Sunday, 03 March 2013 08:58

ይድረስ ለበዕውቀቱ ስዩም እና ለይስማዕከ ወርቁ!

Written by  ተስፋ በላይነህ
Rate this item
(18 votes)

ስነጥበብ እጅግ በጣም የተሰወረውን የውስጥ ስሜት ነግሎ በማውጣት እግር አልባውን እንኳ ክንፍ እስከመስጠት የሚያስደርስ ፀጋ፤ በሀሳብ በምናብ ምናኔ ወደ ፊት እና ወደ ኋላ መብረር የሚያስችል ክንፍ አለው፡፡
በየዘመናቱ ስነ-ጥበብን ያስተዋወቁ ሰዎች ብቅ ብለዋል:: እንደዘጋቢያቸው ወይም መስካሪያቸው የፈረጠመ ጡንቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተትረፈረፈ ሲሰማና ሲታይ ታዝበናል፡፡ በየጊዜው የሚፈጠረው ትውልድ እያነሳ ይጥለዋል፡፡ ነገር ግን በጊዜ ብዛት አያረጅም፤ በዘመን ኮፈን አይጣልም፤ በወቅቶች መፈራረቅም አይጠወልግም:: እንደ ወይን እየጣፈጠ እንደንስር ሀይሉን እያደሰ ዘመኑን ይዋጃል:: የትውልዱ ስልጣኔ ሲዋዥቅ አብሮ ሊዋዥቅ ይችላል፤ የትውልዱ ስልጣኔ ሲያድግ ግን ከፍ ይላል፤ ስለቱም ሊጨምር ይችላል::
ከኢራን/ፋርስ/፣ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅ ከግሪክ፣ ከራሺያ፣ ከእንግሊዝ፣ ከጀርመን፣ ከአየርላንድ፣ ከሊቢያ፣ ከናይጀሪያ እና ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በርካታ የስነ-ጥበብ ፈርጦች ተከስተዋል:: ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው እንደመስካሪያቸው ጡንቻ ብዙ ሊባልላቸው ይችላል:: እንደሚጮኽላቸው የጩኸት ሀይል ስማቸውም ሊገን ይችላል:: ሼክስፒርን ስናይ እንግሊዞች ባላቸው ሀይል ብዙ ተብሎለታል:: ሩሲያዊው ደስቶቭስኪ ደግሞ እንደ ሌሎች ሳይመሰከርለት በመጠቀ የስነ-ጥበብ ሀይሉ ብቻ ስራው ገኖዋል:: የአንዳንድ ሰዎች የስነ-ጥበብ ስራ፤ ስራው በራሱ ባለው ጩኸት መቃብር ፈንግሎ ሊወጣ ይችላል:: ብቻ እውነተኛ እና ሀይል ያለው ስራ ይሰራ እንጂ ቀኑን ጠብቆ መግነኑ አይቀርም:: አሁን ያለንበት ዘመን የመረጃ ዘመን በመኾኑ በ‹‹ቲፎዞ›› በጩኸት ለዕይታ የሚቀርቡ ስራዎች በርክተዋል :: ጯኺ ከሌለ ስራ ተቀብሮ ሊቀር ይችላል:: መስካሪ የሌለው ዳኛ ለፍርድ እንደሚቸገር፣ ጩኸት የሌለው ድምጽ እንደማይሰማ ኹሉ፣ በየጊዜው የሚወጡ የጥበብ ሰዎች ጯኺና መስካሪ እያጡ ሲቸገሩ እናያለን::
የቁራ ጩኸት እንደተባለው አላስፈላጊ ምስክር (የማስታወቂያም ስራ የገቢ ምንጭ መሆኑ ከታወቀ ወዲህ) ጩኸት የማይገባቸው ስራዎች በማስታወቂያ ሰሪው ሀይል ብቻ ገነው ሲወጡ ይታያሉ:: በዚህም የተነሳ ገንዘብ ዋናው መሰረታዊ ነገር እየሆነ፣ ገንዘብ የሌለው የስነ-ጥበብ ሰው በችጋር ሲሰቃይ ማየት የዘወትር ሃቅ ሆኗል:: በዚህ አጋጣሚ በጩኸቱ ስራ የተሰማራችሁ ሰዎች ያልተዘመረላቸውና ያልተጮኸላቸው፣ ነገር ግን ምጥቀትን የያዙ ስራዎችን ብትፈልጉ መልካም ነው::
እንግዲህ አንድ የስነ-ጥበብ ሰው የፈለገውን የተሰማውን በስነ-ጥበብ ሀይል ከባህሩ ዋኝቶ፤ ከጠፈሩ ተንሳፍፎ፤ ከምድሩም ተዋህዶ የቀዘፈውን የቀዳውን የተመለከተውን እንካችሁ የማለት መብትም ግዴታም አለበት:: የዛሬውን ፅሁፍ ለማሰናዳት የተነሳሳሁት በአሁኑ ሰዓት ያለው አንባቢና የጥበብ ተመልካች የሚሰማውን የሚያነበውን የስነ-ጥበብ ፈጠራ ከምን ማዕዘንና እይታ ተመልክቶ እያጣጠመ እንደሚገኝ በማገናዘብ ነው:: ስለተጮኸላቸው ወይስ ስራቸው ስለጮኸ? ምላሹን ለርስዎ! ለዚህም ሀሳብ ዋና ተጠቃሽ የስነ-ጥበብ ሰዎች በእውቀቱ ስዩምና ይስማዕከ ወርቁ ናቸው::
አንድ የሥነጥበብ ሰው የፈለገውን ማምለክ፣ ያሻውን ጎራ ወግኖ መጻፍ የተፈጥሮ መብቱ ነው፡፡ እግዚአብሔርን አለማምለክም፣ይሻለኛል ብሎ ካሰበ ሰይጣንን መምረጥም መብቱ ነው:: የአመላለክ ስርዓቱን፣ የእይታ ጎኑን በፈለገው መልኩ የማቅረብ ሙሉ መብት አለው:: ታዲያ እዚህ ላይ ችግር ውስጥ የሚገባው አንባቢው ነው:: ለምን ቢሉ የሁለቱን ጽንፎች በሚያስተውልበት ጊዜ የመለየትና የአንዱን ጎራ ( የሚያምንበትን) ሃሳብ ለይቶ ግልጽ የሆነ ውሳኔ እንዲሁም መረጃ የማግኘት ሃላፊነትም ግዴታም ስለሚኖርበት ነው:: አንባቢው ወይም ተመልካቹ የሚያነበውንና የሚያየውን ሀሳብ በጥንቃቄ አጉልቶ ማየትና ሊደርስ የሚችለውን ጫና ገምቶ የሚሆነውን የመለየት ብቃት ያለው መኾን ይጠበቅበታል:: ባየኋቸውና ባገኘኋቸው እንዲሁም ባነበብኳቸው የስነ-ጥበብ ፈጠራዎች ምን አገኘሁ? ምን አጣሁ? ምን ለየሁ? ምን ጎደለው? ብሎ ካልጠየቀና ካልመረመረ አንባቢ አይባልም፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ማንበብ ይጠይቃል፤ ብዙ መረዳት ይፈልጋል:: ግልብ ኾነን የምናነብ ከሆነ ጥራዝ-ነጠቅ ከሚባለው ፈርጅ ውስጥ መመደባችን አይቀርም:: በዚህ መሰረት ከላይ የጠቀስኳቸውን ስመ-ጥር የስነ-ጥበብ ሰዎች ስራዎቻቸውን በማየትና አንባቢው ላይ እየደረሰ ያለውን መወናበድ በመመልከት ሀሳብ ለመስጠት ተነሳሁ:: በእርግጥ ብዙም የተለየ ወይም የመጠቀ አስተሳሰብ ይዤ ሳይሆን በመሰለኝና በተረዳሁት መጠን የቀረበ ነው - ፅሁፌ፡፡
በእውቀቱ ስዩም እና ይሰማዕከ ወርቁ አንድ የሚያመሳስላቸው የጋራ መነሻ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁለቱም ምናልባት የቅኔ ትምህርት (የአብነት ትምህርት) እንዲሁም የመለኮታዊውን ክበብ ቀዝፈው የመጡ መኾናቸው፣ ላላቸው ወቅታዊ ስብዕና እና የስነ-ጽሁፍ ፈጠራ አጋዥ መሆኑን የምንስማማበት ሀሳብ ይመስለኛል:: በእውቀቱ ስዩምን በ1995 ዓ.ም ባነበብኳት የግጥም መድበሉ ነው ያወቅሁት:: ‹‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች›› የተሰኘችው ይቺ ስራ ማንም ሳይጮኽላት በራሷ ትልቅ ሀይል የነበራት ናት::
“ግጥም የሕያው ስሜቶች ምስክርነት እንደሆነ እናምናለን፤ ምናባዊ መገለጥ እንደሆነም እናምናለን፤ ለአያቶቻችን ከመለኮት ጋር የሚያገናኝ መሰላል፤ለአባቶቻችን የአብዮት ሰይፍን የሚስል ሞረድ፤ ለእኛ ፍለጋ/ኅሰሳ/ መኾኑን እናምናለን…” እያለ መክሊት…መኾኑን በማመን ሀሳቡን ይጀምራል:: በግሌ ከነበረኝ የግጥም ፍላጎት ከእድሜም አንጻር ‹‹እሳት ወይ አበባ›› የግጥም መድበልን በመያዝ በወቅቱ ስፍጨረጨር የነበርኩትን “ጨቅላ እኔ”ን ግጥም ትግል አለመኾኑን በእውቀቱ ስዩም አበሰረኝ:: በሶስት ብር ከሀምሳ የተገዛችው የሎሬት ባለቅኔ ፀጋዬ ገ/መድህን ‹‹እሳት ወይ አበባ›› የግጥም መድበልን ተውኳት፡፡ በእውቀቱ ስዩም አዲስ ምዕራፍ ከፈተልኝ:: ግጥሞቹን ደጋግሜ አነባቸዋለሁ፤ በቃሌ እደግማቸዋለሁ::
በላዔ ሰብዕ፣ መልካ ሕይወት፣ ዘመን ሲታደስ፣ ሞኝ ፍቅር፣ መሄጃው የታለ፣ ብታውቂ፣ ጣይና አንሺ ፣ ጥጡና ፈታይዋ፣ ፍካሬ እውነት፣ መለየት.. ወዘተ የመሳሰሉ ግጥሞች ተፈጥሮን በተለያዩ ማዕዘኖች እንድመለከት ረድተውኛል፡፡ በሕይወት ዘመንም አንድ ነገር መፈለግ እንዳለብኝ አስተምረውኛል:: ለእያንዳንዱ ግጥም የቀረቡት የስዕል መግለጫዎች በራሳቸው የገጣሚውን ሌላ የስነ-ጥበብ ገጽታ ያሳያሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በወቅቱ ገጣሚውን በግሌ በአንደኝነት የስነ-ጥበብ ጎራ ለማስቀመጥ አስችሎኛል::
በ1990ዎቹ ላይ የሰው የማንበብና የመጻፍ ባህል በመጠኑም ቢሆን የተዳከመበት ወቅት ነበር ለማለት እደፍራለኹ:: በዚህ ወቅት ግድም ነበር በዕውቀቱ ‹‹በራሪ ቅጠሎች›› በሚል ያቀረባትን አጫጭር ልብወለዶች ያካተተች መድበል ያስነበበን፡፡ በመቀጠል ‹‹እንቅልፍ እና ዕድሜ›› የተሰኘውን ከ97ቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ሥራውን አቀረበልን:: ‹‹የእሳት ዳር ሃሳቦች›› የተሰኘችው የግጥም መድበሉም እንደቀዳሚዋ ባትሆንም የበኩሏን ጥበባዊ አስተዋፅኦ አበርክታለች:: በተጨማሪም ‹‹መግባትና መውጣት›› በሚል በቀልድ እያዋዛ ያቀረበው ሥራው የሚደነቅ ነበር:: በእነዚህ አመታት ውስጥ ከጸሐፊው የስነ-ጥበብ አስተሳሰብ ጋር አብሮ መጓዝ የሚጠይቅ መኾኑን ልብ በሉ:: ፀሃፊው ፍለጋ ላይ መኾኑን ራሱ መስክሯል - ለእኛ ፍለጋ/ኅሰሳ/ መኾኑን እናምናለን… በማለት፡፡ እንግዲህ ገጣሚው ፈልጎ ፈልጎ ምን እንዳገኘ በስራዎቹ የምንመዝነው ይኾናል፡፡
ከአንድ ግጥም ወዳጅ ወዳጄ ጋር ስለግጥሞቹ ስንወያይ፤ ገጣሚው በስሜታችን የሌለን በሕይወታችን ያላጋጠመንን የኑሮ ክስተቶች ሆነን እንድንገኝ የማድረግ ኃይል አለው:: ይህም ማለት ለምሳሌ ‹‹ዕረፍቴን አሥሣለሁ›› የሚለው የግጥም ሐሳብ ብሩኩ ወዳጄ ባልኖረበት እና ባላጋጠመው የሕይወት ገጠመኝ ውስጥ እራሱን እንዳገኘው -ሳይከፋው እንደከፋው፤ ሀዘን ሳይሰማው እንዳዘነ፤ በፍለጋ ሕይወት ውስጥ ሳይኖር ብዙ ነገር እንደፈለገና ፈልጎም እንደዋተተ ሲነግረኝ… የፀሃፊውን የስነ-ጥበብ ኃይልና ጫና ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡
ስለዚህ የዚህን ገጣሚ ዱካ መከተል፤በሚጓዝበት የሃሳብ ጎዳና መጓዝን ስለሚያመጣ አንባቢዎች በጥንቃቄ እንዲያነቡና እንዲገነዘቡ ወደሚመክር ጭብጥ እናመራለን:: ፀሐፊው ያሻውን ይጻፍ፣ የማገውን ይተንፍስ አንባቢ ግን በአፅዕኖት፣ በዐርምሞ እና በማስተዋል እንዲያነብ ይመከራል::
ልክ እንደመናፍቅ-ቀኖና እንደጣሰ- እምነት እንደ ካደ ከቀኖች ሰልፍ ውስጥ- ማን ገዝቶ ለየው- ሰንበት ወዴት ሄደ?
ዕረፍት የት ገደመ- ወዴት ተሰደደ?... እያለ ይቀጥላል፡፡
በእኔ በኩል በወቅቱ በታላላቆቹ መጽሐፍት ላይ ( ቁርዓን እና መጽሐፍ ቅዱስ) ትኩረቴን ሰጥቼ ስለነበር እራስን ፈልጎ ማግኘት፤ የሌሎችን ግለሰባዊ አስተሳሰቦች መረዳትና ማስተዋል አልቸገረኝም::
“ዴርቶጋዳ” የተሰኘው ዝነኛ ልቦለድ መፅሃፍ በኢትዮጵያ የንባብ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አብዮት ፈጥሯል:: ትውልድ መጽሐፍ ወደ ማንበብ ባህል እንዲመለስ ማድረጉንም ማንም አይክድም:: ጸሐፊው ይስማከ ወርቁም ይህን የአብዮት እሳት ማቀጣጠሉ ያስመሰግነዋል:: በተለይ እስከ ገጽ 80 ያለው ፈጠራ እጅግ ውብ ነው:: ይህንንም መጽሐፍ ተከትሎ ‹‹የወንድ ምጥ›› በሚል ርእስ ያወጣው የግጥም መድበል በተለየ መልኩ የስነ-ግጥም ሰይፉን የሳለበት ፤የግዕዝ እና የቅኔ ችሎታውን ያሳየበትም ስራው ነው:: ‹‹ሰቆቃወ ቂል›› የተሰኘችውን ግጥሙን በተለየ አፅንዖት ነበር የተመለከትኳት፡፡ ምንም እንኳ ከግል ሕይወቴ ጋር የሚያገናኛት ሐሳብ ባትሰንቅም፣ በስነ-ጥበብ ኃይል ግን በገጣሚው ሐሳብ ስር መደቆሴ አልቀረም:: “የወንድ ምጥ” የተሰኘው ረዥም ግጥም በራሱ ልዩ አፍሪቃዊ እንባን የተላበሰ፤ የአፍሪቃዊያን ታሪክና ህዝቦች ኑዛዜ፤ ጩኧት እንዲሁም ምጥ ነው:: ምናልባት ርዕሱ ከወንድ ምጥ ይልቅ ‹‹ወንድ ሲማጥ›› የሚለው ተስማሚው ሳይሆን አይቀርም እላለሁ:: በሰው ሐሳብና ስም አጠራር ጣልቃ መግባት ባይመከርም፡፡
እንግዲህ ስለ ሁለቱ የስነ-ጥበብ ሰዎች የነበረኝን ከበሬታና ልሰጥ የሚገባኝን አድናቆት በዚሁ ላብቃ - ከዚህ በላይ ማወደስና ማመስገን ወደ አምልኮት ጎራ ስለሚያስመድብ:: ብዙ መውደድና ብዙ ማፍቀር እንደ አርጤምስ እጣ ፈንታ ስለሚያመራ:: አርጤምስ የምትወደውን ልጇን በማጣቷ በተቀረፀ ሀውልት ስታመልከው ተገኘች!
በሁለቱ የስነ-ጥበብ ሰዎች ያየሁት ትልቁ መመሳሰል የቅኔ ገበታን የጠገቡ፤ የመለኮታዊውን ውሃ የጠጡ መኾናቸው እንደሆነ ከላይ ጠቅሼአለሁ:: በእነዚህ መብል እና መጠጥ ውስጥ ግን ሁሌም መደናገርና ወደ ውስጥ በገቡ ቁጥር ለተለያዩ ጥያቄዎች የሚጋብዙ ሐሳቦች ስላሉ፣ ሁለቱ ጸሐፊዎችም የዚህ እጣ ፈንታ ሰለባ መኾናቸውን ተገንዝቤአለሁ:: ፀሃፍቱ በዚህ ፍለጋ ወቅት ወደ አንዱ ተጠግቶ የማመንን ድፍረት አላየሁባቸውም፡፡ በብዛት ግን እያሞገሱና እየደገፉ ያሉት የጭለማውን ጥግ (ሰይጣንን ወደመደገፍ) እንደሆነ በጻፏቸው ጽሑፎችም ሆነ የግጥም ስንኞች ማየት ይቻላል:: ለምሳሌ በእውቀቱ ስዩም ‹‹መልክአ እናት›› በሚለው የግጥም ስንኙ፣ ከጌታ እናት ከማርያም ጋር የተዛመደ ውዳሴ ለወላጅ እናቱ ሰጥቷል - ሰላም ለኪ ለአይኖችሽ፤ ለከንፈሮችሽ፤ ለጣቶችሽ----እያለ በማወደስ:: እናትን ማመስገን ማወደስ ባልከፋ፤ ነገር ግን ‹‹አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ›› ለተባለላት የጌታ እናት የተሰጠውን የመንፈስ ቅዱስ ምስክር ለእናት መስጠት አምልኮ ነው! ምዕመናን የማርያምን ምስጋና የሚያቀርቡት የወለደችውን ጌታ ለማመስገን መኾኑ አይካድም:: እዚህ ላይ ገጣሚው ያመሰገነው እናቱን ቢኾንም በተዘዋዋሪ ግን እሱን የወለደች በመኾኗ ራሱንም እያመሰገነ ነው:: እንግዲህ ትልቁ ችግር ከቅኔ እና ከመለኮታዊው ኃይል ያገኙትን ጥበብ ለራስ ጥቅምና ሸቀጥ ማዋል፣ ህዝብንም ማወናበድ መወላወል በመኾኑ አንባቢ ልብ እንዲል የሚመመክር ሐሳብ ነው የያዝኩት፡፡
ከአንዱ አንዱን መለጠፍ፣ ለአንዱ የተሰጠውን ለሌላኛው መስጠት አንባቢን ግራ ያጋባል:: ምናልባት በሁለቱም ወገን ኾኖ ለሚያነብ ወይንም ሁለቱንም ለማያውቅ አንባቢ ተራ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ አንድን ወገን አጥብቆ ለያዘ ግን ለሁለት ጌታ መገዛት አትችሉም የሚለውን ቃል የሚያፋርስ በመኾኑ ጥቁሩን ከነጭ፤ ብርሃንን ከጨለማ ማቀላቀልና መለጠፍ አይቻልም:: የቄሳር ለቄሳር ነውና!
ይስማከ ወርቁም በ‹‹ወንድ ምጥ›› ስራው የወደድኩለት የግጥም ስንኝ ‹‹ሰቆቃወ ቂል›› በስንኞች መዳረሻው ላይ ‹‹የልቤ ዳጎን›› እያለ የገለጻት ሴት፤ ከትክክለኛ የጣዎት አምልኮ የማይለያይ ሐሳብ በመያዙ በዜሮ የሚያባዛ ቃል ነው:: በዚህ መድበል ላይ ‹‹ሰይጣን የታደለው›› ብሎ ያቀረበው ግጥም ምናልባት ወደ ጨለማው ንጉስ ማዘንበሉንና መከተሉን የሚያመላክት ግጥም ነው፡፡
‹‹የቀንድ አውጣ ኑሮ›› በተሰኘችው መድበል ‹‹ሪቢ›› ብሎ በፃፈው ግጥም ‹‹ኦላ ረቢ ክርስቶስ ውረድ ከጫንቄዬ ውረድ›› እያለ ያቀረበው ሐሳብ፣ ሌላው ማሳያ ነው:: ያሻውን ማምለክ የፈለገውን መከተል የግሉ ምርጫ፣ ተፈጥሯዊ መብቱ መኾኑን ገልጸናል፤ ነገር ግን አንዱን ከአንዱ መለጠፍ፤ የጠራ እምነት እና አመለካከት አለመያዝ ትልቁ ችግር መኾኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ:: ሰይጣንን መከተል ብዙ ጊዜ በፍርሃትና በመጠራጠር ስለሚኾን፣ እርሱን የሚከተሉ ሰዎች ሙሉ በሙሉ አምነው ተደግፈው ሲከተሉ አናያቸውም፡፡ የ‹‹መንፈቅለ መንግስት አለቃ!›› የሚሉት አምላካቸው ዲያቢሎስ አንድን ነገር ፈንቆሎ የመጣ፣ ተቃውሞ የተጣለ በመኾኑ ይህንን ገዥ መከተል ሁልጊዜም ሲዋትቱ ሲቅበዘበዙ መኖር ነው፡፡ ለዚያም ይመስለኛል ሙሉ በሙሉ ቆርጠው አምነው የማይታዩት:: በወንድ ምጥ መድበል ውስጥ ‹‹የአፈ ጉባኤው መዶሻ›› የተሰኘው ግጥም በውስጡ በቀላሉ ሊታይ የማይችል ሐሳብ አለው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ ሰዎች መልዕክት ምዕራፍ 8 የተጠቀሰውን ሐሳብ በመውሰድ በቀጥተኛ ሐሳብ ‹‹በፓርላማ ለሚያንቀላፉ የህዝብ እንደራሴዎች›› ብሎ ያቀረበ ሲሆን ሌላው የማይታየው ሀሳብ ግን አፈጉባኤውን እንደ አብ (አባት እግዚአብሔር)፣ መዶሻውን ደግሞ እንደ ወልድ (ክርስቶስ) አድርጎ መሸፈጡ ነው፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ በመልዕከቱ የሚያጸድቅ ማን ነው? የሚኮንንስ ማን ነው? ብሎ የመሰከረውን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም መዶሻ ብሎ መሰየሙ ለፈራጁ ይቀመጥ፡፡ መፍረድ ለርሱ የተሰጠ በመኾኑ ራሱ አምላክ የሚፈርደው ይሁን!
መዶሻ የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል
የሚያጸድቅ መዶሻ ነው የሚኮንንስ ማን ነው
……..ይልቁንስ…………
ጉልላታችን ያነጸው ካስማ ማገር ያፋቀረው
ወፍጮ ከመጅ የሚወቅረው በአፈ ጉባኤ ቀኝ ያለው
እኛ እኛን የሚወቅረው መዶሻው ነው::›› በማለት በውስጥ ሐሳብ ስራውን ይሰራል፡፡ ለግልብ አንባቢያንም የማይታይ ሐሳብ ይዟል:: የመጽሀፍ ቅዱስን የጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 8 ከቁጥር 33 ዠምሮ ያንብቡ፡፡ የ‹‹ቀንድ አውጣን›› ኑሮ የግጥም መድብል በተደጋጋሚ ሳነብ አምላኬን አምስግኜአለሁ፡፡ ጥቁርና ነጭ አይንን በመስጠቱ እንዲሁም ብርሃናዊ ልቦናን በመቸሩ ይህን ግልብ፤ ጥቁርና ነጭ አለም በሚገባ እንድመለከት አድርጎኛል:: አምላክ በአርአያው በአምሳያው እኛን መፍጠሩ የገረመው ይህ ፀሐፊ፤ የአምላክን ህልውና በሚዳፈር መልኩ የፃፈበትን ሥራውንም ታዝቤአለሁ:: ቆንጆ ናት የሚላትን ሴት፤ አምላክ እሷን ከመሰለ ቆንጆ ነው በማለት አንድን ፍጡር ከፈጣሪዋ የማስበለጥ አምልኮ መኾኑን ተረድቼአለሁ:: በ”ተከርቸም” ስራው ላይም የአንድ ጀብደኛ ሰው አባባል ተርጎሞ በመግቢያው ላይ ማስቀመጡ ከፈጣሪው ጋር የተጣላ መኾኑን ይጠቁማልና የዚህን መጽሐፍ መግቢያ እንድታነቡት እመክራለኹ፡፡ አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር የሚለውን - “ምንማችን ሆይ በምንም የምትኖር ምንምህ ትምጣ…” እያለ ይጠርቃል፡፡ ፈጣሪ የፈጠራቸውን ሲያሰቃይ እኔ ግን በፈጠራዬ ያስቀመጥኳቸውን ገጸ-ባሕርያት አላሰቃይም በማለት ከፈጣሪ ጋር ሲገደራደር መታየቱ ከአባታቸው ከዲያቢሎስ የወረሱት ትዕቢት በመኾኑ አዲስ ነገር አይደለም፡፡
በዕውቀቱ ስዩም በአንድ ፅሁፉ ‹‹የእግዚአብሔር እና የብሔር ብሔረሰቦች ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ አንደ ታቡ/Taboo/ ነው፡፡›› ብላል፡፡ ታቡ የሚለውን ቃል አማርኛው ሲተረጉመው “የተከለከለ ነገር፤ እያደረጉት የማይናገሩት” ይለዋል፡፡ በእውቀቱ ስዩም ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ብሔር ብሔረሰቦች ማውራት እንደ Taboo ይታያል ብሎ ማስቀመጡ በጣም የሚያሳዝን ሐሳብ ነው፡፡ ቀፎው የተነካበት ንብ ሆ! ብሎ ቢዘምት የንብን ቀፎ መንካት Taboo ነው ብሎ መውሰድ ምነኛ ሸፍጥ ነው! ምንም እንኳ ከንብ የበለጥን ፍጡሮች ብንሆንም እግዚአብሔር ሲነካብን ግን ዝም ማለት አንችልም:: ምንም እንኳን እንደ ንብ በመርዝ መናደፍ ባይኖርብንም፣ በጥበቡ ኃይል መመስከርና ሰላማዊ ጣፋጭ ቃሉን (ማሩን) መስጠት ይጠበቅብናል፡፡
ቡጥጫና ቁንጥጫ ማስከተል ባይጠበቅብንም፤ እንደ ንብ መርዝ ማስከተል ባይመከርም የቃላት ሰይፍን ይዘን በመንፈሳዊ ጦር መዋጋት አለብን፡፡ ፀሃፊው ሰው በብሔር ተከፋፍሎ መጋጨቱን ሲተች፤ ሳይንቲስቶች እንኳ ከአሳ-ነባሪ የመጣን ነን ብለው በሚያስተምሩን ሰዓት ሰው በተራ ነገር ሲጎነታተል በማየቱ ማዘኑን ጠቁሟል፡፡ ጥሩ ነው፡፡
ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ ሊተነኳኮስ አይገባም፡፡ ከሰውነት በታች ያደርጋል፡፡
ነገር ግን እሱም ራሱ የአማኞችን እምነት መነካካት ያለበት አይመስለኝም፡፡ሰላማዊ እውነት የያዘ የስነ-ጥበብ ሓሳብ ተገቢ ነው፡፡ ይህንንም ለመቀበል ዝግጁ መኾን አለብን፡፡ ግን ደግሞ በረጋ መንፈስ መመርመር የሚችል አንባቢ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ የሚያነብ ሰው በብዙ ይፈተናል፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን፤ ጨርቅም እንዲሁ በእሳት ይለያልና፡፡ አገራችን በብዛት ያጣችው ይህንን ነው፡፡ ብዙ አንባቢያን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አስተዋይ አንባቢ ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ጥቂት ጸሐፍት አሉን፤ ጥቂት አስተዋይ አንባቢያንም አሉን፡፡ ጥቂት አስተዋይ ሃያሲያንም አሉን፡፡ ብዙ ሳያነቡና ሳይጽፉ ነገር ግን በጩኸት ብቻ የበዙ ጸሐፍት -አንባቢያን ከበዙ ችግር ነው፡፡ አስተያየት መቀበል የሚወዱ ጥቂት ጸሐፍት አሉ፡፡ ብዙ ጥቂቶች ደግሞ ከበዙ ችግር ውስጥ መግባታችን አይቀርም፡፡ ስለዚህ አንባቢያን በምናነብበት ወቅት እንጠይቅ፡፡ ከተለያዩ ማዕዘናት በማየት እናንብብ፡፡ የተጻፈውን ነገር በውል እንለይ፡፡ ጥቁርና ነጩ ሳይምታታብን በሚገባ ተጠንቅቀን እናንብብ፡፡ ስንጽፍም እንዲሁ፡፡ ጸሐፍት በምትጽፉበት ወቅት ጥቁርና ነጩን እየለያችኹ እንድትጽፉልን እንማጸናለን፡፡ ይህ ካልኾነ ግን በመሀል ቤት የሚወቀጠውን ህዝብ እናስብ፡፡ ጎርፍ ጠራርጎ ይወስዳል እንደሚባለው፡፡ ላለመወሰድ መሰረት መያዝ ነው ጎበዝ! በቲፎዞና በጩኸት የሚኖር ህዝብ ከበዛ፣ በተፅእኖ የሚኖር ትውልድ ይበረክታል፡፡ ታላቅ ክሽፈት!
‹‹እሳት ወይ አበባ››ን የተረዳኹባት ጊዜ ደርሶ መቸም በተውሶ የሄደ መጽሐፍ አይገኝምና መፅሃፏን ዋጋ ከማይፍቁ አዟሪዎች ዘንድ ለመግዛት ተጋሁ፡፡ አንዱ አዟሪ ‹‹አለች›› አለኝ፡፡ ዋጋ ስጠይቀው 3ከ50 አሉኝ - አብረውት ከነበሩት ባልደረቦቹ ጋር ተባብሮ፡፡ በዚህ ኑሮ አቀበት በኾነበት ጊዜ መፅሃፏ በቀድሞ ዋጋዋ መገኘትዋ ደንቆኝ ገንዘብ ለመክፈል ሳወጣ ግን አዟሪዎቹ ተሳለቁብኝ! አልገባኝም ነበር፡፡ ለካስ 3ከ50 ያሉኝ ‹‹ሶስት መቶ ሃምሳ ብር” ለማለት ነበር! አበስኩ ገበርኩ!....
ተመልሼ የቀንድ አውጣ ኑሮን መተንተን ዠመርኩ፡፡ ‹‹የማርያም መቀነት›› የምትል ስንኝ አበረታታችኝ፡፡ ‹‹ረቢ›› ለሚለው ሌላኛው ግጥምም የመልስ ምቴን ለጋኹ፡፡ ጥቁርን ከነጭ እንድለይ የጥቁርና የነጭ አምላክን አመሰገንሁ! አንባቢ ሆይ፤ጥቁርና ነጭ አይን እንዳለኽ ኹሉ ለህሊናህ ጥቁርና ነጭ መነጽር በማበጀት ወደ መረጥኸው መንገድ ሂድ፡፡ ይስማዕከ በ”ዣንቶዣራ” መጽሐፉ፤ ስለ ፍሪሜሰን ለመተንተን ሞክሯል፡፡ ዋነኛ መለያቸው ጥቁርና ነጭ ምንጣፍ መኾኑን አላስቀመጠልንም፡፡ እነዚህ ሚስጥራዊ ቡድኖች “Yes, lucifer is god, and unfortunately Adonay is also God, for the eternal law is that there is no light without shade, no beauty without ugliness, no white without black, for the absolute can only exist as two gods, darkness being necessary for light to serve as its foil, as the pedestal is necessary to the statue, and the brake to the locomotive..”. በማለት ማመናቸውን አልተረዳኸውም ወይም በዚህ አስተሳሰብ ቀንበር ስር ነህ ማለት ነው! ለሁለት ጌታ ግን መገዛት አትችሉም፡፡ ብርሃን ከጨለማ ሕብረት የለውም፡፡ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚእብሔር! ቸሩ ቸር ያቆየን…

Read 9879 times