Saturday, 09 March 2013 11:56

ሁለት የመከራ ዓመታት - በደቡብ አፍሪካ

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(2 votes)

ግርማ በዳዳ ለወራት የቀን ቅዠት የሌሊት ህልም ሆናበት የከረመችውን የደቡብ አፍሪካን መሬት እግሩ እንደረገጠ የተሰማውን ደስታ በቃላት መግለጽ አዳጋች ነው፡፡ በተለይ የዋና ከተማዋ የፕሪቶሪያ ውበትና ዘመናዊነት ገነት የገባ ያህል እንዲሰማው አድርጐት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጉድና ጅራት በስተኋላ ነው እንደሚባለው ይህ ሁሉ የደስታ ስሜት እንደጧት ጤዛ ረግፎ ለመጥፋትና ወደ ከፍተኛ ጭንቀትና ግራ መጋባት ለመቀየር የወሰደበት ጊዜ ሁለት ቀናት ብቻ ነበር፡፡ የት ነው የምኖረው? ከማን ጋር ነው የምኖረው? ምን እበላለሁ? ምንስ እሰራለሁ? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ግርማ ግን ባፋጣኝ ሊመልሳቸው የሚችላቸው አልነበሩም፡፡ከሀራሬ አብረውት የመጡት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሁሉም በየፊናው ወደሚሄድበት ተበታትኗል፡፡

ደላላው ቃል በገባለት መሠረት ከሀራሬ ተቀብለው ወደ ደቡብ አፍሪካ ያስገቡት ሁለቱ የጅማ ልጆችም ወደ ደቡብ አፍሪካ ካስገቡት በኋላ መልካም እድል እንዲገጥመው ተመኝተውለት፣ በመጡበት አኳኋን ወደ ሀራሬ ተመልሰዋል፡፡ ግዴታቸውም ይሄው ብቻ ነበር፡፡ ወደ ገሀነም የሚወስደው መንገድ የግራና ቀኝ ጠርዞች ተከምክሞ የተሠራው በአማላይ ቃልኪዳኖች ነው፡፡ የጅማው ጓደኛው ስለደቡብ አፍሪካ የነገረው ያን የመሰለ አማላይ ታሪክ ለካንስ ወደ አስፈሪው ገሀነም ሊያስገባው እያባበለው እንደነበር ግርማ አሁን በሚገባ ለመረዳት ችሏል፡፡ ይህንን ነገር ወደኋላ እየሄደ ለማሰብና በቁጭት ለመንገብገብ የሚሆን ጊዜ ግን ማግኘት አልቻለም፡፡

ቀን ሆዱ ምግብ፤ ሲመሽ ደግሞ ጐኑ ረጅሙን ሌሊት የሚያሳልፍበት የመጠለያ ቦታ በመጠየቅ በከፍተኛ ጭንቀት ወጥረው ይይዙታል፡፡ ጀርባን ሊሰነጥቅ በሚችል ጭንቀትና ግራ መጋባት ከላይ ታች ቢባዝንም ጥያቄዎቹን መመለስ አልቻለም፡፡ የሆዱንና የጐኑን ጥያቄዎች እንደነገሩና በህይወት ለመቆየት ያህል ብቻ መልስ የሚሰጡት የፕሪቶሪያ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎችና የአስፓልት ዳር ታዛዎች ነበሩ፡፡ ግርማ ገና ጅማ ሶኮሩ እያለ ስለ ደቡብ አፍሪካ በተደጋጋሚ የሰማው አማላይ ታሪክ፤ ፕሪቶሪያ ከገባ በኋላ አንዱንም እንኳ እውነት ሆኖ ሊያገኘው ባለመቻሉ በውስጡ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሮበታል፡፡ አበው “እውነትን ብቻ በመናገር ዲያቢሎስን በሀፍረት ኩም አድርጉት፡፡” በማለት የግብረገብ ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካን በተመለከተ ግርማን ያጋጠመው ነገር ግን የዚህ ተቃራኒ የሆነው ነው፡፡ ስለ ደቡብ አፍሪካ የነገሩት ጓደኞቹ ሁሉ አንዳቸውም እንኳ እውነተኛውን ነገር በግልጽ አልነገሩትም፡፡ ሆኖም ሁሉንም ነገር የተሳሳተ ታሪክ በነገሩት ጓደኞቹ ላይ ማላከክ ግን አይቻልም፡፡ ጅማ ሶኮሩ የኪዮስክ ንግዱን ያንቀሳቅስበት የነበረው የኢትዮጵያ ብር ደቡብ አፍሪካ ውስጥም ኪዮስክ ለመክፈት ያስችለኛል የሚል እምነት ነበረው፡፡

በሱሪውና በጃኬቱ ውስጥ አራት ሺ ብር ደብቆ ይዞ የመጣውም በዚህ የተነሳ ነበር፡፡ ይህ አራት ሺ ብር እንዳሰበው ኪዮስክ ሊያስከፍተው ቀርቶ ለምንም አይነት አገልግሎት የማይውል ቁርጥራጭ ወረቀት እንደሆነ ሲረዳ አስፓልት ዳር ላይ ካለው የድንጋይ ወንበር ላይ ተኮራምቶ ተቀምጦ አይኑ እስኪበልዝ ድረስ ተንሰቅስቆ አልቅሷል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ለመኖርና በስራ ላይ ለመሠማራት በቅድሚያ ለደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከቻ በማቅረብና የሚከፈለውን ወደ አምስት ሺ ብር ገደማ ክፍያ በመፈፀም የመኖሪያ ፈቃድ ማውጣት እንዳለበት የነገሩት በአጋጣሚ ያገኛቸው አራት የዲላ አካባቢ ልጆች ነበሩ፡፡ ከጅማ ይዞት የመጣውን አራት ሺ ብርም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ስለምንሄድ በሚል ተቀብለውት በምትኩም ተመጣጣኙን የደቡብ አፍሪካ ገንዘብ (ራንድ) የሰጡትና ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ንፁህ ዳቦ ገዝቶ እንዲበላ ያስቻሉትም እነዚሁ ልጆች ነበሩ፡፡ ግርማ ደቡብ አፍሪካ እንደገባ ያጋጠመው መደናገርና እጅግ አስቸጋሪ የህይወት ፈተና ቅስሙን ክፉኛ አንኮታኩቶ ሰብሮት ነበር፡፡ እናም ተረጋግቶ ለማሰብና ህይወቱን ለማቃናት በእጅጉ አስቸጋሪ ሆነበት፡፡ በፕሪቶሪያ ከተማ ሁለቱን ዓመት እንዴት አድርጐ ማሳለፍ እንደቻለም ጨርሶ አይገባውም፡፡

ብቻ ባጭሩ የደቡብ አፍሪካ አድባር ግርማን አማን ብላ አልተቀበለችውም ነበር፡፡ በመጨረሻ ወደ አዲስ አበባ የመመለሻ የአውሮፕላን ትኬትና ጥቂት ገንዘብ አዋጥተው በመሰብሰብ ያለ መኖሪያ ፈቃድ ከፕሪቶሪያ ፖሊሶች ጋር ለሁለት አመታት ያህል የአይጥና ድመት ጨዋታ እየተጫወተና አይሆኑ አይነት ኑሮ ካሳለፈ በኋላ ለሀገሩ መሬት ያበቁት ድንገት ያገኙት ጥቂት የጅማ ልጆች ነበሩ፡፡ ግርማ ከጆሀንስበርግ አውሮፕላን ማረፊያ የተሳፈረበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አርፎ እንደቆመ፤ መንገደኞቹ ቀላል ሻንጣዎቻቸውን ከአውሮፕላኑ የውስጥ የእቃ መጫኛ ቆጥ ላይ ለማውረድ መጣደፍ ሲጀምሩ ከተቀመጠበት ሳይነሳ እንዲሁ ዝም ብሎ ያስተውላቸው ነበር፡፡ የያዘው ምንም አይነት ሻንጣ ስላልነበረው ከቆጡ ላይ የሚያወርደው ምንም ነገር አልነበረውም፡፡ እርሱ የሚጠባበቀው የአውሮፕላኑን በር መከፈት ብቻ ነበር፡፡

የአውሮፕላኑ በር ተከፍቶ እግሩ የሀገሩን መሬት እንደነካ እንዲህ ነው ብሎ ለይቶ መናገር በማይችለው ስሜት ተይዞ፤ አብረውት የመጡት መንገደኞችና በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እስኪታዘቡ ድረስ እንባውንና ንፍጡን በጃኬቱ የቀኝ እጅጌ እየጠረገ ንፍርቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ ግርማ ራሱን እንደምንም አረጋግቶ አውሮፕላን ማረፊያውን ለቆ ከወጣ በኋላ በሚኒባስ ተሳፍሮ ቀጥታ ወደ መርካቶ አውቶቡስ ተራ አመራ፡፡ የዚያን እለቱን ምሽት አውቶቡስ ተራ ከሚገኙ ሆቴሎች በአንዱ አሳለፈና በማግስቱ ጧት በአውቶቡስ ተሳፍሮ ጅማ፤ከዚያም ሶኮሩ የትውልድና የእድገቱ ቀዬ ገባ፡፡ ሰፈሩ አካባቢ ሲደርስም አንገቱን ደፍቶ በዝግታ እየተራመደ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ የግርማ አባትና ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቹ ግርማ ደቡብ አፍሪካን ጥሎ ለምን እንደመጣ አጥብቀው መጠየቅ ቢዳዳቸውም፤ የሰውነቱ መጐሳቆልና ጠቅላላ ይዞታው እርሱ ሊነግራቸው ከሚችለው በላይ በግልፅ ያስረዳ ነበርና ለመጠየቅ አልደፈሩም፡፡

እውነት ለመናገር ሁለቱ ወንድሞቹና አባቱ በግርማ ላይ ትልቅ ተስፋ አሳድረው ነበር፡፡ በተለይ አባቱ ከአታካቹ የእለት ተእለት የግብርና ኑሮ ይገላግለኝና እፎይ ብዬ በድሎት እኖራለሁ የሚል ትልቅ ተስፋ ጥለውበት ነበር፡፡ ወንድሞቹም ቢሆን ግርማ ባጭር ጊዜ ውስጥ ህይወቱን አደላድሎ ባለፀጋ ከበርቴ ከሆነ በሁዋላ፤ እነሱን ወደ ደቡብ አፍሪካ በመውሰድ እርሱ ካፈራውና ከደቡብ አፍሪካ ተዝቆ የማያልቅ የሀብት እርዚቅ እንደሚያቋድሳቸው በታላቅ ጉጉትና በብሩህ ተስፋ እየተጠባበቁት ነበር፡፡ አሁን ያ ጉጉትና ተስፋ ጨርሶ የለም፡፡

እንደጉም በኖ ጠፍቷል፡፡ ለሁላችንም ይተርፋል ብለው ተማምነውት የነበረው ልጃቸውና ወንድማቸው ግርማ በዳዳ ለራሱም እንኳ መሆን ሳይችል ቀርቶ በደቡብ አፍሪካ ሁለት የችግርና የመከራ አመታትን ካሳለፈ በኋላ እጣ ነፍሱን ብቻ ይዞ እነሱው ጋ ተመልሶ መጣ፡፡ አባትየውና የታላቁ ታላቅ የሆነው ወንድሙ በግርማ ላይ አሳድረውት የነበረው ከፍተኛ ተስፋ ድንገት ብን ብሎ በመጥፋቱ ያሳደረባቸው ብስጭትና የስሜት መከፋት እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህንን ስሜታቸውን ከግርማ አይን ላይ ለመደበቅ የቻሉትን ያህል ቢጣጣሩም አንዳቸውም አልተሳካላቸውም ነበር፡፡ በአፋቸው ክፉ ነገር ባይናገሩትም ፊታቸውን ሊለውጡት ግን ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡በፕሪቶሪያ ያን የመሰለ ስቃይና መከራ ሁለት አመት ሙሉ ሲቀበል የነበረው ግርማ፤ በህይወት ተርፎ በሰላም አባቱና ወንድሞቹ ጋር ሲቀላቀል እንዲህ ያለ ሁኔታ ይጠብቀኛል ብሎ ጨርሶ አልገመተም ነበር፡፡ እናም ሰቀቀኑ ቀድሞውኑ ክፉኛ የተሰበረውን መንፈሱን ዳግመኛ እንዳይጠገን አድርጐ አንኮታኮተው፡፡

ትንሽም ቢሆን “አይዞህ! ያ ረቢ ላንተ ባይለው ነው!” የሚለው ታላቅ ወንድሙ ብቻ ነበር፡፡ ክፋቱ ግን ይሄን ወንድሙን የሚያገኘው ከስንት አንዴ አባቱን ሊጠይቅ ወደ ቤት ብቅ ያለ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ወሬ ከሀይለኛ ሰደድ እሳት በፍጥነትም በክፋትም ይብሳል ይባላል፡፡ የግርማ ከደቡብ አፍሪካ ሳይሳካለት እንዲያ ተጐሳቁሎ የመመለሱ ወሬ በድፍን የሶኮሩ ከተማ ተዛምቶ የሰው ሁሉ መጠቋቆሚያ ለመሆን የፈጀው ጊዜ አንድ ሌሊት ብቻ ነበር፡፡ (ይቀጥላል)

Read 1880 times Last modified on Saturday, 09 March 2013 14:21