Saturday, 09 March 2013 12:11

በሩሲያ 7 ሬስቶራንቶች ያሏቸው ኢትዮጵያዊ ባለሃብት

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(4 votes)

ለሦስት አስርት ዓመታት በራሽያ በትምህርትና በቢዝነስ ሥራ ላይ የቆዩት ዶ/ር አሥራት ለገሰ፤ በቢሾፍቱ ያሰሩት “አዱላላ ሪዞርት” በነገው ዕለት ይመረቃል፡፡ በራሺያም ሰባት ዝነኛ ሬስቶራንቶች እንዳሏቸው ይናገራሉ፡፡ የዛሬ 33 ዓመት እንዴት ወደ ራሽያ እንደሄዱ፣ በምን ምክንያት እዛው እንደቀሩ፣ ወደቢዝነስ የገቡበትን ሁኔታ፣ ለስኬቴ ምክንያት ሆኖኛል ስለሚሉት ራሺያዊ ሼፍ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቢዝነስ ለመጀመር የወጡትን ዳገትና የወረዱትን ቁልቁለት ለጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በስፋት አውግተዋታል፡፡ ስለ ትውልድ፣ ዕድገትና ትምህርት ይንገሩኝ.. የተወለድኩት አዲስ አበባ፣ መድሃኒያለም አካባቢ ነው፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ልደታ ደጅአዝማች ባልቻ ትምህርት ቤት የተከታተልኩ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ እንዳጠናቀቅኩ ዩኒቨርስቲ ለመግባት በቂ ውጤት ቢኖረኝም በወቅቱ በነበረው ሁኔታ አልቻልኩም፡፡ እናም በጅማ ከተማ በተለያዩ የመንግስት መሥሪያቤቶች ውስጥ መሥራት ጀመርኩ - እርሻ ሰብል፣ ጡረታ ሚኒስቴርና የመሳሰሉት፡፡ ከዛም እ.ኤ.አ በ1980 ዓ.ም ስኮላርሺፕ አግኝቼ ራሽያ ሄድኩ፡፡ ኬሚካል ኢንጂነሪንግ የሚባል ትምህርት ልማር ነበር የሄድኩት፡፡ ምክንያቱም ያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዳጅ ይወጣል የሚል ተስፋ ነበር፡፡ ራሽያዎችም ኦጋዴን ውስጥ ነዳጅ እየፈለጉ ነበር፡፡ እንዴት እድሉን አገኙ? የማትሪክ ውጤቴ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂና ሌሎች ትምህርቶችን ውጤት አይተው ነበር የሚመርጡት፡፡

ዝርዝር ነገሩን በወቅቱ ‹‹ሃየር ኮሚሽን›› ተብሎ ይጠራ የነበረ መ/ቤት ነበር የሚመረምረው፡፡ ምን እንደምትማሪ የሚነገርሽ እዛ ከደረስሽ በኋላ ነው፡፡ ለአንድ ዓመት ቋንቋ ከተማርን በኋላ እንደ የዝንባሌያችን በኬሚካል ኢንጂነሪንግ፣ ማይኒንግና ጂኦሎጂ የትምህርት ዘርፎች ተመደብን፡፡ ትምህርቱ ምን ያህል ዓመት ፈጀ? በአጠቃላይ ስድስት ዓመት ሩሲያ ውስጥ ተምሬያለሁ፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የኪስ ገንዘብ ይሰጠን ነበር፡፡ መኖሪያ ቤት በነፃ ነው፤ ዶርምተሪ ውስጥ ነበር የምንኖረው፡፡ ትምህርቱ ሲጠናቀቅ በአገኘነው ውጤት መሠረት ፖስት ግራጅዌት መቀጠል አለመቀጠላችን ለቦርድ ቀርቦ ይወሰናል፡፡ በዛን ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ለትምህርት ወደ ውጭ የተላከ ሰው ‹‹ተጨማሪ ትምህርት ከመቀጠሉ በፊት ወደ አገሩ ተመልሶ ሁለት ዓመት ማገልገል አለበት›› የሚል ደንብ ነበረው፡፡ ሁለት አመት ከሠራ በኋላ ተመልሶ ለፖስት ግራጅዌት መሄድ ይቻላል፡፡ የእኔ የትምህርት ውጤት በጣም ጥሩ ስለነበር የራሽያ ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ተነጋግሮ በዚያው ለፖስት ግራጅዌት እንድቀጥል ተፈቀደልኝ፡፡ አራት ዓመት ተምሬ ተመረቅሁ፡፡

በምን የትምህርት ዘርፍ ተመረቁ? በፊሎሶፊ ኦፍ ኬሚካል ኢንጂነሪንግ ነው የተመረቅሁት፡፡ ወቅቱ የደርግ መንግስት ወድቆ ኢህአዴግ ሥልጣን የያዘበት ነበር፡፡ በራሽያና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ግንኙነት የተቋረጠበት ጊዜ ነው፡፡ በርካታ በራሽያዎች የተያዙ ፕሮጀክቶች ታጥፈው በርካታ ራሽያኖች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነበር፡፡ ከራሽያዎች ጋር ነዳጅ ማውጣት የሚለው ነገር ጥያቄ ውስጥ ገባ፡፡ በቃ እኔም እዛው ቀረሁ፡፡ ራሽያ ውስጥ በተማርኩት ዘርፍ ስራ ፈልጐ መግባት በጣም ከባድ ነበር፡፡ በዚያ ላይ የውጭ ዜጐች እዛ መኖርም ሆነ ተመድበው መስራት አይችሉም፡፡ ብቸኛው አማራጭ የሀገሪቱን ዜጋ ማግባት ነበር፡፡ እናም የራሽያ ዜጋ አገባሁ፡፡ ለስራና ለወረቀት ብለው ነው ያገቡት ወይስ---- ለዜግነት ሳይሆን በቃ ህይወት መጀመር ነበረበት፡፡ ማግባትና መኖር ብቻ ግን በቂ አይደለም “እንዴት ነው የምንኖረው?” የሚለው ገና መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነበር፡፡ ሥራና ገቢ አልነበረዎትም? በወቅቱ ራሽያ ውስጥ በተፈጠረው የሥርዓት ለውጥ የተነሳ የኢኮኖሚ ቀውስ ተከስቶ ነበር፡፡

ሀገሪቱ ለ70 እና 75 ዓመታት ድንበሯ ተደፍሮ አያውቅም፡፡ ያኔ የዲሞክራሲ ለውጥ በመፈጠሩ ድንበሩ ተከፈተ፡፡ እዛ አገር የሌለውን ነገር ከውጭ አስመጥቶ በመሸጥ ትርፍ ለማግኘት ሁሉም መታተር ያዘ፡፡ ሰው ህይወትን ከዜሮ ጀመረ፡፡ በዛን ወቅት ነው በራሽያ ሀብታሞች የተፈጠሩት፡፡ ከዚያ በፊት ግን የራሽያ ባለሙያ ተብሎ የሚሠራ ትልቁ ደሞዙ መቶ ሃያ ሩብል ነበር፡፡ በእርግጥ መንግስት ቤት በነፃ ይሰጣል፡፡ የትምህርት ወጪና የህክምና አገልግሎትም ይሸፍናል፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ደስተኛ ነበር፤ምንም ችግር አልነበረበትም፡፡ ፋብሪካዎች፣ ድርጅቶች፣ ሌላው ቀርቶ ሊስትሮ እንኳን የመንግስት ነበረ፡፡ ካፒታሊዝም ሲመጣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተለወጡ፡፡ የመንግስት ድርጅቶችና ኮርፖሬሽኖች ወደ ግል ባለሃብቶች ሲዛወሩ፤ብዙ ሰዎች መንገድ ላይ ቀሩ፡፡

ለመኖር ሥራ መፈለግ ነበረባቸው፡፡ ፕራይቬታይዜሽን ሲጀመር ፋብሪካዎች፣ አውሮፕላኖች፣ የነዳጅ ጉድጓዶች፣ የወርቅ ማዕድናት ወዘተ በግለሰቦች እጅ ገባ፡፡ በዚህ ቀውስ ውስጥ ማንኛውም ሰው ለማድረግ የሚችለውን ሁሉ ይሞክር ነበር፡፡ ሲጋራ የሚሸጠው ሲጋራ ይሸጣል፤ ማስቲካ የሚሸጠው ማስቲካ ይሸጣል፤እንዲህ እያለ ለመኖር መፍጨርጨር ያዘ፡፡ አንተስ ምን ደረስክ? 120 ዶላር ነበረኝ፡፡ በ120 ዶላር ምንም ዓይነት ቢዝነስ መጀመር አይቻልም በ1990ዎቹ በራሽያ ኮምፒውተር አልነበረም፡፡ ማንኛውም ሰው፤ ከራሽያ ወጥቶ አንድ ኮምፒውተር ይዞ ይመጣ ነበር - ከጀርመን፣ ከሲንጋፖር፣ ከሆንግ ኮንግ፣ ከታይላንድ ወዘተ፡፡ በሁለት መቶና ሦስት መቶ ዶላር የሚሸጠው ኮምፒዩተር ራሽያ ወደ 3ሺህ ዶላር ገደማ ይሸጥ ነበር፡፡

መንግስትም ግለሰቦችም ድርጅቶችም ስራቸውን ለማቀላጠፍና ኮምፒዩተራይዝድ ለማድረግ ይገዛሉ፡፡ ከእኔ ጋር ት/ቤት ሲማር የነበረ ልጅ ሲንጋፖር ይመላለስ ነበር፡፡ እየሄደ አንድ ኮምፒውተር ይዞ ይመጣል፡፡ ሌላ ሰው ይዞ ቢሄድ ግን ሁለት ኮምፒውተር ይዞ መምጣት ይችላል፡፡ እናም ‹‹ወጪህን ችዬ ይዤህ ልሂድ›› አለኝና ሲንጋፖር ተያይዘን ሄድን፡፡ የእኔ ስራ ኮምፒዩተሩን ገዝተን ስንመለስ ለጉምሩክ አንደኛው ኮምፒውተሩ የእኔ መሆኑን መናገር ብቻ ነበር፡፡ ለእርስዎ ወጪ አውጥቶ ምኑን አተረፈ ታዲያ? የእኔ ሙሉ ወጪ 500 ዶላር ነው፤ እሱ ግን 3ሺ ዶላር ይሸጠዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ወደ አራት ጊዜ አብሬው ስመላለስ መንገዱንና መውጫ መግቢያውን አጠናሁ፡፡ ከዛም ራሴን ችዬ መሄድ ጀመርኩ፡፡ ያኔ ነው እንግዲህ ገንዘብ መስራት የጀመርኩት፡፡ እንደውም ሰፋ አድርጌ ኮምፒውተር፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን፣ ካሜራዎች፣ የሙዚቃ መሳሪያዎች ሁሉ ማስገባት ጀመርኩ፡፡ ምን ያህል ገንዘብ አጠራቀሙ? 5ሺ ዶላር ነበረኝ፡፡

ይችን ይዤ ሬስቶራንት ከፈትኩ፡፡ ለዩሮፓውያን የሚሆን ዲሽ የሚሰናዳበት ሬስቶራንትና ትንሽ ባር ከፈትኩ - “ካንትሪ ባር” የሚባል፡፡ በዛን ወቅት ሞስኮ ውስጥ ሬስቶራንቶች ጥቂት ነበሩ፡፡ በሶሻሊዝም ጊዜ በሬስቶራንት ውስጥ ይጠቀሙ የነበሩ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ የሰው ደሞዝ በጣም ትንሽ ስለነበር ሬስቶራንትና ባር ለመጠቀም አቅም አልነበረውም፡፡ በኋላ ግን ካፒታሊዝም ሲመጣ መሸጥና መግዛት የሚባል ነገር ስለተጀመረ ፍላጐት ከፍ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ ባርና ሬስቶራንቶች መከፈት ጀመሩ፡፡ እኔም መሃል ከተማ ላይ ወደ 150 ካሬ ሜትር ቤት ተከራየሁ - ፉስትፉድ ነበር ለመስራት ያሰብኩት፡፡ ቤቱ ባለችው ገንዘብ ተጠጋግኖና ተቀባብቶ፤ለቤቱ የሚያስፈልገው ነገር በሙሉ ተገዛዝቶ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እያለሁ አንድ ሰው በሬን አንኳኩቶ፤ “ምን ልታደርጉ ነው?” ብሎ አፋጠጠን፡፡

“ፋስት ፉድ እየሰራን ልንሸጥ ነው” አልኩት፡፡ “እንዴት ፋስት ፉድ ትሠራለህ?” አለኝ፡፡ “ህዝቡ ፋስት ስለሆነ፤ተርን ኦቨሩ ፋስት ነው፤ስለዚህም ፋስት ፉድ ያዋጣል›› አልኩት፡፡ ‹‹አፍርሱት›› አለ ‹‹ይሄ ፋስት ፉድ የሚባል ነገር የእኛ ልማድ፤የእኛ ባህል አይደለም፡፡ ይህን ምግብ ቤት የማደራጀው ደግሞ እኔ ነኝ፤የደረደራችሁትን በሙሉ አሁን አፍርሱ›› አለን፡፡ እንዴት ማለት --- (ሳቅ) ‹‹በቃ እኔ ነኝ የማደራጀው›› አለኝ፡፡ እኔ ተናድጄ ራሴን አመመኝና ቤቴ ገብቼ ተኛሁ፡፡ በሚቀጥለውም ቀን መጥቶ “አታፈርሱም?” ሲለኝ “አንተ ማነህ፣ ምንድነህ?” ብዬ ጠየቅሁት የሩሲያ መንግስት የሶሻሊስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ምግብ የሚያሰናዳ ሼፍ ነበር፡፡ የአገር መሪዎች ወደ ውጭ አገር ሲሄዱ እሱን ይዘው ነበር የሚሄዱት ያልዞረበት አገር የለም የታወቀ ዓለምአቀፍ ሼፍ ነው፡፡ የ72 ዓመት አዛውንት ነበር፤ ጡረታ ወጥቷል፡፡

በየአገሩ መዞር ሰልችቶታል፡፡ መኖርያው እኔ ልከፍተው ካሰብኩት ቤት ሃምሳ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ እና ምን ነበር ፍላጎቱ? ገንዘብ ሊጠይቅ አስቦ ነው? በፍፁም! በነፃ ነው ማገልገል የፈለገው፡፡ ‹‹የያዝኩትን ሞያ ለወጣቱ ትውልድ ሳላስተላልፍ እንዳልሞት ብዬ ነው… ወጣቶችን በዚህ ሙያ ማሰልጠን እፈልጋለሁ›› አለኝ፡፡ ‹‹ከየት ነው የምታመጣቸው?›› አልኩት፡፡ ‹‹እሱን ለእኔ ተወው---- ብቻ ይህን አፍርስልኝ›› አለ፡፡ በሌለኝ ገንዘብ ያሰማመርኩትን ሁሉ አፈራረስኩት፡፡ ያከራየኝ ሰውዬ ለሶስት ወር ነፃ ኪራይ ነበር የሰጠኝ፡፡ ከሶስት ወር በኋላ ግን ኪራይ መክፈል አለብኝ፤ሶስት ወሯ ደግሞ በጥገናና በፅዳት እንዲሁም ፈቃድ በማውጣት አልቃለች፡፡ እንዴት አምነው አፈራረሱት? ጥርጣሬ ውስጥ አልገቡም? ሶስት ቀን እንቅልፍ አልወሰደኝም፡፡ ሊያታልለኝ ይሆን? ግን ለምን? አልኩ፡፡

ስለሰውዬው ማወቅ የምችልበት መንገድ አልነበረም፤ራሱ የነገረኝን ብቻ አምኜ መቀበል ነበረብኝ፡፡ ‹‹ይሄ ሰውዬ የራሽያ ቤተመንግስት ሼፍ ነበር?›› ብዬ ማንን ልጠይቅ፡፡ ስለዚህ እሱው ባለው መንገድ አፈራርሰን፣ ወንበርና ጠረጴዛ ተደረደረ፡፡ በኋላ ወጣ ብሎ ከሚተላለፈው መንገደኛ “ና አንተ፣ ና አንተ” ብሎ ሰባቱን ይዟቸው መጣ…በጣም ደነገጥኩ፡፡ ‹‹እነዚህ ሞያ የሌላቸውን ልጆች ከመንገድ ሰብስበህ---›› ስለው ‹‹ይሄ የአንተ ጉዳይ አይደለም›› አለኝ፡፡ ምግብ ማብሰል ተጀመረ፡፡ በጣም ስለተደነቅሁ ነገረ ስራውን አይ ነበር፡፡ ሬስቶራንቱ ተከፈተ፤ሜኑ ተፃፈ፡፡ አንድ ወር ሆነው፡፡ ሥራ የለም፡፡ በከተማው ውስጥ ያሉ ሌሎች ባርና ሬስቶራንቶችን ተዟዙሬ ስመለከት ተመጋቢ አላቸው፡፡ የእኛ ሬስቶራንት ደግሞ ግንባር ቦታ ነው፤መስቀለኛ መንገድ ላይ፡፡

ቀስ እያለ አንዱ ሲመጣ በልቶ ሲሄድ፤አንዱ ሲመጣ በልቶ ሲሄድ--- አንዱ ለሌላው እየተናገረ------አምስትም ስድስትም ሆነው ተመልሰው ይመጡ ጀመር ---ከሶስት ወር በኋላ በራፌ ላይ ሰልፍ ሆነ፡፡ በመጨረሻ ጠረጴዛ ለአንድ ወርና ለሁለት ወር ቡክ ማድረግ ተጀመረ፡፡ የተሰጠኝና የተከራየሁት ቦታ መቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ነበር፡፡ ያን ያከራየኝን ሰውዬ ሄድኩና ሁኔታውን አስረድቼ ‹‹ግድግዳውን ገፍቼ ላስፋው›› አልኩት፡፡ መቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ጨመረልኝ፡፡ አሁንም እየሰፋን ሄደን፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ላስፋው ብዬ ጠየቅሁት፡፡ አንድ ሺህ አምስት መቶ ካሬውን በሙሉ ስጠኝ አልኩት፡፡ ራሽያ በጣም ብርድ ስላለ ሰዎች መብላትና መጠጣት ይፈልጋሉ፡፡ ቮድካ ይጠጣሉ፤ምግብ ይበላሉ፡፡ ያከራየኝ ሰው ያልኩሽ የባንክ እዳ ነበረበት፡፡

ገንዘቡን መክፈል ስላልቻለ ባንክ ቤቱን ሊወስደው መጣ፡፡ ሰውየው ወደ እኔ መጥቶ “መንግስት ቤቱን ሊወርሰው ነው፡፡ የአንተም ቢዝነስ ገደል ሊገባ ነው፤ከቻልክ የባንኩን እዳ ክፈልና ይሄንን ቤት ውሰድልኝ” አለ፡፡ ሶስት ዓመት ሰርቻለሁ፤አቅሙ አለኝ አልኩና ቤቱን ገዛሁት፡፡ ሩሲያዊው ሼፍስ በምን ሁኔታ ቀጠለ ---- ለመሆኑ ደሞዝ ወይም ሼር ነበረው? ደሞዝም ሆነ ሼር የለውም፡፡ በወር በሁለት ወር…ለምኜ 5 ሺ 6 ሺ ብር ታግዬ ኪሱ ውስጥ እከትለታለሁ እንጂ ገንዘብ አይፈልግም፡፡ ምን ያህል ሰራተኞች ቀጠራችሁ? በፊት አስራ አምስት ራሽያዎች ነበሩ፤ በኋላ ወደ ሃያ አምስት ደረሱ፡፡ በአሁኑ ሰዓት 50 ደርሰዋል፡፡ ሌሎቹም ከመንገድ ነው የተቀጠሩት? አዎ፡፡ ዛሬ ግን በራሽያ ውስጥ የታወቁ ሼፎች ናቸው፡፡ ሰውየው ኪችን ውስጥ አብሯቸው ነበር የሚሰራው፡፡ “እኔ ለሰው ውሃ ቀቅዬ ማብላት እችላለሁ፤ ምንም ነገር የለም በምትሉት ኪችን አስገቡኝና ምግብ ሰርቼ እወጣለሁ” ይላል፡፡

ከመንገድ ሰብስቦ ያመጣቸውን ልጆች ካሰለጠናቸው በኋላ የማማሰያ ዱላ ይዞ ነው የሚቆመው፡፡ ከአስተማራቸው ወጣ ካሉ፤ እጃቸውን በማማሰያ ይመታቸዋል፡፡ በየቀኑ ቅዳሜ የለ፣ እሁድ ለአስራ ሁለት ሰዓት ቆሞ ይሰራል፡፡ አስቢ....የ72 ዓመት አዛውንት!! ራሽያኖች ስራ ወዳድ ናቸው፡፡ ቤታችን ዝነኛ እየሆነ መጣ፡፡ አንድ ቀን አዛውንቱ ሼፍ መጣና ‹‹መስራት ከጀመርኩ ሦስት ዓመት ሆነኝ፡፡ የቀረችኝ ጊዜ ትንሽ ናት፡፡ በህይወት እያለሁ ሌላ ሬስቶራንት ክፈት›› አለኝ፡፡ ሁለተኛ ሬስቶራንት ከፈትኩ፡፡ እሱ ገብቶ አደራጀው፡፡ ሌሎችንም በተከታታይ በተለያዩ ስሞች ከፈትኩ.....በዚህ ዓይነት ሁኔታ አሁን ሰባት ሬስቶራንቶችን በራሽያ ከፍቻለሁ፡፡ ዝነኛ ሬስቶራንቶች፡፡ ሰውዬው ለሙያው ያለው ፍቅር አስገራሚ ነው- እንደሱ ብቻ መሰለሽ፤ ሁልጊዜ ወደ ሬስቶራንቶቹ ሲመጣ… አለባበሱ ፅድት ያለ ነበር፡፡

ቁመቱ አንድ ሜትር ከሰባ ሁለት ነው፡፡ በዛ ቁመቱ ሱፍ ለብሶ፣ነጭ ሸሚዙንና ከረባቱን አድርጐ፤ .......ጫማው ራሱ ያብረቀርቃል፡፡ ወደ ስራ ሲገባም ከሥራ ሲወጣም እንደዚሁ ነው፡፡ የምግብ መስሪያ ልብሱ (ሽርጥ) ከበረዶ የነፃ ነው፡፡ ያሰለጠናቸው ወጣቶች ታዲያ በሱ ወጡ? ሰልጣኙ ከመንገድም ይምጣ፤ ከዩኒቨርስቲ ስራውን የሚያሳየው ለሰላሳ ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ ፍላጎት የሌለው ሰው ሲገጥመው “ማንኛውም ሰው የሚወደውን ነገር ነው መስራት ያለበት፤ ለስራ ብሎ አይደለም መቀጠር ያለበት፡፡ ሹፌርነት እምቢ ብሎህ ኩክነት ልትቀጠር መጥተህ አንተም እኔም ከምንሰቃይ ሂድና መኪና ንዳ” ይላቸዋል፡፡ አብረን መስራት ከጀመርን ከአምስት ዓመት በኋላ አንድ ቀን 12 ሰዓት ላይ እንደወትሮው ልብሱን እንደለበሰ፤ “ቻው፣ ከዚህ በኋላ በርታ፤ የምንገናኝ አይመስለኝም” ብሎኝ ወጣ፡፡ “ሊሆን አይችልም” ስለው “አይ በቃ ደክሞኛል” አለ፡፡ እኔም “ቢደክምህም ጡረታም ብትወጣ እየመጣህ እዚህ ትቀመጣለህ እንጂ----›› “በፍፁም” ብሎ ተከራከረኝ፡፡

ያን ጊዜ ነገሩን ያየሁት እንደቀልድ ነበር፡፡ ምክንያቱም ብቻውን ነው የሚኖረው፤ ሚስቱ ሞታለች፤ ልጆቹ አድገው ወጥተዋል፡፡ አይቀርም ብዬ ነበር፡፡ ሆኖም ሁለት ሶስት ቀን ጠፋብኝ፡፡ በሶስተኛው ቀን ግን ‹‹ምን ነካው›› ብዬ እርሱ ያሰለጠናቸውን ልጆች ሰብስቤ ወደ መኖሪያ ቤቱ ስሄድ ሞቷል፡፡ ምግብ አዘገጃጅቶ፤ጫማውን ወልውሎ ከረባቱን አስሮ፤ አልጋ ላይ ወጥቶ በሩን ክፍት አድርጐ የተኛ መስሎ ጋደም ብሏል....ግን አሸልቧል፡፡ ወስደን ቀበርነው፡፡ ለእኔ በጣም ትልቅ ሀዘን ነበር፡፡ በዚህ ሰው ምክንያት ነው ይሄን ሁሉ ስራ ያገኘሁት፡፡ ሼፉ ከአረፉ በኋላ ቢዝነሱን ለመቀጠል አልተቸገራችሁም? ያሰለጠናቸው የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች 50 ደርሰዋል፡፡ እነሱ ክፍያቸው አድጎላቸው መስራት ጀመሩ፡፡ እርሱ ጥሎት የሄደው ነገር እስከዛሬም ይሰራል፡፡ በሬስቶራንት ቢዝነስ ለስንት አመት ሰሩ? 17 ዓመት ሰራሁ፡፡

ከዛ ጊዜው እየተለወጠ መጣ፡፡ በሬስቶራንቶችዎ ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች አሉ? አዎ…ግን ብዙዎቹ ሙያ ለመማር አይፈልጉም፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ነው፡፡ ኪችን ውስጥ አስገብተሽው ‹‹ኩክ›› ሁን ብትይው እሽ አይልሽም፡፡ ‹‹ወጥ ሰሪ ልባል›› ይላል፡፡ ዌይተርነትን ይመርጣሉ፡፡ የእኛ ባህል፣ አስተዳደጋችን ጥሩ አይደለም፡፡ ‹‹እናቴ ብትሰማ ኪችን ውስጥ ስጋ እየቀቀለ ነው ብላ ታዝንብኛለች›› ብለው ያስባሉ፡፡ ብዙዎቹ ፈረንሳይ ወይም ጀርመን እስክገባ ድረስ ነው ብለው ዝም ብለው ይቀመጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ እንዴት አሰቡ? በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ እየመጣሁ እነጋገር ነበር፤የማስበውን ስራ አዋጭነት እያጠናሁና እያየሁ እሄዳለሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ወደዚህ አገር መጥተው ቢዝነስ ጀምረው ከስረው የተመለሱትን አያለሁ፤ የሚባለውን እሰማለሁ አጠናለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ግን ወስኜ መጣሁ፡፡ ቢዝነስ ለመጀመር ማለት ነው? አዎ፡፡ መሬት ፍለጋ በየቢሮው ማመልከቻ ይዤ መሄድ ጀመርኩ፡፡ አንዱ እዛ ይለኛል ሌላው እዚህ ይላል፤በቃ እጨርሳለሁ ብዬ ያሰብኩት ቀን አለቀ፡፡ ውጣ ውረዱ ከባድ ነበር፡፡ ነገሩ ሳይያያዝ ይቀርና ተመልሼ እሄዳለሁ፡፡

ከዛ ምን ሆነ ---- የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን ወደ ራሽያ ሲመጡ በኤምባሲው በኩል ራት ሊበሉ እኔ ሬስቶራንት ጎራ ይላሉ፡፡ እኔ ደግሞ ከተማ ውስጥ አልነበርኩም፡፡ ልጆቼን ይዤ ሌላ አገር ቫኬሽን ላይ ነበርኩ፡፡ አቶ ስዩም “ይሄ ሰውዬ ኢትዮጵያ ሲመጣ እኔን ሳያገኝ እንዳይመለስ›› ብለው ሞባይል ስልካቸውን ትተውልኝ ይመለሳሉ፡፡ ከውጭ ስመጣ አምባሳደሩ ጠሩኝና ‹‹አቶ ስዩም በጣም ተናደውብህ ነው የሄዱት፤ሞባይል ስልካቸውን ትተውልሃል፤ እርሳቸውን ሳታገኝ እንዳትመጣ፤ ይህን ብታደርግ ኤርፖርት ላይ ትያዛለህ›› ብለው ቀለዱና ስልካቸውን ሰጡኝ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፤አገኘኋቸውና ለሁለት ሰዓት ገደማ አወራን፡፡ በመንግስት በኩል አስፈላጊው እርዳታ እንደሚደረግልኝና እዛ ማድረግ የቻልኩትን ነገር ሁሉ እዚህ ማድረግ እንደምችል ነገሩኝ፡፡ ለክልል ሰዎች ስልክ ደወሉ ‹‹ለዚህ ሰው ምስክር እኔ ነኝ…አስፈላጊውን ነገር አድርጉለት፤ መጥቶ አውርቶ የሚሄድ ሰው አይደለም፤እዛ አገር የሰራቸውን ነገሮች እዚህ መስራት ይችላል፣ እኔ አውቃለሁ›› አሉ፤ እኔም በጣም ተመላለስኩ፤ ግን አልሆነም፡፡ ችግሩ ምን ነበር ይላሉ? የባለሞያ ብቃት ችግር ይታየኛል፡፡ እየተሳደብኩ አይደለም፡፡ ‹‹ሪዞርት›› ብለሽ ለማስረዳት ስትሞክሪ አይረዱሽም፡፡ የቪዢን (ራዕይ) ጉዳይ፣ ኤክስፖዠር (ያለመተዋወቅ) ስለሌለ ይመስለኛል፡፡ እስከመጨረሻው ተስፋ አልቆርጥም ብዬ መመላለሴን ቀጠልኩኝ፡፡ ቢሆንም ግን አንዴ ‹‹ደብዳቤ›› ይሉኛል... ቢዝነስ ፕሮፖዛሉን ላስገባ አንድ ቢሮ ስሄድ ‹‹እኔ ጋ አይደለም የሚገባው…መዝገብ ቤት ነው›› አሉኝ፡፡ መዝገብ ቤት ሄድኩ፡፡ እዛ ደግሞ ‹‹ኦርሪጂናሉን አንቀበልም፤ ፎቶኮፒውን አምጣ›› አሉ፡፡ ‹‹የት ነው ፎቶኮፒ ያለው?›› ስላቸው ‹‹ከመንገድ ማዶ፣ እዛ ሂድና ኮፒ አድርግ›› አሉኝ፡፡

ወጣሁና በዛው ቀረሁ፤ አልተመለስኩም፡፡ ተስፋ ቆረጡ? ልጆቼን ወደ አሜሪካ ይዤ መሄድ ስለነበረብኝ ነው፡፡ ከዚያም አሜሪካ እህቴ ቤት ቁጭ ብዬ አንድ ጓደኛዬ ደወለልኝ፡፡ “እዚህ ከኢትዮጵያ ኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት መጥተው ኢንቨስት አድርጉ ብለው አሜሪካን እየዞሩ ነውና…እራት የሚበሉበት ቦታ ሄደን ለምን ከእነርሱ ጋር ራት አንበላም” አለኝ፡፡ ከዲሲ ቨርጂኒያ ነድቼ ሄድኩ፡፡ ትልቅ ልኡክ (ዴሊጌሽን) ነው ተሰብስበው ራት ይበላሉ፡፡ ገብቼ ራሴን አስተዋወቅኋቸው፡፡ አቶ ሙክታር ነበሩ፡፡ ‹‹እዚህ አሜሪካ ድረስ መጥታችሁ ከምትጠይቁ እኛ እዛ ድረስ እየመጣን ስንለምናችሁ ለምን አታስተናግዱንም፤ይኸው ከአምስት ዓመት በላይ ተመላልሼ ምንም አልተሳካልኝም›› ስላቸው በጣም ደነገጡ፡፡ ‹‹እኔ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ” ብለው አቶ ሙክታር ሞባይላቸውን ሰጡኝ፡፡ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ አውሮፕላኑ እንዳረፈ ደውልልኝ›› አሉ፡፡ ሞስኮ ተመልሼ ሄጄ ከወራት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፡፡ እንዳሉት ደወልኩላቸው፡፡ ቢሮአቸው ጠሩኝ፡፡ ቢሮ ሄድኩና የደረሰብኝን ሁሉ አጫወትኳቸው...፡፡ ‹‹የት ነው ቦታ የምትፈልገው?›› አሉኝ፡፡ ‹‹እኔ አላውቅም ---- ያላችሁን ቦታ አሳዩኝ›› አልኩ፡፡ በወቅቱ የደብረዘይት ከንቲባ ለነበሩት አቶ ድሪባ ለተባሉ ሰው ደወሉና ‹‹ነገ ጠዋት 3 ሰዓት ደብረዘይት አግኘው›› ብለው ስልክ ሰጡኝ፡፡ በነጋታው ደብረዘይት አየር ሃይል ተቀጣጥረን ተገናኘን፡፡ ብቻቸውን አልነበሩም ሲመጡ መሐንዲሶች፣ የመሬት ይዞታ፣የኢንቨስትመንት ክፍል ሃላፊዎች ተሰባስበው መጡ፡፡ እርስ በእርስ ይነጋገራሉ ‹‹እዛ ጋ ያለውን ...እዚህ ጋ ያለውን ቦታ›› እያሉ፡፡ እኔ ስለሚሉት ሀይቅ ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ያንን ሃይቅ አይቼውም አላውቅ፡፡ አዲስ አበባ ተወልጄ አድጌ ሃይቅም እንዳለ አላውቅም፡፡ እናም ይዘውኝ ሄዱ፡፡ ነገ መርቀን የምንከፍተውን የሪዞርት ቦታ ሲያሳዩኝ ‹‹ይሄ ይሆናል›› አልኳቸው፡፡ ተመልሰን ሄደን ለአቶ ሙክታር ደወለለትና ‹‹ልስጠው?›› አለው፡፡ ‹‹ስጠው›› አለው፡፡ወዲያው ካርታ ሰርተው ሰጡኝና ወሰድኩ፡፡ በ15 ቀን ውስጥ አጥር ማጠር ጀመርኩ፡፡ ተመልሼ ራሽያ ሄድኩ፤ኮንትራክተሮችና ዲዛይነሮችን ማዘጋጀት ጀመርኩ፡፡ በራሽያ በየቦታው ያሉኝን ሬስቶራንቶች ለስራ ከእኔ ጋር ይሰራ የነበረ መሐንዲስ ይዤ መጣሁ ከጠዋት እስከ ማታ ውሏችን እዚያው ቦታ ላይ ሆነ - ድንኳን ጥለን፡፡ የዛሬ ስድስት ዓመት ስራው ተጀመረ እንደ ዳያስፖራ ኢንቨስተር እርስዎ ከገጠመዎት ተነስተው መሻሻል ይገባዋል የሚሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? እዚች አገር ላይ ‹‹ገንዘብ አገኛለሁ፤ትርፍ አገኛለሁ›› ተብሎ ብቻ አይደለም የሚመጣው፡፡ አገር ስለሆነ ለአገር ልጆች የሥራ እድል መክፈትም ደስ የሚያሰኝ ነገር ስላለውም ጭምር ነው፡፡ ኤርፖርት ላይ ግን ሻንጣዬን ከፍቶ የእኔን ፓንት ሲቆጥር ያበሳጫኛል፡፡ ‹‹ይህን ሁሉ ልታደርገው ነው ያመጣኸው ልትሸጠው ነው?›› ብሎ ሲጠይቅ ያናድዳል፡፡

በሆቴልና ቱሪዝም ግንባታ ለተሰማሩ ከቀረጥ ነፃ መብት አላችሁ የሚባል ነገር አለ፡፡ እኔም ተብያለሁ፤ ግን እቃዎቹን ጭኜ ሳመጣ “ይሄ አይቻልም፤ ይሄኛው ምናልባት ይቻል ይሆናል፤ ይሄኛው ደግሞ ምንድነው? ይሄን እኔ ስለማላውቀው ይከፈልበታል…ይሄን ማታ ኢንተርኔት ውስጥ አይቼው እነግርሃለሁ” ብለው ድካምሽን ከንቱ ሲያደርጉት ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ እነዚህ ሰዎች መማር፤መሰልጠን አለባቸው፡፡ መጀመሪያ ጉምሩክ ስትሄጂ አንቺን የሚያስቡሽ እንደ ሌባ፣እንደ አጭበርባሪ ነው .. ያጉላሉሻል፡፡ መንግስት እኮ ኢንቨስተሮችን አበረታታለሁ እያለ ነው? ምን እስኪ ንገሪኝ፡፡ ይህንን የሚከታተል አንድ ከፍተኛ የሆነ የመንግስት አካል መፈጠር አለበት፡፡ እኔ ‹‹ኢንቨስተር ነኝ›› ብዬ ስመጣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ፣ በክልሉ መንግስት ወይም በሚመለከተው ወገን “የእኛ አባት” መፈጠር አለበት፡፡ እኛ እኮ እዚህ አገር ስንመጣ እውር ነን፡፡ እኔ የዛሬ 30 ዓመት ትቼው የሄድኩት አገርና ዛሬ ያለው የተለያየ ነው፡፡ ‹‹በዚህ መስክ ኢንቨስትመንት ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ኢንቨስትመንት ይህንን አድርጉ›› ብሎ ቢያንስ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ‹‹ከምን ደረሰ፣ ምን ችግር አለ? ምን ደረሳችሁ›› ብሎ የሚጠይቀን የለም፡፡ መረጃም ማግኘት ከባድ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ቢሮ ከፍተው ላንድ ክሩዘር ይዘው ‹‹ጉዳይ እናስፈጽማለን›› የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ‹‹ኮንሰልታንት ነን›› ብለው፡፡ ‹‹የጠ/ሚ ቢሮን በእግሬ ነው የምከፍተው፤ ለእኔ ቀላል ነው›› ሲሉሽ አንቺ ግኡዝ ስለሆንሽ…‹‹እሺ፤ አድርግልኝ›› ነው የምትይው፡፡

እንዴት ደብዳቤ እንደሚፃፍ፣ የሚኒስትሩ ቢሮ የት እንዳለ እሱ ያውቀዋል…በዚህ መካከል ብዙ ገንዘቦች ይጭበረበራሉ፡፡ ብዙ ሰዎች አልቅሰው የጀመሩትን ትተው፤የገነቡትን ጥለው ይጠፋሉ፡፡ “ይህቺ አገር” ብለው በመማረር፡፡ ለምን? አባት የለንማ፡፡ ወደፊትስ ምን ያስባሉ? ጥናት እያደረግሁ ይሄንኑ ስራ ነው የማሳድገው፡፡ የምንጣፍ ስራ ያዋጣል ብዬ ወደዚያ አልዞርም፡፡ ከሆቴልና ቱሪዝም ጋር የተገናኙ የቢዝነስ ስራዎች እንጂ ..ሲሚንቶ ፋብሪካ ለመክፈት ወይንም ሌላ የሚያዋጣ ነገር ፍለጋ አልዋትትም፡፡ ዋናው ነገር አስተሳሰብ አመለካከት ነው፡፡ ስራ በጀመርንባቸው በዚህ ስድስት ወር ውስጥ በጣም ጥሩ የሚያሰሩ ሁኔታዎች አሉ፡፡

Read 5637 times