Sunday, 03 March 2013 08:20

ክርስትናና ሶሻሊዝም ምንና ምን ናቸው?

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(4 votes)

“እውነተኛውን የክርስቶስ መንፈስ በሰራተኛው አመፅ ውስጥ ታገኙታላችሁ”
መንፈስን በሚያነቃቁ ወይም ሰብዕናን በሚያበለፅጉ መፃህፍቱ ተጽእኖ መፍጠር እንደቻለ የሚነገርለት አሜሪካዊው ፀሐፊ ዋላስ ዲ.ዋትልስ ከሞተ ወደ አንድ ክ/ዘመን ገደማ አስቆጥሯል፡፡ መንፈስ አነቃቂ ሥራዎቹ ግን ዛሬም ድረስ በአድናቆት ይነበባሉ፡፡ ሥራዎቹ ለብዙዎቹ የዛሬው ዘመን የስኬት መፃሕፍት ደራስያንም መሰረት እንደሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ በእርግጥ ዛሬ የማስቃኛችሁ ዋልትስ የፃፋቸውን ለስኬትና ለብልፅግና የሚያነሳሱ መፃሕፍት አይደለም እኒህን ከፍተኛ ዝና የተቀዳጀባቸውን ሥራዎቹን ሌላ ጊዜ እመለስባቸዋለሁ፡፡ ለዛሬ ግን ድንገት እጄ የገባውን አንድ የጥናት ፅሁፉን ነው የማስቃኛችሁ፡፡ ይሄ ሥራው ከሌሎቹ ሥራዎቹ በተለየ ርዕሰጉዳይ ላይ ነው የሚያጠነጥነው፡፡ ምናልባትም ከፍተኛ ድፍረትን የሚጠይቅ ርዕሰጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡
አሜሪካዊው ፀሐፊ ዋላስ ዲ.ዋትልስ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 11 ቀን 1905 ዓ.ም በሲንሲናቲ በሚገኝ አዳራሽ ውስጥ ያቀረበው ፅሁፍ “Jesus: The man and His work” የሚል ነው፡፡ በ28 ገፆች የተቀነበበው ፅሁፍ በኢየሱስ ክርስቶስ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነበር፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሥራው (ጥናቱ) በወቅቱ ለታዳሚዎች እንዲቀርብ ስፖንሰር ያደረገው የቀዬው የሶሻሊስት ፓርቲ ቢሮ ቅርንጫፍ ነበር፡፡ በፈጣሪ (እግዚአብሔር) አለመኖር አጥብቆ የሚያምነው የሶሻሊስት ፓርቲ ስለ ኢየሱስ የተዘጋጀ ፅሁፍ ለታዳሚዎች እንዲቀርብ ድጋፍ ማድረጉ በእርግጥም አስገራሚ ነው፡፡
ኢየሱስና ሶሻሊዝም ምን አገናኛቸው ብለንም እንድንጠይቅ ይጋብዘናል፡፡እኔም ይሄን ጥያቄ እያብሰለሰልኩ ነበር ፅሁፉን ማንበብ የጀመርኩት፡፡ የመግቢያው ሁለተኛ አንቀፅ ላይም እንደደረስኩ እንቆቅልሹ ተፈታልኝ፡፡ ክርስቶስንና ሶሻሊዝምን ምን እንዳዛመዳቸው ቢያንስ ፍንጭ አገኘሁ፡፡ እናንተም ትንሽ ታገሱ እንጂ ነገርዬውን ትረዱታላችሁ፡፡ በነገራችሁ ላይ ይሄ ባለ 28 ገጽ ጽሑፍ በገለፃ መልክ (ሌክቸር) ከቀረበ በኋላ አብዛኛው ታዳሚ የጽሑፉ ረቂቅ ታትሞ እንዲሰጠው በመጠየቁና የፅሁፉ ባለቤት ፕሮፌሰር ዋትልስም ፈቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ በ”Personal Development institute” አማካኝነት ለህትመት በቅቷል፡፡
ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ ከብዙ አስርት ዓመታት በኋላ በኢንተርኔት ላይ በe-book መልክ ተሰራጭቶ እነሆ ለእኔና ለናንተ የደረሰው፡፡ ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና!! የሆነስ ሆነና ፕሮፌሰር ዋትልስ በዚህ ፅሁፉ ስለክርስቶስ ምንድነው የሚነግረን? ምንስ አዲስ ነገር ይዞልን መጣ ይሆን? አሁንም ትንሽ ታገሱ እንጂ ይዞ የመጣውን አዲስ ነገር ሁሉ ተራ በተራ አስቃኛችኋለሁ፡፡
ደራሲው በፅሁፉ መግቢያ፤በክርስትናና በሶሻሊዝም መካከል ያለውን ዝምድና ሲገልፅ “በእውነተኛው ክርስትናና በሶሻሊዝም መካከል ያለው የሥነምግባር ተመሳስሎ ቁልጭ ያለ ነው፡፡
የሁለቱም የማዕዘን ድንጋይ የቆመው ፍትህ፣ እኩልነትና ወንድማማችነት በሚሉት መርሆች ላይ ነው” ይላል፡፡ በአሁኑ ፋይዳቢስና አሳፋሪ የኢኮኖሚ ስርዓት ግን እነዚህ መርሆዎች ሊተገበሩ አይችሉም፡፡ እያንዳንዱን ቁሳዊ ፍላጐት ፍፁም መሰዋትን ይጠይቃል፡፡ መቼም ከዚህ ተነስተን ዛሬ የናዝሬቱ ኢየሱስ በምድር ላይ ቢኖር ኖሮ ምን ዓይነት ኢኮኖሚያዊ እሳቤ ሊይዝ እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም - ይለናል ደራሲው፡፡ ልብ አድርጉ! በደራሲው ፅሁፍ ውስጥ በዋናነት የተነሳው ሃሳብ የክርስቶስ የኢኮኖሚ እሳቤ ወይም ፖሊሲ አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢየሱስ ሰብዕናና ባህርያት ላይ በእጅጉ የሚያተኩር ነው፡፡ በእርግጥ ይሄን ፅሁፍ በክፍት አዕምሮ ማንበብና መመርመር ይጠይቃል - ለቅድመ ፍርድ ከመጣደፍ በፊት፡፡ ለምን መሰላችሁ? ፀሃፊው ኢ- አማኝ አይደለም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥብቅ ወዳጅ ነኝ ባይ ነው፡፡ በእርግጥ በዘመኑ የነበሩትን ቤተክርስትያናትና ሰባኪዎችን ይተቻል ይነቅፋልም፡፡ ለምን ሲባል? እውነተኛውን ክርስቶስ ለዓለም አልሰበኩም ባይ ነው፡፡ ለዘመናት በአዕምሮአችን ውስጥ ሲቀረፅ የኖረው የክርስቶስ ምስል የተሳሳተ ነው ሲልም ማስረጃ እየጠቀሰ ይከራከራል፡፡ አሁን እንግዲህ እኛም ልንጠይቅ እንችላለን - “የትኛው ነው እውነተኛው ክርስቶስ? የትኛውስ ነው ሃሰተኛው ወይም የተዛባው የክርስቶስ ምስል?” በማለት፡፡ ለዚህ ጥያቄ ደግሞ ራሱ ፀሃፊው “Jesus: The man and His work” በተሰኘ ፅሁፉ መልስ ይሰጣል፡፡ እናም በትዕግስት ንባባችንን እንቀጥል፡፡
የክርስቶስ መንፈስ አልሞተም፤ በዘመናዊ ቤተክርስትያናችን ውስጥ ግን መንፈሱ የለም (ከመቶ ዓመት በፊት የተፃፈ መሆኑን ልብ በሉ) የሚለው ዋትልስ፤ የክርስቶስን መንፈስ ታዲያ የት ነው የምናገኘው ሲል ይጠይቃል ይሄ አባባሉ ለአብዛኛው ክርስትያን ፈታኝ ጥያቄ እንደሚሆንበት እገምታለሁ - እኔም ራሴ ክርስትያን በመሆኔ፡፡ ደራሲው ራሱ ላነሳው ጥያቄ መልስ ሲሰጥም እንዲህ ይላል “ዓይናቸውን ለእውነት የገለጡ ሰዎች የትክክለኛ ክርስትያንነት መገለጫን በመላው ዓለም የሠራተኛ መደብ አመጽ ውስጥ ያገኙታል፡፡” አያችሁልኝ--- ፀሃፊው እንዴት ሶሻሊዝምን ከክርስትና ጋር ለማዛመድ እንደዳከረ! ገና ከጅምሩ ላይም በሦስት መርሆዎች እንዳስተሳሰራቸው እንዳትዘነጉ - “ፍትህ፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነት” በሚሉ፡፡
የናዝሬቱ ኢየሱስ እንኳንስ በኋላ በመጡት ተከታታይ ትውልዶች ቀርቶ በራሱ ዘመንም በትክክል የተረዳው አልነበረም ሲልም ይከራከራል፡፡
የሚያስገርመው ደግሞ ወዳጆቹና ተከታዮቹ ነን በሚሉ ወገኖች ነበር ስለኢየሱስ ሃሰተኛ የሆነ ምስልና የተዛባ ሰብዕና ሲሰጥ የኖረው ይለናል፡፡
የክርስትና ሃይማኖት በምድር ላይ የተዋወቀው ገዢው መደብ ህዝቡ ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛለት በሚፈልግበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ንጉሳዊው መደብና ቀሳውስቱም ህብረተሰቡ ባርነትን በፀጋ እንዲቀበል፣ለቀረጥና ግብር ሸክም ጫንቃውን እንዲሰጥ፣ ማንኛውንም ኢኮኖሚያዊ በደል ያአንዳች ተቃውሞ እንዲሸከም የሚገፋፋው ሃይማኖታዊ አርአያ (ተምሳሌት) ይፈልጉ ነበር፡፡ ከዚህ ፍላጐት ውስጥ ነው ዛሬ እንደትክክለኛ ነገር የሚቆጠረው የኢየሱስ ክርስቶስ ሰብዕናና የመልዕክቱ ጽንሰ ሃሳብም የተወለደው ይላል - ፀሃፊው፡፡ ግን ግን ፀሃፊው የተሳሳተ ወይም የተዛባ የሚለን የኢየሱስ ምስል ከየት ተፈጠረ? ይሄ የተዛባ የክርስቶስ ምስል (ገፅታ) ክርስቶስ ከመወለዱ 700 ዓመት በፊት ከተፃፈው ትንቢተ ኢሳያስ ግጥም የተወሰደ ነው የሚለው ዋትልስ፤የኢየሱስን ህይወትና ስራ እማኝ በመሆን ታሪኩን የመዘገቡት ግን አራቱ ወንጌላውያን ናቸው፣ትክክለኛውን የክርስቶስ ምስል ማግኘት የሚቻለውም ከእነሱ ነው ብሏል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ለዘመናት ሲነገረንና ስንሰበክ የኖርነው በኢሳያስ ትንቢት ላይ በተገለፀው መልኩ ነው በማለት ይሄም ትክክለኛው የክርስቶስ ማንነት አይደለም ሲል አጥብቆ ይሟገታል - ደራሲው፡፡
በትንቢተ ኢሳያስ ስለክርስቶስ ከተገለፀው ውስጥ ጥቂቶቹን በምሳሌነት ሲጠቅስም “በሰዎች የተናቀና የተገለለ ነበር…ሃዘንና ስቃይ ተለይቶት አያውቅም፤ስቃይና በደል ቢደርስበትም ፈጽሞ አይናገርም…ዝም ብሎ አራጁ ፊት እንደሚቀርብ በግ…” ይላል፡፡ እኒህ ገለፃዎች የሚጠቀሱት የክርስቶስን የዋህነትና ትሁትነት እንዲሁም በደልንና ኢ - ፍትሃዊነትን በፀጋ የተቀበለበትን መንፈስ ለማሳየት ነው፡፡ የዓለማችን አዳኝ ተብሎ የተነገረን ክርስቶስ የተናቀ፣ ባልንጀሮች የሌሉት፣ ምስኪን የቀን ሰራተኛ፤ ከዝቅተኛ የህብረተሰብ መደብ የተወለደና በዚህም ሳቢያ የተገለለ እንደነበረ ተደርጐ ነው፡፡ ቤት እንደሌለውና ረሃብተኛ እንደነበር፤ ዘለፋና መሳደድን በፀጋ እየተቀበለ እንደኖረ፤ ክብር ለነፈገውና ለሚሳለቅበት ዓለምም ሁልጊዜ እጆቹን እያነሳ ቡራኬ ይሰጥ እንደነበር ተገልጿል ይላል፡፡
ይሄ ሰብዕና ነው የክርስትና ተምሳሌት ተደርጐ የቀረበልን የሚለው ፀሐፊው፤ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክትም “የዋህ ሁኑ፣ በደልን በፀጋ ተቀበሉ፣ እንደበጓ አራጃችሁ ፊት ቅረቡ፣ ለእግዚአብሔር ክብር መስዋዕት ስለሆናችሁም ሃሴት አድርጉ” የሚል መሆኑን ይገልፃል፡፡
ከመስበኪያ ሰገነቱ ላይ ሲቀርብልን የኖረው ክርስቶስ ደካማ ሰብዕና ያለው ነው - ይለናል ዋትልስ፡፡ ሌላው ቀርቶ ለፕሬዚዳንትነት እንኳን የምናጨው ዓይነት ሰው አይደለም፡፡ ተከታዮቹ በሚሰራቸው ተዓምራት በእጅጉ እምነት ቢኖራቸውም የዚህን ዓለም ጉዳዮች በመምራት ግን ፈጽሞ እምነታቸውን የሚጥሉበት ዓይነት ሰው አይደለም፡፡ የዚህች አገር ፕሬዚዳንት ዛሬ ሥልጣን እንደሚለቅና ነገ ኢየሱስ ቦታውን እንደሚረከብ ቢሰማ፣ 95 በመቶ ያህሉ ክርስትያን የቢዝነስ ሰዎች ገንዘባቸውን ከባንክ ያወጣሉ፡፡ (በየዋህነቱ ጉድ እንሆናለን በሚል) ፀሐፊው ይሄን ሁሉ ከገለፀ በኋላ፣ “ዛሬ (በወቅቱ ማለቱ ነው) በየትኛውም ቦታ ባለ ቤተክርስትያን ሃሰተኛውን ክርስቶስ ነው የሚሰብኩት” በማለት፤እኔ ግን ትክክለኛውን ክርስቶስ ላሳያችሁ እሻለሁ - ያኔ በምድር ላይ የነበረውንና አሁን ያለውን፤ ወደርየለሹንና ሃያሉን ክርስቶስ እነሆ ይለናል - ተዛብቶ ቀረበ ያለውን የክርስቶስ ሰብዕናና ምስል እየጠቀሰና እያቃና፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የያኔው ክርስቶስ በሠራተኛነቱ ይናቅ ነበር የሚለው አያስኬድም የሚለው ደራሲው፤በወቅቱ ባህል መሠረት እያንዳንዱ ይሁዲ ራቢ ወይም የተማረ ነው የሚባል ሁሉ ሥራ እንዲኖረው ይጠበቅ ነበር በማለት አብነቶችን ይጠቅሳል፡፡
“--- የእጅ ባለሙያው ራቢ ጆሃናን እና ጫማ ሰፊው ራቢ ይሳቅ የተማሩና እጅግ የተከበሩ ነበሩ፡፡ አናጢው ራቢ ኢየሱስም ተመሳሳይ ነበር፡፡ በጣም የተማረ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በሙያው ድንኳን ሰሪ ነበር---”
ኢየሱስ በወጣበት የህብረተሰብ መደብ ወይም በትውልድ መሰረቱ ሳቢያ ንቀትና መገለል ይደርስበት ነበር የሚለውም አሳማኝ አይደለም ባይ ነው፡፡ እንዴት ቢሉ --- በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ ትውልዱ ከመሳፍንት ወገን የሆነ የንጉሳውያን ቤተሰብ ልጅ ተደርጎ ይታሰብ ነበርና፡፡ ብዙ ጊዜም “የዳዊት ልጅ” እየተባለ እጅ ይነሳለት እንደነበር የጠቀሰው ደራሲው፤በመቀጠልም ሁለተኛውን የመከራከርያ ነጥቡን ያነሳል፡፡
ክርስቶስ በእውቀት ማነስ ፈፅሞ የሚታማ አልነበረም ስለዚህም ማንም ሰው ሊንቀው አይችልም ሲል የተሟገተው ዋትልስ፤በወቅቱ በጣም የተማረና አዋቂ እንደነበር ምሳሌዎችን በመጥቀስ ያስረዳል፡፡ ቤተክርስትያን በሄደ ጊዜ ሁሉ የሃይማኖት ህግጋትን ለማንበብና ምዕመናን ለማስተማር የሚመረጠው እሱ ነበር - ለሥራው ከሁሉም የላቀ ብቃት ስለነበረው፡፡ “ዝናው በዙሪያው ሁሉ ናኘ፤በቤተመቅደሳቸውና በምኩራባቸው ውስጥም ከሁሉም ልቆ ያስተምር ነበር” በሚል በሉቃስ ወንጌል የተፃፈውን ጠቅሷል፡፡ ለነገሩ ኀይለኛ ሃይማኖታዊ ውዝግቦች በነበሩበት በዚያ ዘመን እውቀት የሌለው ሰው የእሱ ዓይነት ቦታ ሊያገኝ አይችልም የሚለን ፀሃፊው፤በአይሁድ ህግጋተ-ሃይማኖት በቅጡ የተካነ ነበር፡፡ ከቅዱስ መፅሃፍ ላይ አግባብ ያላቸው ጥቅሶችን በመጥቀስ የሚገዳደሩትን ሁሉ ዝም የሚያሰኝበት መንገድ እንከን የለሽ ዕውቀቱን አስመስክሮለታል ይላል፡፡ እንኳን ወዳጆቹና ተከታዮቹ ቀርቶ ጠላቶቹም እንኳን ማስተር ወይም መምህር እያሉ ይጠሩት እንደነበርም ዋትልስ ገልጿል፡፡ ፀሃፊው በሦስተኛ ደረጃ ያነሳው ደግሞ ክርስቶስ ድሃ አልነበረም፤ ሞልቶ የተትረፈረፈው ባለፀጋ እንጂ የሚለውን የመሟገቺያ ሃሳብ ነው፡፡ ስለዚህም በድህነቱ የተነሳ ማንም ሊንቀው አይችልም ባይ ነው፡፡ “---- በርካታ ባለፀጋና ተጽእኖ ፈጣሪ ወዳጆች ነበሩት፡፡ ላዛሩስ እና እህቶቹ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ኢየሱስ በገዢዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቤተሰብ ውስጥ በመገኘት የበሽተኞችን ደዌ ፈውሷል፡፡ እነሱም በበኩላቸው የገንዘብ ፍላጐቱን በማሟላት ውለታቸውን ይመልሱ ነበር፡፡
በእርግጥ ሪል እስቴት አልነበረውም፤ ነገር ግን በአለባበሱ አይታማም - ምርጥ እጀ-ጠባቦችን ነበር የሚለብሰው፤የገንዘብ እጥረትም ጐብኝቶት አያውቅም፡፡ የሚበላውና የሚጠጣው ሞልቶ የተረፈው ነበር፤ለተቸገሩ የሚመፀውተው በቂ ገንዘብም ነበረው፡፡ ” ሲል ደራሲው አብራርቷል፡፡
የዘመኑ የክርስትያን ሰባኪዎች ክብር ከሚገባው የሰው ልጅ ይልቅ ለማምለኪያነት የተሰሩ ህንፃዎችንና ሃይማኖታዊ በዓላትን አብዝተው ያከብራሉ በማለት ክፉኛ የሚነቅፈው ዋትልስ፤ በቅዱስ መፅሃፍ ሰንበት ለሰው ልጅ ተሰራ እንጂ የሰው ልጅ ለሰንበት አልተሰራም መባሉን በመጥቀስ ይሟገታል፡፡
ክርስቶስ ከሰው ልጅ ወገን መሆኑን ነው ተናግሯል የሚለው ፀሃፊው፤የሰው ልጆችን ከበደልና ኢ- ፍትሃዊነት፤እንዲሁም ከመከራ ቀንበር ለማላቀቅ ወደ ምድር መምጣቱን ይናገራል፡፡
ቀደም ሲል ክርስትናና ሶሻሊዝም ምን አገናኛቸው በሚል ላነሳነው ጥያቄም እግረመንገዱን መልስ መስጠቱ ይመስለኛል፡፡
እንግዲህ ከዚህ ፅሁፉም ሆነ እኔ ካነበብኳቸው ሌሎች የደራሲው ሥራዎች ለመገንዘብ የቻልኩት እውነተኛው ክርስቶስ ምስኪን፤ የዋህና በደልን በጄ ብሎ የሚቀበል ያጣ የነጣ ድሃ ሳይሆን ሞልቶ የተትረፈረፈው፤ግርማሞገሱ የሚያስፈራ፤ተናግሮ የሚያሳምን፤የእውቀት ቁንጮ እንዲሁም የሰላም፤የእኩልነትና የፍትህ ተሟጋች መሆኑን ነው፡፡ በመጨረሻ ከደራሲው ጋር የማልስማማበትን አንዲት ነጥብ ላንሳና ፅሁፌን ልቋጭ፡፡
በፅሁፉ መግቢያ ላይ ክርስትናና ሶሻሊዝም የሚመሳሰሉባቸውን መርሆች ሲገልፅ ሁለቱም በፍትህ፤በእኩልነትና በወንድማማችነት መርሆዎች ላይ መመስረታቸውን ጠቅሷል፡፡
እኛ በተግባር የምናውቀውም ሆነ በሌሎች አገራት የነበረው ሶሻሊዝም ግን ከዚህ ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ በመሆኑ ሁለት የሰማይና የምድር ያህል ርቀት ያላቸውን ነገሮች ማቅረቡን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ ወይስ ዓለም ሲተገብረው የኖረው ሶሻሊዝም ትክክለኛው አልነበረም? በነገራችሁ ላይ ይሄን የደራሲውን ፅሁፍ መነሻ አድርጎ ሃሳብ ማንሸራሸር ይቻላል - መድረኩ ክፍት ነው፡፡ ሰላም፤ፍቅርና ጤና ለሁላችንም ይሁን!!

 

 

Read 2660 times