Saturday, 09 March 2013 11:01

የመንግስት ግዥ ህግ አፈፃፀም ክፍተቶች አሉበት ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

በመንግስትና በግል ዘርፍ ለሚደረግ የምክክር መድረክ ማጠንጠኛነት የተዘጋጀው የዳሠሣ ጥናት በመንግስት ግዢ ህግ አፈፃፀም ላይ ክፍተቶች እንዳሉ አመለከተ፡፡ ጥናቱ ለአራተኛው የምክክር መድረክ መወያያነት በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በግል ዘርፍ ማበልፀጊያ ማዕከል አማካኝነት በአማካሪዎች የተጠና ሲሆን “የመንግስት ግዢና የግል ዘርፍ በኢትዮጵያ፤ አዝማሚያዎች፣ ተስፋዎች፣ ተግዳሮቶችና የውሳኔ ግብአቶች” የሚል ርዕስ ተሠጥቶታል፡፡ የዳሠሣ ጥናቱ ትላንትና ረፋድ ላይ በሂልተን ሆቴል ቀርቦ በባለ ድርሻ አካላት ውይይት የተካሄደበት ሲሆን ጥናቱ ከጠቆማቸው ስድስት ያህል ክፍተቶች መንግስት አብዛኛዎቹ መኖራቸውን አምኗል፡፡

ይሄው ጥናት በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ በአቶ ተሾመ በየነ የቀረበ ሲሆን ጥናቱ የጠቆማቸው እያንዳንዱ ነጥብ ለታዳሚዎች በዝርዝር ቀርቧል፡፡ ክፍተቶች ተብለው ከቀረቡት አንዱ “ልዩ አስተያየት” የሚል ሲሆን ይህ ልዩ አስተያየት በመንግስት ግዥ ህግ አፈፃፀም ለግንባታ ለአገር ውስጥ ተጫራቾች ስራ 7.5%፣ ለመድሀኒትና ለህክምና መገልገያዎች 25%፣ ለአገልግሎት 7.5% እንዲሁም ለአነስተኛና ጥቃቅን 3% የልዩ አስተያየት ምጣኔ የተፈቀደ ቢሆንም ይህ አስተያየት ከሌሎች ሶስት የአፍሪካ አገራት እንደሚያንስ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

የተጋነነ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና መጠየቅ፣ የውል ማስከበሪያ ዋስትና በጊዜ አለመለቀቅ፣ በዋጋ ማቅረቢያ በሚፈፀሙ ግዥዎች ያለው ተደጋጋሚነት፣ ግልፅ ጨረታን እንደ ዋና የግዢ ዘዴ አለመጠቀም እና የመንግስትና የግል ሽርክና አለመተግበር የሚሉት ነጥቦች በዳሠሣ ጥናቱ እንደ ክፍተት የተቀመጡ ናቸው፡፡ በትላንትናው የሂልተኑ ውይይት ላይ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ክፍተቶችን ለመሙላትና የተሻሉ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ በ2001 ዓ.ም የወጣው የመንግስት ግዥ አፈፃፀም አዋጅና እሱን ተከትሎ የወጡ መመሪያዎች ማሻሻያ እየተደረገባቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በፌደራል የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ እና በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አራተኛ ዙር የምክክር መድረክ ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በበኩላቸው፤ በመንግስት ገንዘብ (Public money) ለሚፈፀም ግዥ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያወጣው፣ መልሶ የሚወስደውና ባስገኘው ውጤትም በጋራ ተጠቃሚ የሚሆነው የንግዱ ህብረተሠብ በመሆኑ በመንግስት የግዥ ዝርጋታ እና አፈፃፀሙ ላይ በየጊዜው እየተገናኙ መወያየትና የተሻሉ ሃሣቦችን በማፍለቅ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Read 5317 times