” ከሚባሉ የሙዚቃ ባለሞያዎች ጋር ለትንሽ ጊዜ ሰራሁ...፡፡ እነሱን የማውቃቸው ቺካጎ ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ተም ተም ዋሽንግተን›› የሚባል በጣም ከባድ አሬንጀር አለ፡፡ በአሜሪካ ምርጥና ድንቅ የሚባል፡፡ በሱ በኩል ነው የተዋወቅኋቸው፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥህን እናውራ--- ኢትዮጵያ ከመጣሁ አምስት አመቴ ነው፡፡ ላይንስ ዴይ ሆቴል የሚባል አለኝ፡፡ ባለቤቴ ነች የምታስተዳድረው፡፡

በጣም ጎበዙ ልጅ ናት፡፡ ሶስና ሽፈራው ትባላለች፡፡ ሁለት ልጆች አሉን፡፡ ሌሎችንም ስራዎች በአገሬ መስራት ጀመርኩ፡፡ የማዕድን ስራ፣ እርሻውን.. ከባለሞያዎች ጋር እየሰራን ነው፡፡ አዲስ የሙዚቃ ባንድም አቋቁመሃል ----- አዎ፡፡ ብዙ ልምድ አለኝ፡፡ ያለኝን ነገር ይዤ መሄድ አልፈልግም፡፡ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ እንደመጣሁ በሙዚቃው ንፍቀክበብ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ በየክለቡ፣ አንዳንድ ቦታዎች እየዞርኩ ሙዚቀኞችን አያለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ምን ወሰንኩ---በቃ የሙዚቃ ባንድ መመስረት አለብኝ አልኩኝ፡፡ የራሳቸው ሳውንድ እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ...ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ እንደ አትሌቶች..ደራርቱ፣ ጥሩነሽ፣ሃይሌ የአገራችንን ህዝቦች እንደሚወክሉ ሁሉ በሙዚቃው ደግሞ ይህን ሃላፊነት መውሰድ አለብኝ በሚል‹‹ጃኖ ባንድ›› ተጠነሰሰ፡፡ ይሄንን ሳደርግ ደግሞ ኤርምያስ አመልጋ (አክሰስ ሪል ስቴት) ባለቤት ጓደኛዬ ነው፤ ሄጄ አማከርኩት፡፡ ከመቶ መቶ ሃምሳ ከጎንህ ነኝ አለኝ፡፡ ‹‹አብረን እናድርገው›› አለ፤ከእርሱ ጋር አብረን ጀመርን፡፡ እኔ ነኝ ልጆቹን የሰበሰብኳቸው - ስምንት ሴቶች፣ አስራ አምስት ወንዶች መረጥኩኝ፡፡

ከኒውዮርክ እንዲረዳኝ ብዬ ቤላስዌልን ጠራሁት፡፡ ሴቶቹን በሙሉ አባረራቸው (ሳቅ)፡፡ ወንዶቹንም ስምንት ልጆች ብቻ ይበቃናል አለ፡፡ ፈትናችኋቸው ነው? አዎ እንዲዘፍኑ አደረግን.. ከዛ ሁለት ሴቶች ሃሌ ሎያና ሄዋንን እኔ ጨመርኩኝ፡፡ ‹‹ጃኖ ባንድ›› ተመሰረተ፡፡ ‹‹ተተካኩ›› ብላችሁ አይደል (ሳቅ) ጅምሬ ወዴት እንደሚሄድ አውቀዋለሁ...ትልቅ ነገር ነው የምንሰራው---- የኢትዮጵያን ስም የሚያስነሳ፡፡ ዲሲፕሊን ካላቸው ልጆች ጋር እየሰራሁ ነው፡፡ ቪዥነሪስ ናቸው፡፡ የምፈልገውን ራዕዬን (ቪዢኔን) የሚያሟላልኝ ቡድን ተፈጠረ፡፡ በጣም ጎበዞች ናቸው፡፡ ቢላስዌል እንደ ፕሮዲዩሰር ነው የመጣው፡፡ እሱ ደግሞ አራት ኢንጂነሮች ይዞ መጣ፡፡ ስራችን ሁሉ በዓለም የሙዚቃ ደረጃ የሚሰራ ነው፡፡ ‹‹ኤርታሌ›› የሚል ስያሜ የሠጠነውን የመጀመሪያ አልበማችንን እኔ ሪኮርድ አድርጌ ይዘን ሄድን፤ አሜሪካን አገር፡፡ እዚያ ተሰርቶ ተላከልን፡፡ እኛ ደግሞ ሲዲውን እዚህ ለቀናል፡፡

ሁለት ዓመታችን ነው፤ አንዳንድ ሾዎችን መስራት ጀምረናል፡፡ ዛሬ በ‹‹ላፍቶ ሞል›› ኮንሰርት አለን፡፡ ከዛ በኋላ አራት የኢትዮጵያ ዋና ከተማዎች ውስጥ ሰርተን ለፋሲካ ወደ አሜሪካ እንሄዳለን፡፡ ሮክ በእኛ አገር አልተለመደም---- እንደውም የሰው አቀባበል በጣም ነው ያስደነቀኝ፡፡ ከማምነው በላይ ነው የሆነብኝ..በየመኪናው፣ በየመገናኛ ብዙሃኑ፣ በየክለቡ ዘፈኑ ሲለቀቅ እሰማለሁ...ከክፍለ ሃገር መልክት ይደርሰኛል፡፡ በማህበራዊ ድረ ገፆች የሚመጣውን አስተያየት አያለሁ፡፡ በአጭር ጊዜ ነው ይህ የመጣው፡፡ የምሰራውን ነገር የሀገሬ ህዝብ ሲያደንቅልኝ አስቢ--- ምን ሊሰማኝ እንደሚችል፡፡ ትልቅ ደስታን የሚያጎናፅፍ ነገር ነው፡፡ ‹‹ጃኖ›› የሚለው የባንዱ ስያሜ እንዴት ወጣ?. በዲሞክራሲ አምናለሁ፡፡ የኖርኩበት የአሜሪካ ማህበረሰብ ያስተማረኝ ነው...በዚህ ሁኔታ ልጆቹ ስም ለማውጣት በጣም የተለያዩ አማራጮችን አቅርበው ነበር፡፡ ለሁለት ሳምንት ተከራክረንበታል፤ግን በተደጋጋሚ ይህ ስያሜ ስላሸነፈ በጃኖ ተሰየመ፡፡ ጃኖ ባንድ በዓለም ላይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በማስተዋወቅ እንደ ቦብ ማርሊ.. ከሳውዝ አሜሪካ እንደወጡ የተለያዩ ሙዚቀኞች ይህችን የምንወዳትን ሃገራችንን በሰፊው ለማስተዋወቅ አልመናል፡፡ መድረሻችንን አውቀዋለሁ፡፡ ይህም በቅርብ ይሆናል፡፡

  •  “ጃኖ ኢትዮጵያዊ መለያችን ነው” ኪሩቤል ተስፋዬ የጃኖ ባንድ ኪቦርድ ተጫዎችና የቡድን መሪ ሲሆን ለ12 ዓመት በተለያዩ ባንዶች ውስጥ እንደሰራ ይናገራል፡፡ የ28 ዓመቱ ኪሩቤል በባንዱ ውስጥ ካሉ የሙዚቃ ባለሞያዎች በዕድሜ ትልቁ ነው፡፡ ስለጃኖ ባንድ ስያሜ ንገረኝ--- ከሙዚቃችን ተነስተን ነው፡፡ ሙዚቃችን ከግማሽ በላይ አማርኛ ነው፡፡ አገርኛ ነው፤ ባህላዊ፡፡ ያንን የሚያንፀባርቅ፣ሙዚቃችንን የሚገልፅ፣ ሰዎች ሲሰሙት ለጀሮ የሚቀል በሚል ነው--- ብዙ ስሞች መጥተው መጨረሻ ላይ ‹‹ጃኖ›› ላይ ፀናን፡፡ ጃኖ በራሱ የአገር ልብስ ጥለት ነው፤ ኢትዮጵያዊ መለያችን ነው፤ያምርብናል፤ ደመቅ ያለ ያማረ..በባህልና በስርዓት ለየት ላለ በዓል የሚደረግ ነው...የክብር ልብስ! ሁልጊዜ የሚደረግ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነታችንን በጣም ይገልፅልናል፡፡ እኛም እያደረግን ያለነው የአገራችንን ሙዚቃ ሌላው የዓለም ክፍል በሚረዳው መልኩ ለማቅረብ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ሙዚቃ እንዳላት ከዚህ በፊት ከተሰራው በተሻለ አቅም ለማስተዋወቅ ስለሆነ ጃኖ ባንድ ይገልፀዋል፡፡ የአልበማችሁን ስም ደግሞ “ኤርታሌ” ብላችሁታል---- ኤርታሌ በኢትዮጵያ አፋር ክልል ውስጥ የሚገኝ ድንቅ ነገር ነው፡፡ እኛም የመጀመሪያ ኮንሰርታችንን ስንሰራ አዲስ የታመቀ ሃይል ፈንድቶ ሲወጣ፤ ሃይላችንን አቅማችንን አሳየን፡፡ ጊዜያችንን ሰጥተን የለፋንበት ስራ ነው፡፡ እሳተ ጎሞራም እንዲሁ ነው፤ ካልታሰበ ቦታ ገንፍሎ የሚወጣው አንፀባራቂ የሆነ ነገር----- እሳተ ጎሞራውም ወደ አለትነት ይቀየራል፡፡ ያ ደግሞ ያለን አቅምና ሃይል ነው የሚገልፀው፡፡ የመጀመሪያ አልበማችን ይህን ይገልፀዋል፡፡ አልበሙ ውስጥ ስለሃገር፣ ስለፍቅር፣ ስለማንነት፣ተዘፍኗል፡፡ አልበሙንና እኛን የሚገልፅ ስም ይሆናል በሚል ነው ‹‹ኤርታሌ›› ያልነው፡፡ ሙዚቃ እንጂ ድምፃዊያን የላቸውም፣ ለዜማና ለግጥም አይጨነቁም የሚል አስተያየት ይሰነዘራል----- እንደዚህ ዓይነት አስተያየት አለ፤ ከብዙ አቅጣጫ፡፡ አዲስ ነገር እኛ አገር ይዘሽ ስትመጪ፤ ቶሎ ለመቀበል ይቸግራል፡፡ እኛም ፈርተነው ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ እያስለመድነው ወደ ምንፈልገው ደረጃ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም ደረጃ እነሱ በሚያውቁት መልኩ ለማቅረብ፣አገር ውስጥ ላለው ደግሞ ከተለመደው ከሚሰማው የተለየ ብንሰጠው ይወደዋል ብለን ነው የሰራነው፡፡ ተቀባይነቱ ከጠበቅነው በላይ ነው፡፡ ከአልበሙ ውስጥ ሶስትና አራት ሙዚቃዎች ሃይል ኖሯቸው መደመጥ ችለዋል፡፡ በየዘመኑ የተለያየ ሳውንድና ሙዚቃ ይመጣል፡፡ ለውጥ ይኖራል፡፡ የመጀመሪያውን የእኛን አገር ብትወስጂ ኦርኬስትራ ባንድ ነበረ፣ ዘመናዊ ሙዚቃ መጣበት፣ ከዚያ ወደ ዲጂታል እያለ ወደዚህ መጣ፡፡ በመጀመሪያው አልበማችን ሰውን ሁሉ እንቆጣጠራለን ብለን አናስብም፡፡ ቀስ በቀስ ግን እንመጣለን፡፡ በዛሬው ኮንሰርት ምን የተለየ ነገር ታቀርባላችሁ? ብዙ አዲስ ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት ወደ አምስት ኮንሰርቶች ሰርተናል፡፡ ትንንሽ ኮንሰርቶችን፡፡ በዛ ጊዜ ውስጥ የሰራናቸው ሙዚቃዎች አሉ፡፡ ብዙዎቹ አዳዲሶች ናቸው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ይኼ ላያዝናና ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰው የሚያውቀውን ሙዚቃ ስትጫወችለት ነው ደስ የሚለው፡፡ ሰው የማያውቃቸውን አዳዲስ ዘፈኖች አንጫወትም ብለናል፡፡ የድሮ ክላሲክ የሆኑ ሙዚቃዎችን እንጫወታለን፤የሃገራችንን ዘፈኖች፡፡ አሁን ወጣቱ የሚሰማቸውን አዳዲስ የውጪ ዘፈኖች፤ በየክለቡ የሚዝናናባቸውንም እናቀርባለን፡፡ አራት ድምፃዊያን አሉ፤ እየተፈራረቁ ያዝናናሉ፡፡ አልበሙ ላይ ያሉትንም እንጫወታለን፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሰላሳ ዘፈኖች ይቀርባሉ፡፡ ከምሽቱ 2፡00 ሠዓት ሲሆን በዲጄ ሲያዝናኑ ይቆይና ከ4፡00 ጀምሮ ጃኖ ባንድ በድንቅ ስራዎቹ ብቅ ይላል፡፡ ልዩ ቀን ነው፡፡ 
  •  “ለህዝብ አዲስ ነገር ለማሳየት እንፈልጋለን ሚካኤል ሃይሉ የጃኖ ባንድ ሚዩዚካል ዳይሬክተርና ሊዲ ጊታሪስት ነው፡፡ በጊታሪስትነት ከተለያዩ ባንዶች ጋር የተጫወተው ሚካኤል፤ በራሱ ስቱዲዮ ውስጥ ሙዚቃ ያቀናብራል፡፡ እስካሁን የሚካኤል በላይነህ፣የቴዲ አፍሮ፣የአቤል ሙሉጌታና የዘሪቱ ከበደን አልበም አቀናብሯል፡፡ አንድ ህልም ነበረኝ፡፡ ወደፊት ቢሆንልኝ ብዬ የማስበው፡፡ የዚህ ባንድ ባለቤት አዲስ ገሠሠ ትግል ላይ ነበር፡፡ ልጆች ሰባስቦ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በውጭው ዓለም እንዲታወቅ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ሰዓት እኔ ጋ ደውሎ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ፤ ምን ትላለህ?›› ሲለኝ ሃሳቡና ሃሳቤ ተገጣጠሙ፡፡ ህልሜን እውን ለማድረግ ጃኖን ተቀላቀልኩ፡፡ የዚህችን አሪፍ አገር ባህሏን፣ ህዝቦቿን የውጭው አለም እንዲያውቋት-----ስለዚህች አገር የተለያየ አመለካከት ነው ያለው፤ ..ብዙ ጊዜ በመጥፎ ነው የምትነሳው... ያለን ነገር ብዙም አይታወቅም፤ ለአለም በሚገባ በሙዚቃ ቋንቋ ያለንን ለማስተዋወቅ ነው ሃሳባችን፡፡ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ያላት ሀገር ናት፡፡ አለም ያላየውን ብዙ ጉድ የሚያሰኝ ሙዚቃ ለዓለም ለማሳየት ነው ዓላማችን፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከሮክ የሙዚቃ ሥልት ጋር ቀላቅለን ማስተዋወቅ ነው የምንፈልገው፡፡ በእኛ አገር ደረጃ ሙዚቃ በደንብ በሃላፊነት ደረጃ ተጠንቶ የተሰራበት ጊዜ የለም፡፡ ለህዝብ አዲስ ነገር ለማሳየት ነው የተነሳነው፡፡   ወጣት ሃሌሎያ ተክለፃዲቅ የባንዱ ድምፃዊት ናት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ስራ ኮሌጅ አካውንቲንግ ምሩቅ ናት፡፡ በ
  • ‹‹ኮንሰርታችንን ተጋበዙ፤ትደነቃላችሁ››‹‹ኤርታሌ አልበም›› ውስጥ አጃቢ ድምፃዊት ናት፡፡ ወደ ሙዚቃ የገባሁት ት/ቤት እያለሁ ነው - ካቴድራል ት/ቤት፡፡ ካርኒቫሎችና ፌስቲቫሎች ላይ እዘፍን ነበር፡፡ የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎችን ነበር የምዘፍነው፡፡ ከአኩስቲኮች ጋር እጫወት ነበር፡፡ ያን ጊዜ ነው ከአዲስ ጋር የተዋወቅሁት፡፡ አላመንኩትም ነበር፤ በጣም ትልቅ ነገር ስለሆነ፡፡ እኔንና ሄዋንን ቤላስዌል መጥቶ አየን፤ጥሩ ነው ብሎ ቀጠልን፡፡ ጥሩ ባንሆን ያስወጣን ነበር፡፡ ከጃኖ ባንድ ጋር ብዙ ኮንሰርቶችን እየሰራን ነው፤ በጣም ደስ የሚል ስብስብ ነው፡፡ አስራችንም እንደ አንድ ሰው ነው የምንጠራው፤ ‹‹ጃኖ ባንድ›› ተብለን፡፡ ለሃገራችን አልመን እየሰራን ስለሆነ ተመልካቾች የዛሬን የላፍቶ ሞል ኮንሰርታችንን ተጋበዙ እዩን፤ትደነቃላችሁ...
Read 5873 times Last modified on Saturday, 09 March 2013 14:46
Administrator

Latest from Administrator