Saturday, 09 March 2013 12:04

የክርስቶስ መንገድ ወደ ሮም አይወስድም!

Written by  እዮብ ተስፋዬ Manyob1964@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

በመጀመሪያ “ክርስትናና ሶሻሊዝም ምንና ምን ናቸው?” በሚል ርዕስ ባለፈው ሳምንት የጋዜጣው ዕትም በወጣው ፅሁፍ ላይ አስተያየት ከመስጠቴ በፊት የፅሁፉን አቅራቢ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም አንብበው እንደራሳቸው እምነት ከማንፀባረቅ ይልቅ የደራሲውን ሀሳብ በቀጥታ በማስተላለፋቸው፡፡ ይህ መቼም የተከበረ አካሄድ ነው፡፡ እናም የፀሀፊው መንገድ ለሁላችንም ትምህርት ይሆናል፡፡ አሁን ወደ አስተያየቴ ልሂድ፡- እኔ በዋናነትና በይበልጥ ለማተኮር የፈለግሁት የሰማይና የምድር ያህል ርቀት ያለውን (በእውነቱም ቢሆን ክርስትናና ሶሻሊዝም የሰማይና የምድር አስተሳሰቦች ናቸው) የክርስቶስን መንገድ ከሶሻሊዝም አይዲኦሎጂ ጋር ለማመሳሰል የተሞከረበትን ምልከታ አይደለም፡፡ የኢሳ.ም.53 (ደራሲው ወይም ፀሐፊው ምዕራፉን ባይጠቅሱም፤ ስለዚህም ነው አስተያየት የተሰጠው) ክርስቶስ በምድር ላይ ሲያስተምር የነበረውን ሰብዕና አይገልፅም የተባለውን ነው፡፡

ወደዚያ ከመሄዳችን በፊት ግን በጥቂቱ ስለ ሶሻሊዝሙ ጉዳይ እንይ፡- ደራሲው ክርስቶስን በቀና መንገድ ሊገልፁት ሞክረዋል፤ የተሳሳቱት ከአለማዊ አይዲኦሎጂ (ከሶሻሊዝም) ጋር ሊያዛምዱት ሲሞክሩ ነው፡፡ የክርስቶስ ፍትህ፣ ወንድማማችነትና እኩልነት ከሶሻሊስቶቹ ሀሳብ ጋር ፍፁም የተመሳሰለ አይደለም፡፡ ክርስቶስ አመፀኛም ሆነ አብዮተኛ አልነበረም፡፡ ክርስቶስ በመጀመሪያ የተሰጠንን ተስፋ ሊፈፅም ነው የመጣው፡፡ ሀብታችንን በመሳሳት የጣልነውን ፀጋችንን እንድንቀበል እራሱን መስዋዕት በማድረግ ከአምላክ ጋር እርቅ እንድንፈፅም ነው ያደረገን፡፡ የውጭውን ሳይሆን በውስጣችን ያለውን ሀብታችንን ነው ያሳየን፡፡ የተወሰኑት ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም እንደሳትን ነው የነገረን፡፡ ሰራተኛውን ወዛደሩን ሳይል ሁላችንንም ነው የወደደን፤ ጭቁኖችን ብቻ ሳይሆን ጨቋኞችንም ነው ነፃ ያወጣው፤ ተገፊዎችን ብቻ ሳይሆን ገፊዎችንም እንጂ፡፡ የክርስቶስ መንገድ ከሶሻሊስታዊ አይዲኦሎጂ እጅግ ሩቅ በሆነ ልዩነት ላይ ያለ አስተምህሮት ነው፡፡ በእውነትም ደራሲው ሊቀልዱ እንደሞከሩት (ቢያንስ ለኔ ቀልድ ነው) ክርስቶስ ለዚህ ለተሳሳተ አለም ገዢ የማይሆን እንደሆነ ሁሉ፤እሱ በሚገነባው መንግስት የሚነግስባቸው ህዝቦች ገንዘባቸውን ባንክ ስለማያስቀምጡ ደራሲው ያሳሰባቸው ችግር አይከሰትም፡፡ አሁን ደሞ ለኔ በትክክል ሊብራራ ይገባዋል ወደምለው የፅሁፉ አንኳር ክፍል እሄዳለሁ፡፡

የኢሳ.ም.53 የክርስቶስን ሰብዕና ዝቅ አድርጓል፣ ደካማና ጐስቋላ አድርጐ አቅርቦታል፤ በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች ያን ሰብዕና ሲያንፀባርቁ ይታያል፤ ነገር ግን ት.ኢሳያስ ም. 53 በትክክል ክርስቶስን አይገልፀውም የተባለውን ነው፡፡ ደራሲው በሌላ ቦታ ስለዚህ ጉዳይ ፃፉት የተባለው (በነገራችን ላይ እኔ በቀጥታ ጋዜጣው ላይ ከሰፈረው ሀሳብ በመነሳት ነው ሀሳቤን ያቀረብኩት) ከኢሳያስ ይልቅ አራቱ ወንጌላውያን በትክክል የክርስቶስን ሰብዕና ገልፀዋል ይሉና፤ በክርስቶስ ሰብዕና ላይ አራቱ ወንጌላውያንና ትንቢተ ኢሳያስ የተለያየ አመለካከት ያላቸው አስመስለው አቅርበዋል፡፡ ይህ አስተያየት ግን በጣም የተሳሳተ ነው፤ምክንያቱም ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱ የሆነው ቅዱስ ሉቃስ በፃፈው የሐዋርያት ሥራ ላይ ይሄው ምዕራፍ ተጠቅሷል፡፡ በሐ.ዋ.ሥ.ም. 8 ቁ.26 ላይ ያለው፤ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ያነበው የነበረው የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ይሄ የትንቢተ ኢሳያስ ም.53 ነበር፡፡ ክርስቶስ ለመጀመሪያ ጊዜ (ቅዱስ ጳውሎስም ክርስትናን ከመቀበሉም በፊት) ለአህዛብ የተደረገውን የክርስቶስን መገለጥ መንገድ ሀዋርያው ፊልጶስን በመነጠቅ ተዓምር ተጠቅሞ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እንዲያበስር ሲልከው፤ ጃንደረባውን ያገኘው ይህንን ትንቢት ሲያነብ ነበር፡፡

ፊልጶስ ለጃንደረባው ስለ ክርስቶስ ያበሰረውና ያጠመቀው ይሄንን የኢሳያስ ትንቢት መነሻ አድርጐ ነው፡፡ እናም ከሁሉም በተሻለ የክርስቶስን ሰብዕና የሚገልፅ ምዕራፍ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚያም አልፎ ከአሁኑ መወያያችን ያለፉ ታላላቅ ጉዳዮችን የያዘ ምዕራፍ ነው፡፡ (አንድ ቀን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በዚህ ምዕራፍና በጃንደረባው ጉዳይ ላይ አንድ ፅሁፍ ለማቅረብ ቃል እገባለሁ) እንዴት ነው ታዲያ ይሄ የኢሳያስ ትንቢት በደራሲው ላይ መደናገርን የፈጠረው? ከዚህ በፊት በሌላ ፅሁፌ ላይ እንዳልኩት የቅዱስ መፅሐፉን ቃል አተኩሮ ካለማየት የመጣ ነው፡፡ ኢሳ.ምዕ.53 ላይ የተናገረው ትንቢት፤95 በመቶ ያህል ስለ ኢየሱስ የመጨረሻ የተልዕኮው ሰዓታት ነው - ማለትም ሀሙስ ማታ በጭፍሮች ከተያዘበት ጀምሮ እስከ አርብ 9 ሰአት ነፍሱን እስከሰጠበት ሰዓት ድረስ ያለውን ማለት ነው፡፡ የምዕራፉን የመጀመሪያ ሁለት ስንኞች ማንበብ የኢሳያስን አባባል ለመረዳት ያስችላል፡፡

ትንቢተ ኢሳ.ቁ.1 እንዲህ ይላል “የሰማነውን ነገር ማን አመነ? የእግዚአብሔር ክንድስ ለማን ተገልጧል?” ምንድነው እግዚአብሔር ለኢሳያስ የነገረው ለሌሎች ያልተገለጠ? ይህ ጥያቄ መልስ ሲያገኝ ሌላው የምዕራፉ ክፍል ይገባናል፡፡ እንግዲህ ኢሳያስ ይህን ምዕራፍ ጥያቄ በመጠየቅ ሲጀምር ለማለት የፈለገው፤ ጌታ በዚህ ምዕራፉ እንደገለጽኩት ነው የመሰላችሁ፤ነገር ግን ይሄ የሆነው እኛ ሰምተን የነገርናችሁን ስላላመናችሁ ክንዱም ስላልተገለጠላችሁ ነው፡፡ ምን እንደሰጣችሁና ምን እንደከፈለላችሁ አልተረዳችሁም - ነው፡፡ ይህንንም በራሱ አባባል ሲገልጽ በም 53 ቁ 4 ላይ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንን ተሸክሟል እኛ ግን እንደተመታ በእግዚአብሔር እንደተቀሰፈ እንደተቸገረም ቆጠርነው” ይለናል፡፡

ኢሳያስ የክርስቶስ ማንነት ተገልፆለታል፤ ምንኛም ጠንካራ እንደሆነ ያውቃል፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔር ደካማው ነገር እንኳን ለአለም ብርቱ ነውና የአምላክ ክንድ የሆነው ክርስቶስ ምን ያህል ባለ ግርማ ሞገስ (በዛ ያለውን ሁኔታ የዚህ አለም ቃላት ለመግለጽ በቂ ባይሆኑም) ውብና ሃያል እንደሆነ ኢሳያስ፤ ክርስቶስ በክብሩ ላይ ሳለ ስላየው ታላቅ ሃይል፤ ያ ቃል ያ ሃይል ወደ ሰዎች ሲወርድና ሰዎችን ሲመስል ሰዎች እንደጠንካራ ቢያዩት እንኳን የጥንካሬውን አንድ ሚሊዮንኛ አላወቁም ማለት ነው፡፡ ያ ነው እንግዲህ በኢሳያስ አባባል ለሰዎች ያልተገለጠው፡፡ የኢሳያስ አይነቶቹ የክርስቶስን ክብር ለሚያውቁ፤ ጌታ በምድር ሲመላለስ ከሚሊዮን በሚበልጥ ክፍልፋይ ሃይሉን ቀንሶ ነበር፡፡ ስለዚህም ኢሳያስ በቁ 2 እና 3 ላይ የገለፀው የክርስቶስ ማንነት እሱ ከሚያውቀው የክርስቶስ ሰብዕና ጋር አወዳድሮ ነው (በነገራችን ላይ የትንቢተ ኢ.ግማሽ ያህሉ ወይም 33 ምዕራፎች) ስለ ክርስቶስ መገለጥ የተነገሩ ናቸው፡፡ ከቁጥር 4 ጀምሮ እስከ ምዕ. መጨረሻ ድረስ ግን (95 ከመቶ) ከላይ እንደገለጽኩት ጌታ በጭፍሮቹ ከተያዘ በኋላ ስላለው ግዜ የሚገልጽ ነው፡፡

በደራሲ ዋላስ የተገለፀው በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተወስዶ ሲሟላ “ተጨነቀ፣ ተሰቃየ አፉንም አልከፈተም፣ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም…” እያለ የሚቀጥለው ክርስቶስ በምድር እያስተማረ በተመላለሰበት ጊዜ ያሳያቸው ባህሪዎች ሳይሆኑ ተይዞ ታላቁን የተልዕኮውን ክፍል ለመፈፀም የተጠቀመበት መንገድ ነው፡፡ ህዝቡን ለማስተማር በምድር በተመላለሰበት ግዜ ግን (በደራሲው ዘመንና ለደራሲው ቅርብ የነበሩ የክርስትና ሰባኪዎች ክርስቶስን እንደደካማ አድርገው ይገልፁት ከነበር ምንም ለማለት አይቻልም፤ አልተረዱትም ማለት ይበቃል) እኛና ስለክርስቶስ የሚያውቁ ብዙ ክርስቲያኖች ግን (ክርስቶስ ወደ አባቱ ከሄደበት ጊዜ ጀምሮ ያሉ) ክርስቶስን እንዲህ አናውቀውም፤ ጌታ በምድር ሲመላለስ ሁሌም አለቃ፣ በስልጣን የሚያስተምር፣ ጠንካራና ወሳኝም ነበር፡፡ ገና በ12 አመቱ እራሱን መምራት እንደሚችል ተናግሯል፤ ቤተክርስቲያንን ያረከሱ ነጋዴዎችን በአለንጋ አባሯል፣ ጠረጴዛዎቻቸውን ገለባብጧል፡፡ ደካሞችን እምነት የሌላቸውን እንዳይፈሩ በአምላክ ላይ ልባቸውን አሳርፈው ረጋ ብለው እንዲኖሩ በምድር በተመላለሰበት ግዜ ሁሉ መክሯል፡፡ ያለ ፍርሃት በሚቃወሙት መሃል ተመላልሷል፡፡ “ንጉሱ ሊገድልህ ይፈልጋል” ሲሉትም “ለዛች ቀበሮ ጊዜዬ ገና አልደረሰም በሏት” ብሏል፡፡

ጊዜው እስካልደረሰ ድረስ ማንም ምንም ሊያደርስበት እንደማይችል ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ እናም በእኛ ህሊና ያለው የክርስቶስ ሰብዕና የተናቀና ደካማ ስዕልን የሚያሳይ አይደለም (ይህን አመለካከት የያዝነው ሙሉ ለሙሉ የትንቢተ ኢሳያስ ም. 53 ሃሳብ ተረድተን ነው፤ በሱ ምክንያት ምንም የተፈጠረብን ግጭት የለም) ከላይ እንዳልኩት ደራሲው ስለተሰበከላቸው ነገር ባናውቅም፡፡ ስለዚህም የኢየሱስ የመጨረሻው ሰዓታት ስናይ ምዕራፉ ሙሉ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ክርስቶስ ሃሙስ ማታ ሊይዙት የመጡትን ጭፍሮች ሊዋጓቸው ለፈለጉት ደቀመዛሙርቶቹ ያላቸው ነገር ክርስቶስ እራሱን አሳልፎ የሚሰጥበት ሰዓት መድረሱን የሚያበስሩ ነበሩ፤ እንዲህ ነው ያለው - “ይህንን ፍቀዱ!” ለጭፍሮቹም ሰዓቱ ስለደረሰ እንጂ ከዚህ በፊት ሊይዙት እንደማይችሉ ሲነግራቸው “እለት እለት በቤተ መቅደስ ስመላለስ አላረጋችሁትም” ነው ያላቸው፡፡ ይሄ ሰዓት ግን ጊዜ የተቆረጠለት የተልዕኮው ፍፃሜ ሰዓት ነበር፡፡ ስለዚህም የተልዕኮው ክፍል ስለሆነ አልተቃወማቸውም፤ ምንም አልተናገረም፤አልተከራከረም፡፡ በዛ ፋንታ ስቃዩን በፀጋ ተቀበለ፡፡ ሆኖም ግን አላዋቂነት ካልሆነ በስተቀር እንኳን በምድር ሲመላለስ ቀርቶ በዚህም ሰዓት ከሚገባው በላይ ጠንካራ ነበር፡፡ ለሚያውቁት ክንዱ ለተገለጠላቸው ይህ ድርጊቱ የሚያሳያቸው የአለምን ግፍና ሃጥያት ያለ ክርክር ያለ ማሳበብ በፀጋ መቀበልንና ማሸነፉን ነው፡፡ ጌታ በተጨማሪም ለሰቃዮቹ በመፀለይ ያንን ጥንካሬውን የመጨረሻ ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡ ክርስቶስ ወደ ምድር የወረደው ይህንን ውብ መንፈሳዊ ድል በፀጋ ለመቀበል ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ነው እሱ እንዳሸነፈ ተከታዮቹ እንዲያሸንፉ የሚፈልገው፡፡ ከዚህ የበለጠ ጠንካራነት በዚህ ምድር ላይ ምን ይሆን?

Read 2788 times