Saturday, 09 March 2013 12:07

“የጨረታ መነሻ ዋጋ አስቀምጠን አናውቅም” - ኤግዚቢሽን ማዕከል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለ10 ዓመታት ኮንትራት ወስዶ እያስተዳደረው ቢሆንም ባለቤቱ ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው- ኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት አማካይ አመታዊ ገቢው 450 ሺ ብር ነበር፡፡ አሁን ግን ዓመታዊ ገቢው 20 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከዚህ ገቢ 50 በመቶውን የሚሸፍኑት ለአዲስ አመት፣ ገናና ፋሲካ በዓላት ባዛርና ኤግዚቢሽን በሚገኘው የጨረታ ገቢ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ማዕከሉ ከጊዜ ወደጊዜ እየናረ ለመጣው የጨረታ ዋጋ መንስኤዎቹ ተጫራቾች ናቸው ቢልም የኤግዚቢሽንና ባዛር አዘጋጆች ግን የማዕከሉም ፍላጐት አለበት ይላሉ፡፡

የጨረታውን መናር፣ አጠቃላይ የማዕከሉን እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክታ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ፤ ከማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከአቶ ታምራት አድማሱ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ለምንድነው የጨረታ ዋጋው በየጊዜው እየናረ የመጣው? በመሠረቱ ማዕከሉ ሁለት አይነት አሠራር ነው ያለው፡፡ አንደኛ የአዲስ አመት የገና እና የፋሲካ በአሎች በአዘጋጆች፣ በተሣታፊዎችና በጐብኚዎች በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቁና የሚፈለጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሶስቱ በሁሉም በኩል ከፍተኛ ተፈላጊነት ስላላቸው ሶስቱን በጨረታ እንሰጣለን፡፡ ሁለተኛውና ሌሎቹ በሽያጭ ማኑዋል መሠረት ዝቅተኛ ክፍያ ነው የሚጠየቅባቸው፡፡ ሌሎች ሲሉ የትኞቹን ነው? እንግዲህ በየዘርፉ ያሉ ልዩ የንግድ ትርዒቶች እንዲበረታቱ በሚል በICT፣ በባህል፣ በቱሪዝም፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርናና በመሳሰሉት ዘርፎች ከ50 በላይ ዝግጅቶች በዓመት ውስጥ ይካሄዳሉ፡፡ እነዚህ ኤግዚቢሽኖች በመደበኛ ዋጋና በመደበኛ አሠራር የሚካሄዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሲከናወኑ ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ ፕሮግራም እንዲይዙ በማድረግ የሚስተናገዱበት ሁኔታ አለ፡፡

ይሄኛው ከንግድ ትርኢትና ኤግዚቢሽን መስፋፋት አኳያ ኤግዚቢሽን ሲካሄድ ለአገር እድገትና ልማት ያለውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ አገር አዘጋጆች በጣም በዝቅተኛ ዋጋ ነው የምንሰጠው፡፡ ከእነዚህኞቹ ማለትም ከአዲስ አመት፣ ከገናና ከፋሲካ ጋር በምንም መልኩ አይገናኙም፡፡ ሁለቱ አሠራሮች እነዚህ ናቸው፡፡ የአዲስ አመት፣ የገናና የፋሲካ በዓላት የጨረታ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የሄደበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ? ከላይ የገለጽሻቸው የኤግዚቢሽንና ባዛር ጨረታዎች የበዙት ፍላጐቶች እየጨመሩ በመሄዳቸው ነው፡፡ እኛ የጨረታ መነሻ ዋጋ አንጠይቅም፡፡ ገበያው የሰጠንን ነው የምንወስደው፡፡ በእርግጥ በጨረታ ሰነዱ ላይ ባለፈው ዓመት አዲስ ዓመት ዝግጅት ላይ ጨረታውን ያሸነፈው እከሌ የተባለ ድርጅት ያሸነፈበት ዋጋ ይሄ ነው ብለን በግራፍ እናሳየለን፤ ዳታውን፡፡ ከዚያ በተረፈ በዚህ መነሻ ተጫረቱ የሚል ነገር አላስቀመጥንም፤ አናስቀምጥም፡፡

መጠየቁን ያልፈለግነው ለአሠራራችን እንዲያመቸን ነው፡፡ እኛ የሚሰጠን ዋጋ ላይ በመንተራስና ራሳችን ታሳቢ የምናደርጋቸውን ነገሮች በመጨመር ይቀጥል አይቀጥል የሚለው ይወሰናል፡፡ በነእዚህ መሠረት አዘጋጆች፣ ተሳታፊዎችና ጐብኚዎች በጉጉት የሚጠብቋቸውን እነዚህን በዓላት የሚመጥን አዘጋጅ ካላገኘ ማዕከሉ የማስተናገድ ግዴታ አለበት፡፡ አይመጥኑም የሚባሉት ምን ምን ነገሮች ናቸው? ገበያው ላይ በምንገባበት ሰዓት ገንዘቡ ባለፈው አመት ያን ያህል ከሆነ በዘንድሮው ዓመት ስንት ይመጣል ሲባል ወጪዎች እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ ተፈላጊነቱም ይጨምራል፤ የብር ግሽበቱም አለ፡፡ ስለዚህ ይህንን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ ያዋጣናል የሚሉትን ማምጣት የእነርሱ ድርሻ ነው፡፡ የገቢ ምንጫቸው በማያሻማ ሁኔታ ይታወቃል፡፡ ወጪያቸውም ቢሆን አንደኛውና ዋናው ለማዕከሉ የሚከፍሉት ነው፡፡ ሁለተኛ ለአስተዳደራዊ ሥራዎች፣ ለፕሮሞሽንና ኢንተርቴይመንት ሥራዎች ብለው የፕሮጀክት ሰነድ አዘጋጅተው እንዲቀርቡ ነው የምንመክራቸው፡፡ ይሄ ራሱ ራሱን የቻለ ትልቅ ፕሮጀክት በመሆኑ በተሟላ መልኩ መሠራት አለበት፡፡ እና በዚህ መልኩ ደረጃውን ጠብቆ ካልተሠራ አይመጥኑም እንላለን፡፡ ምክንያቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰው ከኤግዚቢሽኑ የሚጠብቀው ነገር ከፍ እያለ መጥቷል፡፡

አንዱ አስተማማኝ ነገር ሰው በየበዓላቱ የሚጠብቀው በመሆኑ የገበያ ችግር የለበትም፡፡ ችግሩ ምን ያህል ለውድድር ላቅርብ የሚለው ነው፡፡ አንደኛ ከሚባለው ሰው በትኬት ምን ያህል እናገኛለን ሲሉ በአማካይ በቀን 20ሺ ሰው ይገባል የሚል አለ፡፡ በአንድ ወቅት የጐብኚዎች መግቢያ ሶስት ብር ነበር፡፡ ከዚያ አምስት ስድስት እየተባለ አሁን አስር ብር ደርሷል፡፡ ሌሎችም አዘጋጆች ሲያጠኑ ይህንኑ ነገር ያውቁታል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ እናድርግና እንጨምር ቢሉ ጐብኚው አይመጣም፡፡ ሁሉም አሠራሮች ይታወቃሉ፡፡ በዚህ መሠረት ይቀጥላል፡፡ የዘንድሮው አሸናፊ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው “አንድነት ፕሪንተር” የተባለ ድርጅት ነው፡፡ ከተወዳዳሪዎች በስንት ብር ብልጫ ነው ያሸነፈው? እንግዲህ በአሁኑ ሰዓት በገንዘብ ደረጃ ያሸነፈው አንድነት ፕሪንተር የተባለ ድርጅት ነው፡፡ በ4.9 ሚሊዮን ብር ማለት ነው፡፡ 555 ብር ብልጫ በማሳየቱ ነው ሴንቸሪ ፕሮሞሽንን በልጦ የተገኘው፡፡ ይሄ የሚያመለክተው በጥናት እየተሠራ መሆኑን ነው፡፡ ተቀራራቢ የሆነ መረጃ ነው የሚያገኙት ማለት ነው፡፡ ዋናው ነገር እኛ መረጃ ለአዘጋጆች ከመስጠት ውጭ የመነሻ ዋጋ አናስቀምጥም፡፡

የመጫረቻ ዋጋው እየናረ በሄደ ቁጥር አዘጋጆቹ በተሳታፊዎችና በጐብኚዎች ላይ በሚጨምሩት ዋጋ የተነሳ ለመሳተፍም ሆነ ለጉብኝት አያበረታታም በሚል የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ምላሽዎ ምንድን ነው? አሁን ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ሃላፊነት ስላለብን እንመለከታለን፤ እንከታተላለን፡፡ የዝግጅቱ ዋና ዋና ነገሮች ምንድን ናቸው ስንል አሁን የመዝናኛውን ሁኔታ ማየት ይቻላል፡፡ አዘጋጆቹ ለመዝናኛው ብቻ ከ900ሺ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ ያወጣሉ፡፡ ይሄ ማለት ከተማዋ ውስጥ አሉ የተባሉ አርቲስቶች ይመጣሉ፡፡ ህብረተሰቡ እነዚህን አርቲስቶች ኮንሰርት ላይ ላግኝ ቢል ሁለት መቶና ሶስት መቶ ብር እንዲከፍል ይጠየቃል፡፡ ስለዚህ ጐብኚዎች 10 ብር ከፍዬ እነዚህን የማደንቃቸውን አርቲስቶች ካገኘሁ በተመጣጣኝ ዋጋ የምፈልገውን ከገበየሁ፣ ምግቡን መጠጡንና አጠቃላይ የበዓሉን ድባብ ካየሁ ትልቅ ነገር ነው ይልና በስፋት ይገባል፡፡ ይህ ፍላጐት እየጠነከረ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሄደውም ህብረተሰቡ በቀላል ዋጋ ሁሉንም በአንድ ቦታ የሚያገኝ በመሆኑ ነው፡፡ እኛ አሁን በጣም እየተቸገርን ያለንበት ሁኔታ ይሄው የሰው ብዛት ነው፡፡

አንዳንዴ ጠጠር መጣያ እንኳን ቦታ ይጠፋል፡፡ ጐብኚው በጣም እጅግ በጣም ይመጣል እና ህዝቡ ታሳቢ የሚያደርጋቸው ጥቅሞች ስላሉ መግቢያው 10 ብር መሆኑ ከመምጣት አላገደውም፡፡ የተሳታፊዎቹ ጉዳይስ እንዴት ይታያል? የጨረታ አሸናፊዎች (አዘጋጆች) ዋጋ በጨመረ ቁጥር በተሳታፊዎቹ ላይ መጫናቸው አይቀርም ይሄ ያበረታታል ይላሉ? ዋናውና ዋናው ነገር ተሳታፊዎችም ቢሆኑ ባያዋጣቸው አይመጡም፡፡ ዋናው ጥቅማቸው ለረጅም ጊዜ አከማችተው ይዘውት የነበረውን መዓት እቃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሸጠው ያጠናቅቃሉ፡፡ ያለኝ መረጃ የተሳፊዎቹ የጥቅም ምስጢር ያለው እዚህ ነጥብ ላይ ነው፡፡፡ አሁን ፉክክሩም ብሩም የበዛው፣ ተጫራቾችም ፍላጐት እያሳዩና ዋጋ እየጨመሩ የመጡበት ሁኔታ የኤግዚቢሽን አቀራረቡ ከፍ እያለ በመምጣቱ ነው፡፡ ሁሌ አዳዲስ ፈጠራ አለ፡፡ ህዝቡ 10 ብር ከፍሎ ሲገባ ሁሉ ተሟልቶለት፣ ሁሉንም ነገር አግኝቶ ተዝናንቶ ገዝቶ ይሄዳል፡፡ ተሳታፊውም ዓመት ሁለት ዓመት ይዞት የተቀመጠውን እቃ በአንዴ ሸጦ እና አጠናቅቆ ይሄዳል፤ አዘጋጆቹም ከዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ አትርፈውና ተደስተው ቢሄዱ ነው በየጊዜው የጨረታ ብሩን ከፍ እያደረጉ የሄዱት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ ተሳታፊም ሆነ ጐብኚ ምንም አይነት ዋጋ ብትጨምሪ አይቀርም፡፡

ያ ማለት ግን ዝም ብሎ ገንዘብ እየተጫነ ገበያውን የማያረጋጋ ነገር እየጨመሩና ባልተጠና አካሄድ እየሄዱ፣ የነገና ከነገ ወዲያን ደንበኝነት የሚያበላሹ ይቀጥላሉ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አሁን በትክክል ያለው ነገር እነዚህን ዓመታዊ በዓላት ማንም ያዘጋጀው ማንም ህብረተሰብ ዝግጁ ሆኖ በጉጉት የሚጠብቅ መሆኑን ነው የማውቀው፡፡ ማዕከሉ ራሱን እንደ ነጋዴ ነው የሚያየው ወይስ? ነው እንጂ! የመንግስት የልማት ድርጅት አይደለም እንዴ? ይሄ እኮ ግልጽ ነው፤ ለትርፍ የተቋቋመ የልማት ድርጅት በመሆኑ ነጋዴ ነው፡፡ ከአንዳንድ አዘጋጆች በሰበሰብኩት አስተያየት የጨረታ ዋጋው አሁን ባለበት ከቀጠለ አስጊ በመሆኑ ቋሚ ዋጋ ኖሮት አዘጋጆች በዓመትም ሆነ በሁለት ዓመት ቢደርሰን ጥሩ ነው የሚል ሃሳብ አንስተዋል፡፡ ምን አስተያየት አለዎት? እኔ በዚህ ላይ አስተያየት ለመስጠት ይከብደኛል፡፡ በዓመት ውስጥ ከሚካሄዱት 50 ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ውስጥ ሶስቱ እነዚህ ናቸው፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ ለትርፍ የተቋቋመ በመሆኑ ከተቋቋመበት አላማ አኳያ መስራት ያለበትን መስራት አለበት የሚል እምነት አለን፡፡ በማዕከሉ የውጭም ሆነ የውስጥ ነጋዴዎች መጥተው በየአመቱ ቋሚ በሆነ ዋጋና አሠራር የሚያካሂዱበት አለ፡፡ ሶስቱ በዓላት ሲመጡ ግን ከተለመደው አሠራር ይወጣል፡፡ የፌስቲቫል መልክ ይይዛል፡፡ በዓሉን ተንተርሶ የማይሸጥና የማይገዛ ነገር የለም፡፡ እቃዎች ከውጭ ሁሉ ይመጣሉ፡፡ ይህንን ስንመለከትና በምን አቅጣጫ እንሂድ ስንል በጣም ፈታኝ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ገንዘብም እንፈልጋለን፡፡

ይሄ ሁኔታ ባለበት ገንዘብ ተምነን በተራ እናስተናግድ የሚለው ብዙም አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም ምንድን ነው? የተጫራቾች ፍላጐት ጨምሯል፤ ተሳታፊም በስፋት አለ፣ ጐብኚም በሠልፍ ነው የሚገባው እያልን የምንለካባቸው የራሳችን አሠራሮች አሉ፡፡ በውጭ ያለውን የገበያ ሁኔታና እኛም ጋ ያለውን ሁኔታ … በንጽጽር ያለውን ልዩነት እንሠራለን፡፡ በአብዛኛው ሰው ያለው ግንዛቤ በባዛር ኤግዚቢሽን ቦታ እቃዎችን ከመደበኛው ዋጋ ባነሰ እናገኛለን የሚል ቢሆንም ይሄ ጉዳይ ለስሙ እንጂ ነጋዴዎች ከመደበኛ ሱቃቸው በላይ ዋጋ እየጨመሩ እንደሚሸጡ ይነገራል፡፡ ማዕከላችሁ ይህን ጉዳይ ያውቀዋል? መቆጣጠርስ የማን ሃላፊነት ነው? በዋናነት በማዕከሉ የሚካሄደው ኤግዚቢሽን ሳይሆን ባዛር ነው፡፡ ባዛር በአብዛኛው ከሽያጭ ጋር ይገናኛል፡፡ በነዚህ ሶስት በዓላት ማለቴ ነው፡፡ ለምሣሌ በአዲስ ዓመት ባዛር ላይ ከትምህርት ቤት መከፈት ጋር ተያይዞ ጊዜውን የጠበቁ በርካታ ሸቀጦች ይገባሉ፡፡ ገናም ሲሆን እንዲሁ ከገና በዓል ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች ይቀርባሉ፡፡ የሚመጡት ከክፍለ ሀገር ሁሉ ነው፡፡ በዓሉን ምክንያት አድርገው በአንድ ላይ መሠባሠባቸው ይሄ ራሱን የቻለ ውበት ነው፡፡ ሆኖም ነጋዴዎቹ ከመደበኛው ዋጋ ይጨምራሉ ለተባለው ህብረተሠቡን በየጊዜው የምንመክረው በውጭ ያለውን ዋጋ ያውቀዋል፡፡

ስለዚህ አመዛዝኖና ለውሳኔ ሳይቸኩል መርጦ መግዛት ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም የሚገዛቸውን እቃዎች ሁሌም ስለሚገዛቸው ያውቃቸዋል፡፡ አዲስ ነገር የለም፡፡ እኛ ግን እንደ ስራ የተዘጋጁ ነገሮችን ለምሣሌ እንደ ዘይትና ዱቄት እጥረት በሚኖርበት ሠዓት እነዚህ አምራች ድርጅቶች በፋብሪካ ዋጋ ይዘው ገበያውን እንዲቀላቀሉ እንመክራለን፡፡ ለምሣሌ እንደ ሞጆ ዘይት ያሉት የዘይት እጥረት በተፈጠረ ጊዜ በፋብሪካ ዋጋ ይዘው ገብተው አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ይመክራሉ፡፡ በተለይም ከበዓል ጋር ግንኙነት ያላቸውና እጥረት ያሳዩ እቃዎች ሲኖሩ ነጋዴዎች ገብተው እንዲያረጋጉ ይደረጋል፡፡ አንዳንድ ትልልቅ ፋብሪካዎች እንደውም ጨምሬና አትርፌ ልሽጥ የሚል ከላይ ያነሳሽው አይነት ችግር የለባቸውም፡፡ እንዲያውም ገበያ ማረጋጋቱን እንደ አንድ ትልቅ እገዛና አላማ ቆጥረው እቃቸውን ቀጥታ በፋብሪካ ዋጋ ይዘው መጥተው አረጋግተው ይሄዳሉ፡፡ እናም የፈለገውን ያህል እቃቸው ተፈላጊ ሆኖ መዓት ሠው ቢሠለፍ፣ በፋብሪካ ዋጋ ብቻ ሸጠው ይሄዳሉ እንጂ አምስት ሳንቲም አይጨምሩም፡፡ ሌሎቹ ግን የያዙት እቃ በጣም ሲፈለግ ሲመለከቱ፣ ዛሬ አንድ ዋጋ ነገ አንድ ዋጋ፣ ከነገ ወዲያ ሌላ ዋጋ እየጠሩ ያጭበረብራሉ፡፡

ስለዚህ ሠው ሲገበያይ ግራ ቀኙን ማየትና መጠንቀቅ አለበት፡፡ በእኛ በኩል ደግሞ ናሙና በመውሠድ በየቀኑ ያለውን ሁኔታ እንከታተላለን፡፡ ይህንን እንደ አንድ የማርኬቲንግ ስራ ነው የምናየው፡፡ በውጭ ዋጋው ይሄን ያህል ነው፤ እዚህ እንዴት ሊሆን ቻለ እያልን እናመዛዝናለን፡፡ ዋጋ ጨምረው በሚሸጡ ሠዎች ላይ የምትወስዱት እርምጃ ይኖራል? ምንም እንኳ ነፃ ገበያ ቢሆንም ዋጋ ጨምረው ከሚሸጡት ሠዎች ጋር የምንነጋገርበት ጊዜ አለ፡፡ እርምጃ እንኳን ባይሆን ለምን ባልተገባ ዋጋ እንደሚሸጡ እና አግባብ እንዳልሆነም እንናገራለን፡፡ ይሄን የበዓል ባዛር ልዩ የሚያደርገው መርካቶም ሆነ የትም ሄደሽ ያላገኘሽውንና ያጣሽውን ነገር ባዛር ላይ ታገኛለሽ፡፡ ያኔ ለመግዛት ባታስቢ እንኳን እቃውን ድንገት ስለምታገኝው ገዝተሽ ትሄጃለሽ፡፡ ይሄ በጣም ጠቃሚውና ልዩው የባዛሩ ጐን ነው፡፡ ነጋዴውም ዋናው ጥቅሙ ዋጋ ጨምሮ ከሚሸጠው ይልቅ በብዛት የሚሸጠው ነው፡፡ ከብዛት ብዙ ትርፍ ያገኛሉ፡፡ በቀን 20ሺህ ሠው ገባ ማለት፣ ይሄ ደግሞ ለ15 እና ለ16 ቀናት ቀጠለ ማለት አስቢው፡፡ የገባ ሁሉ ይገዛል ባይባልም … 20ሺ በአማካይ ነው፤ ባለፈው በተካሄደው ዝግጅት በቀን እስከ 50ሺህ ሠው የገባበት ሁኔታ ነበር፡፡ የገባ ሠው ይገዛል ወይ ሁሉም ላይገዛ ይችላል ግን እኛ ጐብኚ እቃ ተሸክሞ ያለ እረፍት ሲጓዝ እናያለን፡፡

ነጋዴውም ኤግዚቢሽኑ ከመዘጋቱ በፊት እቃ እየጨረሠ ባዶውን ቁጭ ይላል፡፡ እንኳን ሌላ የውጭ ተሳታፊዎችም በትልቅ ኮንቴይነር ነው ጭነው መጥተው ጨርሰው የሚሄዱት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ 4.9 ሚሊዮን ብር እያስከፈላችሁ ነው፡፡ የሠው ፍላጐትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነግረውኛል፡፡ ማዕከላችሁ ምን ምን እሴቶችን ጨምሯል? ማዕከሉ አቅም በፈቀደ መጠን በየጊዜው የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሠጣል፡፡ በቀጣይም በመካከለኛ ጊዜ ፕሮግራም ይሄ ማዕከል መሻሻል አለበት የሚል ትኩረት ተሠጥቶታል፡፡ ምክንያቱም ለአገሪቱ ብቸኛ ማዕከል ነው፡፡ ስለዚህ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ለመስራት ሠፊ የማሻሻል ሥራ እቅድ ተይዟል፡፡ እንደውም ከባልደረቦቼ ጋር በዚህ ጉዳይ ስብሠባ ተቀምጬ ስነጋገር ነው የመጣሽው፡፡ ለዚሁ ማዕከል ማሻሻያ ተብለው የተጠኑና ተጨባጭ ነገሮች በእቅድ ተይዘዋል፡፡ እየተጠኑ ያሉም አሉ፡፡ ስለሆነም አገልግሎቱ የመቀየሩ ነገር የግድ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በምንሠጠው አገልግሎት በጣም በከፍተኛ ሁኔታ የሀይል አቅርቦትን ማቅረብ አስፈላጊ በመሆኑ እሱን ማድረግ ችለናል፡፡ የመጠባበቂያ ጀነሬተሮች፣ የመፀዳጃ ቤት ማስፋፊያዎች፣ ህዝብ በግቢ ውስጥ በሚበዛበት ጊዜ የደህንነት ጉዳይ ቁጥር አንድ ነው፡፡

ከሚመለከታቸው አካላት የተሠባሠቡበት የደህንነት ኮሚቴ ሁሉ አለን፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቢነሳ የሠው ደህንነት ቢስተጓጐል ፈጥኖ ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአገር ደህንነትም ሆነ ከውጭ የሚመጡ ተሣታፊዎች ደህንነት እንዲሰማቸው፤ የአገሪቱ ዜጐችም በነፃነት ተገበያይተውና ተዝናንተው መሄድ ስላለባቸው መጠበቅ አለባቸው፡፡ ማዕከሉንም በየጊዜው በሠው ኃይል እናጠናክራለን፡፡ እነዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመርንና እያሻሻልናቸው የሄድናቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ትንሽ ወደ ኋላ እንመለሥና መጀመሪያ ላይ ትንሹ የጨረታ ዋጋ አሸናፊ በስንት ብር አሸንፎ ነው ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጀው፡፡ የዚህ ማዕከል ባለቤትስ ማን ነው? ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው ባለቤቱ፤ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡ ነገር ግን አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሻሻል ሲል በ1998 ዓ.ም አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ኮንትራት ወስጄ ለምን አላሻሽለውም የሚል ጥያቄ ለመንግስት አቅርቦ ነበር፡፡ የመንግስት የልማት ድርጅት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ምክር ቤቱ ለ10 ዓመት ኮንትራት ወስዶ፣ አሁን ስምንተኛ አመቱ እየተጠናቀቀ ነው፡፡ ማኔጅመንቱ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ይሠራል፡፡

ባለቤቱ አሁንም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡ እናም ስንረከበው አመታዊ ገቢው ከሠባት ስምንት አመት በፊት 450ሺህ ነበር፡፡ አሁን አመታዊ ገቢው ወደ 20 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ልዩነቱን ማየት ትችያለሽ፡፡ ከገቢው 50% በላይ የሚገኘው በሶስቱ በዓላት ከሚገኘው የጨረታ ገቢ ነው፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙት እነዚህ ሶስት በዓላት ናቸው፡፡ እኛ ስንረከበው የመጀመሪያው አሸናፊ ያሸነፈበት ዋጋ በትክክል ትዝ ባይለኝም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ አሁን ወደ አምስት ሚሊዮን እየተጠጋ ነው፡፡ አሁን በመደበኛም ሆነ በጨረታ ኤግዚቢሽንና ባዛር የሚያዘጋጁት ድርጅቶች ስንት ደረሱ? በፊት በፊት ሶስትም አራትም ነበሩ፡፡ አሁን ከመቶ በላይ አዘጋጅ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ በመደበኛም በጨረታም አጠቃላይ ናቸው፡፡ በጨረታ የሚያዘጋጁት አስር አስራ ሁለት ናቸው፡፡ ነገር ግን ቅድም እንዳልሽው በብር ብዛትም ፈታኝ ነገርም እየገጠማቸው እየከበደ ሲመጣ፣ ጨረታ ሠነድ ሲወጣ በሚዲያ አዳዲስ አዘጋጆችን እናበረታታለን እንላለን፡፡ ምክር በመስጠት እናበረታታለን እያልን እንናገራለን፡፡

ሁልጊዜ አንድ ሠው ሁለት ሠው እንዲጫረት እየተደረገ አማራጭ ከጠፋም ማዕከሉ እንዲያዘጋጅ ይገደዳል፡፡ ኤግዚቢሽን ማዕከሉ የሚገደድበት ነጥብ ምንድን ነው? ለምሣሌ ተጫራች ጠፋ እንበል! ደግመን ጨረታ አውጥተን የሚጫረት ቢጠፋ ራሣችን እንገባበታለን፡፡ ዋጋው ከጨመረባችሁስ? ዋጋው ላይ በምንመጣበት ጊዜ ዋጋው ከጨመረ እንደ መንግስት የልማት ድርጅት ራሣችን መክረን የምንወስዳቸው እርምጃዎች ይኖሩናል፡፡ ተጫራች ከጠፋ የግድ አመታዊ በዓል ነው፡፡ የገቢ ምንጫችንም ነው፤ የማዘጋጀት ግዴታም አለብን፡፡ ከዚህ በመነሣት ምን እናድርግ ወደሚለው እንሄዳለን ማለት ነው ከገባን ደግሞ ብዙ ልዩነቶችን ፈጥረን እንወጣለን ብለን እናምናለን አሁን ባለው ሁኔታ ግን አዘጋጆች እንዲበረታቱ ነው የምንጥረው፡፡ አሁን 4.9ሚ ያቀረበው ድርጅት አሸንፏል 10 ሚሊዮን የሚያቀርብ ቢመጣ እንዴት ታጣጥሙታላችሁ? እንደዛ ሊመጣ አይችልም! በየት በኩል ያልፋል? ቅድም እንደተናገርኩት ነው፡፡ ተጫራቾች በጣም ልዩነቱ የጠበበ ዋጋ አቀረቡ ማለት የገቢ ምንጮች ይታወቃሉ፡ገቢዎቹ ቢተልቁ እስከ ምን ድረስ ሊተልቁ እንደሚችሉ ይታወቃሉ፡፡ የጐብኚውም ትልቁ መጠን ታውቋል፡፡ አሁን ምናልባት እንግዲህ አንዳንድ አዘጋጆች ስፖንሠር የሚያገኙ ከሆነ እሱ ላይ ነው ቀዳዳው ያለው፡፡ አንዱ ተጫራች ጥሩ ኔትወርክ ካለውና ስፖንሠሮችን ካገኘ ገቢው ትልቅ ሊሆንለት ይችላል፡፡

ሌላው ከስፖንሠር አንፃር ደካማ ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ድርጅታቸው ወጪያቸውን የሚሸፍንበት ሁኔታ አለ፡፡ በዛም አለ በዚህ የቱንም ያህል ገቢ ይኑር እንዲህ አይነት ልዩነቶች አይኖሩም፡፡ ሁሉም በጥናትና በመረጃ የተደገፈ ስለሆነ በጣም በጠበበ ልዩነት ነው እየተጫረተ ያለው፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ አሁን 555 ብር ብቻ ነው ልዩነቱ፡፡ እኛ አናስተናግድም አንልም፤ ግን በ10 ሚሊዮን ብር የሚመጣበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ የዛሬ አመቱ አሸናፊ በስንት ብር አሸነፈ? የዛሬ አመቱ ከአሁኑ ጋር ልዩነቱ 335ሺህ ብር ነው፡፡ ባለፈው ዓመት 4.6 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ አሁን የዝግጅቱ ደረጃ እያደገ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ታስታውሱ እንደሆነ ያሬድ ፕሮዳክሽን የሚባል ድርጅት ከሶስት ዓመት በፊት ይመስለኛል ባሸነፈ ጊዜ በመክፈቻ ስነሥርዓቱ ላይ ሄሊኮፕተር እስከማብረር ደርሰው ነበር፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ፈጠራ አለ፡፡ ድሮ ለመዝናኛ ብለው ሁለት መቶ ሺህ እና ከዚያ በታች ያቀረቡ ነበር፡፡ አሁን እንደዛ የለም፤ አሁን አሉ የተባሉት እነዘመን ባንድ ይቀርባሉ፡፡ ስለዚህ የዚህን ዝግጅት ደረጃ ልሸራርፍ ብትይ የህዝብ ጩኸትን ነው የሚፈጥረው፡፡ በአጠቃላይ ተጫራቾች ከ85-90 በመቶ ባለው ነገር ላይ ይግባባሉ፡፡ በባዛር ወቅት የማዕከሉ ፈታኝ ሁኔታ ምንድን ነው? እኛ በጣም የምንቸገርበት ጉዳይ የህዝቡ ብዛት ነው፡፡ እዚህ ቦታ ነፍሰጡሮች ይመጣሉ፤ አካል ጉዳተኞች ይመጣሉ፡፡ የእነርሱን ደህንነት ለመጠበቅ፣ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ከፍተኛ ፈተና አለ፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው፤ የገበያውም ደረጃ ከፍተኛ ነው፡፡

ዘንድሮ “አንድነት ፕሪንተር” የተባለው ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደማሸነፉ ማዕከሉ ምን ምን ድጋፎችን ያደርጋል? ዘንድሮ እንዳልሽው በ4.9 ሚሊዮን ብር አንድነት አሸንፏል ግን ገና አለየለትም፡፡ እንዴት? የመጣው ንግድ ፈቃድ ትንሽ ማጣራትን ይፈልጋል፡፡ ንግድ ፈቃዱ በእንጨትና በእንጨት ስራዎች ዙሪያ የሚንቀሳቀስ ነው ይላል፡፡ እዛው ላይ ሚዲያ የሚል ነገርም አለው፡፡ እኛ ጨረታ ሰነድ ላይ ከማስታወቂያ ከፕሮሞሽንና ተያያዥ ስራዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው በሚል ነው ላለመገደብ ብለን ያወጣነው፡፡ ስለዚህ “አንድነት ፕሪንተር” አሁን ያቀረበው ንግድ ፈቃድ ምን ማለት ነው? ይህን ስራ ለመስራት ያስችለዋል ወይ በሚል እያጣራን ነው፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ በግልጽ እንዲመልሱልን ጠይቀናል፡፡ እነሱ ምላሽ ሲሰጡን እንጂ አሁን ሙሉ በሙሉ አሸናፊው አልታወቀም፡፡ በዋጋ ግን የተሻለ ዋጋ አቅርቧል፡፡ አሁን አልተወሰነም፡፡ ባለፈው ዓመት በ4.6 ሚሊዮን ብር ጨረታውን ያሸነፈው “ሴንቸሪ” በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞት ኪሣራ ደርሶበታል የሚባል ነገር ይወራል፡፡ እውነት ነው? ሃሰት ነው፡፡

እኛም የዛን ጊዜ ለህዝቡ ስንል ብዙ ነገሮችን ግምት ውስጥ በመክተት ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደናል፡፡ ለምሣሌ በራሳችን ወጪ ቀኖችን ጨምረናል፡፡ ስለዚህ ስለ ኪሣራው የምናውቀውም የሰማነውም የለም፡፡ እስካሁን በጨረታ የሚወዳደሩት ድርጅቶች በብዛት ይታወቃሉ፡፡ በብዛት በማሸነፍ ሪከርድ የሰበረው ማነው? በአብዛኛው ለአዲስ አመትም ለገናም ለፋሲካም ብዙ ጊዜ የሚያሸንፈው “ሴንቸሪ ፕሮሞሽን” ነው፡፡ በአብዛኛው እሱ ነው፤ አሁን ግን አዳዲስ እየመጡ ነው፡፡

Read 2487 times