Sunday, 03 March 2013 08:24

አብቹን ምን በላው? ላሊበላንስ ማን ቀበረው?

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(2 votes)

አብቹ የ16 አመት ጉብል ነው፤ ግን ደግሞ የራስ ዳሽንን ያህል ግዙፍ ታሪክ ባለቤት፡፡ ግን ደግሞ ተንኮል፣ ግብዝነትና ቅናት በወለዱት ከንቱ አስተሳሰብ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል ቦታ ያልተሰጠው ምስኪን ጀግና! አብቹ በቼኮዝሎቫኪያዊው ጸሐፊ አዶልፍ ፓርለሳክ ብዕር በአጭሩ እንዲህ ይገለፃል፡፡
አብቹ የተወለደው በ1912 ዓ.ም ነው፤ ቦታው ደግሞ የዛሬው ሰሜን ሸዋ (ኦሮሚያ ክልል) ወረጃርሶ ወረዳ፡፡ አባቱ የወረጃርሶ ጦር መሪ ነበሩ፡፡ በጣሊያን ወረራ ዋዜማ ላይ በተፈጥሮ ህመም ሞቱና ዘመድ አዝማድ አልቅሶላቸው በወጉ ተቀበሩ፡፡
አባት ሲሞት ልጅ በአባቱ እግር ተተክቶ ኃላፊቱን መወጣት የቆየ ልማድ ነበረና የጃርሶን ጦር የአብቹ ሁለት ወንድሞች እንዲመሩት ይደረጋል፡፡ የሰላሌና የበጌምድርን ጦር በበላይነት የሚመሩት ራስ ካሳ ቢሆኑም የጃርሶ ጦር መሪዎች የሚታዘዙት ግን ለራስ ካሳ ልጅ ደጃዝማች አበራ ነበር፡፡ በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን አገራችንን መውረሩ እንደተሰማ ዘገራቸውን በቁጣ ከነቀነቁ እውነተኛ ኢትዮጵያን መሃል የአብቹ ወንድሞች ተጠቃሽ ሆኑ፡፡ የሁለቱን አናብስት ወንድሞቹን ወኔ የተመለከተው የ16 አመቱ ጉብል (አብቹም) “ከወንድሞቼ ጋር ካልዘመትሁ ሞቼ እገኛለሁ” አለና ቤተሰቡን አስቸገረ፡፡ እንኳን ጥይትን ራሱ ሞት ጥርሱን አግጥጦ ቢመጣበትም ፈርቶ አንዲት ጋት መሬት እንኳ ወደኋላ ላያፈገፍግ በምኒሊክ ስም ማለ፡፡
የልጃቸውን ከብረት የፀና አቋም የተረዱት እናትም “የአብቹን ነገር አደራ!” ብለው ለደጃዝማች አበራ አስረከቡ፡፡ ደጃዝማች አበራ አውሮፓ ሄዶ ሲማር የነበረ ብልህና ወጣት መኮንን ነው፡፡ አብቹም አገሩ ላይ በወቅቱ ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት አጠናቅቆ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አውሮፓ ሊሄድ ሲሰናዳ አውሮፓዊ ጠላት መጣና ሩቅ የነበረ ህልሙ ተደናቀፈ፡፡
ስለዚህ አብቹ ያገሩን ጠላት ለመፋለም ከወንድሞቹ ጋር መዝመት አለበት፤ ዘመተ፡፡ ከወንድሞቹ ጋር ይዝመት እንጂ የደጃዝማች አበራና የእሱ ፍቅር ለጉድ ነው፡፡ አብቹ አዕምሮው ብሩህ ጉብል ነው፡፡ እድሜውና ድርጊቱ በፍፁም ሊገናኙ የሚችሉ አይመስሉም፡፡
ከሰላሌ የተንቀሳቀሰው ጦር የቻለ ስንቁን በፈረስ፣ በበቅሎና በአህያ ጭኖ፤ ያልቻለ ደግሞ በትከሻው ተሸክሞ ለሰባት ወራት በእግሩ ሲኳትን ከቆየ በኋላ ለጦርነት የተፈጠረ ከሚመስለው የትግራይ ተራራማ ግዛት አምባላጌ ደረሰ፡፡ የአንበሳው አሉላ አባነጋ የትውልድ ቦታ ከሆነው ቆላ ተምቤን በመውረድም አምባራዶም ከተባለ ቦታ ላይ ከወራሪው ኃይል ጋር የሞት ሽረት ትግል አካሄደ፡፡
በውጊያው ላይ እጅግ በርካታ የፋሽስት መንጋ አንገቶችን እንደ ጐመን የቀነጠሱ ጀግኖች የአገራቸውንና የወገናቸውን ቀጣይ ውርደት ሳያዩ በክብር ወደቁ፡፡ ከእነዚህ አንበሶች መሃል የአብቹ ወንድሞች ይገኙበታል፡፡ አንደኛው ወንድሙ ይማረክ ወይም ይሙት እርግጡ ያልታወቀ ሲሆን የሌላኛውን ወንድሙን አስከሬን ግን ከአንዲት ዋርካ ዛፍ ስር ቀብሮ እርሙን ተወጣ፡፡
ሆኖም ደጃዝማች አበራን ክፉኛ የፈተነ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ አብቹ በአደራ የተሰጠው ጓደኛውም የአደራ ልጁም ነው፡፡ ይህ እንደ ነፍሱ የሚወደው የክፉ ቀን ባልደረባው ከወንድሙ መቃብር አጠገብ ካለች አንዲት ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ሌት ከቀን ይተክዝ ጀመር፡፡ እህል ውሃ ሳይቀምስ ለሁለት ቀናት በመቆየቱም ደጃዝማች አበራን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ገጠመው፡፡
አብቹ “እህልም ሆነ ውሃ አልቀምስም” ብሎ ያስቸገረው ሞቱን አይቶ ለቀበረው ወንድሙ አዝኖ ሳይሆን ሞቱም ሆነ ህይወቱ ያልታወቀው ሌላኛው ወንድሙ ምን እንደነካው፣ የት እንደደረሰ ቁርጡን ሳያውቅ እህል ውሃ እንደማይቀምስ ለራሱ ስለማለ ነው፡፡ በዚህ ላይ የጃርሶ ጦር መሪ የለውም ወንድማማቾች በጋራ ይመሩት ነበር፤ እነሱም በአንዲት ጀንበር ጦርነት ተለዩት፡፡
ደጃዝማች አበራን ያስጨነቀውም የአብቹ እህል ውሃ ለመቅመስ “አሻፈረኝ” ማለትና የጃርሶ ጦር መሪ ማጣቱ ነው፡፡ እርግጥ መሪነቱን ለሌላ ሰው መስጠት ይቻላል፤ ግን አብቹ ቢቀየመውስ? መጀመሪያ ለብዙ ዘመናት አባቱ፤ ከዚያም “የማይጨው ዘመቻ” የሚባለው ግዳጅ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ወንድሞቹ በጋራና በፍቅር ሲመሩት ነበር፡፡ ይህንን የቆየና ህዝቡ አምኖ አክብሮት የቆየውን ልማድ እንዴት መሻር ይቻላል? “አብቹ ይምራው” እንዳይባል ገና የ16 አመት ጉብል ነው፡፡ በ16 አመት ጉብል የሚመራ ጦርስ እንዴት ከሰለጠነ፣ ከተደራጀና በመሳሪያ ፍፁም የበላይነት ካለው የአውሮፓ ጦር ጋር ውጊያ ማካሄድ ይቻላል? የደጃዝማች አበራ ጭንቅላት በሃሳብ እንደ እንቧይ ሊፈርጥ ምንም አልቀረውም፡፡
የሚያደርገው ቢያጣ ሽማግሌዎችንና ሌሎች አማካሪዎቹን ሰብስቦ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጊዜ የፈጀ ውይይት ተካሄደ፡፡ መጨረሻ ላይ አንድ የጃርሶ ጦር አባል “እኔ አሳምነዋለሁ፤ እህል ውሃ እንዲቀምስም አደርጋለሁ” ብሎ ኃላፊነቱን ወሰደ፡፡ በምን ዘዴ እንዳሳመነው ባይታወቅም እውነትም አብቹ ሁለት ቀንና ሁለት ሌት ብቻውን ከተቀመጠበት ድንጋይ ላይ ተነስቶ ከጦሩ ጋር ተቀላቀለ፡፡ ግን እህል የሚቀምሰው ጥያቄው ከተመለሰለት ብቻ መሆኑን አስገነዘበ፡፡
ጥያቄውም “ሁለት መቶ ወጣቶች ይሰጡኝና ወንድሜን ከጣሊያን ምርኮ ነፃ ላውጣው” የሚል ነው፡፡ የጃርሶን ጦርም አጐቱ ቀኛማች ገለታ እና ቀኛዝማች ሼህ ሁሴን አባወርቁ እንዲመሩት ፈቀደ፡፡
ወጣቶችን ብቻ ከጐኑ ለማሰለፍ ያቀረበው ሃሳብ በቦታው የነበሩ አንዳንድ አዛውንቶችን ቢያስቀይምም ደጃዝማች አበራን ግን ከህሊና ምጥ ገላገለው፡፡ የጠየቀው እንደሚሟላለትም ቃል ገባለት፡፡
የደጃዝማቹን ፈቃድ ሲያገኝ የአብቹ ደስታ ወሰን አልነበረውም፡፡ እንዲያውም ያንን የልጅነት አዕምሮውን ክፉኛ የበጠበጠውን ሀዘኑን እርግፍ አርጐ ትቶ በሚገርም ደስታ ቀየረው፡፡ የቀሩትን ሦስት በሬዎች አርዶም ጦሩን ሲጋብዝ፣ ሲዘፍንና ሲያዘፍን አመሸ፡፡ ሊነጋጋ ሲል የተመረጡለትን 200 ያህል ወጣቶች አስከትሎ በሞቀ ቀረርቶና ፉከራ ወደ ጣሊያን ምሽግ ገሰገሰ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ “አብቹን አየሁ” የሚል ጠፋ፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የአብቹ ዝና በትግራይ ሰማይና ምድር ብቻ ሳይሆን በሮማ ከተማ ጭምር በመናኘቱ እጅግ በርካታ ወጣቶች አለቆቻቸውን፤ ማለትም ራስ ካሳን፣ ራስ ሥዩም መንገሻንና ደጃዝማች አበራን በመክዳት ከእሱ ጦር ጋር ይቀላቀሉ ጀመር፡፡
በአብቹ የሚመራው ጦር ጠላቱ ላይ ጥቃት የሚፈፅመው ጠላት ባላሰበው አሳቻ ስፍራና ሰዓት በመሆኑ ነፍሰ በላዎቹን ፋሽስቶች ብርክ ያስይዛቸው ጀመር፡፡ የአብቹን ጥቃት መቋቋም የተሳነው ፋሽስት፤ ሰላማዊውን ሰውና እንስሳትን ሳይቀር በአረመኔነት መጨፍጨፉን ስላጠነከረ ንጉሡና ራሶች አብቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ወሰኑ፡፡ ግን አብቹን ማን ይይዘዋል? አብቹኮ በለጋነቱ የሚታወቀው ጉብል ሳይሆን ተዓምር ሊባል በሚችል ሁኔታ እሳተ ነበልባል ሆኗል፡፡
አብቹን አባብለውም ሆነ በሃይል ይዘው እንዲመጡ የሚላኩት ሰዎች ሁሉ የአብቹ አመራር እየማረካቸው በዚያው እየቀሩ ራሶችንና ደጃዝማቾችን አስቸገሩ፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ኢትዮጵያን ለመውጋት ከጣሊያን ፋሽስቶች ጋር የመጣ አንድ ባታሊዮን ኤርትራዊ ጦር አዛዡን ጣሊያናዊ ገድሎ ከአብቹ ጦር ጋር መቀላቀሉ ነው፡፡ከጣሊያን በሚማርከው ትጥቅና ስንቅ የአብቹ ክንድ እየፈረጠመ፤ እግረ መንገዱንም በጣሊያኖችና አሽቃባጮቻቸው ላይ የሚፈፅመው ቅጣት እየጠነከረ በመሄዱ ጣሊያኖች በመርዝ ጋዝ ህዝቡን ያሰቃዩት ጀመር፡፡ በዚህ የተነሳ አብቹ በወገኖቹም በጠላቱም እጅግ ተሳዳጅ ሆነ፡፡
ንጉሡም ሆኑ ራሶች “ልጁን እሰሩት!” የሚል ቀጭን ትእዛዝ ለበታች ሹሞቻቸው በተደጋጋሚ ቢያስተላልፉም አብቹ የእሳት አሎሎ ሆነ፡፡ እንዲያውም ከትግራይ በጄኔራል ተስፋ ጽዮን፣ ከኤርትራ በጄኔራል ሃብቶም፣ ከጐጃም በጄኔራል ጋሹ፣ አንዲሁም ከሰላሌ በጄኔራል ወርቁ የሚመራ አንድ አንድ በድምሩ አራት ባታሊዮን ጦር ተቀላቀለውና በንጉሡም ሆነ በፋሽስት ጠላቶቹ ዘንድ ቁጥር አንድ ስጋት እየሆነ መጣ፡፡ “የልጁ ሠራዊት በዚህ በኩል አለፈ” ከተባለ ምድረ ፋሽስትና ባንዳ እንደ ቄጠማ እየራደ የሚይዝ የሚለቀውን ማጣት የየእለት ተግባሩ ሆነና አረፈው፡፡ የአብቹን እጅ በቀላሉ መያዝ አልሆንለት ያለው ደጃዝማች አበራ፤ አንድ ቀን የተሻለ ዘዴ ተጠቀመና ተሳካለት፡፡ እሱም “አበራ በጠና ታሟልና በነፍሱ ድረስ ብላችሁ ንገሩት፡፡ በእኔ የሚጨክን አንጀት የለውም” የሚል መልእክት በታማኝ ወዳጁ አማካይነት ለአብቹ እንዲደርሰው ማድረግ ነበር፡፡
መልእክቱ ሲደርሰው እውነትም አብቹ መዋል ማደር አልቻለም፡፡ ድንገት ከደጃዝማች አበራ ዋሻ ዘው ሲል ደጃዝማቹም ሆነ አብረውት የነበሩ መኳንንትና አሽከሮች ልክ መብረቅ የወረደባቸው ያህል ክው ብለው ቀሩ፡፡ ከጥቂት የመረጋጋት ጊዜ በኋላ ደጃዝማች አበራ በአይን ጥቅሻ ለአሽከሩ የሆነ ምልክት ሰጠው - “እሰሩት” የሚል ነው መልእክቱ፡፡
የደጃዝማቹ አሽከር ተጨማሪ አሽከሮችን ለመጥራት ከድንኳን በፍጥነት ቢወጣም በሌላ ሃይል እየተነዳ በምርኮኛ መልክ ሁለት እጁን ወደላይ ሰቅሎ ሲመለስ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ በዚህ ጊዜ “ኮሌኔል ኮኖቫሎቭ” የተባለ ሰው (ዋሻው ውስጥ ከነበሩት አንዱ) ደንግጦ “ምርኮኞች ሆንን ማለት ነው?” ብሎ አብቹን ሲጠይቀው አብቹ የተሟላ ህሊና ያለውን ሰው ቀርቶ የግራኞችን ባህር አንጀት ሳይቀር የሚያላውስ መልስ ይሰጣል፡፡ እንዲህ ሲልም ይጠይቃል፡-
“ደጃዝማች ገና ከሰላሌ ስንነሳ ታማኝነቴን በምኒሊክ ስም ቃል የገባሁት ላንተ እንጂ ለሽማግሌዎች (ራስ ሥዩምንና ራስ ካሣን ማለቱ ነው) ወይም ለንጉሡ አይደለም፡፡ እኔ ንጉሥ አይደለሁም፤ ተራ ወታደር እንጂ፡፡ እና እኔ ሁለት ሦስት ወር ደሴ ተጐልቼ (ቆላ ተምቤን፣ አምባራዶምና አቢአዲ አካባቢ ዘግናኝ ጦርነቶች ሲካሄዱ ንጉሡ ደሴ ሆነው “ተከላከሉ እንጂ አትዋጉ” ሲሉ ስለነበር ያንን በአሽሙር ለመግለጽ ፈልጐ ነው) ጣሊያኖች እጄን እስኪይዙኝ አልጠብቅም፡፡ ላንተ ግን አሁንም በምኒሊክ ስም፣ በምኒሊክ አምላክ በድጋሚ ቃሌን እሰጣለሁ፡፡ ላንተ እሞታለሁ፡፡ ተመለስ! ላልኸው ግን የት ነው የምመለሰው? ምንስ መመለሻ ቤት አለኝና? እዚህም እዚያም እሳት እየነደደ እንዴት ቁጭ ልበል? ሽማግሌዎቹ ጦር ሊሰዱብኝ አስበው ከሆነ ደግ፤ ምንም ችግር የለም፡፡ ግን እኔ ከእነሱ ጠብ እንደሌለኝና የሀገሬ ታማኝ ወታደር እንደሆንኩ አስረዳልኝ፡፡ ደጃዝማች ስማኝማ! ምንአልባት ካልተገናኘን እማማን ደስተኛ እንደነበርኩ ንገራት፡፡ በእሳተ ገሞራ መሃል ማለፍ ቢኖርብኝም ወደ ሰላሌ እመለሳለሁ” አለና የደጃዝማች አበራን ዋሻ ለቅቆ ወጣ፡፡ የት እንደሄደ ግን የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ወታደሮቹን በትግራይ በረሃዎች እያዟዟረ ጣሊያኖችንና ባንዳዎችን ድባቅ መምታቱን ቀጠለ፡፡ አቢአዲ አለ ሲባል አምባ አራዶም፤ አምባራዶም ታየ ሲባል መቀሌ፣ መቀሌ አለ ሲባል ማይጨው እየተወረወረ እንኳን ጠላቱን ወዳጆቹን እነደጃዝማች አበራንና ሁለቱን ራሶች፣ እንዲሁም ንጉሠ ነገሥቱን ግራ አጋባቸው፡፡
እንዲያውም አንዳንዴማ በሌለበት ቦታ ሁሉ “እዚህ አካባቢ አብቹ ታየ” ከተባለ ጣሊያን ጓዙን ሸክፎ መፈርጠጥ ይጀምራል፡፡ ግና ምን ያደርጋል፤ አብቹ ጦርነት ውስጥ የገባው ከጣሊያን ጋር ብቻ ሳይሆን ከገዛ ወገኖቹ ጭምር ነው፡፡ እሱ “ጣሊያንና ባንዳን ቀጥቼ ሀገሬን ከወረራ አድናለሁ” ሲል የንጉሡን ትእዛዝ ያለምንም ማቅማማት የሚፈፅሙት ራሶች ደግሞ “ምን ሲደረግ?” ባዮች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለአንድ የ16 አመት ጉብል የማይታሰብ ቢሆንም አብቹ ግን እንደ ብረት ጠንካራ በመሆን ሁሉንም የመከራ አይነቶች በፅናት መጋፈጡን ቀጠለ፡፡
በአስቸጋሪዎቹ የተምቤን ተራራዎች ጣሊያንን አይቀጡ ቅጣት ሲቀጣ ቆይቶ የወገን ጦር ወደማይጨው እንዲሰባሰብ በመታዘዙ ምንም እንኳ ከጦሩ እዝና ቁጥጥር ውጭ የሚንቀሳቀስ፣ በንጉሡና በራሶች ዘንድ ባለጌና ወሮበላ ተደርጐ የሚታይ ቢሆንም ለደጃዝማች አበራ የተለየ ፍቅር ስለነበረው ጀግኖቹን እየመራ ለወሳኝ ፍልሚያ ወደማይጨው ተጓዘ፡፡
ጉዞው ግን በቃል ሊገለፅ የማይችል መራራና ሌት ከቀን ከሞት ጋር በመጋፈጥ ሞትን ራሱን አሸንፎ ማለፍን የሚጠይቅ ነበር፡፡ የመጨረሻው የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ማይጨው ላይ በመሆኑም በራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ከሚመራው ጦር በቀር የሶስቱ ራሶች (ራስ ሥዩም መንገሻ፣ ራስ ሙሉጌታ ይገዙና ራስ ካሣ ኃይሉ) ጦር አንድ ቦታ ላይ በመቀናጀት ጠላትን ቀጥቶ ዳግማዊ አድዋን በማይጨው ለመድገም ተወስኗል፡፡ ምንም እንኳ ራሶችና ደጃዝማቾች በእድሜም ሆነ በስልጣንና በጦር ብዛት የተራራ ያህል ቢበልጡትም አብቹ ለዚህ ወሳኝ ጦርነት አስፈላጊነቱ ጥርጥር የለውም፡፡ አብቹም ሆነ በእሱ የሚመሩት አንበሶች መንገድ ላይ የሚገጥማቸውን መሰናክል ሁሉ በከፍተኛ ወኔ እየተጋፈጡ ማይጨው ደረሱ፡፡
ከፊት ነፍሰበላው የጣሊያን ጦር ከኋላ ደግሞ መንጋ የባንዳ ግባሶ የጥይት በረዶ እያዘነበባቸው ከሰው የተፈጠሩና በሞት የሚረቱ ሳይመስሉ ግዳጃቸውን ተአምር በሚመስል ሁኔታ ተወጡ፡፡ ከጣሊያን ምሽግም እየዘለሉ ገቡና የተወለደበትን ቀን ያስቆጥሩት ጀመር፡፡ ግና ምን ይሆናል ከወገን በኩል ምንም አይነት አጋዥ ኃይል ማግኘት አልቻሉም፡፡ ስለሆነም ጄኔራል ተስፋ ጽዮንና ጄኔራል ጋሹ የተባሉትን ምርጥ አዛዦችንና በርካታ አባሎቻቸውን አጥተው ወደ ሰላሌ መመለስ ግድ ሆነባቸው፡፡
ሰላሌ ከመጡ በኋላ ከደጃዝማች አበራና ከሌሎች ወዶ ዘማች ፈረንጆች ጋር ተሰነባብተው ወደ ጃርሶ አመሩ፡፡ በተለይ አብቹ ከአንድ የጣሊያን ጀኔራል የማረከውን ሽጉጥ ለደጃዝማች አበራ፣ ሁለት ጐራዴዎችን ለሁለት ፈረንጆች በሽልማት መልክ ሰጥቶ በጥቁር ፈረሱ ላይ ወጣና ቁልቁል ወደ ጃርሶ ከነፈ፡፡ ግን የት ደርሶ ይሆን? የሳምንት ሰው ይበለን፤ እንመለስበታለን፡፡

 

Read 2298 times