Sunday, 03 March 2013 08:40

የአፍሪካ አንድነት 50ኛ ዓመት በኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ይከበራል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበት ሃምሳኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች እንደሚከበር የበዓሉ አዘጋጅ ብሔራዊ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዋቀረው ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት የዛሬ ሳምንት በአምቦ ከተማ በተዘጋጀ አውደ ጥናት ላይ እንደተገለፀው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት ዋነኛ እለት ግንቦት 17 የሚከበር ሲሆን ከዚያ በፊት እና በኋላ የተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ይቀርባሉ፡፡ “ፓን አፍሪካኒዝምና የአፍሪካ ሕዳሴ” በሚል መሪ ቃል በሚከበረው የወርቅ ኢዮቤልዩ፤ ታዋቂ ድምፃውያን እና እግር ኳስ ተጨዋቾች ወደ አዲስ አበባ ተጋብዘው ከአድናቂዎቻቸው ጋር ይገናኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጥናታዊ ፊልም የሚቀርብ ሲሆን የምስረታውን ጉዞ የተመለከቱ ቴምብሮችም ይታተማሉ ተብሏል፡፡ ከስምንት ሳምንት በላይ የሚቆይ የአማርኛና እንግሊዝኛ ጥያቄና መልስ ውድድር ከታሚሶል ኮሙኒኬሽን ጋር በመተባበር እንደሚዘጋጅም ታውቋል፡፡

Read 3137 times